የሕዝብ ብሶት የሚያባብሱ ይቀነሱ
“ለዘመናት ለሕዝብ ብሶት ሲታገል የነበረው ጀግናው የኢህአዴግ ሠራዊት ደርግ ሲጠቀምበት የነበረውን ሬዲዮ ጣቢያ ለሰፊው ሕዝብ ጥቅም ተቆጣጥሮታል ግንቦት 29 …” የሚል እንደነበር ትዝ ይለኛል ።
የሕዝብ ብሶት የሚያባብሱ ይቀነሱ
ይቤ ከደጃች. ውቤ
ጀግናው የኢህአዴግ ሠራዊት የዛሬ 27 ዓመት አዲስ አበባ ሲቆጣጠራት ከቤተሰቦቼ “ባቡር መንገድ እንዳትወጣ ” የሚል ጥብቅ ማስጠንቀቂያ ተሰጥቶኝ ነበር። አስፋልት አትውጣ ሲሉኝ ነው። እኔ ግን ተደብቄ ከቤታችን ሦስት ደቂቃ በማትርቀው መርካቶ ሰባተኛ አካባቢ ከአብሮ አደግ ጓደኞቼ ጋር ሄጄ አየሁዋቸው።ተገረምኩ የደርግን ክፋትና ደግነት ባላመዛዝንም ሬዲዮ ሲከፈት ከምሰማው መልዕክት አንፃር “ ታጋዮቹ ” ሰዎችም አልመሰሉኝም ነበር። የደርግ ፕሮፓጋንዳ በታዳጊ አዕምሮዬ ጭራቅ አድርጎ ስሎብኝ ስለነበር ነው።
እነርሱን ለማየት የሚርመሰመሰው ሕዝብ ፣የለበሱት ልብስ ፣የታጠቁት መሣርያ ታንኮቻቸው ሁሉ ለእንደኔ ዓይነቱ ብላቴና አዲስ ነገር ነበሩ። በወቅቱ ለረጅም ሰዐት በሬዲዮ ሲተላለፍ የነበረው መልዕክት “ለዘመናት ለሕዝብ ብሶት ሲታገል የነበረው ጀግናው የኢህአዴግ ሠራዊት ደርግ ሲጠቀምበት የነበረውን ሬዲዮ ጣቢያ ለሰፊው ሕዝብ ጥቅም ተቆጣጥሮታል ግንቦት 29 …” የሚል እንደነበር ትዝ ይለኛል ።
ኢህአዴግ በጤናው ዘርፍ ከሆስፒታል እስከ ጤና ኬላዎች በማቋቋም የጤና ኤክስቴንሽን ባለሙያዎች በነዋሪዎች የቅርብ ቦታዎች በመመደብ በሠራው ሥራ በዓለም አቀፍ ተቋማት ጭምር ምሳሌ መሆን ችሏል። በዚህ ሥራ የኢፌዴሪ ጤና ጥበቃ ሚኒስትር የነበሩት ዶ/ር ቴዎድሮስ አድሃኖም የዓለም ጤና ድርጅት (WHO) ኃላፊ ሆነው መመረጣቸውን አንዘነጋም። በዚህም ለኢትዮጵያ ብሎም ለአፍሪካ የሚያኮራ ሥራ ተከናውኗል።
በትምህርት ዘርፍም በተሠሩት ሥራዎች ህፃናት በአፍ መፍቻ ቋንቋ እንዲማሩ ትምህርት ቤቶችም በየአካባቢው (በአርብቶ አደር አካባቢዎችም ጭምር ከኑሮ ዘያቸው ጋር የሚስማማ) ተደራሽ እንዲሆኑ መደረጉም የሚጠቀስ እንደ ፋኖ የሚያበራ ጉልህ ሥራ መሆኑን ይታወቃል።
ካለፉት 24 ዓመታት ወዲህ ትምህርት በሁሉም አካባቢዎች ተደራሽ በመሆኑ ከ39ሺህ በላይ አንደኛ ደረጃና 3ሺህ300 ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ደርሰዋል። በዚህም ከ28 ሚሊዮን በላይ ተማሪዎች ማስተናገድ ተችሏል።
ከሁለት አሥርት ዓመታት በፊት 4ሺህ ብቻ የነበሩት የመጀመሪያ ደረጃና 278 ሁለተኛ ደረጃ ት/ቤቶች በአጠቃላይ ከሁለት ሚሊዮን ያልበለጡ ተማሪዎችን ያስተምሩ ነበር ይህም ሀገሪቱን በዓለም ላይ በዝቅተኛ የትምህርት ተሳትፎ ከሚጠቀሱት ሀገሮች ተርታ ያሰለፈ እንደነበር የትምህርት ሚ/ር በቅርቡ በትምህርትና ሥልጠና ችግሮችና መፍትሔዎች ዙሪያ ለውውይት ያሳተመው ፍኖተ ካርታ (Road map) ይጠቁማል።
በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ሁለት ብቻ የነበሩት ዩኒቨርስቲዎቻችን በተለያዩ አካባቢዎች ተቋቁመው ወደ 46 አድገዋል።ከዚህ በተጨማሪ 130 የሚሆኑ የግል ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተከፍተው ከፍለው ለመማር ለሚሹ ምቹ ሁኔታ ተፈጥሯል።በዘርፉ ሀገሪቱ ከራሷ አልፎ ከጎረቤት ሀገሮች ሱዳን፣ ጅቡቲና ሶማሊያ ተማሪዎችን ተቀብላ ማስተማርና ማስመረቅ የቻለችበት ዘመን ላይ ደርሳለች።
በሕዳሴው ግድብ ዙሪያም የተሠራው ሥራ ዘወትር ሊጠቀስ የሚችል ሀገሪቱን ከዓለም አቀፍ ተቋማትና ሀገራት ለግድቡ ግንባታ ሲባል ገንዘብ ከመጠበቅ ያላቀቀ ለሌሎች የአፍሪካ ሀገራት ምሳሌ ሊሆን የሚችል በጎ ጅማሬ ነው።በዚህም ነፍስ ሔር ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ መለስ ዜናዊ ለሀገሪቱ ዘመን ተሻጋሪ መሠረትን ጥለው አልፈዋል።
በመንገድ ዝርጋታም በየክልሉ ከተሠሩት የአስፋልት መንገድ ሥራዎች በተጨማሪ የአዲስ አበባ ቀለበት መንገድ፣ የአ∙አ አዳማ ፈጣን መንገድ፣ የአ∙አ ቀላል ባቡር መጓጓዣ እንዲሁም የኢትዮ ጅቡቲ የባበር ሃዲድ ዝርጋታ ተጠቃሽ ሥራዎች ተሠርተዋል። በተለያዩ ከተሞች የተቋቋሙት የኢንዱስትሪ ፓርክ ግንባታዎችና የውጪ ባለሀብት በመሳብ ረገድ እያሳዩት ያለው የተስፋ ጭላንጭል ሊፈጥሩ የሚችሉት የሥራ ዕድል ሊሞገስና ሊወደስ የሚችል ተግባር ነው።
በመግቢያው ላይ እንደ ተጠቀሰው ኢህአዴግ የታገለው ለሕዝብ ብሶት ነው።ነገር ግን በአውራው ፓርቲ ሥር የተሰገሰጉ ነባርም ሆኑ አዳዲስ አባላት ሕዝብን ለማገልገል ተመልምለው ሕዝቡን ገለል አድርገው ራሳቸውንና ቤተሰቦቻቸውን ብሎም ዘመዶቻቸውን ማገልገል ጀመሩ ። በአፍሪካ ትልቁን የጦር ኃይል የደመሰሰው ኢህአዴግ ማንም አያንገዳግደኝም በሚል ለሕዝብ ብሶት ታግሎ የዜጎችን ብሶት ማበስ ሲገባው ወደ ማባባስ ውስጥ ገባ። ምናልባት ከዋሻ ከበረሃና ከሞት መስዋዕትነት ወጥቶ አዲስ ዓለም ውስጥ ስለገባ አልያም ጦር የለመደ እጅ መንበር ሲቆጣጠርና ብር ሲቆጥር መደነጋገር ቢፈጠር ነው ብዬ እገምታለሁ ።
በተለይ አፈሩ ይቅለላቸውና የቀድሞው ጠ/ሚር ታላቁ ታጋይ አቶ መለስ ዜናዊ ካረፉ በኋላ ችግሩ እየተባባሰ ሥርዓተ አልብኝነት እየነገሠ መጣ። ሃይ ባይ እንደሌለበት ድግስ ሁሉም በየፊናው ሙስናውንና ምዝበራውን ተያያዘው። በየጊዜው በፓርቲውም ሆነ በየመሥሪያ ቤት ኃላፊዎች ኪራይ ሰብሳቢነትን ለመዋጋትና መልካም አስተዳደርን ለማስፈን ጥረት እየተደረገ መሆኑን ሲሰጡ የነበሩ መግለጫዎችን መቃኘት ይቻላል። ቃላቶቹ ዘወትር ሲደመጡ በሕዝቡ እየተሰለቹ በመምጣታቸው ከሚዲያ ፍጆታ የዘለለ ሚና አልነበራቸውም።
የተወሰዱ የተወሰኑ ርምጃዎች ቢኖሩም እንኳ ለሌላው ትምህርት መስጠት ያልቻሉ ወደ አንድ ጎን ያዘመሙ ነበሩ ሲሉ የፖለቲካ ሰዎች ቅሬታ ማሰማታቸው ይታወሳል። ፍትሐዊ የሀብት ክፍፍል የሚል ጥያቄና ሌሎችም ተደራርበው መጥተው ባለፉት ሦስት ዓመታት ሀገሪቱ በተለያዩ አካባቢዎች ዐይታ በማታውቀው በሁከትና ቀውስ ስትናጥ ከርማለች። በዚህም የጠፋው የሰዎች ሕይወትና የደረሰው የንብረት ውድመት ቤት ይቁጠረው ማለት ይሻላል።
“ የፉክክር ቤት ሳይዘጋ ያድር ” እንዲሉ የሀገር ንብረት እየመዘበሩ የግል ሀብት ለማፍራት ሲጥሩ የነበሩ አባላት ፓርቲው የታገለበት ፈሩን እንዲስት አድርገውታል።ለዚህ ይሁን ስተው ‘መልካም ምሳሌ’ አድርገው ተከትለውታል ማለት ይቻላል።
ይህን ችግር ለመፍታት በተወሰደ ርምጃ በግምገማ ከኃላፊነታቸውም ሆነ ከአባልነታቸው የተወገዱ፣ በፍርድ ቤት ውሳኔ በእስር የተቀጡ፣ ከሀገር የተሰወሩና የተሰደዱ ፣በማረፊያ ቤት ሆነው የፍርድ ቤት ውሳኔ ሲከታተሉ የነበሩት ብዙ ናቸው። በየጊዜው በሚካሄድ ግምገማ ኪራይ ሰብሳቢነትን ለመዋጋት፣ መልካም አስተዳደርን ለማስፍን እስከ ጥልቅ ተሃድሶ ግምገማ ድረስ ጥረትና ሙከራ መደረጉም ይታወሳል። ነገር ግን የተወሰዱ የመፍትሔ ርምጃዎች ግን ጥልቅ ሳይሆኑ ግልብ እና ለብለብ፣ ለሚድያ ፍጆታ ከመዋል የዘለለ ፋይዳ አልነበራቸውም።
የብሔር ብሔረሰቦች መብት መከበሩ ዜጎች በአፍ መፍቻ ቋንቋ የሚማሩበት መንገድ መመቻቸቱ እያደነቅን ሀገራዊ ስሜት ግን እንዲወድቅ ማድረጋችን ጉልህ ድክመት ነው።ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱን አክብሮ ለማስከበር ያደረግነው ጥረት ደካማ በመሆኑ ኢህአዴግን ዋጋ አስከፍለውታል።ማለትም ከላይ ያሉ ኃላፊዎች ዝሆን የሚያክል ጥፋት ሲፈፅሙ እየታለፉ ትንኝ የሚያክል ጥፋት የሚፈፅሙ ዜጎች ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱን በኃይል ለመናድ ይንቀሳቀሳሉ፣ አሸባሪዎች ናቸው፣ በሙስና ተዘፍቀዋል እየተባለ የታሰሩ፣ የተሰደዱ ብዙዎች ነበሩ።
አንዳንዶቹ “ የመለስን ሌጋሲ እናስቀጥላለን ” የሚሉ ታጋዮች አድርባዮች ነበሩ።ሌጋሲያቸውን ለማስቀጠል ሲጥሩ ሆነ ሲተገብሩ የማይታዩ በአፍ እየደገፉ ፓርቲውን እየተጋፉ የአቶ መለስን ሌጋሲ የሚያደናቅፉና የሚያጨናግፉ እንደ እንቦጭ አረም የተስፋፉበት ዘመን ላይ ደርሰን ነበር። የግል ጥቅማቸው የሚያሳድዱና የሚያስፋፉ የእነቦጭ አረሞችን መንቀል ጊዜ ሊሰጠው አይገባም።የለውጥ ጅምር እንዲሰምር የሕዝብን ብሶት የሚያባብሱ ይቀነሱ ።
ባለንበት በዚህ የለውጥ ዘመን ዶ/ር ዐቢይ አሕመድ በኢህአዴግ ም/ቤት ለጠቅላይ ሚኒስትርነት የታጩትም የአቶ መለስን ሌጋሲ ለማስቀጠል መሆኑ ግልፅ ነው።በዚህ በመደመር ዘመን የሚደነባበሩ ወደ ሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ ጎዳና በሚወስደው ባቡር መሳፈር አለባቸው።“በአንድነት እንደመር በይቅርታ እንሻገር” ብለን በምናከብረው አዲሱ ዘመናችን የታላቁን ታጋይ በጎ ጅማሬዎች ለማስቀጠል ዘወትር መጣር ይጠበቅብናል።