Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

አረ እናንተ ሆዬ፣ አንዴ ቆም ብለን  አካሄዳችንን …

0 868

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

አረ እናንተ ሆዬ፣ አንዴ ቆም ብለን  አካሄዳችንን …

አባ መላኩ

ግዴላችሁም  ስሜታችንን እንግታው፤ አካሄዳችንንም አንዴ ቆም ብለን እንፈትሸው።  የመንጋ ፍርድ ወደ ማጡ እንዳይጎትተን እስኪ ቆም እንበልና ዙሪያ ገባችንን  እንቃኘው። በመንጋ የሚሰጥ ፍርድን ሁላችንም እናውግዘው። በኦሮሚያ፣ አማራ፣ ኢትዮጵያ ሶማሌ፣ በደቡብ  አንዳንድ አካባቢዎች የተሰጡ የመንጋ ብያኔዎች በአገራችን ታሪክ ላይ ምን ያህል ጠባሳ እንደሚያሳርፉ ውለው አድረው  የታሪካችን አካል እንዳይሆኑ ልንጠነቀቅ ይገባል። በእርግጥ እንዲያ ያሉ ቅጥ ያጡ ፍርዶች ህዝብን እንደማይወክሉ ቢታወቅም  የተፈጸሙት ግን ከዚያ ህብረተሰብ በወጡ አካላት ነውና ከወቀሳ ማምለጥ አይቻልም።

በጥላቻ ሰላምም ሆነ ፍትህ አይረጋገጡም። ጥላቻ ስሜታዊ ያደርጋል፤ ጥላቻ ሚዛናዊነትን ያቃውሳል፤ ጥላቻ ባህልን የበርዛል፤ ጥላቻ ሃይማኖትን ያሳንሳል፣ ወዘተ ።   ከጥቂት ወራት በፊት አገራችን የነበረችበትን ሁኔታ ስናስታውስ ዛሬም በርካታ ኢትዮጵያዊያን ያስፈራናል ያስደነግጠናልም። አዎ መሽቶ በነጋ ቁጥር የአገራችን እጣ ፈንታ ምን ይሆን? ስንል ራሳችንን እንጠይቅ ነበር። በሰላም ወጥቶ መግባት ስጋት ሆኖ እንደነበር ለእናንተ መንገር  አይገባኝም። ሶሪያን፣ ሊቢያን፣ የመንን፣ ኢራቅን፣ ሶማሊያን ያየ እና የእኛ አገርንም ነባራዊ ሁኔታ ላጤነው ስጋቱ ትክክል ነበር። ባለፉት 27 ዓመታት መንግስት ተሳስቶባቸዋል ብዬ ከምናገርባቸው ነገሮች መካከል ቀዳሚው የዘር፣ የቋንቋ፣ የሃይማኖት፣ የጎጥ ፖለቲካ  መራገቡ ነው። አዎ ያ ጣጣ እንዲህ በዋዛ በአጭር ጊዜ የሚፋታን አይመስለኝም። ምክንያቱም ሰው በብሄርና ሃይማኖት ማሰብ ከጀመረ ምክንያታዊነት ይቀጭጫል።

ሁሉን ማጨለም  ተገቢ አይደለም።  ዛሬ በርካታ ነገሮች በእጅጉ መቀየር ጀምረዋል።  ትላንት የት ነበርን? አሁንስ የት ነን? ነገስ የት እንሆን? ስል ራሴን  አብዝቼ እጠይቃለሁ። የሚያዝናና ባይሆንም እፎይ የሚያስብል ሁኔታዎች በአገራችን  ተፈጥረዋል። ይህን ሁኔታ ማሰቀጠል ከቻልን አገራችን ወደከፍታው ዘመን እንደምትሸጋገር  ጥርጥር የለኝም። የዛሬው የአንድነት መንፈስ በህዝቦች መካከል መልካም ግንኙነቶች እንዲፈጠሩ  እያደረገ ነው። ዛሬም አንዳንዶች የዘረኝነት መንፈሱ እንደተጠናወታቸው እዛው ቀድሞ የቆሙበት ቦታ  ናቸው።

ከዘረኝነት የሚገኝ ጥቅም ማንንም አይጠቅም፤ የማታ ማታ ሁሉንም ይዞ የሚጠፋ እኩይ ተግባር ነው። ማህበራዊ ሚዲያ የህዝቦችን አብሮነት ማጠናከሪያ፣ ዴሞክራሲያዊ መብቶችን ማጎልበቻ፣ የአገራችንን ገጽታ መቀየሪያ፣ ወዘተ ቢውል እጅጉን ይጠቅመናል።  የእኛ አገር የማህበራዊ ሚዲያ አገልግሎት ለእርስ በርስ መበያያ መድረክ እያዋልነው ነው። የማህበራዊ ሚዲያ ባላባቶች (አክቲቪስት ነን ባዮች) ይህን አባት የሌለው የሚመስለውን ሚዲያ እጅግ በክለውታል። በዚህ ሚዲያ የሚሰራጩ የተንሸዋረሩ ሃሳቦች እንኳን አገርን ይቅርና  ቤተሰብንም ሊበትኑ የሚችሉ ናቸው።

 

ስሜታዊነት ምክንያታዊ እንዳንሆን ያደርገናል። ማስመሰል እውነታን ለጊዜው ይሸፍነው ወይም ያሳንሰው  እንደሆን እንጂ በየትኛውም መስፈርት እውነታን ለዘለዓለሙ ሊደብቀው ወይም ሊያደበዝዘው አይችልም። ባለፉት 27 ዓመታት ኢህአዴግ ያመጣውን ልማት መካድ እንደማይቻል ሁሉ  በሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች ጥሰትንም ማድበስበስ አይቻልም። አንዳንዶች ስለኢህአዴግ ልማት መስማት አይፈልጉም ሌሎች ደግሞ በኢህአዴግ የተፈጸሙ ለጆሮ የሚዘገንኑ የሰብዓዊ  መብት ጥሰቶች እንዲነሳ አይፈልጉም።

እንደእኔ እንደኔ ኢህአዴግ ለኢትዮጵያ ያስፈልጋታል። በመሆኑም ድርጅቱ ራሱን አብዴት ማድረግ ይኖርበታል። ኢህአዴግ   ለውጡን የሚደግፉ ብቻ ሳይሆን አዳዲስ አስተሳሰብ ማፍለቅ የሚችሉ የወቅቱን የህዝብ ፍላጎት የሚመጥኑ አመራሮችን   ወደፊት ማምጣት ካልቻለ ተደፍልቆ እንደሚጠፋ ሊያውቅ ይገባል። ዛሬ ኢህአዴግ የሚወዳደረው ከኦነግ፣ ከግንቦት ሰባት፣ አብን፣ ወዘተ እጅግ በርካታ የህዝብ ድጋፍ ካላቸው ፓርቲዎች ጋር መሆኑን ማወቅ ይኖርበታል። ኢህአዴግ በቀድሞው አመራሮቹ እዚህ አድርሶናል ከእንግዲህ ግን እነዛ አመራሮች አዲስ ሃሳብ ማፍለቅ ሳይሆን አዲስ ሃሳብ መቀበል አይችሉም።

በህዝብ  የተወደዱትና  የተወደሱትን ዶ/ር አብይን ጨምሮ አቶ ለማ መገርሳን የመሳሰሉ ወጣት አመራሮችን  ያፈራው ኢህአዴግ እነደሆነ ሁሉ በ60ዎቹና 70ዎቹ የዕድሜ ክልል የሚገኙ ያሉ አዛውንቶች  ከፖለቲካው ተገለልን በማለት የሚጮሁበትን ሁኔታ እየተመለከትን ነው። ሁሉም የኢህአዴግ እህት ድርጅቶች  አዛውንት አመራሮቻቸውን ማሰናበት ካልቻሉ እርስ በርሳቸው ይደማመጣሉ ብዬ አላስብም። ምክንያቱም አዛውንት አመራሮች ሁሉን የሚመለከቱት በትላንት መነጽራቸው  በመሆኑ ለውጥ አይዋጥላቸውም። ዛሬ ላይ ደግሞ ህብረተሰቡ ለውጥ ፈልጓል።

አሁን ላይ በአገራችን በመነጋገር ለችግሮች መፍትሄ ማግኘት የሚቻልበት ሁኔታ በመፈጠር ላይ ነው። በመሆኑም ይህን መልካም ጅምር  ማጠናከር ሲገባን ከሃይማኖታችንና ከባህላችን ውጪ የሆኑ አስነዋሪና አስፈሪ የሆነውን የመንጋ ፍርድ ሁላችንም ልናወግዘው ይገባል። ችግሮችን በሃይል እልባት እንዲያገኙ ከመሞከር ይልቅ በሰከነና በሰለጠነ መንገድ መፍትሄ መፈለግ  የመጀመሪያም የመጨረሻም አማራጭ ሊሆን ይገባል። በመንጋ ፍርድ መስጠት የህግ የበላይነትን ይጻረራል፤ የህዝቦችን አብሮነት ይጎዳል፤ አንድነትን ያላላል፤ የአገራችንን የዴሞክራሲ ስርዓትንም ይጎዳል፤ የአገራችንንም ገጽታ ይጎዳል። ይህ ደግሞ ውወሎ አድሮ  በልማታችን ላይ ተጽዕኖ ማሳደሩ አይቀርም። በመንጋ ፍርድ የሚሰጥበት አገር ማንም ኢንቨስት ማድረግ አይፈልግም። በመሆኑም በማንኛውም መስፈርት በዚህ ጸያፍ ተግባር ላይ የሚሰማሩ ማንኛውም ሃይል ለህግ ተላልፈው መሰጠት ይኖርባቸዋል።

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy