NEWS

የሱዳን ፕሬዚዳንት ኦማር አልበሺር ካቢኔያቸውን በተኑ

By Admin

September 10, 2018

ፕሬዚዳንቱ ሀገሪቱን ከገባችበት ኢኮኖሚያዊ ቀውስ ለማውጣት ነባሩን የመንግስት ካቢኔ ሙሉ በሙሉ ከሃላፊነት በማንሳት አዲስ ጠቅላይ ሚኒስርር ሹመዋል። አልበሽር እዚህ ውሳኔ ላይ የደረሱት የመንግስት ፍጆታ ለመቀነስና የገጠማቸውን የምንዛሬ እጥረት ለማስተካከል መሆኑንም ይፋ አድርገዋል፡፡ በከሪ ሀሰን ሳልህ ተነስተው አዲስ የተሾሙት ጠቅላይ ሚኒስትር ሙታዝ ሙሳ አብደላህ ደግሞ የሚኒስትሮችን ብዛት ከ31 ወደ 21 ዝቅ በማድረግ አዳዲስ ካቢኔዎችን እንዲሾሙ በአልበሺር ታዘዋል። ይህም የወጪ ቅነሳን ያለመ መሆኑ ነው የተነገረው። ሳልህ ከፈረንጆቹ 2017 ጀምሮ በምክትል ፕሬዚዳንትነትና በጠቅላይ ሚኒስትርነት ሲያገለግሉ የነበረ ሲሆን አሁን በምክትል ፕሬዚዳንተነታቸው ብቻ ይቀጥላሉ ተብሏል። አል በሺር ጣልቃ ገብተው የካቢኔ ለውጥ እንዲደረግ መወሰናቸው በሀገሪቱ ያለውን አጠቃላይ ህዝባዊ ጥርጣሬ እና ቀውስ ለመቅረፍ አስፈላጊ መሆኑን የፕሬዚዳንት ዕህፈት ቤት ያወጣው መግልጫ ያሳያል። አል ቢሺር ነባሩ የመንግስት ካቢኔ እንዲለወጥ ያቀረቡት ጥያቄ በገዥው ናሽናል ኮንግረስ ፓርቲ ከፍተኛ አመራሮች ውሳኔ አግኝቷል። በሀገሪቱ ያለው ኢኮኖሚያዊ ቀውስ የመንግስት ባለስልጣናትን ለመቀየርና የሚኒስትሮችን ቁጥር ለመቀነስ እንዳስገደዳቸውም የአልበሺር ከፍተኛ ረዳት ፈይሰል ሀሳን ኢብራሂም ለጋዜጠኞች ተናግረዋል። በዚህም መሰረት በጠቅላይ ሚኒስትርና ምክትል ፕሬዚዳንት በከሪ ሀሰን ሳልህ የተመሰረተው ነባሩ የመንግስት ካቢኔ ማለትም የክልል ባለስልጣናት፣ የፌደራል ባለስልጣናት ሁሉ ከስልጣን ተነስተዋል። 21 አባላት ያሉት የሚኒስትሮች ካቢኔ በአስቸኳይ እንዲመሰርትም አዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትር ሙታዝ ሙሳ አብደላህ ከፕሬዚዳንት አል በሺር ትዕዛዝ ተቀብለዋል። ሱዳን የዋጋ ግሽበቱ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ አሁን ምጣኔው 65 በመቶ ደርሷል። የሀገሪቱ የመገበያያ ገንዘብ የሱዳን ፓውንድ ከውጭ ሀገራት ገንዘቦች ጋር ያለው የምንዛሬ አቅም ተዳክሟል። የእለታዊ ፍጆታ ሸቀጦችን ጨምሮ የዋጋ ንረቱ አሳሳቢ ደረጃ ላይ ደርሷል፤ መንግስት የሚያደርገውን ድጎማ ማቆሙን ተከትሎ የዳቦ ዋጋ በእጥፍ መጨመሩ ሱዳናውያንን አሰቆጥቷል። ምንጭ፦ቢቢሲ እና ፕሬስ ቲቪ