Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

የትስስሩ ድር

0 580

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

የትስስሩ ድር

                                                   እምአዕላፍ ህሩይ

እንደ አንድም፣ ሶስትም የሚቆጠር ግንኙነት። ወደ አራተኛነትም ሊሻገር በማኮብከብ ላይ ያለ ቁርኝት— የኢትዮጵያ፣ የኤርትራና የሶማሊያ የትስስር ድር። በአሁኑ ወቅት አራተኛዋ ሀገር ልትሆን የምትችለው ጂቡቲ ናት። ኤርትራና ጅቡቲ በይገባኛል የሚወዛገቡበትን የራስ ዱሜራ ኮረብታዎችንና ደሴቶችን ችግር ለመፍታት ኢትዮጵያና ሶማሊያ በተገኙበት በጂቡቲ ስምምነት ላይ ደርሰዋል። ታላቅ ተስፋ። እንዲህ ዓይነቱ የኢትዮጵያና የአጋሮቿ  በቀጣናው ውስጥ አስተማማኝ ሰላምን የመፍጠር ጥረት፤ በቅርቡ ጂቡቲን የትስስሩ አካል ሊያደርጋት የሚችል ይመስለኛል—“የሚያጠግብ እንጀራ ከምጣዱ ያስታውቃል” እንዲሉ አበው፤ በሀገራቱ መካከል እየተፈጠረ ያለው ተግባር ይህን ሃቅ የሚያስረዳ ነውና።

የትስስሩ ድር እየሰፋ ሄዶ ቀጣናውን ሊያካልል የሚችል ለመሆኑ ምርምር የሚጠይቅ ጉዳይ አይደለም። የአራት ኪሎው የሰላም፣ የእርቅና የይቅርታ መንደር—“ጨፌ አራራ” ወደ ምስራቅ አፍሪካዊ የኢኮኖሚ የትስስር ድር እየተሸጋገረ ነው። ትስስሩ እያደር የቀጣናውን ህዝቦች ሁሉ የሚጠቅም መሆኑ አሌ አይባልም። ድሩ ደግሞ በጋራ ተያይዞ ለማደግ የሚደረግ ኢኮኖሚያዊ ፍላጎት ነው። ይህ “የጨፌ አራራ” የሰላምና ተባብሮ የማደግ ትልም፤ የምስራቅ አፍሪካ ሀገራት የተፈጥሮ ፀጋዎቻቸውን በጋራ በመጠቀምና በንግድ በመተሳሰር እጅ ለእጅ ተያይዘው እንዲበለፅጉ የሚያደርጋቸው ነው።

በሰላም ፈላጊነት እየበለፀገ የቀጠለው ኢኮኖሚያዊ የትስስር ድሩ የተግባር ቅኝት የተጀመረው፤ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ከቻይና-አፍሪካ የትብብር ፎረም ጉባኤ ቆይታቸው በኋላ በቀጥታ ወደ ኤርትራዋ የወደብ ከተማ- አሰብ በማቅናት ነበር። ኢትዮጵያና ኤርትራ ቀደም ሲል የደረሱት ስምምነት ወደ ተግባር መሸጋገሩንና መሬት መውረዱን ለማረጋገጥ በማሰብ ወደ ኤርትራ ያቀኑት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ከአሰብ እስከ ኢትዮጵያ ድንበር ያለውን 71 ኪሎ ሜትር የየብስ ትራንስፖርንም ጎብኝተዋል— ከኤርትራው ፕሬዚዳንት ኢሳይያስ አፈወርቂ ጋር።

በዚህም በኤርትራ በኩል ወደቡን ለማስጀመር ዝግጅት መኖሩን መገምገማቸውን ገልፀዋል። ወደቡም ሰሞኑን ስራ ይጀምራል። ይህ ሁኔታ በሁለቱ ሀገራት መካከል የተፈረመው የሰላም ስምምነት የወለደው ፍሬ ነው። የሀገራቱ ትስስር ለቀሪው የቀጣናው ሀገሮች ተምሳሌታዊ ነው። ርግጥ ሀገሮቹ ከኢትዮጵያና ኤርትራ የሰላምና ተጋግዞ የማደግ ቁርጠኛ አቋም ብዙ ሊማሩ ይችላሉ። በአጭር ጊዜ ውስጥ የሰላም ስምምነት ተፈራርሞ፣ በዚያው ፍጥነት በጋራ ተጠቃሚነት መንፈስ አብረው መስራት መጀመራቸው ከፍቅርና ከመደመር እንጂ፤ ከመናቆርና ከቁርሾ ምንም የማይገኝ መሆኑን የሚገነዘቡት ይመስለኛል።

ዶክተር አብይ በኤርትራ ቆይታቸው በምፅዋ ወደብ በመገኘትም አንድ የኢትዮጵያ መርከብ፤ ከወደቡ ዕቃ ጭና ወደ ቻይና ስትጓዝ ተመልክተዋል። ይህም ለሀገራችን መርከቦች ሌላ ስራ ዕድል ፈጣሪ ሆኗል። በዚህም ኢትዮጵያና ኤርትራ ያጡትን የኢኮኖሚ ጥቅሞች መልሶ ለማግኘት የሚያስችላቸው ነው። ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ፤ አትዮጵያ የአሳ ምርቶችን የምታስገባው ከሩቅ ሀገር መሆኑንና በአሁኑ ወቅት ግን ይህን ምርት ከኤርትራ በማስገባት፣ እርሷም ወደ ኤርትራ የግብርና ምርቶችን በመላክ በውጭ ምንዛሬ የንግድ ልውውጥ ማድረግ እንደሚቻልም ገልፀዋል።

በእኔ እምነት፤ ይህ የዶክተር አብይ ንግግር በሁለቱ ሀገራት መካከል የጋራ ተጠቃሚነትን በማስፈን ህዝቦቻቸው ተጠቃሚ እንዲሆኑ ያደርጋል። ላለፉት ሁለት አስርት ዓመታት የታጣው ይህን መሰሉ ተጠቃሚነት የብርሃን ፀዳል እንደ አዲስ ይፈነጥቅበታል። አንዱ የሌለውን ለሌላው በማቅረብ የመጠቃቀም ሰንሰለቱ፣ የአብሮነት ድሩና የህይወት ትስስሩ ተጠናክሮ ይቀጥላል። ሁለቱ አገራት፤ አንድም ሁለትም ሆነው ይቀጥላሉ። ኤርትራም በተፈጥሮ ፀጋዎቹ እንዲሁም ከሀገራችን ጋር በምታደርገው የንግግድ ልውውጥ ተጠቃሚ ትሆናለች።    

የምስራቅ አፍሪካ ሀገራት የተፈጥሮ ሃብት ባለፀጋ ናቸው። በምድር ውስጥ የሚገኙ ሁሉንም የተፈጥሮ ሃብቶች አቅፈው ይዘዋል። የባህር ንግድ ማካሄድ የሚችሉበት ኮሪደሮችና ወደቦች ባለቤትም ናቸው። ህዝባቸውም አስተማማኝ ሰላም ከተፈጠረለት ማልማትና መለወጥ የሚችል አቅም ያለውና የዓለም የዕድገት ተጠቃሽ መሆን እንደሚችል እንደ ኢትዮጵያ ያሉ ሀገራት በተግባር አሳይተዋል፤ እያሳዩም ነው።

 

እናም ቀደም ሲል እንዳልኩት፤ በኢትዮጵያና በኤርትራ መካከል እየተከናወነ ያለው እንዲህ ዓይነቱ የተፈጥሮ ሃብትን በጋራና በእኩልነት የመጠቀም የትስስር ድር ወደ ሶስተኛ ሀገርም ተሻግሯል—ወደ ሶማሊያ። ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ፣ ፕሬዚዳንት ኢሳይያስ አፈወርቂና የሶማሊያው ፕሬዚዳንት ሞሐመድ አብዲላሂ በአስመራ ተገናኝተው የሶስትዮሽ ቀጣናዊ ትስስራቸውን በማጠናከር የየሀገራቸውን፤ ህዝቦች የበለጠ ለማቀራረብና ተጠቃሚነታቸውን ለማሳደግ በሚያስችሉ ጉዳዮች ላይ ተስማምተዋል። ስምምነቱ በኢኮኖሚ፣ በፖለቲካ፣ በባህል፣ በማህበራዊና በደህንነት ጉዳዮች ላይ የሚያተኩር ሁሉን አቀፍ ትብብርን ያቀፈ ነው። በቀጣናው ሰላምና ፀጥታ ዙሪያም በጋራ ለመስራት ያለመ ነው፤ ስምምነቱ። 

 

በዚህ የትስስር ድር ውስጥ የ“ጨፌ አራራው” ሰው ዶክተር አብይ አህመድ እስካሉ ድረስ ለቀጣናው ሰላም፣ እርቅና ይቅርታ አበክረው መስራታቸው የሚቀር አይመስለኝም። ይህን አመላካች የሆነ ነገር መመልከት ችያለሁ። ይኸውም ኤርትራና ጂቡቲ በመሃከላቸው ያለውን የድንበር ውዝግብ በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት ይችሉ ዘንድ፤ የኢትዮጵያ፣ የኤርትራና የሶማሊያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ወደ ጂቡቲ ማምራታቸው ነው። ሁለቱ ሀገራት (ኢትዮጵያና ሶማሊያ) በተገኙበት የተካሄደው ውይይት አጥጋቢ ነበር። ጂቡቲና ኤርትራ ባካሄዱት ውይይት የድንበር ችግራቸውን በመነጋገር ለመፍታት ተስማምተዋል።

 

ርግጥ ይህ ትልቅ ድል ይመስለኛል። የኤርትራና የጂቡቲ የድንበር ጉዳይ እልባት ሳይገኝለት እስካሁን ድረስ ቆይቷል። የመንግስታቱ ድርጅት፣ የአፍሪካ ህብረትና ኢጋድ እንዲሁም ሌሎች አሸማጋይ ወገኖች ችግሩን ለመፍታት ጥረት አድርገዋል። ዳሩ ግን ምንም ዓይነት ረብ ያለው ውጤት አልተገኘም።

 

ዛሬ ግን አንድ ርምጃ ወደፊት መጓዝ ተችሏል። ይህም የምስራቅ አፍሪካን ሰላም ወደ ተሻለ ደረጃ ማሻገር የሚችል በጎ ፍንጭ ሰጭ መሆኑ ነው። እንዲሁም የቀጣናው ሀገራት ከጦርነት ምንም ሊያገኙ እንደማይችሉ በመገንዘብ ሰላምን በማምጣት በትብብር ህዝባቸውን ከድህነት አረንቋ ለማላቀቅ ምን ያህል ፍላጎት እንዳላቸው የሚያመላክት ይመስለኛል። የትስስሩ ድር ጂቡቲንም በቅርቡ አቅፎ አራቱም ሀገራት በትብብር ያላቸውን እምቅ ሃብት በመመንዘር የህዝቦቻቸውን ዘላቂ ልማትና ዕድገት የሚያረጋግጥ ቀጣናን ይፈጥራሉ ብዬ አስባለሁ።

 

የሀገራቱ የትስስር ድር ቀጣናው የሚታወቅበትን የጦርነት ተምሳሌታዊ መገለጫነቱ እንዲያበቃ ሊያደርግ የሚችል ጅምር ተግባር ነው። የዓለም መገናኛ ብዙሃን ምስራቅ አፍሪካን የጦርነት መናኸሪያ አድርገው ይቆጥሯታል። የእርስ በእርስ መጠፋፋት ማሳያ አድርገውም ሲስሏት ነበር። ይህ የቀጣናው ምስል መለወጥ ይኖርበታል።

 

እንደ እውነቱ ከሆነ፤ ጅምሩ የትስስር ድር ከተጠናከረ ይህን የጦርነትና የእርስ በርስ መተላለቅን ምስል ከቀጣናው ሰማይ ላይ ማስወገድ ይቻላል። የቀጣናውን ሰማይ በሰላምና በፍቅር መቀየር የማይቻልበት ምንም ዓይነት ምክንያት የለም—የየሀገራቱ ቁርጠኝነት እስካለ ድረስ። እናም ሶስቱ አገራት የተስማሙባቸው ጉዳዩች አራተኛዋን ሀገር ጂቡቲን ማቀፍ ከቻለ፤ በዚያ አካባቢ የሚስተዋለው የጦርነት ድባብ ተወገደ ማለት ነው።

 

ምን ይህ ብቻ! አራቱ ሀገራትና ኢጋድ በደቡብ ሱዳን ውስጥ የሚታየውን የእርስ በርስ ግጭትን በእውነተኛነት ለማስወገድ፤ ተቀናቃኝ ወገኖችን በጠረጴዛ ዙሪያ ድርድር አግባብተው የዚያችን ሀገር እልቂት በአስተማማኝ ሁኔታ ከፈቱ፤ ቀጣናው ፊቱን ወደ ጋራ ልማት በማዞር ህዝቦቹን ወደ ብልፅግና ምዕራፍ ሊያሻግራቸው የሚያስችለውን ዕቅድ ሊቀይድ እንደሚችል በርግጠኝነት መናገር ይቻላል። ለዚህም በሀገራቱ መካከል የተጀመረው ሁለንተናዊ የትስስር ድር ተጠናክሮ ተደማሪ ሰላም አምጭ ሰበዞችን እየመዘዘ መስራት ይኖርበታል እላለሁ። ሰላም ለቀጣናው ህዝቦች!   

 

  

 

 

   

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy