Artcles

የተበላሸውን ቆርጣችሁ ጣሉ!

የተበላሸውን ቆርጣችሁ ጣሉ!

By Admin

September 12, 2018

የተበላሸውን ቆርጣችሁ

ጣሉ!

አባ መላኩ

“ጨው ሆይ  ለራስህ ስትል ጣፍጥ፤ አለበለዚያ ድንጋይ ተብለህ ትጣላለህ”። እውነት እውነቱን  እንነጋገር ካልን የኢህአዴግ መስተካከልም ሆነ መበላሸት በቅድሚያ የሚጠቅመውም ሆነ የሚጎዳው አመራሩንና አባሉን ነው። አገርና ህዝብ በቀጣይ  የሚመጡ ነገሮች ናቸው። በአዲሱ ዓመት በቅድሚያ እህት ድርጅቶች ከዚያም ኢህአዴግ ራሱ ጉባዔውን ለማድረግ ሽር ጉድ በማለት ላይ ይገኛሉ። ኢህአዴግ በዚህ ጉባዔ ወደ ቀድሞው ህዝባዊ መስመሩ መመለስ የሚያስችለውን ውሳኔዎች  ያሳልፋል ተብሎ ይታሰባል።

አሁን ላይ አገር ብቻ ሳትሆን  ኢህአዴግም በፈጣን የለውጥ ዑደት  ውስጥ ነው። ኢህአዴግ ሆይ ከህዝብ የለውጥ ፍላጎት ጎን መሰለፍ ካልቻልክ ህልውናህ አደጋ ውስጥ እንደሚገባ የተረዳኸው ይመስላል። ከቅርብ  ጊዜ ወዲህ በኢህአዴግ ውስጥ የሚስተዋሉ ተቀጽላ ባህሪዎች ድርጅቱን ከመስመሩ እንዲወጣ እና ህዝባዊ ድጋፉን እንዲያጣ ምክንያት  ሆነዋል።

የኢህአዴግን አበቃቀልና  የአስተዳደግ ባህል በአጽዕኖት ለተመለከተው፣ ኢህአዴግ እዚህ መድረስ የቻለው በህዝብ ጠንካራ ድጋፍ ማትረፍ በመቻሉ ነው። ኢህአዴግ  የመጣበትን ህዝባዊ መንገድ አጥብቆ መያዝ ተስኖት በተለይ ካለፉት ሶስትና አራት ዓመታት ወዲህ ፓርቲው ሲንገዳገድ ቆይቶ አገሪቱን ለሁከትና ነውጥ ዳርጓት ነበር።  ይሁንና ካለፉት አምስት ወራት ወዲህ ድርጅቱ በወሰዳቸው እርምጃዎች ወደ ቀድሞው አቋሙ ለመመለስ የሞት ሽረት ትግል በማድረግ ላይ ያለ ይመስላል።

እውነት እውነቱን እንነጋገር ካልን ኢህአዴግ  በአገራችን የስኬትም ሆነ የውድቀት ታሪክ ጉልህ ድርሻ ያለው ፓርቲ ነው።  በእያንዷንዷ የአገራችን ስኬት ላይ የኢህአዴግገ ጉልህ አሻራ አርፎበታል።  አገራችን በዓለም ዓቀፍ ደረጃ የተመሰከረለት ፈጣን የኢኮኖሚ ዕድገት ለተከታታይ ለ15 ዓመታት በማስመዝገብ የዜጎች ህይወት መለወጥ ኢህአዴግ  ከፍተኛ ድርሻ አበርክቷል፤ ኢህአዴግ የአገራችን የገነገነ የነበረውን ድህነትን ከግማሽ በላይ እንዲቀንስ አድርጓል። በጦርነት ትታወቅ የነበረች አገር  ዛሬ አስተማማኝ ሰላም ማረጋገጥ በመቻሏ የኢንቨስትመንት መዳረሻ ለመሆን በቅታለች፤ በስንዴ ልመና ትታወቅ የነበረች አገር ዛሬ ላይ በምግብ ሰብል ራሷን ችላለች ከዚህም አልፋ እጅግ ከባድ የተባለውን ድርቅ በአመዛኙ  በራሷ አቅም መወጣት ችላለች። አገራችን በምትከተለው የውጭ ግንኙነት ፖሊሲዋ የዲፕሎማሲ የበላይነት እንዲኖራት በማድረግ በአፍሪካ ብቻ ሳይሆን በዓለም ዓቀፍ መድርኮች ተሰሚነት እንዲኖራት ኢህአዴግ ስኬታማ የዲፕሎማሲ ስራዎችን  አከናውኗል። ዛሬ ላይ ኢትዮጵያ በአካባቢያዊም ሆነ አህጉራዊ እንዲሁም በዓለም ዓቀፋዊ መድረኮች ያላት ተሰሚነት እጅጉን አድጓል። በዓለም ፈጣን የኤኮኖሚ ዕድገት እንድትታወ አዲስ ገጽታ እንድትላበስ ኢህአዴግ የአንበሳውን ድርሻ አበርክቷል። በማበርከትም ላይ ነው።  እንግዲህ እነዚህ ሁሉ ስኬቶች የኢህአዴግ አይደሉምን?

በሌላ በኩል  ደግሞ ኢህአዴግ  ባለፉት 27 ዓመታት ጽንፍ የወጣ  ብሄርተኝነትንና ዘረኝነትን አራግቧል፤ በተለይ ባለፉት አራትና አምስት ዓመታት ሙሰኝነት ልቅ እንዲወጣ ምክንያት ሆኗል፤  አገራዊ አንድነትን አዳክሟል፤ ህዝብ በመልካም አስተዳደር እጦት እንዲማረር አድርጓል፤ ለቡድን መብት መከበር ያደረገውን ጥረት ለግለሰብ መብት መከበር ጥረት ባለማድረጉ  ግለሰቦች ከፍተኛ በደል ደርሶባቸዋል።

ይሁንና  ኢህአዴግ በራሱ  የፈጠራቸው ችግሮችም  ቀላል የሚባሉ እንዳልሆኑ  ብስማማም ለሁሉም የአገራችን ችግሮች   ምንጩ ኢህአዴግ እንዳልሆነ ግን በዕርግጠኝነት መናገር ይቻላል። አሁን ላይ በኢህአዴግ ላይ የሚሰነዘሩ አንዳንድ አስተያየቶች አሳፋሪ ናቸው። አንዳንድ  የፖለቲካ ትርፍ ለማግኘት የሚሯሯጡ ቡድኖችና ግለሰቦች ኢህአዴግን ለማሰጠን የአገራችን ችግሮች ሁሉ ምንጭ ኢህአዴግ ነው በማለት ፓርቲው በአገሪቱ ማስመዝገብ የቻላቸውን ስኬቶች በሙሉ በዜሮ የማጣፋት ሸፍጥ ሲሰሩ ይስተዋላሉ።  በመንግስት የአቅም እጦት መንገድ ያልተዘረጋላቸው ወይም ውሃና ኤሌክትሪክ ያልቀረበላቸው አካባቢዎች በኢህአዴግ ሳቢያ የመልካም አስተዳደር ችግር እንደተፈጸመባቸው ወይም ኢ-ዴሞክራሲያዊ ተግባር እንደተፈጸመባቸው አድርገው ሲያቀርቡ ይስተዋላሉ።  

ለአገራችን የሚበጃት  ሁሉንም ችግሮች በየፈርጁ ብንመለከታቸውና   በጋራ ሆነን መፍትሄ ብንፈልግላቸው እንጂ እኛና እነርሱ በመባባል ማዶ ለማዶ  ሆነን ጥፋትና ሁከትን በማቀነባበር አይደለም። አገራችን በፈጣን የለውጥ ሂደት ውስጥ ናት፤ እውነቱን እንነጋገር  ከተባለ አሁን ላይ ለሚስተዋለው ለውጥም ቢሆን የኢህአዴግ አመራሮች የነበራቸው አስተዋጽዖ በቀላሉ የሚታይ አይደለም። ባለፈው  የኢህአዴግ ስራ አስፈጻሚ ስብሰባ ወቅት ለአገራችን ችግሮች ከፍተኛ አመራሩ ሃላፊነትን ወስዷል። በእርግጥ ይህ አካሄድ አገርን አረጋግቷል። ይሁንና ኢህአዴግ ለሁሉም ችግሮች ድርጅቱ ብቻውን  መፍትሄ ሊያመጣ ከቶ እንደማይቻለው ሊያውቅ ይገባል። በመሆኑም አሳታፊ መድረኮችን አሁንም ሊያሰፋ ይገባል።

በየትኛውም መስክ ለጥፋት ሃይሎች የሚሆን ምቹ ምህዳርን ማሳጣት አንዱ የመንግስትና የገዥው ፓርቲ   ተግባር መሆን መቻል አለበት። የተሰጣቸውን ህዝባዊ አደራ መወጣት የማይችሉና ህዝባዊ ድጋፍ የሌላቸው፣ ለግል ጥቅማቸው ያደሩ አልፎ አልፎ ደግሞ ድብቅ ተልዕኮ ይዘው በመንግሥት መዋቅር ውስጥ የተሰገሰጉ ኃይሎችን በፅናት መታገል  ያስፈልጋል። ህዝቡ የነውጥና የሁከት ጋሻጃግሬዎች እነማን እንደሆኑ ጠንቅቆ ያውቃል። በመሆኑም እነዚህን አካላት ለህግ አሳልፎ መስጠት የህብረተሰቡ ሃላፊነት ነው።

ለአገራችን የሚበጃት ለችግሮቻችን መፍትሄ መፈለግ ያለብን በሰከነና ምክንያታዊ በሆነ መልኩ መሆን መቻል ይኖርብናል።  በአሁኑ ወቅት መንግስት ከህብረተሰቡ፣ ከተቃዋሚ ፓርቲዎች፣ ከተለያዩ የሲቪክ ማህበራት፣ ከዳያስፖራ፣ ወዘተ ጋር የፊት ለፊት ውይይት በማድረግ ችግሮችን በጋራ ለመፍታት የሚያደርገው  ጥረት ተጠናክሮ መቀጠል ይኖርበታል። በአገራችን የውይይት ፖለቲካ ሊዳብር የሚገባው ባህል ይገባል። መስማማት ወይም አለመስማማት አንድ ነገር ሆኖ፤ ቁጭ ብሎ መነጋገርና መወያየት መቻል  በራሱ ትልቅ ነገር ነው። ጤነኛ የሃሳብ ልዩነት የዴሞክራሲ ስርዓት መገለጫ በመሆኑ የተለያዩ ሃሳቦች መኖራቸው ክፋት የለውም።

ለኢህአዴግ  ጥንካሬ መሰረቱ  ጠንካራ የግምገማ  ባህሉ ነው። ኢህአዴግን ከትጥቅ ትግሉ ጀምሮ እስከ አገርና ህዝብ መምራት ደረጃ ውጤታማ እንዲሆን ካደረጉት አበይት ምክንያቶች ውስጥ አንዱና ቀዳሚው ይህ ጠንካራ የግምገማ  ባህሉ እንደሆነ በርካቶች ይስማማሉ፡፡ ይህ የግምገማ ባህሉ አባላቱ ጥሩ የስነ ምግባር ምንጭ እንደሆናቸው፣ አባላቱ ተጠያቂነትን እንዲያውቁና የተጣለባቸው ኃላፊነት በአግባቡ እንዲወጡ ካደረጋቸው ምክንያቶች ቀዳሚውና ዋንኛው ጉዳይ ነው፡፡ በእርግጥ  አሁን ላይ እነዚህ የኢህአዴግ ጠንካራ መሰረት እየተሸረሸሩ እንደመጡ አንዳንድ ሁኔታዎች ያመላክታሉ።

ከኢህአዴግ  ባህሉና ከጥንካሬው  አኳያ ድርጅቱ ወደ ቀድሞው አቋሙ ለመመለስ የሚከብደው አይመስለኝም።  ኢህአዴግ በቡድን አሰራር ላይ መሰረት ያደረገ ፓርቲ በመሆኑ አንዳንድ ግለሰቦች ቢበላሹም ድርጅቱ  ላይ የሚከሰተው ተጽዕኖ እጅግም ነው። ግለሰቦች ተበላሽተው ሊሆን ይችላል፤ ነገር ግን ዛሬም ኢህአዴግ በህዝብ  እጅግ ተወዳጅ የሆኑ ጠንካራ ስብዕና ያላቸው አመራሮችና አባላት ባለቤት በመሆኑ ወደ ቀድሞው አቋሙ ለመመለስ አይከብደውም።  ማንም በሰራው ጥፋት ተጠያቂ ይሁን እንጂ በብሄር ቡሉኮ እንዳይጀቦን መከላከል ሁሉም አባልና አመራር ትግል ማድረግ ይኖርባቸዋል። ሌባ ብሄርና ሃይማኖት  የለውም። ሁላችንም ሌባን ሌባ የማለት ሞራላዊ ብቃት ሊኖረን ይገባል። ኢህአዴግ በዚህ ጉባዔው ውስጣዊ ችግሩን በመቅረፍ፣ በፍጥነት ወደ ቀድሞ አቋሙ ሊመለስ  ይገባል። የኢህአዴግ አመራሮችና አባላት መጀመሪያ ለራሳችሁ ስትሉ በመቀጠልም ለአገራችሁና ለህዝባችሁ ስትሉ የተበላሸውን የድርጅቱን አካል ቆርጣችሁ ጣሉ።