Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

የታሪካዊ ወቅት አቅጣጫ

0 9,603

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

የታሪካዊ ወቅት አቅጣጫ

                                                   እምአዕላፍ ህሩይ

ሰሞኑን የገዥው ፓርቲ (ኢህአዴግ) አባል ድርጅት ከሆኑት ውስጥ አንዱ የሆነው የብሔረ አማራ ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ (ብአዴን) ማዕከላዊ ኮሚቴ የአቋም መግለጫ አውጥቷል። መግለጫው፤ የድርጅቱ 12ኛ ድርጅታዊ ጉባኤ በህዝቡ ሁለንተናዊ ተሳትፎና ባለቤትነት መንፈስ በሀገር አቀፍ ደረጃና ብአዴን በሚመራው የአማራ ክልል የተጀመረውን የለውጥ ጉዞ አጠናክሮ ለማስቀጠል ወሳኝና ታሪካዊ ጊዜ ላይ የሚካሄድ መሆኑን የሚያትት ነው።

ድርጅቱ የመሪነት ሚናውን ከምንጊዜውም በላይ አጠናክሮ ለማስቀጠል የሚያስችሉ አቅጣጫዎችና ውሳኔዎች ማስቀመጡን የሚገልፀው መግለጫ፣ እነዚህ አቅጣጫዎችና ውሳኔዎች የተጀመረውን ሀገራዊ ለውጥ በአስተማማኝ ሁኔታ ለማስቀጠል ያለውን ቁርጠኝነት የሚያሳዩ ናቸው። ብአዴን አሁን ባለበት ጠንካራ ድርጅታዊ ቁመና መድረኩ የሚጠይቀውን ጉዳዩች ለመፈፀምና የህዝቡን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ እየተከተለ ያለው በሳል መንገድ ‘ይበል’ የሚያሰኝ ነው።

ብአዴን እንደ አማራ ክልል መሪ ድርጅነቱ በክልሉ እየተቀጣጠለ ያለውን ለውጥ ጠብቆ መሰረቱን እያሰፋና ቀጣይነቱንም ይበልጥ እያረጋገጠ ክልላዊና ሀገራዊ ፋይዳ ያላቸውን ርምጃዎችን እንደሚወስድ አስታውቋል። እነዚህ ርምጃዎች ተከታታይ ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ህጋዊ የለውጥ ተግባራት ናቸው።

ድርጅቱ ወቅቱ የሚጠይቀውን የፖለቲካ ተክለ ቁመና ማሟላት የቻለ ተመራጭ የፖለቲካ ፓርቲ ሆኖ የአማራንና የኢትዮጵያን ህዝቦች የዴሞክራሲና የልማት ጥያቄዎች የሚመልስ ፋና ወጊ አታጋይ ድርጅት ሆኖ እንደሚቀጥል ቁርጠኝነቱን ገልጿል። ርግጥም ድርጅቱ እስካሁን ትክክለኛ አመራር እየሰጠ የመጣባቸው መንገዶች ይህን ቁርጠኝነቱን የሚያሳዩ ከመሆናቸውም ሌላ፣ ወደፊትም ትርጉም ያለው ለውጥ ሊያመጣ የሚችል ነው።

ብአዴን የሚመራውን ክልል ህዝብ  ከዚህ ቀደም ታሪክ፣ ትግል፣ ባህልና ስነ ልቦና በአግባቡ የተገነዘበና የተረዳ እንዲሁም አሁን ከተፈጠረው የሚያድግ ሀገራዊና ክልላዊ ሁኔታ ጋር አብሮ የሚሄድ የፖለቲካ ፕሮግራምና መተዳደሪያ ደንብ ለማርቀቅም አስቧል። ይህን ሲያከናውንም፤ ቀደም ሲል ሲመራበት የነበረው ፕሮግራምና መተዳደሪያ ደንብ የህዝቡንና የአባላቱን ፍላጎት መሰረት በማድረግ ግልፅ በሆነ ተሳትፎ እንደሚያሻሽል ይፋ አድርጓል። የአባላቱ ጥያቄ እስከሆነ ድረስም የድርጅቱን መጠሪያ ስም ጨምሮ ሌሎች ፖለቲካዊ ጉዳዩችን በመፈተሽ አግባብ ባለው መንገድ ማሻሻያ እንደሚያደርግም ገልጿል። እንደ እውነቱ ከሆነ፤ ማንኛውም የፖለቲካ እንቅስቃሴ የሚቀያየር (dynamic) ስለሆነ ድርጅቱ ወቅቱን የሚጠብቅ ለውጥ ለማድረግ መወሰኑ ተራማጅነቱን የሚያሳይ ይመስለኛል። ይህ ተራማጅነቱ ለክልሉና ለሀገሪቱ ህዝቦች የራሱን አስተዋፅኦ ማድረጉ የሚቀር አይመስለኝም።

አሁን በምንገኝበት ታሪካዊ ወቅት ላይ የተሰጠው የድርጅቱ መግለጫ፤ የአማራ ብሔርተኝነትንም የዳሰሰ ነው። ይኸውም የአማራ ብሔርተኝነት በህብረ-ብሔራዊነትና በዴሞክራሲያዊ የኢትዮጵያ አንድነት ላይ ተመርኩዞ እንዲገነባ ድርጅቱ በፅናት የሚታገል መሆኑን አስታውቋል። በዚህም ሀገራችን እየተከተለች ባለችው ፌዴራላዊ ስርዓት ውስጥ የህዝቦች ራስን በራስ የማስተዳደር፣ የእኩልነትና ፍትሐዊ ተጠቃሚነት፣ ከቦታ ቦታ ተንቀሳቅሶ በነፃነት የመስራትና የመኖር መብቶች በትክክለኛው ገፅታና በተሟላ መንገድ እንዲከበሩ ይተጋል። ይህም ሀገራችን ለሁሉም ዜጎች የተመቸች እንድትሆን የሚያደርግ ሲሆን፤ ይህን ለማከናወንም ድርጅቱ ከሌሎች እህት ድርጅቶችና ከሚመለከታቸው አካላት ጋር አብሮ ይሰራል።  

ይህን ተመርኩዞም የሪፐብሊኩ አባላት የሆኑት ክልሎች አከላለል በህዝቦች እውነተኛ ፍላጎትና ንቁ ተሳትፎ፣ ብዝሃነትንና ሀገራዊ አንድነትን በሚያጠናክር አግባብ ሕገ መንግስቱን መሰረት አድርጎ እንዲፈፀም እንደሚታገል አስረድቷል። በመሆኑም ባለፉት የትግል ዓመታት የአማራ ክልልን ጨምሮ በመላ ኢትዮጵያ ለህዝቦች መፈናቀልና መሰደድ፣ ለህይወት መጥፋትና ንብረት መውደም ምክንያት የሆኑ የወሰንና የማንነት ጥያቄዎች ትኩረት ተሰጥቷቸው በህዝብ ነፃ ተሳትፎ መፈታት ይችሉ ዘንድ፤ ድርጅቱ በምክንያት ላይ የተመሰረተ ዴሞክራሲያዊ ትግል ያካሂዳል። በእኔ እምነት፤ ይህን መሰሉ ምክንያታዊ ዴሞክራሲያዊ ትግል የክልሉን ህዝቦች መብት ይበልጥ የሚያስጠብቅ እንዲሁም የሌሎች የሀገራችን ህዝቦችን መብቶች የሚያስጠብቅ በመሆኑ ተጠናክሮ መቀጠል ይኖርበታል።

ብአዴን በመግለጫው ላይ ሁለት ጉዳዩችንም አክሏል። አንደኛው፤ ሀገራዊና ክልላዊ የህግ ማዕቀፎችን የማስከር ሲሆን፤ ሁለተኛው ደግሞ ለሩብ ዓመታት ማሻሻያ ያልተደረገባቸው አንዳንድ ህገ መንግስታዊ ድንጋጌዎችን የተመለከተ ነው። በዚህ መሰረት የሀገራችንም ሆነ የክልሉ ህጎች ዘመናዊ፣ ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብቶችንና ድንጋጌዎችን አሟልተው የያዙ እንዲሁም የዜጎች የቃል ኪዳን ሰነዶች ስለሆኑ ለህገ መንግስታዊ መብቶች መከበር በፅናት እንደሚታገል ገልጿል። በሌላ በኩልም፤ ላለፉት 25 ዓመታት የዘለቁት አንዳንድ ህገ መንግስታዊ ድንጋጌዎችን አስመልክቶ፤ ህዝቡ ሀገራችን ከደረሰችበት የዴሞክራሲ የዕድገት ደረጃ ጋር ተጣጥመው መሄድ ይኖርባቸዋል የሚል አስተያየት እየሰነዘረና ጥያቄም እያቀረበ በመሆኑ፤ ጥያቄው የህዝቡ እስከሆነ ድረስ ድርጅቱ በበጎነት እንደሚመለከተው አብራርቷል።

ታዲያ ይህን መሰል ጥያቄዎች ህገ መንግስቱ ራሱ ባስቀመጠው አሰራር መሰረት እስከቀረቡ ድረስ የሚነቀፉበት ምክንያት እንደሌለና የሀገራችን ዴሞክራሲያዊ ስርዓት ይበልጥ እንዲጠናከር ህጋዊና ትክክለኛ ምላሽ እንዲያገኙ ድርጅቱ በቁርጠኝነት እንደሚሰራ ገልጿል። በእኔ እምነት፤ ይህ የድርጀቱ አቋም ህዝብን ያማከለና የህዝብ ጥያቄንና አስተያየትን አድምጦ ምላሽ ለመስጠት ያለውን ምልከታ የሚያረጋግጥ ነው። በሌላ በኩልም፤ ብአዴን እንደ ክልሉ መሪ ድርጅት ለመረጠው ህዝብ ያለውን ከበሬታ የሚያረጋግጥ ስለሆነ አቋሙ ሊጠናከር የሚገባው ነው እላለሁ።

የድርጅቱ መግለጫ ላይ በአቋምነት የተያዘው ሌላው ጉዳይ የህግ የበላይነትን የተመለከተ ነው። የህግ የበላይነት መከበር ለዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ወሳኝ መሆኑ ያነሳው የድርጅቱ መግለጫ፤ በእስካሁኑ ትግል በዜጎች ላይ የተፈፀመውን ማንኛውንም ኃላፊነት የጎደለውን ኢ-ህገ መንግስታዊ ተግባር እንደሚያወግዝ ገልጿል። ስለሆነም በመሰል ድርጊቶች ውስጥ ገብቶ የተገኘ ማንኛውም ቡድን፣ የመንግስት ባለስልጣንና ግለሰብ በሀገሪቱ ህግ መሰረት ለህግ ቀርቦ ተጠያቂ እንዲሆን በፅናት እንደሚሰራ አስታውቋል። እንዲህ ዓይነት ድርጊቶች ውግዝ መሆናቸውንም አጥብቆ እንደሚያምን ገልጿል።

በእኔ እምነት፤ የህግ የበላይነትን ማስከበር የየትኛውም መንግስት ቀዳሚ ተግባር ነው። ዴሞክራሲን በጥብቅ በሚከተል ሀገር ውስጥ የህግ የበላይነት ጉዳይ ለድርድር የሚቀርብ አይደለም። በዴሞክራሲ ውስጥ ዜጎች ያሻቸውን አቋም ሊይዙ፣ በፈለጉት የፖለቲካ መስመር ታቅፈው ሃሳባቸውን በነፃነት ሊገልፁና በሃሳባቸው ምክንያትም ምንም ዓይነት አዕምሮአዊና አካላዊ ጉዳት ሊደርስባቸው አይገባም። ህጋዊ ከለላ ሊሰጣቸው ይገባል።

በአንድ አካባቢ ወንጀል ቢፈፀም እንኳን፤ ወንጀለኛውን በህግ አግባብ በመያዝና በህግ ጥላ ስር ማዋል እንጂ፣ ራስ ከሳሽ ራስ ፈራጅ የሚሆነበት አሰራር በዴሞክራሲያዊ ስርዓት ውስጥ ተቀባይነት የለውም። ከዚህ አኳያ በአንዳንድ የሀገራችን አካባቢዎች የሚታየው የደቦ ፈርድ የዜጎችን ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች የሚጋፋ በመሆኑ ድርጅቱም እንዲህ ዓይነቱን ተግባር በመቃወም የህግ የበላይነትን ለማስከበር እወስዳቸዋለሁ ያላቸው ርምጃዎች ጥቅሙ መልሶ ለህዝቡ በመሆኑ ህዝባዊነቱን የሚያሳዩ ናቸው። እናም ተጠናክረው ሊቀጥሉ ይገባል።

መግለጫው የግለሰብና የቡድን መብቶችንም አንስቷል። የግለሰብና የቡድን መብቶች ተጣመረው መከበር እንዳለባቸው፣ የግለሰብ መብት ባልተከበረበት የቡድን መብት ቦታ እንደማይኖረውና የቡድን መብት ባልተከበረበትም የተሟላ ዴሞክራሲ እንደማይኖር እናምናለን ያለው ድርጅቱ፤ ባለፉት ዓመታት ሁለቱንም መብቶች አጣጥሞ ከመሄድ አኳያ ህገ መንግስቱ ብዙ ርቀት መሄዱን አስታውሷል። ሆኖም ለቡድን መብት መከበር የተሰጠውን ያህል ትኩረት ለግለሰብ መብት ስላልተሰጠ፤ የቡድንን በምት የማስከበር ስራውን በማጠናከር፤ ትኩረት ተነፍጎት የነበረው የግለሰብ መብትም በሚዛናዊነት የሚከበር ስርዓት እውን እንደሚደረግ አስታውቋል። ርግጥም ይህ ሁሉንም መብቶች በእኩል ሁኔታ የማስኬድ መንገድ በተለይ ተረስቶ የነበረውን የግለሰብ መብትን የሚያጠናክር ስለሆነ ሃሳቡን አጎልብቶ መሄድ ተገቢ ነው ብዬ አምናለሁ።

ድርጅቱ ያነሳው ሌላው ጉዳይ ትኩረት ስለሚሰጠው የአመራር ግንባታ ስራ ነው። ብአዴን ጤናማ የአመራር ቅብብሎሽ እንዲኖር ይሰራል። በዚህም በአሁኑ ወቅት የሚታየውን ከፍተኛ የፖለቲካ ንቃትና ምርጥ ህዝባዊ ማዕበል እንደ እድል በመጠቀም በብቃት የተገነባ፣ ብልህ፣ አርቆ አሳቢና አስተዋይ ተኪ አመራር እንዲኖር የተማረውን ወጣት ያማከለ የአመራር ምልመላና የግንባታ ስራ እንደሚያካሂድ አስታውቋል።

በሌላ በኩልም፤ አሁን ከተደረሰበት የትግል መድረክና ከለውጡ እንቅስቃሴ ጋር አብረው መጓዝ የተሳናቸው የድርጅቱ ከፍተኛ አመራሮች ላይ ርምጃ መወሰዱን የገለፀው ድርጅቱ፤ ወደፊትም ራሱን የማጥራት እንቅስቃሴውን አጠናክሮ እንደሚቀጥል ግልፅ አድርጓል—የብአዴን 12ኛ ድርጅታዊ ጉባኤ ይህንኑ ግምት ውስጥ ያስገባ ውሳኔ የሚተላለፍበት እንዲሆን ጥሪውን በማቅረብ ጭምር። ርግጥ ድርጅቱ የሚያካሂደው አመራሮችን የማብቃት መንገድና ከለውጡ ጋር አብረው የማይሄዱ አመራሮችን የማጥራት ተግባሩን ለማጠናከር መወሰኑ ለድርጅታዊ ጥራቱ የሚበጀው ስለሆነ ተጠናክሮ መቀጠል አለበት።

በመግለጫው ላይ የተመለከቱት፤ ሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድን ለማሳለጥ የሚያደርጋቸው ሁሉን አቀፍ ርብርቦች፣ የክልሉ ህዝብ ሃብተ የሆኑት የልማት ድርጅቶች (ጥረት ኮርፖሬትና የአማራ ብድርና ቁጠባ ተቋም) ተጠሪነታቸው ለክልሉ መንግስት እንዲሆን መወሰኑ፣ የዴሞክራሲ ምህዳሩን ለማስፋት በሀገር ውስጥ በሰላማዊ መንገድ ከሚንቀሳቀሱና ውጭ ቆይተው ከመጡ ተፎካካሪ ፓርቲዎች ጋር ተቀራርቦ እንደሚሰራ እንዲሁም ክልሉን የሚያዋስነው የሱዳን የድንበር አካባቢ ያለውን ችግር ከፌዴራል መንግስት ጋር በመሆን ታሪካዊ ዳራውን ሳይለቅና የሀገርን ሉዓላዊ ጥቅም ባስከበረ መንገድ የማስተካከያ ርምጃ ተወስዶ እንዲፈታ ለማድረግ ያሳለፋቸው ጠንካራ ውሳኔዎች ድርጅቱ ህዝብንና የህዝብን ተጠቃሚነት ማዕከል አድርጎ እየሰራ መሆኑን የሚያሳዩ ናቸው። በተጨማሪም የአማራ ምሁራን የክልሉን የልማትና የመልካም አስተዳደር ችግሮች ለመፍታት በሚደረገው ርብርብ የበኩላቸውን ለመወጣት የሚያሳዩትን ተሳትፎና “ጥቁር መጋረጃውን” የቀደደ ሙያዊ ግዴታን የመፈፀም ታሪካዊ ዘመቻን አድንቋል።

በእኔ እምነት፤ ብአዴን በመግለጫው የመሪነት ሚናውን በላቀና ህዝቡን ባሳተፈ ሁኔታ እንደሚወጣ ገልጿል። ይህ ሚናው በሁሉም የክልሉ ህዝቦች መደገፍ ይኖርበታል። ድርጅቱ የለውጥ ሃይል እንደመሆኑ መጠን፤ የተቀጣጠለውን ለውጥ በመምራት ለክልሉና ለሀገራችን ተጨባጭ ለውጥ ማምጣት ይችላል። እናም በታሪካዊ ወቅት የተሰጠው የድርጅቱ አቅጣጫ ወደ ተግባር ይቀየር ዘንድ ሁሉም የድርሻውን ርብርብ ማድረግ ይኖርበታል እላለሁ።     

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy