Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

የአዲስ ምዕራፍ አዲስ መንፈስ

0 286

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

የአዲስ ምዕራፍ አዲስ መንፈስ

አሜን ተፈሪ

ኢህአዴግ ሥር በሰደዱ ችግሮች ተጠልፎ በመውደቅ፤ የስርዓት ቀውስ ሊጋብዝ የማይችል ጠንካራ ድርጅት መሆኑን በሚያምኑ በርካታ የድርጅቱ አባላት እና ደጋፊዎች ዘንድ፤ ያለፉት ሦስት አራት ዓመታት የከባድ ድንጋጤ ዓመታት እንደነበሩ አያጠራጥርም፡፡ አባላት እና ደጋፊዎቹ ቀርቶ ድርጅቱን ከእነ እንከኑ ለመደገፍ የተገደዱ፤ እንዲሁም የፌዴራላዊ እና ዴሞክራሲያዊ ስርዓቱ ጸንቶ መቆየት ከኢህአዴግ ጋር ተያይዞ የሚታያቸው እና ኢህአዴግን የስርዓቱ አለኝታ አድርገው ይመለከቱት የነበሩት ዜጎችም፤ ራሱ ኢህአዴግ ‹‹የስርዓቱ ጠላት›› ከመሆን የሚያደርስ ችግር ውስጥ ገብቶ ሲመለከቱ እጅግ ከፍተኛ ድንጋጤ አድሮባቸዋል፡፡

ድርጅቱ በመንግስት እና በፓርቲ መዋቅር የሚያሳየው አመራር እየተበላሸ፤ ከአንድ የከሸፈ ተሐድሶ ወደ ሌላ ተሐድሶ    እየተንከባለለ፤ ችግሮች ከመሻሻል ይልቅ እየተባባሰሱ በሐገሪቱ ውጥረት ነግሶ ቆይቷል፡፡ ኢህአዴግ በህዝቡ ዘንድ ይታይ የነበረውን ተስፋ የማጣት ዝንባሌ ቀልብሶ በተስፋ እና በእርካታ ለመተካት ባለመቻሉ፤ በሁሉም ማዕዘናት የሚታየው ችግር አሳሳቢ እና ለሐገር ህልውና ጭምር አስጊ ወደ መሆን ሲያመራ ብዙዎች ከፀሎት በቀር ሌላ መፍትሔ ማየት ከማይችሉበት ነጥብ ደርሰው ነበር፡፡

በዚህ ዓይነት ሐገራዊ ድባብ ውስጥ እንደሆንን፤ ገዢው ፓርቲ ኢህአዴግ በሥራ አስፈጻሚ ደረጃ ግምገማ አካሄደ፡፡ ከዚያም ግምገማው ወደ አባል ድርጅቶች የሥራ አስፈጻሚ ወይም ማዕከላዊ ኮሚቴዎች እንዲሸጋገር አደረገ፡፡ አባል ድርጅቶቹም በክልል ደረጃ ያላቸውን ቁመና ፈትሸው፤ የግል እና የአካል ግምገማ አድርገው የመፍትሔ አቅጣጫ አስቀመጡ፡፡ ቀጥሎ የየሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴዎቹ ግምገማ ወደ መካከለኛው አመራር ወረደ፡፡ እነርሱም በላይኛው አመራር የተካሄደውን ግምገማ መርምረው ውሳኔ በማሳለፍ እና የበላይ አመራሩ የለያቸውን የግምገማ ነጥቦች መሠረት በማድረግ በየአካባቢው ጉባዔ ከፍተው መወያየት ጀመሩ፡፡ በመካከለኛ ወይም በዞን አመራሮች የተካሄደው ግምገማ ሲጠናቀቅ፤ በዚህ ደረጃ የተካሄደው ግምገማ ተጠናቅሮ በወረዳ ወይም በቀበሌ ለሚካሄደው ግምገማ መነሻ እንዲሆን ተደርጎ፤ የታችኛው መዋቅር የራሱን ግምገማ አካሄደ፡፡ ይህ ከተደረገ በኋላ መላውን ህዝብ የሚያሳትፍ የውይይት መድረክ ተከፈተ፡፡ ይህ ሂደት ሲጠናቀቅ፤ ለህዝብ ቅሬታ እና ቁጣ ምክንያት የሆኑ ችግሮች አንድ በአንድ ይወገዳሉ የሚል ተስፋ ተፈጥሮ የነበረ ቢሆንም፤ ተስፋው እውን ሳይሆን ቀረ፡፡ ቀውሱም ተጠናክሮ ቀጠለ፡፡

ታዲያ ነገሩ ገደብ የሌለው አይደለም፡፡ ከገደቡ ሲደርስ፤ ‹‹የግል ክብር እና ሥልጣን ገደል ይግባ፡፡ የእኛ ክብር እና ሥልጣን ከሐገር አይበልጥም›› ከሚል አቋም የደረሱ አመራሮች ተፈጠሩ፡፡ በዚህ መንፈስ የተጀመረው እና ‹‹ከሰማይ በታች ያለ እና ሊነሳ የሚችል ነገር ሁሉ የተነሳበት›› በተባለ መድረክ ለአስራ ሰባት ቀናት ውይይት ተደርጎ የመፍትሔ አቅጣጫ ተቀመጠ፡፡ እንደጋሸበ እህል ፍሬ አልባ በሆኑት መድረኮች የተሰላቸው ህዝብ የመጨረሻ ተስፋ ይዞ፤ የጉባዔውን ውጤት በጉጉት ጠበቀ፡፡ የድርጅቱ አባላት እና ደጋፊዎች ብቻ ሳይሆኑ፤ ለወትሮው የፖለቲካ ነገር ፈጽሞ ደንታ የማይሰጣቸው ዜጎች ጭምር አንድ መፍትሔ ሊገኝ ይችላል ብለው አቆብቁበው ጠበቁ፡፡ በመጨረሻ ድርጅቱን በሊቀመንበርነት ሲመሩ እና ሐገሪቱን በጠ/ሚኒስትርነት ሲያስተዳድሩ የቆዩት አቶ ኃይለ ማርያም ደሳለኝ፤ ‹‹የመፍትሔው አካል ለመሆን፤ የያዝኩትን ስልጣን በገዛ ፈቃዴ ለመልቀቅ ወስኛለሁ›› አሉ፡፡ ኢህአዴግም ጥያቄአቸውን መቀበሉን አስታወቀ፡፡ አዲስ አመራር ለመምረጥ ዝግጅት ማድረግ ተጀመረ፡፡ በዚህ ሂደት የለውጥ ኃይል የሆኑ የድርጅቱ አባላት ወደፊት መምጣት እና ከፍተኛውን የመንግስት እና የድርጅት ኃላፊነት ለመያዝ የሚችሉበት ዕድል ተመቻቸ፡፡  በዚህ የተነሳ፤ አዲስ ጠቅላይ ሚኒስትር ተመረጠ፡፡

ህዝቡ አዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትር ምን አዲስ ነገር ይዘውለት እንደ መጡ እንኳን ሳያውቅ፤ በኢህአዴግ ምክር ቤት ምርጫ ብቻ ከፍተኛ ደስታ እንደ ተሰማው በይፋ ለመግለጽ ጀመረ፡፡ ከዚህ በኋላ ለሦስት እና አራት ዓመታት በሐገራችን አንዣብቦ የቆየው የጨለማ ድባብ መግፈፍ ያዘ፡፡ አዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትር፤ በተወካዮች ምክር ቤት ፊት ቀርበው፤ የመጀመሪያ ንግግራቸውን አድርገው፤ የፖለቲካ ራዕያቸውን በገለጹ ጊዜ፤ የህዝቡ ስሜት ናረ፡፡ የህዝቡ ተስፋ ማንሰራራት እና ለሦስት እና ለአራት ዓመታት የቆየው የጨለማ ድባብም ተገለጠ፡፡ በዚህ ሁኔታ ለሦስት እና ለአራት ዓመታት ከብዶ የቆየው የጨለማ ተወግዶ ለሐገራችን ህዝቦች እፎይታን የቸረ የለውጥ እንቅስቃሴ ተጀመረ፡፡

የአዲሱ አመራር የለውጥ እንቅስቃሴው፤ ኢትዮጵያን ከጥፋት አፋፍ ከመመለስ እና ሐገርን ከቀውስ ከመጠበቅ ባሻገር፤ ለተጀመረው የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ እንቅስቃሴ ዘላቂ ፋይዳ ሊያስገኝ የሚችል የፖለቲካ ባህል ለውጥም እንዲፈጠር አደረገ፡፡ አዲሱ አመራር ሁሉም ወገን ሰከን ባለመንፈስ እንዲንቀሳቀስ የሚያደርግ የእርቅ መንፈስ ፈጥሮ፤ ኢትዮጵያውያን ለአንድ ሐገራቸው በአንድ ልብ መስራት የሚችሉበትን ድባብ ከማመቻቸት ተሻግሮ፤ አዲስ ምዕራፍ መክፈት የቻለ ሆነ፡፡ በተለያየ ጊዜ ከሰላማዊ የፖለቲካ መድረኩ እየሸሹ ወደ ስደት የገቡ፤ ነፍጥ ያነሱ የፖለቲካ ድርጅቶች እና ግለሰቦች ወደ ሐገር ቤት ገቡ፡፡ ‹‹አክቲቪስቶች›› እና የተሰደዱ ጋዜጠኞችም መጡ፡፡

የመንግስት ከፍተኛ የፖለቲካ አመራሮች የአመለካከት አጥር ሳይገድባቸው፤ በወንድማዊ መንፈስ ‹‹የእንኳን ደህና መጣችሁ›› ደማቅ አቀባበል እያደረጉ ተቀበሏቸው፡፡ ዜጎችም የመሰላቸውን መልዕክት ቀርጸው እና የተለየ አርማ አንግበው፤ በነጻነት ወደ አደባባይ በመውጣት ድጋፋቸውን ገለፁ፡፡ ይህ የሐገራችን የፖለቲካ ባህል እየተቀየረ መሆኑን እና መጪው ዘመንም ብሩህ መሆኑን የሚያመለክት ክስተት ነበር፡፡ በጦር መሣሪያ ለመፋለም ሜዳ የወጡ የፖለቲካ ኃይሎች፤ ‹‹እኛ በዚህች ሐገር ዘላቂ ዋስትና ያለው ዴሞክራሲ እንዲገነባ ለማድረግ የበኩላችንን ሚና ከመጫወት የላቀ ግብ የለንም›› ከማለት አልፈው፤ ‹‹ለዚህ ዓላማ ስኬታማነት ከመንግስት ጋር በመመካከር እንሰራለን›› በማለት አስተያየት ሲሰጡ ሰማን፡፡  

በእርግጥ ቀደም ባለው ዘመን የሐሳብ ልዩነቶች በርዕዮተ ዓለም ጎራ ከወዲያ እና ከወዲህ አቁመው ለመወጋገዝ እና ደም ለመፋሰስ ሲያበቃ ተመልክተናል፡፡ የሐሳብ ልዩነት፤ የልዩነት ጎራ ፈጥሮ፤ የርዕዮተ ዓለም ባንዲራ አስይዞ፤ ይህ ‹‹ወገን›› – ያኛው ‹‹ጠላት›› ነው በሚል አስፈርጆ፤ በባላንጣነት ግራ – ቀኝ ሲያሰላልፈን በታሪክም ሆነ በህይወት ልምድ እናውቃለን፡፡ የሐሳብ ልዩነቶችም ለግጭት ምክንያት ተደርገው ሲያዙ አይተናል፡፡

ነገር ግን አሁን ማየት እንደምንችለው፤ የሐሳብ ልዩነት፤ የግድ – ሁልጊዜ የግጭት መንስዔ አይሆንም፡፡ የሐሳብ ልዩነት፤ በአንድ መድረክ ተቀምጦ ከመወያየት አያግድም፡፡ ሰዎች የተለየ ሐሳብን ይጠሉ ይሆናል እንጂ ሐሳቦች ሰዎችን አይጠሉም፡፡ ሐሳቦች ሐሳብን አይጠሉም፡፡ ሐሳቦች ጥራት እና ብቃት የሚያገኙት፤ የህግ እና የቋሚ እውነት ማዕረግ የሚያገኙት በተቃራኒ ሐሳብ ድጋፍ ነው፡፡ የሐሳብ ከተማ ውይይት ነው፡፡ አሁን ‹‹መደመር›› ሰላማዊ የውይይት ከተማ በመሆን እያገለገለች ነው፡፡

በፍቅር እና በመደመር መፈክሩ የሚታወቀው አዲሱ አመራር፤ ሐገሪቱን ለዘመናት ሲያደማ ለቆየው ፖለቲካዊ ችግር መፍትሔ እያዋለደ ይመስላል፡፡ በምድሪቱ የሰላም አየር እንዲነፍስ ያደረገው አዲሱ የለውጥ አመራር፤ ሐገራችንን እና ህዝቦችዋን በድህነት ግርግም አስሮ የኖረው የእርስ በእርስ ጦርነት እንዲቆም እና ኢትዮጵያውያን የሰላም – የልማት – የዴሞክራሲ ጣዕምን እንዲቀምሱ ለማድረግ እየሰራ ይገኛል፡፡

ኢህአዴግ ሥር የሰደዱ እና የቆዩ ችግሮቹን መቀበሉ፤ ይህንም ችግር ለማስወገድ እንቅስቃሴ መጀመሩ፤ በህዝቡ ዘንድ ተስፋ አሳድሯል፡፡ ለችግሮቹም ትክክለኛ መፍትሔ እያስቀመጠ በድል ጎዳና መጓዝ ጀምሯል፡፡ ኢህአዴግ፤ ‹‹ታመመ! -በቃ ሞተ!›› ሲሉት፤ አፈር ልሶ – እንደ ንስር ታድሶ እየተነሳ፤ ችግሮቹን እያሸነፈ በድል መንገድ እየተራመደ፤ ረጅም የትግል ጎዳናውን በድል መዝሙር እያደመቀ በመደመር ጎዳና ጉዞውን ይቀጥላል፡፡ በመንገዱ ርዝመት፣ በጎዳናው ጠመዝማዛነት፣ በፈተናው ውስብስብነት፣ በትግሉ አስቸጋሪነት እና በመከራው ጽናት ሳይሸነፍ ይራመዳል፡፡ አሁንም በአዲሱ አመራር ለፈተናዎች እጅ ሰጥቶ ሳይንበረከክ ይጓዛል፡፡

ይህ ድርጅት፤ እንደ ጣዝማ ደረቅ ግንድን በሚሰረስር የግምገማ መድረክ አማካኝነት በየጊዜው የሚገጥሙትን ችግሮች በመለየት ራሱን እያረመ የመጓዝ ልዩ ባህል የነበረው ይህ ድርጅት፤ ዛሬም የህዝቡን ኢኮኖሚያዊ እና ፖለቲካዊ እንቆቅልሾች በአዲስ ዓይን የማንበብ፣ የመረዳት እና የመተንተን ብቃት እንዳለው አሳይቷል፡፡ ይህ ድርጅት፤ ራስን ያለ ርኅራኄ በመፈተሽ ባህሉ እየታገዘ፤ አዲሱን ምዕራፍ በድል ችቦ አጸሕይቶ ወደፊት መጓዙን ይቀጥላል፡፡

አሁን ድርጅቱ በአዲስ የፈተና ምዕራፍ ውስጥ ይገኛል፡፡ በያዝነው ወር ይካሄዳል ተብሎ በሚጠበቀው ድርጅታዊ ጉባዔም የገጠሙትን ቀሪ ችግሮች የመረዳት እና የማረም ብቃቱ ዳግም ይፈተናል፡፡ በየምዕራፉ የሚፈጠሩትን ወሳኝ የትግል አጀንዳዎችን ነቅሶ እያወጣ እና ራሱን ያለ ርኅራኄ እየገመገመ፤ መድረኩ የሚጠይቀውን የትግል አቋም በመገንባት ረጅም መንገድ የተጓዘው ይህ ድርጅት፤ አሁን ‹‹በጥልቅ የመታደስ›› ንቅናቄ አልፎ ባለፉት ወራት እንደገና ነፍስ ዘርቷል፡፡ ዳግም ነፍስ ለመዝራት ያበቃው አንድ ጥንካሬ አለው፡፡ ጥንካሬው ምንጭም የችግሩን መንስዔ ውጫዊ በማድረግ የቅዠት እንቅልፍ ለመተኛት የሚሻ ድርጅት አለመሆኑ ነው፡፡ ከሌሎች የሐገራችን የፖለቲካ ፓርቲዎች በተለየ ኢህአዴግ ለሚገጥሙት ችግሮች ኃላፊነት የመውሰድ ባህል ያለው ይመስለኛል፤ እንደኔ አስተያየት የድል አድራጊነት ታሪኩ ምስጢርም ይኸው ይመስለኛል፡፡

እንደሚታወቀው፤ ለሚገጥሙት ችግሮች ሁሉ ራሱን ኃላፊ የሚያደርግ ሰው (ድርጅት)፤ ራሷን አሸዋ ውስጥ በመቅበር አደጋውን ለማምለጥ እንደምትሞክር ሰጎን፤ ራሱን ለአደጋ አጋልጦ አይተኛም፡፡ እናም የሚያስብ አዕምሮውን በሰበብ ካቴና ጠፍሮ አይዘናጋም፡፡ ዘጠኝ ሞት ሲመጣበት አንዱን ግባ ብሎ ከችግሮች መደብ ላይ አይጋደምም፡፡ ለሚገጥሙት ችግሮች ሁሉ ራሱን ተጠያቂ በማድረግ የሚነሳ ሰው (ድርጅት)፤ ለህመሙ ፈውስ የሚሆነውን መድኃኒት ለማግኘት የሰው እጅ አይመለከትም፡፡ ‹‹የችግሩ ባለቤት እኔ ነኝ›› የሚል ሰው፤ ራሱን የመፍትሔው ባለቤት ያደርጋል፡፡ እጅጌውን ሰብስቦ ለሥራ ይነሳል፡፡ በችግሮቹ ላይ ባለሥልጣን ይሆናል፡፡

ባለፉት ዓመታት ‹‹የችግሩ ምንጭ ከፍተኛ አመራር ነው›› እያለ በተለመደው መንገድ ለችግሩ ኃላፊነት ቢወስድም፤ ለችግሩ መፍትሔ ብሎ የሚያስቀምጣቸውን አቅጣጫዎችን ተግባራዊ ማድረግ ተስኖት ከቆየ በኋላ፤ አዲሱ አመራር ይህን ችግር በማስወገድ አመርቂ ስኬት ማስመዝገብ መቻሉን የኢህአዴግ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ በቅርቡ ባወጣው መግለጫ አመልክቷል፡፡ ድርጅቱ በዝንጋዔ ወይም በ‹‹ቆይ ነገ›› በሽታ ሲታሽ ቆይቶ፤ በመጨረሻ ራሱን በድፍረት በመመርመር፤ ጠላቶቹ በማጥላላት መንፈስ የሚያወርዱበትን ውግዘት በሚያስከነዳ ኃይል ችግሮቹን ፈትሾ፤ የመፍትሔ አቅጣጫ ቀይሶ፤ አዲስ ምዕራፍ ከፋች ንቅናቄ ውስጥ ገብቷል፡፡

ድርጅቱ በኪራይ ሰብሳቢነት ችግር በመተብተቡ እና ችግሮችን የመረዳት እና የማረም ብቃቱ በመዳከሙ፤ አሁን ለሚገኝበት የትግል መድረክ ራሱን ብቁ ለማድረግ ብዙ መሥራት ይኖርበታል፡፡ ኢህአዴግ ‹‹በሌዘርጀት›› ትኩረት ችግሮቹን መርምሮ እና አብጠርጥሮ አይቶ የለውጥ እርምጃ በመውሰዱ በህዝቡ ዘንድ አዲስ ተስፋ ፈጥሯል፡፡ ስለዚህ የመድረኩን ልዩ ባህርይ ተንትኖ፤ የመድረኩን አጀንዳዎች አጉልቶ እና ግልጽነት ፈጥሮ ለመሄድ የሚያደርገው ሙከራ፤ ድርጅቱ ቀጣዩን ምዕራፍ በስኬት ለመጓዝ የሚያበቃ ኃይል ይዞ ከወደቀበት እንደሚነሳ መናገር ይቻላል፡፡ ወድቆ መነሳትን ደጋግሞ የሚያውቀው ኢህአዴግ፤ ችግሮቹን እንደ ፀሐይ አጥርቶ በሚያሳይ የግምገማ ባህሉ ታግዞ፤ ብልሽቱን ገላልጦ በማየት እና መፍትሔ በማስቀመጥ፤ በአዲስ ኃይል ተሞልቶ የልማት፣ የሰላም እና የዴሞክራሲ ትግሉን አጠናክሮ ይቀጥላል፡፡ በህዝብ የተሰጠውን ሥልጣን እና አደራ አክብሮ፤ ህዝባዊ ባህርይውን ጠብቆ፤ የህዝብ ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ በሚያስችል አኳኋን ራሱን አስተካክሎ የትግል ጉዞውን ይቀጥላል፡፡ ዛሬ ክራቫት እያስተካከሉ በሥራ ሰዓት ቢሮ በመቀመጥ ሳይሆን፤ የሥራ ሰዓት ሳይቆጥሩ ዓይን እስኪቀላ መሥራት ያስፈልጋል፡፡

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy