Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

“አንዲትም ቃል ከህገ መንግስቱ…!”

0 2,032

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

“አንዲትም ቃል ከህገ መንግስቱ…!”

                                                              ዋሪ አባፊጣ

“በአሁኑ ወቅት የአንድነት ኃይሉ ስለፈለገ ከህገ መንግስቱ የሚቀነስ ወይም ፌዴራሊዝምን የሚደግፉ አካላት ስላልፈለጉ የሚቀር ህገ መንግስት ኢትዮጵያ ውስጥ የለም። ‘ህዝቡን እንመራለን’ በሚል የተሰባሰቡ የፖለቲካ ፓርቲዎች የህግ የበላይነትን ካላከበሩ፤ ተራው ዜጋ እንደምን አርአያነታቸውን ተከትሎ ሊያከብር ይችላል?… በመጀመሪያ ህዝቡን ሳይወክሉ የህጎች ሁሉ የበላይ ህግ በሆነው ህገ መንግስት ዙሪያ አተካራ ውስጥ መግባትስ የራስን ጊዜ ቀርጥፎ ከመብላት ባሻገር፤ ከፈረሱ የቀደመ ጋሪ አይሆንምን?…”

 

ሰሞኑን የተለያዩ መገናኛ ብዙሃንና ማህበራዊ ድረ ገፆች አክቲቪስትና የኦሮሚያ ሚዲያ ኔትወርክ ስራ አስኪያጅ አቶ ጃዋር መሐመድ “…አንዲትም ቃል ከህገ መንግስቱ መቀየር አይቻልም ብለዋል” የሚሉ የተለያዩ ሃሳቦች ሲንሸራሸሩ ነበር። ሃሳቦቹ ምንም ይሁኑ ምን፤ በየትኛውም ዴሞክራሲያዊ ምህዳር ውስጥ መኖር ያለባቸውና ከበሬታም ሊቸራቸው የሚገቡ ናቸው። የሃሳቦቹ ባለቤቶች፤ በአመዛኙ “የአንድነት ኃይሎች” ተብለው የሚጠሩ ወይም የተሰየሙ ኢትዮጵያዊያን ወገኖቻችን ናቸው። አቶ ጃዋር ደግሞ ፌዴራሊዝምን አጥብቀን መያዝ አለብን ከሚሉት ወገኖች ይመደባሉ። የክርክሩ ደርዝ፤ በእነዚህ ሁለት እሳቤዎች ዙሪያ የሚያጠነጥን ነው ማለት ይቻላል። ‘የሁለት ዓለም ወግ’ ብንለውም ከእውነታው አንርቅም።

ያም ሆኖ፤ እኔ እስከሚገባኝ ድረስ፤ “አንዲትም ቃል ከህግ መንግስቱ…!” የሚለው የአቶ ጃዋር ምልከታ፤ ከህግ የበላይነት ጋር የተያያዘ ነው። ይኸውም ህገ መንግስቱን ለማሻሻል አሊያም ለመቀየር በመጀመሪያ የህዝብ ውክልናን መያዝ ያስፈልጋል ከሚል መሰረታዊ ጉዳይ የተነሳ ይመስለኛል።

ርግጥ ሁሉም የፖለቲካ ፓርቲዎች በተፈጠረው ለውጥ ሳቢያ እዚህ ሀገር ውስጥ የገቡት፤ በህጋዊና ሰላማዊ መንገድ በመንቀሳቀስ ሃሳባቸውን ለህዝቡ አቅርበው በምርጫ ስልጣን ለመያዝ ነው። ይህም ያለውን ህጋዊ አሰራር አክብሮና ተከትሎ መሄድን ጭምር ያጠቃልላል። አሁን ሀገሪቱ በምትገኝበት ሁኔታ፤ በስራ ላይ ያለው የኢፌዴሪ ህገ መንግስት ነው። ህገ መንግስቱን ሌላ የፖለቲካ ሃይል ተመርጦ አሻሽለዋለሁ ወይም ቀይረዋለሁ ብሎ እስካለሰበ ድረስ ህጋዊና ገዥ (legal and binding) ነው። እናም ከዚህ መሰረታዊ አስተሳሰብ ስነሳ፤ አቶ ጃዋር “አንዲትም ቃል ከህገ መንግስቱ….!” ያሉት አባባል ሚዛን የሚደፋ ሆኖ አግኝቼዋለሁ።

እንደ እውነቱ ከሆነ፤ ህገ መንግስቱን ለማሻሻልም ይሁን ለመቀየር የራሱ አሰራሮች አሉት። የህገ መንግስተ ባለቤቶች የኢትዮጵያ ህዝብ እንደመሆኑ መጠን፤ የማሻሻሉም ይሁን የመቀየሩ ስልጣን የሁሉም የኢትዮጵያ ህዝቦች እንጂ የፖለቲካ ደርጅቶች ወይም የግለሰቦች አይደለም። በእኔ እምነት፤ ህገ መንግሰቱ ከሰማይ ሶስት አራተኛ ክፍሉ ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶችን የያዘ በመሆኑ እጅግ ተመራጭና ተራማጅ ነው። ያም ሆኖ ህዝቦች ‘ከውስጡ ምናወጣቸው አሊያም በውስጡ የምናክላቸው ነገሮች አሉ’ ብለው እስካመኑ ድረስ ይህ የማይሆንበት ምክንያት የለም።

ነገር ግን፤ ህገ መንግስት፤ አንዳንድ ወገኖች እንደሚያስቡት፤ “የዓይንህ ውሃ አላማረኝም” ተብሎ የሚወረወር ጉዳይ አይደለም። ህግና ስርዓትን ተከትሎ የተረቀቀና የፀደቀ በመሆኑ፤ አሰራሩ የህግ ማዕቀፍን ተከትሎ የሚፈፀም ይሆናል። በህግ ማዕቀፉ መሰረትም የዛሬ ዓመት ገደማ ምርጫ ይካሄዳል። በምርጫው ላይ ሁሉም የፖለቲካ ፓርቲዎች ነፃ፣ ግልጽና ተዓማኒ በሆነ መንገድ ተሳትፈውና ህዝቡም አመኔታ ከጣለባቸው ሀገሪቱንና ህዝቧን ይጠቅማል በሚሉት መሰረት የህግ ማዕቀፍ ሊያበጁ አሊያም ያለውን ሊያስቀጥሉ ይችላሉ። አሁን ባለው ሁኔታ ግን በስራ ላይ የሚገኘውም ህገ መንግስት አክብሮ መንቀሳቀሱ ተገቢ ይሆናል። የአቶ ጃዋር “አንዲትም ቃል….!” አባባል ከዚህ አኳያ ውሃ የሚቋጥር መከራከሪያ ለመሆኑ መጠራጠር አያስፈልግም። ትልቁ ነገር ህጋዊ የህዝብ ውክልናን የመያዝ (legitimacy) ጉዳይ ነውና።

ስለሆነም በአሁኑ ወቅት የአንድነት ኃይሉ ስለፈለገ ከህገ መንግስቱ የሚቀነስ ወይም ፌዴራሊዝምን የሚደግፉ አካላት ስላልፈለጉ የሚቀር ህገ መንግስት ኢትዮጵያ ውስጥ የለም። ‘ህዝቡን እንመራለን’ በሚል የተሰባሰቡ የፖለቲካ ፓርቲዎች የህግ የበላይነትን ካላከበሩ፤ ተራው ዜጋ እንደምን አርአያነታቸውን ተቀብሎ ሊያከብር ይችላል?… በመጀመሪያ ህዝቡን ሳይወክሉ የህጎች ሁሉ የበላይ ህግ በሆነው ህገ መንግስት ዙሪያ አተካራ ውስጥ መግባት የራስን ጊዜ ቀርጥፎ ከመብላት ባሻገር፤ ከፈረሱ የቀደመ ጋሪ አይሆንምን?…

በተለያዩ ወቅቶች ከሚነሱ ጉዳዩች እንደተረዳሁት፤ ከውጭ የገቡ የፖለቲካ ፓርቲዎች (ሁሉም ባይሆኑ በአመዛኙ) ከሚያነሷቸው ሃሳቦች ውስጥ አንዱ የሽግገር መንግስት ጉዳይ ነው። ለዚህ ጥያቄ ምላሽ ይሆን ዘንድ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ከዳያስፖራው ጋር ለመነጋገር ወደ አሜሪካ ባቀኑበት ወቅት፤ “እኔ አሻግራችኋለሁ” የሚል ምላሽ መስጠታቸውን አስታውሳለሁ። ይህ ማለት ደግሞ፤ “የሽግግር መንግስት አያስፈልግም፤ በህገ መንግስቱ መሰረት ተወዳድራችሁ ካሸነፋችሁ የራሳችሁን መንግስት መመስረት ትችላላችሁ” ማለት እንደሆነ፤ እንኳንስ በፖለቲካ ስራ ጥርሳቸውን ለነቀሉት ሃይሎች ይቅርና ለእኔም ለተራው ዜጋ በቀላሉ የሚገባኝ ነው።

ያም ሆኖ፤ በአሁኑ ወቅት፤ ‘የሽግግር መንግስት ያስፈልገናል’ የሚሉ አካላት ካሉ፤ አሁንም ጉዳዩ የህገ መንግስት ግንዛቤ አመክንዩ ከመሆን የሚዘል አይመስለኝም። እንደሚታወቀው፤ ምርጫው ትክክል ይሁንም አይሁን፤ በሀገሪቱ ህገ መንግስት መሰረት ኢህአዴግ ሀገሪቱን እንዲመራ ተመርጧል። ወይም በህጉ መሰረት ሀገር እየመራ ነው። ኢህዴግ መንግስት የመሰረተ ገዥ ፓርቲ ነው። ፓረቲው እዚህ ሀገር ውስጥ ህጋዊ መንግስት እየመራ ነው። በውጭ የሚገኙ የፖለቲካ ፓርቲዎችን ‘ኑ!..በዴሞክራሲያዊ መንገድ ለሀገራችን አብረን እንስራ’ የሚል ግብዣን አቅርቦ የጠራቸው ህጋዊ መንግስት ባለበት ሀገር ውስጥ ‘የሽግግር መንግስት’ እንመስርት የሚል ጥያቄ አስቂኝ ነው የሚሆነው።

ሁላችንም እንደምንገነዘበው፤ የሽግግር መንግስት የሚመሰረተው ሀገር ችግር ውስጥ ስትሆንና ያለው መንግስት መምራት ሲያቅተው ነው። ኢትዮጵያ ውስጥ ያለው መንግስትን የሚመራው ኢህአዴግ ግን በውስጡ ለውጥ አካሂዶ በተለይ ላለፉት አምስት ወራት ሀገሪቱን ወደ አንፃራዊ ሰላም መውሰድ የቻለ ነው። ኧረ እንዲያውም በአሸባሪነት ተፈርጀው የነበሩ የፖለቲካ ድርጅቶችን በሰላም ወደ ሀገራቸው እንዲገቡ ያደረገም ጭምር ነው።

በህዝቡ የባለቤትነት መንፈስ እውን የሆነውን ለውጥም እየመራ ሀገራዊና ቀጣናዊ ብሎም አህጉራዊ ሰላምን ለማረጋገጥ እየሰራ ነው። “የኦቦ ለማ ቲም” እየተባለ የሚጠራው የለውጥ ኃይል ከታጋሽነቱ ባሻገር፤ እዚህ ሀገር ውስጥ ሊከሰቱ የሚችሉ ማናቸውንም ችግሮች መፍታት የሚችል አቅምና ብቃት ያለው መሆኑን ሁሉም ወገን የሚገነዘበው ይመስለኛል።

እናም በእኔ እምነት፤ የሽግግር መንግስት የሚባል እሳቤ፤ ከአፍቅሮተ-ስልጣን ወይም በአቋራጭ የስልጣን እርካብ ላይ ለመውጣት ከማለም የመነጨ ሊሆን ይችላል ብዬ አስባለሁ። ይህ ደግሞ፤ በምርጫ ተወዳድሮ ማሸነፍን መሰረት ያደረገውን ሀገ መንግስት መገዳደርና ከፍ ሲልም በህገ መንግስቱ ለመገዛት ያለመፈለግ ዝንባሌ ይመስለኛል። እንዲህ ዓይነቱ ዝንባሌ ከህዝብ ጋር ሊያጋጭ የሚችል በመሆኑ ሁሉም ፓርቲዎች አመኔታቸውን እንዳያሳጣቸው ጥንቃቄ ማድረግ ያለባቸው ይመስለኛል።

በህገ መንግስቱ መሰረት አጠቃላይ የሀገሪቱ ምርጫ የሚካሄደው በ2012 ዓ.ም ነው። ግፋ ቢል የአንድ ዓመት ተኩል ዕድሜ ቢቀረው ነው። በዚህ አጭር ጊዜ ውስጥ ፓርቲዎች በቅድሚያ ራሳቸው ህጋዊ ሆነው (የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ከውጭ የመጡ የፖለቲካ ፓርቲዎች እኔ ዘንድ መጥተው አልተመዘገቡም የሚል መግለጫ ማውጣቱን አስታውሳለሁ) በመመዝገብ ያላቸውን ፕሮግራም ከወዲሁ ለህዝብ በማስተዋወቅ ራሳቸውን በምርጫ ተወዳድረው ለማሸነፍ ዝግጁ ማድረግ ይኖርባቸዋል። ከዚህ ውጭ ተሽቀዳድሞ ስለ ህገ መንግስቱና ስለ ሽግግር መንግስት ማውራትና በቃላት ጥይት መታኮስ ጉንጭ አልፋ ከመሆን የሚዘል አይሆንም። ለዚህም ነው—የአቶ ጃዋር “አንዲትም ቃል ከህገ መንግስቱ መቀነስ አይቻልም!” የሚለውን አስተሳሰብ ከህገ መንግስታዊነት አኳያ እጋራዋለሁ የምለው። ሰናይ ጊዜ ለሁላችን!  

       

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy