NEWS

ዛሬ እየታየ ያለውን ተስፋ ሰጪ ለውጥ ጠብቆ ወደ ተሻለ ደረጃ ማሸጋገር ይጠቃል

By Admin

September 29, 2018

በኦሮሞ ህዝቦቸና በሌሎች የኢትዮጵያ ወንድም ህዝቦች ትግል ዛሬ ላይ የታየውን ተስፋ ሰጪ ለውጥን ጠብቆ ወደ ተሻለ ደረጃ ማሸጋገር እንደሚጠበቅ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ገለጹ።

ጠቅላይ ሚኒስት ዶክተር አብይ የታላቁን የኢሬቻ በዓል ምክንያት በማድረግ የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል።

እሬቻ የፍቅር፣ የአንድነት፣ የይቅርታ እና የውበት እንዲሁም የሰብዓዊ ማንነት ክብር፣ የኦሮሞ ህዝብ አንድነት የሚንጸባረቅበት ቀን ነው ሲሉ ነው የገለጹት።

ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ፤ የጸደይ በረከት መቋደስ የሚቻልበት፣ ወደ አዲስ የድል ምዕራፍ ለመሸጋገር ቃል የሚታደስበት፣ በፍቅር በማቀፍ ጥላቻ የሚሸነፍበት በዓል እንዲሆን በተመኙበት መልዕክታቸው ለውጥን ጠብቆ ወደ ተሻለ ደረጃ የማሸጋገር ጉዳይን አጽንኦት ሰጠውታል።

“አንድነታችንን አጠናክረን የጋራ ቤታችን የሆነችውን ኢትዮጵያ በመገንባት በአዲስ ጎዳና” ማስኬድ ግዴታ መሆኑን የጠቀሱት ጠቅላይ ሚኒስትር  አብይ፤ ለዚህም ኦሮሞ ከገዳ ሥርዓቱ ባገኘው ትውፊት “የግንባር ቀደምነት ሚናውን እንዲያበረክት ታሪክ ያስገድደዋል” ነው ያሉት።

የገዳ ስርዓት ለዘመናዊ አስተዳደር ስርዓት ምንጭ መነሻ መሆኑን ገልጸው፤ የኦሮሞ ሕዝብ “የአቃፊነት እና የአክባሪነት አሴቱን ለትውልድ ለዓለም አበርክቷል” ብለዋል።

“ኦሮሞ አቃፊ እና ዴሞክራሲያዊ ነው ስንል፣ የገዳ ስርዓት ያስተማረንን የአስተዳደር እርከን ተንተርሰን ነው። ኦሮሞ የዘመናዊ ዴሞክራሲ ስርዓት ባለቤት ነው ስንል በየስምንት ዓመቱ ከአንድ አባገዳ ወደ ሌላ አባ ገዳ የሚተላለፈው ሰላማዊ የስልጣን ሽግግር ተምሳሌትነትን ልናስተምርበት ነው” ብለዋል።

ይህ ደግሞ ‘ከሜልባ’ እስከ ‘ምችሌ’ ያለው ስልጣን መተካካትን ዛሬ ላይ ሆኖ ነገን መገንባት የሚቻልበት ተሞክሮ የሚቀሰምበት መሆኑን ነው አጽንኦት የሰጡት።

“ኦሮሞ የሰላም ምንጭ ስንል የስልጣን መተካካት ስርዓቱ ወይም ‘ባሊ ደባርሱ’ ማንነታችንን የሚናገርና አሳታፊነታችንን  የሚያሳይ ነው” ሲሉ የገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ የኦሮሞ ገዳ ጥላቻን የሚጠየፉበት የእርቅ ሥነ ስርዓትና ህግና ስርዓት የሚደነገግበት ልዩ ውበት መሆኑን ጠቁመዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንደገለጹት፤ በፖለቲካው ባህል ላይ እየታየ ያለው ለውጥ ከመነካከስ እና መለያየት ምዕራፍ ወጥቶ የጥላቻ ፖለቲካ ተወግዶ፣ መለያየትና ስም ማጥፋት ላይመለስ እንዲቀበር የዘንድሮ የአሬቻ በዓል ልዩ መልዕክት የሚተላለፍበት መድረክ ይሆናል።

“ለኦሮሞ አንድነት፣ ሰላም ለማስፈን፣ የህግ የበላይነትን ለማረጋገጥ፣ የፌዴራሊዝም ስርዓት ለመገንባት፣ ዴሞክራሲ ለማስፋፋት እና መሰል ጉዳዮችን ለመተግበር ጥሩ መነሻ ሆኖ ያገለግላል” በማለት ነው የዘንድሮን የእሬቻ በዓልን የገለጹት።

አስሩ የገዳ ሥርዓት ደረጃዎች ከህጻንነት እስከ ሽምግልና ወይም ዩባ/ ገደሞጂ ድረስ ባለው ተዋረድ የዴሞክራሲ ስርዓት የሆኑ ሂደቶች የሚንጸባረቁበት መሆኑን አውስተው፤ በገዳ ስርዓት ውስጥ በቅሎ ያደገው፣ የውበትና የፍቅር ተምሳሌት የሆነው እሬቻ ታላቅ ታናሹን በማብቃት፣ ታናሽ ደግሞ ታላቁን በማክበር ለትውልድ እየተወራረሰ ዛሬ ላይ መድረሱን ነው ያተቱት።

የእሬቻ በዓል የኦሮሞ ልዩ ውበትና የኢትዮጵያውያን እንዲሁም የውጭ ዜጎች እና ቱሪስቶች በደስታ  እና በፌሽታ የሚሳተፉበት ልዩ የአንድነት ማጠናከሪያ ስርዓት መሆኑን ገለጸዋል።