Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

ካለሰላም አይበጅም

0 404

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

ካለሰላም አይበጅም

ኢብሳ ነመራ

በደልን – የዴሞክራሲና የመልካም አስተዳደር እጥረትን፣ የሰብአዊ መብት ጥሰትን፣ ምዝበራን በመቃወም የሚነሱ ህዝባዊ ንቅናቄዎች በአግባቡ ካልተገሩ ውጤታቸው ከህዝብ ፍላጎት በተቃራኒ ሊሆን ይችላል። ይህን የዓለማችን የቅርብ ጊዜ ታሪክ አሳይቶናል።  በሶሪያ የአል አሳድን አምባገነናዊ ሥርአት በመቃወም በሃገሪቱ የተለያዩ ከተሞች ታላቅ ህዝባዊ ንቅናቄ ተቀስቅሶ እንደነበረ ይታወሳል። ይህ ህዝባዊ ንቅናቄ ግን ሥርቱን ማስወገድ ካለማስቻሉም በተጨማሪ፣ ሥርአቱን እንቃወማለን የሚሉ የተለያዩ ትናንሽ ታጣቂ ቡድኖች እንዲፈለፈሉ አድርጓል። በርዕዮተ አለም ልዩነት መነሻ የሶሪያን መንግስት የማይደግፉ ምእራባውያን ሃገራት፣ እነዚህን ትናንሽ ታጣቂ ቡድኖች መሳሪያ አስታጥቀው ከሶሪያ መንግስት ሃይል ጋር ያካሄዱት ውጊያ እየተጠናከረ ሄዶ የሃገሪቱን መንግስት ህግ የማስከበር ጉልበቱ አዝለውት ነበር። በዚህ መሃከል በተመሳሳይ ሁኔታ የህግ የበላይነት ማስከበር የማይችል መንግስት ተፈጥሮባት በነበረችው ኢራቅ የተወለደ እስላማዊ ቡድን ወደሶሪያም ዘልቆ የሶሪያና ኢራቅ እስላማዊ መንግስት (Islamic State of Iraq and Syria/ISIS) በሚል ስያሜ ገንኖ ወጣ። ከዚህ በኋላ ሶሪያ እንኳን ቀደሞ የታሰበላት ዴሞክራሲ ሊመጣ ከሁለተኛ የዓለም ጦርነት ወዲህ ዓለማችን ባላስተናገደችው ሁኔታ ዜጎቿ በገፍ ለረሃብ፣ ሰደት፣ ሞት የተጋለጡበት  የስቃይና ዋይታ ሃገር ሆነች።

በሊቢያም ተመሳሳይ ሁኔታ አጋጥሟል። ሊቢያውያን የሙኡመር ጋዳፊን አምባገነናዊ መንግስት ለማስወገድ የጀመሩት ህዝባዊ ንቅናቄ በምእራባውያን የአውሮፕላንና የሚሳኢል ድበደባ ታግዞ ጋዳፊን ከስልጣን አስወግዷል። ይሁን እንጂ በምትኩ ዴሞክራሲያዊ ሥርአት አልተገነባም። ከዚህ ይልቅ ሥርአቱን ለማስወገድ በተደረገው እንቅስቃሴ መሳሪያ ታጥቀው በየጎበዝ አለቃቸው እየተመሩ ይታገሉ የነበሩ ቡድኖች በየፊናቸው ግዛት ተቆጣጥረው በሊቢያ የህግ የበላይነት የጠፋበት ሥርአተ አልበኝነት እንዲሰፍን አድርገዋል። ይህ ሥረአተ አልበኝነት ሊቢያን የስቃይ ሃገር አድርጓታል። ይህ ሁኔታ አሁንም አልተቀየረም።

በጽሁፉ መግቢያ ላይ ህዝባዊ ንቅናቄዎች ሁኔታዎችን አስቀድሞ በመረዳት በጥንቃቄ ተገረተው ካለተመሩ የተፈለገውን ሳይሆን ተቃራኒ ወጤት ሊያስከትሉ ይችላሉ ያልኩት ይህን ተጨባጭ ሁኔታ ከግንዛቤ በማስገባት መሆኑ ይታወቅልኝ።

በኢትዮጵያም በ2008 ዓ/ም መግቢያ ላይ በተለያዩ የሃገሪቱ አካባቢዎች በተለይ በኦሮሚያ በአመዛኙ ወጣቶች የተሳተፉባቸው የአደባባይ ህዝባዊ ተቃውሞዎች ተቀስቅሰው እንደነበረ ይታወሳል። የእነዚህ ህዝባዊ ተቃውሞዎች መነሻ የመልካም አስተዳደር ጉድለት፣ የፖለቲካ ምህዳር መጥበብ፣ ፍትሃዊ የሃብት ክፍፍልና ተጠቃሚነት እጦት፣ ምዝበራ ወዘተ ነበር። ይህ ህዝባዊ ተቃውሞ እያደረ ከመብረድ ይልቅ እየተጋጋለ በሌሎችም ክልሎች ተገቢ የሆነም ያልሆነም አጀንዳዎችን ሰበብ እያደረገ የተቀጣጠለበት ሁኔታ እንደነበረም ይታወሳል።

ይሄኔ፣ አስቀድሞም በሃገሪቱ ያለው የኪራይ ሰብሳቢነትና የመልካም አስተዳደር ችግር የሥርአቱ አደጋ የሆነበት ደረጃ ላይ ደርሷል የሚል ግምገማ የነበረው ገዢው ፓርቲ ኢህአዴግ የህዝቡን ቅሬታዎች መፍታት ጊዜ የማይሰጠው ጉዳይ መሆኑን አሳወቀ። ህዝባዊ ተቃውሞውን የቀሰቀሰው ተገቢ ቅሬታ መሆኑንም አምኖ ህዝቡን ይቅርታ ጠየቀ። ራሱን በጥልቀት መርምሮ በአዲስ መልክ ለመታደስም ግንቦት 2008 ዓ/ም ላይ የጥልቅ ተሃድሶ ፕሮግራም ነድፎ ራሱን የማከም እንቅሰቃሴ ጀመረ።

በጥልቀት የመታደሱ እርምጃ በታወጀ በወራት ውስጥ በኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት ተሃደሶውን በተጨባጭ ማሳየት ያስቻለ እርምጃ መወሰድ ተጀመረ። በኦሮሚያ አዲስ የለውጥ አመራር ወደሃላፊነት መጣ። በተሃደሶ አዲስ የለውጥ አመራር ወደሃላፊነት የማምጣቱ ጉዳይ ዘግይቶም ቢሆን በሌሎች ክልሎችም ታይቷል። በተለይ በትግራይ። በአማራ ክልላዊ መንግስት አዲስ የመሪ ፊት ባይታይም፣ የነበረው አሰላለፉን በሌሎች ክልሎች ከተፈጠረው ጋር አስተካክሏል። በደቡብም እጅግ በጣም ዘግይቶ በቅርቡ አዲስ መሪ ወደሃላፊነት መጥቷል።

ይህ በክልሎች የታየው የተሃድሶ እንቅስቃሴ በፌደራል መንግስት ውስጥ በካቢኔ ደረጃ ሲካሄድ ቆይቶ፣ ጠቅላይ መኒስትር የነበሩት ሃይለማርያም ደሳለኝ ስልጣናቸውን በገዛ ፍቃዳቸው እንዲለቁ ያደረገ ግፊት ፈጠረ። በዚህ አጋጣሚ በተለይ ቀድሞ ስር ነቀል ሊባል የሚችል የተሃደሶ እርምጃ ወስዶ የነበረው የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስትና ክልሉን ሲያስተዳድር የነበረው የኦሮሞ ህዝብ ዴሞክራሲያዊ ድርጅት (ኦህዴድ) አመራሮች ወደፊት መጡ። ይህ ሁኔታ በኦሮሚያ ተጀምሮ የነበረው ጠንከር ያለ የተሃድሶ እርምጃ በፌደራል መንግስት ደረጃ ከተሃድሶም አልፎ የለውጥ ባህሪ እንዲይዝ አደረገ።

በፌደራል መንግስት ውስጥ፣ በገዢው ፓርቲ ኢህአዴግና በአባል ድርጅቶቹ ውስጥ ከ2008 ዓ/ም ማገባደጃ ጀምሮ የተሃድሶ እርምጃ መወሰድ ባይጀመርና ኢህአዴግ ግትር ቢሆን ኖሮ፣ ያልተደራጀው ህዝባዊ ተቃውሞ መንግስትን አዳክሞ ሃገሪቱ በጽሁፉ መግቢያ ላይ እንደተመለከቱት ሶሪያና ሊቢያ የመሆን እድል ይገጥማት የነበረ መሆኑን መገመት አያዳግትም። በመሆኑም የኢህአዴግ ራሱን የማረም ባህል ሃገሪቱን ታድጓታል ማለት ይቻላል። ያም ሆነ ይህ፣ ወደሃላፊነት የመጣው የለውጥ አመራር በተለይ የዴሞክራሲ ምህዳሩን ለማስፋትና የሃገሪቱን ገጽታ እስከማበላሸት ዘልቆ የነበረውን የሰብአዊ መብት አያያዝ የሚያሻሽሉ እርምጃዎችን ወሰደ።

ከእርምጃዎች መሃከል በተለይ የዴሞክራሲ ምህዳሩን ለማስፋት የወሰዳቸው ጉልሆች ናቸው። ከእነዚህ መሃከል ከፖለቲካ ጋር በተያያዘ የወንጀል ጉዳይ ተከሰው ቅጣት የተወሰነባቸውን ፍርደኛ እስረኞችና በክስ ሂደት ላይ የነበሩ ግለሰቦችን በይቅርታና ክሳቸውን በማቋረጥ እንዲፈቱ መደረጉ ተጠቃሽ ነው። በዚህ እርምጃ በፌደራልና በክልሎች በአጠቃላይ እስከ 30 ሺህ ሊደርሱ የሚችሉ ዜጎች ተለቀው ወደቀደሞ ሰላማዊ ህይወታቸውና የፖለቲካ እንቅስቃሴያቸው እንዲመለሱ ሆኗል። የሰብአዊ መብት አያያዝን በማሻሻል ረገድም በተለይ በማረሚያ ቤቶችና በወንጀል የምርመራ ሂደት ላይ ይፈጸም የነበረውን አስከፊ የሰብአዊ መብት ጥሰቶች በጉልህ ማሻሻል የሚያስችሉ እርምጃዎች መወሰዳቸውም ይታወቃል።

ሌላው የፖለቲካ ምህዳሩን ለማስፋት የተወሰደው ጉልህ እርምጃ፣ በውጭ ሃገራት የትጥቅ ትግልን ጨምሮ የፖለቲካ እንቅስቀሴ ሲያካሂዱ የነበሩ ድርጅቶችና ግለሰቦች ወደሃገር ቤት ተመልሰው ሰላማዊ የፖለቲካ እንቅስቀሴ ውስጥ እንዲሳተፉ የቀረበ ጥሪ ነው። በዚህ ጥሪ መሰረት በፊትም የሰላማዊ ፖለቲካ ጥሪ ሲያቀርብ የነበረው በአንጋፋ የኦሮሞ ነጻነት ታጋዮች የሚመራው የኦሮሞ ዴሞክራሲያዊ ግንባር (ኦዴግ) ከነአመራሮቹ ወደሃገር ቤት በመግባት ቀዳሚነቱን ይዟል። ይህን ተከትሎ በጀነራል ከማል ገልቹ የሚመራው የኦሮሞ ነጻነት አንድነት ግንባር (ኦነአግ) እና ሌሎችም የኦሮሞ ነጻነት ታጋይ ግለሰቦች ወደሃገር ቤት ገቡ።

በሃገሪቱ የጸረሽብርተኝነት አዋጅ መሰረት በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በሽብርተኝነት የተፈረጁት የኦሮሞ ነጻነት ግንባር (ኦነግ)፣ የኦጋዴን ብሄራዊ ነጻነት ግንባር (ኦበነግ) እና ግንቦት 7 የተባሉት ድርጅቶችም ወደሃገር ቤት መግባት እንዲችሉ የሽብርተኝነት ፍረጃቸው ተነሳ። በአዲስ መልክ ግልጽ ሆኖ በተዘጋጀ የምህረት አዋጅ መሰረት ለቡድኖቹ ምህረት ተደረገላቸው።

በዚህ መሰረት ከ1960ዎቹ መጀመሪያ አንስቶ ለኦሮሞ ህዝብ ነጻነት በመታገል በሚታወቁት አቶ ዳዉድ ኢብሳ የሚመራው የኦሮሞ ነጻነት ግንባር (ኦነግ) በአስመራ ከመንግስት ጋር ድርድር በማደረግ ወደሃገር ቤት ለመመለስ ተስማማ። በስምምነቱ መሰረት የተወሰኑት ከፍተኛ አመራሮቹና የተዋጊ ሃይሉ አባላት ወደሃገር ቤት ገብተዋል። አቶ ዳዉድ ኢብሳም በቅርቡ ወደሃገር ቤት ይገባሉ ተብሎ ይጠበቃል። ኦነግ በሃገር ቤት ሰላማዊ የፖለቲካ እንቅስቃሴ ማድረግም ጀምሯል። ሰሞኑን ወደኢትዮጵያ የገባው የኦነግ ልዑካን ቡድን አባል የሆኑት ኢብሳ ነገዎ የተባሉት የግንባሩ አመራር፣ በሃገር ቤት ሰላማዊ የፖለቲካ እንቅስቀሴ ሲያደርግ ከቆየውና በዶ/ር መረራ ጉዲና ከሚመራው የኦሮሞ ፌደራላዊ ኮንግሬስ (ኦፌኮ) ጋር ለመጣመር ውይይት መጀመራቸውን አስታውቀዋል። ይህ የሚደነቅ የሰላማዊ ፖለቲካ እርምጃ ነው።

በተመሳሳይ የፌደራል መንግስት ከፍተኛ አመራሮች ከግንቦት 7 ጋር ድርድር አካሂደው ድርጅቱ ወደሃገር ቤት ለመግባት ተስማምቷል። ሰሞኑን በትጥቅ ትግል ላይ የነበሩ አባላቱና ሰራዊቱ በሰሜን ምዕራብ በኩል ከኤርትራ ወደኢትዮጵያ እየገቡ መሆኑን ሰምተናል። የግንቦት 7 ከፍተኛ አመራሮች ሰሞኑን አዲስ አበባ ይገባሉ ተብሎ ይጠበቃል። በቅርቡ ደግሞ የኢፌዴሪ መንግስት ተወካዮች ከትግራይ ህዝብ ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ (ትህዴን) ጋር በአስመራ ድርድር አካሂደው ንቅናቄው ወደሃገር ቤት ለመግባት ተስማምቷል። የአማራ ክልላዊ መንግስት ልዑካንም በኤርትራ የትጥቅ ትግል በማካሄድ ላይ ከነበረው የአማራ ነጻነት ንቅናቄ ከተሰኘ ድርጅት ጋር ድርድር ማድረጋቸውንና ድርጅቱ ወደሃገር ቤት ለመገባት መወሰኑን ሰምተናል። በውጭ ሃገር ይኖሩ የነበሩ ታዋቂ ፖለቲከኞች፣ አክቲቪስቶችም መንግስት ባደረገው ጥሪ መሰረት ወደሃገር ቤት ገብተዋል።

ከላይ የተጠቀሱት በሃገሪቱ ህዝባዊ የተቃውሞ እንቅስቃሴ አስነስተው ለነበሩ የዴሞክራሲ ምህዳር መጥበብና የሰብአዊ መብት ጥሰት ጉዳዮች የተሰጡ ምላሾች በህዝቡ ዘንድ ተሰፋ ፈጥረዋል። ለእነዚህ ፖለቲካዊ ጉዳዮች የተሰጠው ምላሽ በልማት ተጠቃሚነት ዙሪያ የተነሱ ኢኮኖሚያዊ ጥያቄዎችም በጊዜ ሂደት መፍትሄ ያገኛሉ የሚል እምነት አሳድሯል። በአጠቃላይ በህዝቡ ዘንድ መጪው ጊዜ ብሩህ ሊሆን ይችላል የሚል ተስፋ ይታያል።

ይሁን እንጂ፣ አሁንም አልፎ አልፎ ግጭቶች ያጋጥማሉ። የተቃወሞ እንቅስቃሴውን ሲያካሂዱ በነበሩ ወጣቶች ስም – በኦሮሚያ ቄሮ በአማራ ፋኖ ስም የሚንቃሰቀሱ ቡድኖች እጅግ አስነዋሪና አሰቃሲ የሰብአዊ መብት ጥሰት እየፈጸሙ ነው። ሰዎች በማንነታቸው ብቻ በድንጋይ ተወግረው የሚገደሉበት አጋጣሚ የተለመደ ሆኗል። የመሬት ወረራ፣ ህገወጥ ግንባታ፣ ተሽከርካሪ አቁሞ የመዝረፍ ወንጀል የተለመደ ሆኗል። በአንድ ወገን ስለእርቅ፣ ፍቅርና መደመር እየተነገረ፤ በሌላ ወገን ከዚህ ቀደም በሃገሪቱ ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ የብሄር ጥላቻ እየተሰበከና በድርጊትም እየተገለጸ ይገኛል።

ይህ በቡድን  የሚፈጸም የሰብአዊ መብት ጥሰትና የዘረፋ ወንጀል በጊዜ ካልታረመ ፖለቲካን ሽፋን አድርጎ በተደራጀ መልክ በመሳሪያ ሃይል ወደሚካሄድ የወንጀል እንቅስቃሴነት ማምራቱ አይቀሬ ነው። በተለይ በትጥቅ ትግል ላይ የነበሩ ድርጅቶች ከነታጠቀ ሰራዊታቸው ህዝብ ውስጥ እንዲገቡ ከመደረጉ ጋር ተያይዞ፣ በሶሪያና ሊቢያ እንደሆነው በየአካባቢው በተደራጁ ታጣቂ ቡድኖች የሚካሄድ የእርስ በርስ ግጭት ሊነሳ የሚችልበት እድል አለ።

በአጠቃላይ፤ በሃገሪቱ ሰላምና የህግ የበላይነትን ማረጋገጥ ካልተቻለ የተሟላ ዴሞክራሲያዊ ስርአት የመገነባት፣ የዜጎች ሰብአዊ መብቶች በማንኛውም ወገን እንዳይጣሱ የማረጋጋጥ፣ የመልማትና ህዝቡን የልማት ተጠቃሚ የማድረግ ራዕይ በሙሉ ህልም ሆኖ ነው የሚቀረው። በሶሪያና በሊቢያ እንደሆነው የታሰበው ዴሞክራሲና ልማት ሳይሆን፣ የማይፈለገው እልቂትና ሰቆቃ ሊነግስ ይችላል። እናም የኢትዮጵያ ህዝብ በተለይ ወጣቱ ካለሰላም እንደማይበጅ አውቆ ሰላምን ለማስከበር መንቃት አለበት። መንግስትም ለጥላቻና ለግጭት ሰበብ ሊሆኑ የሚችሉ ቀዳዳዎችን መክፈት የለበትም። የተከፈቱትም ሰፈተው መድፈን የማይቻልበት ደረጃ ላይ ከመድረሳቸው በፊት በጠባብነት እድሜያቸው ሊወትፋቸው ይገባል። ካለሰላም አይበጅም።

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy