Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

የማይነጣጠሉ ህዝቦች

0 359

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

የማይነጣጠሉ ህዝቦች

                                                   ዋሪ አባፊጣ

የ20 ዓመታት ናፍቆት ድንበር አልገደበውም። ፍቅርና ይቅርታ ተደማምረው የሁለቱን ወገኖች ህዝቦች በማይበጠስ ገመድ እያቆራኟቸው ነው። እናም አንደኛው ወደ ሌላኛው ይነጉዳሉ። ይተምማሉ—የኢትዮጵያና የኤርትራ የድንበር አካባቢ ህዝቦች። በጢያራ ተሳፍረውና አየሩን ሰንጥቀው ከሁለቱም ሀገራት መዲናዎች ከሚነሱት ህዝቦች ባሻገር በድንበር አካባቢ የየሀገራቸውን ባንዴራ በመያዝ የሚጓዙት ወንድማማችና እህትማማች ህዝቦችን መመልከትና በድርሳነ ዜና መስማት አዲስ ክስተት አይደለም። የተለመደ ሆኗል።

የሰሞኑን እንኳን ብንመለከት በትግራይ ክልል ራማ አካባቢና በዛላንባሳ በኩል ከሁለቱም ወገኖች የሚተመው ህዝብ እጅግ አስገራሚ ነው። ይህም በሁለቱም ህዝቦች መካከል ያለው ከውስጥ የመነጨ ትስስር ምን ያህል ጠንካራ መሆኑን የሚያሳይ ነው። ርግጥ በደም፣ በባህል በቋንቋ የተሳሰረን ህዝብ ተለያይቶ ሊለያይ አይችልም። ጠንካራ ስነ ልቦናዊና አካላዊ ትስስር ያለው በመሆኑም ሁሌም እንደተፈላለገ መኖሩ እውነት ነው።

ከዚህ አኳያ የኢትዮጵያና የኤርትራ ህዝቦች ላለፉት 20 ዓመታት ሲነፋፈቁ መኖራቸውን መካድ አይቻልም። ይህ ናፍቆት ደግሞ የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድና በፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ አማካኝነት ሰላም ሲፈጠር፤ ህዝቡ ያሳየው ደስታ ወደር የሌለው እንደነበር ተረጋግጧል።

ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ወደ ኤርትራ ሲያቀኑ የአስመራ ህዝብ ያደረገላቸው ከልብ የመነጨ እውነተኛ አቀባበል የዚህ አባባሌ አስረጅ ነው። እንዲሁም ፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ ሀገራችንን ለመጎብኘት ሲመጡ፤ እጅግ የበዛው የአዲስ አበባ ህዝብ የሁለቱን ሀገራት ባንዴራ ይዞ ያደረገላቸው እውነተኛ ደስታን የሚያንፀባርቅ አቀባበል ይህን የሚያስረዳ ነው። ፕሬዚዳንቱ የሀዋሳ ኢንዱስትሪያል ፓርክን ሲጎበኙም የሀዋሳና የሻሸሜ ነዋሪዎች ያሳዩአቸው ከፍተኛ ፍቅር የሁለቱን ሀገራት ስር የሰደደ ፍቅርና ናፍቆት አረጋጋጭ ነው ማለት ይቻላል። በሚሊየም አዳራሽ በተካሄደው ዝግጅት ላይ ፕሬዚዳንት ኢሳያስ መናገር እስኪቅታቸው ድረስ በሁሉም ኢትዮጵያዊ ይቸራቸው የነበረው አክብሮት እንዲሁም ይሰጣቸው የነበረው ፍቅር በሁለቱ ሀገራት መካከል ምንም ዓይነት ልዩነት ያለ አያስመስለውም ነበር።

ርግጥም በኢትዮጵያና በኤርትራ ህዝቦች መካከል ካለው ልዩነት ይልቅ አንድነታቸው እጅግ የበዛ ነው። በተለይ በድንበር አካባቢ የሚገኙ ዜጎች በጋብቻ ተሳስረውና ተዋልደው የሚኖሩ ናቸው። እንዲህ ዓይነቱ ግንኙነት ለ20 ዓመታት ያህል ተገድቦ ሲቆይ እጅግ ያማል። ይፈታተናልም። ምስጋና ለለውጡ አመራር ይሁንና ያ የጨለማ ግርዶች ተገፍፏል። ዛሬ ለእዚያ ህዝቦች የደመቀ ብርሃን ወጥቷል። ፍቅራቸው ድንበር እየጣሰ ጭምር እየተፈላለጉ ነው። በቅርቡ ከኤርትራ በዛላንበሳ በኩል አድርገው በአውቶቡስ የገቡ ኤርትራዊያን እንዲሁም በሑመራ በኩል አድርገው ወደ ኤርትራ-ኦምሃጀር የሄዱት ዜጎች የህዝብ ለህዝቡ መፈላለግና መነፋፈቅ ማሳያዎች ይመስሉኛል።  

ርግጥ ላለፉት 20 ዓመታት በ“ሞት አልባ ጦርነት” ስር የነበሩት የድንበር አካባቢ ህዝቦች የሰላምን ዋጋ ጠንቅቀው የሚያውቁ ናቸው። ምን ዓይነት የስነ ልቦና ጫና ውስ እንደነበሩ በደንብ ይገነዘቡታል። እነዚያ ህዝቦች ከውጥረትና ከጭነቀት ኪሳራ እንጂ ትርፍ እንደማይገኝ በሚገባ ይረዳሉ። በኢትዮጵያ በኩል፤ ከኤርትራ ጋር በሚያዋስኑን አካባቢዎች የሚኖሩት እንደ ሑመራ፣ ዛላንበሳ፣ ኢሮብ-አሊቴና፣ ባድመና አካባቢው የመሳሰሉ እንዲሁም በአፋር አካባቢ የሚኖሩ ተጎራባች ኢትዮጵያዊያን ለሁት አስርታት ያሳለፉት የሰቀቀን ህይወት እንደምን ከባድ እንደነበረ ለማወቅ ብዙም ምርምር አይጠይቅም—ግልፅ ነውና።

እነዚያ ህዝቦች ‘ነገ ምን ይፈጠር ይሆን?’ በሚል የስጋት ደመና ውስጥ ቆይተዋል። “ከአጋም ጋር የተጠጋች ቁልቋል፣ ስትደማ ትኖራለች” እየታቡ የስቃይን በትር ሲቀበሉ ነበር። ሌላው የሀገራችን ክፍል በምጣኔ ሃብት ሲያድግና ሲመነደግ እነርሱ ከዛሬ ነገ ጦርነት ሊከፈት ይችላል በሚል የስነ ልቦና ቀውስ ውስጥ ሆነው ጊዜያቸውን አሳልፈዋል። ለራሳቸውም ይሁን ለሀገራቸው ኢኮኖሚ ማበርከት የሚገባቸውን ነገር ሳያደርጉ እነዚያን 20 ዓመታት በጭንቀት ውስጥ ሆነው አልፈዋቸዋል።

እናም ዛሬ ድንበር እያቋረጡ ከወንድሞቻቸውና ከእህቶቻቸው ጋር ቢፈላለጉ የሚፈረድባቸው አይደሉም። በእውነቱ በሁለቱም ሀገራት ድንበር ላይ የሚገኙት ህዝቦች ሁኔታ አንጀት የሚበላ ነው። በእኔ እምነት የፍቅርና የሰላም ግንኙነትን በመፍጠር ለዘላቂ ሰላም መጣራቸው ተገቢና ትክክል ነው። እንዲያውም መንግስት የሚፈልገውንና በቅድሚያ መሆን አለበት ብሎ የሚያምንበትን የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት የሚያጠናክር አካሄድ ይመስለኛል።

የሁለቱ ሀገር የድንበር አካባቢ ህዝቦች አንዱ ወደ ሌላኛው ድንበር እያቋረጠ መምጣቱ አንድ የሚሰጠን ትልቅ ትምህርት አለ። እርሱም የህዝቦችን መፈላለግ ድንበር የማይገድበው መሆኑን ነው። ድንበር መሬት ላይ የሚገኝ ሃሳባዊ መስመር ነው። መፈላለግ ግን በሰዎች ልብና አዕምሮ ውስጥ የሚገኝ ተፈጥሯዊ ስሜት ነው። እናም የትኛውመ ሃሳባዊ መስመር ይህን ውስጣዊ ስሜት ሊገድበው አይችልም።

እንኳንስ ሁለቱም ህዝቦች ያለፉትን 20 ዓመታት ጠባሳዎች ለመሻር የጋለ ፍላጎት እያላቸው ይቅርና፣ እንኳንስ እነዚያ በታሪክ የተቆራኙ ህዝቦች ቤተሰቦቻቸውን ለመፈለግ በራሳቸው ፈቃድ አንዱ ወደ ሌላኛው መሄዱ ይቅርና፣ እንኳንስ መቃቃርንና መወጣጠርን ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ እርግፍ አድርገው በመተው በፍቅርና በይቅርታ ለመኖር መወሰናቸው ይቅርና፤ አንዱ በተናጠል ብቻ እንዲህ ዓይነት ፍላጎት ካለው በፍቅር ገፋፊነት ድንበርን ተሻግሮ መምጣቱ አይቀርም። ታዲያ ሁሌም ፍቅር ያሸንፋልና እንዲህ ዓይነቱን ክስተት ማስቆም አይቻልም። እንዲያውም ፍላጎት የሌለው ጥቂት ወገን ቢኖር እንኳን ወደ ኋላ ላይ በፍቅር መሸነፉ የሚቀር አይደለም።

እናም የትኛውም ድንበር የህዝቦችን ውስጣዊ መፈቃቀድና ፍቅር ሊገድበው አይችልም። ለዚህም ነው—በሑመራ፣ በዛላንበሳና በራማ የድንበር አካባቢዎች ከወዲያ…ወዲህ እና ከወዲህ…ወዲያ አንዱ ህዝብ የየሀገሩን ባንዴራ ይዞ ሲተም የምንመለከተው። ለዚህም ነው— የፍቅር ሃያልነት በህዝቦች የቆየ ውስጣዊ ሲገለጥ የምንመከተው። ለዚህም ነው— የድንበር አካባቢ ህዝቦች ሲገናኙ አንገት ላንገት ተቃቅፈው ለመላቀቅ እስኪያስቸግራቸው ድረስ ሲሳሳሙ የምንመከታቸው። እንዲህ ዓይነቱ ህዝባዊ ፍቅር በሁለቱም ሀገር መንግስታት የሚደገፍ በመሆኑም በዚያ አካባቢ የሰላም አውድ መጉላቱ የሚቀር አይደለም።

ላለፉት 20 ዓመታት ከድንበር ባሻገር አንድ ሰው ሲሞት በወዲህኛው ወገን ግለሰቡ ስለሚታወቅ ቀብሩን ተራራ ላይ ቆሞ እያለቀሰ ያስፈፅም የነበረው የሁለቱም ሀገር ዜጋ፤ ዛሬ ክፉን አያምጣውና ያለ ሰቀቀንና ፍርሃት ሊቀብርና እርሙን ሊያወጣ የማይችልበት ምክንያት የለም። ከ20 ዓመታት በፊት የነበረው በሐዘንም ይሁን በደስታ የመገናኘትና አብሮ በፍቅር ተደምሮ የመኖር ሁኔታ በቅርብ ጊዜያት ውስጥ መመለሱ አይቀርም። አሁን የተጀመረውና እነዚህ ሁለት ህዝቦች የማይነጣጠሉ መሆናቸውን እያሳዩት ያሉት የፍቅርና የይቅርታ መንገድ ተጠናክሮ መቀጠል የሚኖርበት ነው።   

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy