Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

ክረምቱንና ተግዳሮቶቹን…

0 408

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

ክረምቱንና ተግዳሮቶቹን…

                                                     ይሁን ታፈረ

ባለንበት የክረምት ወቅት ህብረተሳቡ ከተላላፊ በሽታዎችና ከጎርፍ አደጋዎች ጥንቃቄ በማድረግ የክረምቱ የልማት ስራ እንዳይስተጓጎል ማገዝ አለበት። በያዝነው የመስከረም ወርም ጠንካራ ዝናብና ጎርፍ እንደሚኖር ብሔራዊ የሜትሮሎጂ ድርጅት ትንበያ ያመለክታል። ስለሆነም አርሶ አደሩ ጥንቃቄ በማድረግ በግብርና ስራው ምርትን ለማሳደግ እየተካሄዱ ባሉ እንቅስቃሴዎችን ላይ ማተኮር ይኖርበታል።

በየአካባቢው እያጋጠመ ያለውን የጎርፍ አደጋ በቅድሚያ ለመከላከል በመንግስት በኩል እየተወሰደ ያለውን እርምጃ በመደገፍ ምርትና ምርታማነቱ በተሻለ መንገድ እንዲያድግ መጣር ይኖርበታል። እናም ክረምቱና ተግዳራቶቹ ሊያስከትሉት የሚችሉትን ጫና በመገንዘብ፣ በተጠናከረ ሁኔታ ፊቱን ወደ ምርታማነት በማዞር አለበት።

የሚፈለገውን ያህል ባይሆንም ባለፉት ጊዜያት ምርትና ምርታማነት በማደጉ ሳቢያ የአርሶ አደሩ ህይወት በአያሌው ተለውጧል። እንዲያውም በአንዳንድ አካባቢ የሚገኙት አርሶ አደሮች ትርፍ አምራች እንዲሆኑ አስችሏቸዋል።

ይህ ትርፍ አምራችነታቸውም ከተጠቃሚነታቸው ባሻገር ሌሎች አካባቢዎች በተፈጥሮአዊው የድርቅ አደጋ በሚጠቁበት ወቅት የሚፈጠረውን ክፍተት እንዲሞሉ አድርጓቸዋል። ምርትና ምርታማነት በማደጉ ሳቢያ ከፍተኛ ምርት ማግኘት ይቻላል።

መንግስት አርሶ አደሩም በእሸትና በቡቃያ ደርጃ ያሉ ምርቶችን በአግባቡ የመጠበቅ፣ በየጊዜው ማሳውን የመፈተሽ ሰብሉ በአረም እንዳይጠቃ ክትትል እያደረገ ነው። ይህ ክትትል የጉዳዩ ባለቤት በሆነው አርሶ አደር መደገፍ ይኖርበታል።

እርግጥ በመንግስት በኩል ከፍተኛ ስራዎች እየተከናወኑ ነው። በአሁኑ ሰዓት ተባዮችንና አረሞችን በባህላዊ መንገድ መከላከል ከአቅም በላይ በሚሆንበት ወቅትም ፀረ- ተባይ ኬሚካሎችን በመርጨትና በመከላከል በአሁኑ ሰዓት ምርትን ለማሳደግ የሚመለከታቸው አካላት ሁሉ ርብርብ እያደረጉ ነው።

ከዚህ በተጨማሪ የሰብል ምርቱን ለማሳደግ አዳዲስና ዘመናዊ ቴክኖሎጂዎችን ለአርሶ አደሩ ለማስተዋወቅ ሰፊ ተግባራት እየተከናወኑ ነው። እንዲሁም የአርሶ አደሩን ጉልበት የሚያግዙ የሚደግፉና ጉልበቱን ውጤታማ የሚያደርጉ መጠነኛና አነስተኛ የሜካናይዜሽን ስራዎች እንቅስቃሴ ውስጥ እንዲገባ ጥረት እየተደረገ ነው።

አርአያ የሚኑ አርሶ አደሮች ምርታማነት ደረጃ ላይ የደረሱ በርከት ያሉ አርሶ አደሮች ያሉ በመሆኑ የግብርና ምርምር ተቋማትን አቅም በማጐልበትና በማበረታታት እነዚህ አርሶ አደሮች ወደ ግብርና ምርምር ተቋማት የምርታማነት ደረጃ እንዲቀራረቡ ተጨማሪ ፓኬጆች ተዘጋጅተው ርብርብ እየተደረገባቸው ነው።  

የአርሶአደሩን የሰብል ልማት የማስፋትና ምርታማነቱንና ጥራትን ከፍ በማድረግ በገበያ ተወዳዳሪ ከመሆን በተጨማሪ የአትክልትና ፍራፍሬ የማልማት አቅሙን የማሳደግና በዘርፉ እመርታ ለማምጣት እየተሰራ ነው።

አምራቹ አርሶአደር በራሱ፣ ከተማሩ ወጣቶች፣ ከአነስተኛ የግብርና ባለሃብቶች ወይም ከአገር ውስጥና ከውጭ ባለሃብቶች ጋር በመቀናጀት ምርታማነትን እንዲያረጋግጥ እየተሰራ ነው።

ይህን መሰሉ የተቀናጀ አሰራር አነስተኛ ማሳ ላይ የሚያመርቱ አርሶአደሮችን በአካባቢ ስፔሻላይዜሽን እንዲሳተፋ የሚያደርግ እንዲሁም የገበያ፣ የመሰረተ ልማትና ሎጅስቲክስ አቅርቦት ማነቆ እንዳይሆን የሚያግዝ ሆኖ ተገኝቷል።

የሰብል፣ የአትክልትና ፍራፍሬ ልማት ሥራ በቂ እርጥበት ባለበት ሁኔታ እንዲካሄድ ለማድረግ የጀመርነውን የተፈጥሮ ሃብትና የተፋሰስ ልማት ስራ ወደ ሚቀጥለው ደረጃ እንዲሸጋገሩ እየተደረገ ነው።

የውሃ አጠቃቀማችንን በማሻሻልና የመስኖ ሥራ እንደ የአግሮ ኢኮሎጅው ሁኔታ በማካሄድ ምርታማነቱን በማረጋገጥና የግብርና ልማት ዘላቂነትን በማረጋገጥ መስራት ይገባል።

በአርሶ አደር አቅም የሚሰራው የመስኖ ልማት በማጠናከር በትራንስፎርሜሽንና ዘላቂ ልማት ዕቅድ ዘመን ከአራት ሚልዮን ሄክታር በላይ መሬት እንዲለማ ለማድረግ ጥረት እየተደረገ ነው።

እንዲሁም በክልልና በፌዴራል መንግሥት ደረጃ የሚሠሩ አነስተኛና መካከለኛ የመስኖ ልማትና ግድብ እንዲጠናከሩ እየተሰራ ነው። ይህም ምርታማነትን በማሳደግ በኩል የራሱን አስተዋጽኦ ያበረክታል።

መንግስት ግብርናውን በማዘመን ምርትና ምርታማነትን ማስፋት ያስፈልጋል። ምርትና ምርታማነት ሲሰፉና ሲጎለብቱ የድርቅ አደጋ በሚያጋጥምበት ወቅትም ቢሆን ትርፍ ምርት ለመያዝ ይቻላል። ስለሆነም በምርት ላይ አደጋ እንዳይደርስ ማድረግ የድርቅ አደጋን ለመከላከል ያስችላል።

አርሶ አደሩ ከራሱ ተርፎ ለገበያ በማምረት ተጠቃሚ የሚሆንበት ደረጃ ላይ እንዲደርስ፣ አገሪቱም ከግብርናው ዘርፍ ማግኘት የሚገባትን ጥቅም እንድታገኝ ለማድረግ የሚያስችል የለውጥ ጎዳና እንዲፈጠር አድርጓል። ለዚህ ስኬት መንግስት በአጭር ጊዜ ውስጥ እርምጃዎችን እየወሰደ ነው።

አሁንም ቢሆን ባለፉት ጊዜያት የተፈጠረው አቅም ተጠናክሮ እንዲቀጥል መላው አርሶ አደር ግብርናን በማዘመን፣ የተፈጥሮ ሃብትን በመጠበቅ እንዲሁም በመንከባከብና ለአፈር እና ለውሃ ጥበቃ የተሰጠውን ትኩረት ማጎልበት ይኖርበታል።

በተለይም ክረምቱ ሊፈጥረው የሚችለውን ችግር ለአርሶ አደሩ በማሳወቅ የሚመለከታቸውወገኖች ሃላፊነት ነው። ይህን ማድረግ መንግስት እያደረገ ያለውን ምርትን የማሳደግ ተግባርን ማገዝ ነው።

ያም ሆኖ ከላይ የተጠቀሱት መንግስታዊ ተግባሮች በአርሶ አደሩ መታገዝ አለባቸው። አሁን ባለንበት የክረምት ወቅት የሚከሰተውን ጎርፍ እንዲሁም መጤ አረሞችን በመከላከል ቡቃያዎችን ከጥፋት መታደግ ያስፈልጋል።

የክረምቱ ወቅት ጎርፍ ቡቃያዎችን እንዳያበላሽ መተላለፊያ በመስራት፣ የማይታወቁና የሚታወቁ አረሞች ሲከሰቱም ለሚመለከታቸው የግብርና ኤክስቴንሽን ሰራተኞች ፈጥ የማሳወቅና በባህላዊ ዘዴም የሚወገዱ ከሆነም በዚያው መንገድ መከላከል ያስፈልጋል።

ቡቃያዎች ማሳ ላይ እያሉ በጎርፍ ከተጠቁ አልያም በአረም ከተጎዱ የሚፈለገውን ምርት ሊሰጡ አይችሉም። ይህም የአርሶ አደሩን ልፋት ከንቱ የሚያደርገው ከመሆኑም በላይ በአገር ላይ ችግር ያስከትላል። ስለሆነም አርሶ አደሩ የክረምቱንና ተግዳሮቶቹን በጥንቃቄ በማለፍ ለምርታማነቱ ትኩረት መስጠት ይኖርበታል።

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy