Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

ኢሕአዴግ ከአብዮታዊ ዴሞክራሲ ወዴት?

0 1,578

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

‹‹ኢሕአዴግ በአብዮታዊ ዴሞክራሲ ፕሮግራም የሚመራና በፕሮግራሙ ላይ ለሰፈሩት ዓላማዎች የሚታገል ድርጅት ነው፡፡ ያነገባቸው ዓላማዎች ዴሞክራሲያዊና አብዮታዊ በመሆናቸው በተግባር ላይ ከዋሉ ኅብረተሰባችንን ከሚገኝበት ድህነትና ኋላ ቀርነት አላቀው ለፍትሕ፣ ለዴሞክራሲና ለብልፅግና ያበቁታል፡፡›› ከላይ የተገለጸው ከኢሕአዴግ መተዳደሪያ ደንብ መግቢያ አንቀጽ ላይ የተወሰደ ነው፡፡

ኢሕአዴግ አብዮታዊ ዴሞክራሲን በርዕዮተ ዓለምነት የተቀበለበት ምክንያት በማኅበራዊ በፖለቲካዊና በኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች ሥር ነቀል ለውጥ በማምጣት ዕድገትን በፍጥነት ለማረጋገጥ በመተለም መሆኑን፣ አቶ በረከት ስሞኦን በቅርቡ ባሳተሙት ‹‹ትንሳዔ ዘ ኢትዮጵያ›› መጽሐፋቸው ላይ ይገልጻሉ፡፡

የብሔር ብሔረሰቦች የቋንቋ፣ የባህልና የታሪክ እኩልነት፣ እንዲሁም ራሳቸውን በራሳቸው የማስተዳደር መብትና ጥቅም በተሟላ ደረጃ ለማስከበርና ውጤቱንም ለማስገኘት የሚቻለው፣ አሮጌውን ሥርዓት ከእነ አፋኝ ተቋማቱ በመጠራረግ ወይም ሥርዓቱ ፈጽሞ እንዳያንሰራራ አድርጎ ማስወገድ ሲቻል መሆኑን ያስረዳሉ፡፡

በኢትዮጵያ አብዮታዊ ዴሞክራሲን አስፈላጊ ያደረገውም አገሪቱ በአምባገነናዊ አገዛዝ ሥር ዴሞክራሲን ተነፍጋ በመቆየቷ መሆኑን ያትታሉ፡፡

በኢትዮጵያ ላለፉት 27 ዓመታት የታየው ፈጣን ኢኮኖሚ ዕድገት የአብዮታዊ ዴሞክራሲ ውጤት መሆኑን በስፋት ይናገራሉ፡፡ በመጋቢት ወር 2010 ዓ.ም. በኢሕአዴግ ውስጥ የነበረውን የሥልጣን ትግል የኦሮሞ ሕዝብን ከጀርባ በማድረግ አሸንፈው ሥልጣን የተቆጣጠሩት የኢሕአዴግ ሊቀመንበርና የአገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር)፣ የአብዮታዊ ዴሞክራሲ ርዕዮተ ዓለም ይዘው አገር ለመምራት ፍላጎት ያላቸው አይመስልም፡፡ ወደ ሥልጣን በመጡ በመጀመርያዎቹ 100 ቀናት ውስጥ ያሳለፏቸው ውሳኔዎች የዚህ መገለጫ ምልክቶች ተደርገው ሊቆጠሩ ይችላሉ፡፡

በዋናነትም ግዙፉ የኢኮኖሚ አቅም የሆኑ በርካታ የመንግሥት ድርጅቶችን በከፊልና ሙሉ በሙሉ ለግል ባሀብቶች ለማዘዋወር፣ እንዲሁም ተፅዕኖ ፈጣሪ የሆኑ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ከስደት ወደ አገር ቤት ተመልሰው በሰላማዊ መንገድ የፖለቲካ ፉክክር ውስጥ እንዲሳተፉ ያሳለፏቸው ውሳኔዎችና በተግባርም መታየት መጀመራቸው ሊጠቀሱ የሚችሉ ማሳያዎች ናቸው፡፡

ኢሕአዴግ ለፈጠረው ግንባር ዘልቆ እንዲቆይና ውጤታማ ተግባር እንዲፈጽም ያደረገው ዋናው መሣሪያ አብዮታዊ ዴሞክራሲ፣ የፖለቲካ ፕሮግራሙ እንደሆነ  አንድርያስ እሸቴ (ፕሮፌሰር) ይናገራሉ፡፡ ከጥቂት ሳምንታት በፊት የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲና ፎረም ኦፍ ፌዴሬሽንስ፣ ‹‹የኢትዮጵያ ፌዴራሊዝም አዲስ ፈተናዎች›› በሚል ርዕስ በጋራ ባዘጋጁት የውይይት መድረክ ላይ ባቀረቡት ጽሑፍ፣ ኢሕአዴግ ዋናው መሣሪያውን (አብዮታዊ ዴሞክራሲን) ትቶ ወደ ሌላ የፖለቲካ ፕሮግራም በመሸጋገር ላይ የሚገኝ እንደሚመስላቸው ተናግረዋል፡፡ ‹‹ቁልጭ ብሎና ጉልህ ሆኖ ባይወጣም ምልክቶች ይታያሉ፤›› ብለዋል፡፡

በአዲስ አበባ በሚገኝ አንድ ዓለም አቀፍ ተቋም ውስጥ የፖለቲካ ጉዳዮች አማካሪ በመሆናቸው ስማቸው እንዳይገለጽ የጠየቁ አንድ የፖለቲካ ተንታኝም፣ ኢሕአዴግ አብዮታዊ ዴሞክራሲን በመተው ወደ አዲስ የፖለቲካ ፕሮግራም በመሸጋገር ሒደት ላይ ስለመሆኑ ከበቂ በላይ ምልክቶች በመታየት ላይ መሆናቸውን ያስረዳሉ፡፡

ኢሕአዴግ አብዮታዊ ዴሞክራሲን ሲተገብር ለዜጎች መብት ቅድሚያ ከመስጠት ይልቅ፣ የአገሪቱን ደኅንነትና ሰላም እንደሚያስቀድም፣ የመንግሥትንና የፓርቲያቸውን መሠረታዊ ምሰሶዎች የሚጠይቁ የፖለቲካ ፓርቲዎችን፣ የሲቪክ ማኅበራትን እንዲሁም ተፅዕኖ ፈጣሪ ግለሰቦችን ሕግ በማውጣት እንዲገለሉ፣ አልያም ከአገር እንዲወጡ፣ እነዚህን የማይቀበሉትን ደግሞ እስር ቤት በመወርወር ከሁለት አሠርት ዓመታት በላይ መጓዙን ያስረዳሉ፡፡

አሁን ግን ጽንፍ የወጣ የፖለቲካ አስተሳሰብ ያላቸውም ሆነ ነፍጥ አንግበው ሲታገሉ የነበሩትን ወደ አገር እንዲገቡ በማድረግ ላይ በመሆኑ፣ አብዮታዊ ዴሞክራሲን ትቶ ወደ ሌላ የፖለቲካ ሽግግር ላይ ስለመሆኑ ማሳያ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

የልማታዊ መንግሥት ማስፈጸሚያ የነበሩ ተቋማትን ለግሉ ዘርፍ ለማስተላለፍ መወሰኑ፣ እንዲሁም በጠቅላይ ሚኒስትሩ ዙሪያ በአማካሪነት የተሰበሰቡ ወይም በእሳቸው ይሁንታ ሹመት እያገኙ ያሉ ባለሥልጣናት ባህሪና የሥራ ልምድ፣ ከአብዮታዊ ዴሞክራሲ ጎራ የሚመደብ አለመሆኑ ሌላኛው ማሳያ መሆኑን ይገልጻሉ፡፡

‹‹ሌላው ኢሕአዴግ አብዮታዊ ዴሞክራሲን በመላ አገሪቱ ለመተግበር እንደ ማስፈጸሚያ የተጠቀመው ዴሞክራሲያዊ ማዕከላዊነትን ነው፡፡ ይህም የልማታዊ መንግሥት ፕሮግራሞችን ከመተግበር ባለፈ፣ ከብሔር ተኮር ፌዴራሊዝም ፀንቶ እንዲቆይ በመሣሪያነት አገልግሏል፤›› ያሉት የፖለቲካ ተንታኙ፣ ‹‹አሁን ግን ዴሞክራሲያዊ ማዕከላዊነት በመናድ ላይ መሆኑ በግልጽ ታይቷል፤›› ሲሉ የፕሮግራም ሽግግር ወይም ለውጥ ስለመኖሩ ያስረግጣሉ፡፡

ከላይ የተገለጹት ምሁራን ኢሕአዴግ የሽግግር ለውጥ እያደረገ ስለመሆኑ በማሳያነት ከተጠቀሙባቸው ምልክቶች በተጨማሪ፣ የግንባሩ አባል የሆነው የብሔረ አማራ ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ (ብአዴን) ማዕከላዊ ኮሚቴ የሁለት ቀናት ስብሰባ ካደረገ በኋላ፣ ነሐሴ 19 ቀን 2010 ዓ.ም. ለሕዝብ ይፋ ያደረገው መግለጫ የኢሕአዴግ የፖለቲካ ፕሮግራም ያበቃለት ስለመሆኑ በሁለት መንገዶች የሚጠቁም ነው፡፡ አንድም በግልጽ ብአዴን የፖለቲካ ፕሮግራሙን ለመለወጥ ውሳኔ ማሳለፉ ሲሆን፣ ሁለተኛው ደግሞ ከግንባሩ ውጪ በተናጠል የተላለፈ ውሳኔ በመሆኑ ነው፡፡

‹‹የአማራን ሕዝብ ታሪክ፣ ትግል፣ ባህልና ሥነ ልቦና በአግባቡ የተገነዘበና የተረዳ፣ እንዲሁም አሁን ከተፈጠረው አዳጊ የአገራዊና ክልላዊ ሁኔታ ጋር አብሮ የሚራመድ የፖለቲካ ፕሮግራምና መተዳደሪያ ደንብ በማስፈለጉ፣ የሕዝቡንና የአባላቱን ፍላጎት መሠረት በማድረግ ግልጽ በሆነ ተሳትፎ እንዲሻሻል ያደርጋል፤›› በማለት ማዕከላዊ ኮሚቴው መወሰኑን ይፋ አድርጓል፡፡

የኢሕአዴግ መተዳደሪያ ደንብ በመግቢያው ላይ እንዳሰፈረው፣  የኢሕአዴግ አባል ድርጅት መሆን የሚቻለው የአብዮታዊ ዴሞክራሲ ዓላማን በግልጽ በፕሮግራማቸው ላይ የቀረፁ ድርጅቶችን ብቻ መሆኑን፣ ነገር ግን ይኼንን ፕሮግራም መቀበል ብቻ ሳይሆን በተግባር ለፕሮግራሙ ተፈጻሚነት የሚታገሉ፣ አባላቱም ይኼንኑ የሚያሟሉ መሆን እንዳለባቸው በመሥፈርትነት ያስቀምጣል፡፡

ከዚህ በመነሳት ብአዴን ሰሞኑን ባወጣው መግለጫ የሚመራበትን አብዮታዊ ዴሞክራሲ ፕሮግራም ለመቀየር መወሰኑን መግለጹ፣ ሌላው ግልጽና ተጨባጭ ማሳያ ነው፡፡

ይሁን እንጂ ቅዳሜ ነሐሴ 19 ቀን 2010 ዓ.ም. ወደ ሥልጣን ከመጡ ለመጀመርያ ጊዜ ጋዜጣዊ መግለጫ የሰጡት ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ (ዶ/ር)፣ ኢሕአዴግ የፕሮግራም ለውጥ የማድረግ ሒደት ውስጥ እንደሆነ ተጠይቀው ምንም የተለወጠ ነገር አለመኖሩን በተድበሰበሰ መንገድ ገልጸዋል፡፡

ከአብዮታዊ ዴሞክራሲ ወዴት?

ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ (ዶ/ር) ኢሕአዴግ የፖለቲካ ርዕዮተ ዓለሙን የመለወጥ ፍላጎት እንዳለው ለቀረበላቸው ጥያቄ የሰጡት ምላሽ የተድበሰበስ የሚያደርገው፣ ምላሻቸው እስካሁን የተቀየረ ነገር ስላለመኖሩ ወይም አሁን ያለው ሁኔታ ላይ ብቻ የተወሰነ በመሆኑ ነው፡፡

ለዚሁ ጥያቄ የሰጡት ዝርዝር ምላሽ የተጤነ እንደሆነ ግን የፕሮግራም (ርዕዮት) ለውጥ በመጪዎቹ ጊዜያት፣ ወይም ከኢሕአዴግ ጠቅላላ ጉባዔ በኋላ ሊታይ የሚችል እንደሆነ ያመላክታል፡፡

‹‹ኢሕአዴግ በጥልቅ መታደስ አለብኝ ብሎ ወስኗል፡፡ በጥልቅ መታደስ ማለት አርጅቻለሁ፣ ሻግቻለሁ ማለት ነው፤›› ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ‹‹መለወጥ ያስፈልገናል፡፡ እስካሁን ግን አይዲኦሎጂን በሚመለከት የተነሳ ነገር የለም፤›› ሲሉ ምላሽ ሰጥተዋል፡፡

ኢሕአዴግ ቅድሚያ የሚሰጠው ሰላምና ልማትን ማረጋገጥ እንደሆነ፣ ይኼንን የሚጠቅም ሐሳብ እስከመጣ ድረስ እየተቀበሉ መሄድ ያስፈልጋልም ብለዋል፡፡

‹‹እኛ ቆመን ማኅበረሰቡ ከቀደመን ልንመራው አንችልም፡፡ ቢያንስ አንድ ርቀት እየቀደምን ማየት አለብን፡፡ አዳዲስ ሐሳቦችን እየጨመርን መሄድ አለብን፤›› ሲሉ ተናግረዋል፡፡

ያልተመለሰው ጥያቄ ግን ኢሕአዴግ መለወጥ የሚፈልገው ወዴት አቅጣጫ ነው የሚለው ነው፡፡

አንድርያስ (ፕሮፌሰር) ባቀረቡት ጽሑፍ፣ በኢሕአዴግ ውስጥ እየታዩ ያሉ ለውጦች ግንባሩ ወደ ሊበራላዊ ዴሞክራሲ የመሸጋገር አዝማሚያ የሚታዩበት መሆኑን ይጠቅሳሉ፡፡

‹‹ይህ ኒዮ ሊብራሊዝም ከሚባለው አስተያየት የተለየ ነው፡፡ ኒዮ ሊብራሊዝም በአስተዳደር የመንግሥትን ሚና የሚያንኳስስ፣ የነፃ ገበያውንና ዋና ተጠቃሚዎቹን ለከፍተኛ ቦታ የሚዳርግና አብዮታዊም ሆነ ሊበራላዊ ዴሞክራሲን የሚቃረን ነው፤›› ሲሉ ልዩነቱን ይገልጻሉ፡፡

ሽግግሩ ወደ ሊበራል ዴሞክራሲ ከሆነ በሽግግሩ መሳካት የኢንዱስትሪያዊ ኢኮኖሚ መስፋፋት፣ በዚያውም የመካከለኛ ገቢና የኢንዱስትሪ ሠራተኞች መደብ ማደግና መደራጀት መለኪያዎች እንደሚሆኑ ያስረዳሉ፡፡

ስማቸውን መግለጽ ያልፈለጉት የፖለቲካ ተንታኝም፣ እየታዩ ያሉ ምልክቶች የሊበራል ዴሞክራሲ መሆናቸውን በመግለጽ ከፕሮፌሰር አንድርያስ ጋር ይስማማሉ፡፡

‹‹ለአብዮታዊ ዴሞክራሲ ማስፈጸሚያ ጥቅም ላይ ሲውሉ የነበሩ ሥልቶችን በመተው፣ የሊበራል ዴሞክራሲ መገለጫ የሆነ ለምሳሌ ሚዲያዎችን ክፍት ማድረግ፣ የአውራ ፓርቲነት ዝንባሌን ከማስጠበቅ ይልቅ የፖለቲካ ውድድርን ለሁሉም ክፍት ማድረግና የመሳሰሉት መገለጫዎች ናቸው፤›› ብለዋል፡፡

ወደ ግል ይዞታ እንዲዘዋወሩ ውሳኔ የተላለፋባቸው ቁልፍ ተቋማት ላይ መንግሥት የበላይ ድርሻ ለመያዝ መፈለጉ ኢኮኖሚውን ለሁሉም ክፍት (ሊበራላይዝ) የማድረግ ፍላጎት የሌለው፣ ይህም የልማታዊ መንግሥት ሚናን የመተው ፍላጎት እንደሌለው የሚያሳይ በመሆኑ፣ ወደ ኒዮ ሊበራሊዝም የመሄድ ፍላጎት አለመኖሩን እንደሚጠቁም እኚሁ ተንታኝ ተናግረዋል፡፡

ብአዴን ሰሞኑን ባካሄደው የማዕከላዊ ኮሚቴ ስብሰባ ድርጅቱ የሚመራበትን አብዮታዊ ዴሞክራሲ ፕሮግራም በመለወጥ ከጊዜውና ከሕዝቦች ፍላጎት ጋር ወደ ሚስማማ ፕሮግራም ለመሸጋገር ይወስን እንጂ፣ ወዴት አቅጣጫ መሄድ እንዳለበት አለመወሰኑን የድርጅቱ ማዕከላዊ ኮሚቴ ጽሕፈት ቤት ምክትል ኃላፊ አቶ ምግባሩ ከበደ ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡

‹‹ድርጅቱ በሚመራበት የአብዮታዊ ዴሞክራሲ ፕሮግራም ላይ ጥያቄዎች ከውስጥም ከውጭም ምሁራንን ጨምሮ እየተነሱ ነው፡፡ ይህ ፕሮግራም በአገር አቀፍ ደረጃ ካለው ነባራዊ የፖለቲካ ሁኔታ አንፃር ረዥም ርቀት ለማስኬድ ፍቱን ምርጫ ባለመሆኑ፣ አዲስ መስመር መከተል እንደሚገባ ተወስኗል፤›› ብለዋል፡፡

በዚህ ውይይት ላይ አብዮታዊ ዴሞክራሲን ይዞ መቀጠል ይቻላል የሚሉ ሐሳቦች የተንፀባረቁ ቢሆንም፣ በአመዛኙ ግን በአዲስ ፕሮግራም መመራት እንደሚገባ ይኼንን አዲስ ፕሮግራም የመወሰን ኃላፊነት ግን በመጪው መስከረም 2011 ዓ.ም. የሚካሄደው የድርጅቱ ጠቅላላ ጉባዔ እንደሚሆን አቶ ምግባሩ ተናግረዋል፡፡

ይሁን እንጂ የተለያዩ አማራጭ የፖለቲካ ፕሮግራሞች በማዕከላዊ ኮሚቴው ውይይት ወቅት መቅረባቸውን ጠቁመዋል፡፡

ከእነዚህ ውስጥ አንዱ የሊብራል ዴሞክራሲ ቢሆንም፣ ሶሻል ዴሞክራሲ እንዲሁም ልማታዊ ዴሞክራሲ በአማራጭነት ውይይት የተደረገባቸው መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

ብአዴን ፕሮግራሙን ለመለወጥ እንቅስቃሴ ማድረጉ ከኢሕአዴግ ማፈንገጡን እንደማያመላክት የሚከራከሩት አቶ ምግባሩ፣ የኢሕአዴግ የፖለቲካ ፕሮግራም ከኢሕአዴግ ብቻ መንጭቶ ወደ ሌሎቹ የሚንቆረቆር አለመሆኑን ተናግረዋል፡፡

የብአዴን ፍላጎትም አዲስ የፖለቲካ ፕሮግራም ይዞ ለብቻው ተግባራዊ ለማድረግ ሳይሆን፣ ኅብረ ብሔራዊነትን ይዞ እንዲተገበር ፍላጎት ያለው መሆኑን አስረድተዋል፡፡

ብአዴን ፕሮግራሙን ለመለወጥ ፍላጎት ቢያሳይም አቅጣጫው አልታወቀም፡፡ የለውጥ ምልክቶቹ ኢሕአዴግን ወዴት አቅጣጫ እንደሚወስዱት ግልጽ አይደለም፡፡ ሪፖርተር ያነጋገራቸው የፖለቲካ ተንታኞች ግን አዝማሚያው ወደ ሊብራል ዴሞክራሲ አቅጣጫ መሆኑን ይናገራሉ፡፡

ይህ ቢሆንም ሊብራል ዴሞክራሲን ተግባራዊ ለማድረግ በአገሪቱ ያሉ ፖለቲካዊ ባህሪያት አስተሳሰቡን ለመሸከም ብቁ አለመሆናቸውን በመጠቆም፣ ጥንቃቄ መደረግ እንዳለበት ያሳስባሉ፡፡

በትጥቅ ትግል የሚንቀሳቀሱና በፖለቲካ አስተሳሰብ ጽንፍ የነበሩ ፓርቲዎች በቀጣይ በሚደረገው ምርጫ ማሸነፍ ባይችሉ ሊብራል ዴሞክራሲን አዲስ ፕሮግራሙ ያደረገ መንግሥት እንዴት ያስተናግደዋል ሲሉ በመጠየቅ፣ ሽግግሩ ጥንቃቄና ተቋማዊ መሠረትን አስቀድሞ ማከናወን እንዳለበት ያሳስባል፡፡

አንድርያስ (ፕሮፌሰር) በሊብራል ዴሞክራሲ ሥርዓት ውስጥ የብሔር ፌዴራሊዝምና በዚህ መንገድ የተደራጁ ክልሎች የአስተዳደርና የኢኮኖሚ ነፃነት መብቶች እንዴት ይስተናገዳሉ የሚል ጥያቄ ያነሳሉ፡፡ ይህ ለሊብራል ዴሞክራሲ እንግዳ በመሆኑ ጥንቃቄ ያስፈልጋል ይላሉ፡፡

FacebookTwitterLinkedInShare

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy