Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

የፖለቲካ ነጋዴዎችን ሸፍጥ ያመከነ የብልህ ተግባር

0 536

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

 

የፖለቲካ ነጋዴዎችን ሸፍጥ ያመከነ የብልህ ተግባር

ሰዒድ ከሊፋ

ባለፈው ሣምንት የተሰኑ ልባም ወጣቶች ወደ ታሪካዊው የአንዋር መስጊድ በመሄድ የጽዳት ሥራ ማከናወናቸውን አይተናል፡፡ እነዚህ ወጣቶች በአዲስ አበባ ከተማ የኮልፌ ወጣቶች ክርስቲያን ማህበር አባላት ናቸው፡፡ የክርስትና እምነት ተከታዮች የሆኑት እነዚህ ልባም ወጣቶች ከኮልፌ ወደ መርካቶ ሄደው በአንዋር መስጊድ የጽዳት ሥራ ለማከናወን የተነሳሱት፤ የሐገራቸው አኩሪ ቅርስ የሆነን ማህበራዊ እሴት ጠብቆ ለማቆየት እና የፖለቲካ ነጋዴዎችን ሴራ ለማክሸፍ ነው፡፡

የኢትዮጵያን ታሪክ ጠንቅቆ ለሚያውቅ ሰው በሁለቱ እምነት ተከታዮች ዘንድ ባለው ልዩ መስተጋብር ከመደነቅ ይልቅ፤ በሁለቱ እምነት ተከታዮች ዘንድ በሚፈጠር ግጭት መደንገጡ አይቀርም፡፡ በቅርቡ በኢትዮ-ሶማሌ ክልል የታየው፤ ሐይማኖትን ዒላማ ያደረገ ጥቃት፤ ከሁሉ በላይ የክልሉን ህዝብ አስደንግጧል፡፡ አሳፍሯል፡፡ አንዳንድ ሽማግሌዎች፣ የሐይማኖት መሪዎች እና ኡጋሶች፤ በሚዲያ ቀርበው የሰጡት አስተያየት፤ በተከሰተው ነገር ምን ያህል ስሜታቸው እንደተጎዳ የሚያመለክት ነው፡፡ በረጅም ዘመን የአብሮ መኖር ታሪክ እንዲህ ዓይነት ነገር አይቶ የማያውቀው የክልሉ ህዝብ  ቀርቶ ታሪክ የኢትዮጵያን ለሚያውቅ የውጭ ሐገር ሰውም አስደንጋጭ መሆኑ አይቀርም፡፡ የተፈጠረው ነገር ለማንም ሰብአዊ ፍጡር አሳዛኝ መሆኑ እንደተጠበቀ ሆኖ፤ ክስተቱን ይበልጥ አስደንጋጭ የሚያደርገው፤ ጥቃቱን ያቀነባበሩት የፖለቲካ ነጋዴዎች የያዙት ዓላማ ነው፡፡ ጥቃቱን ያቀነባበሩት ወገኖች ይዘውት የነበረው ግብ፤ በቀላሉ ሊበርድ የማይችል እና በፍጥነት የሚቀጣጠል የግጭት እሣት መለኮስ ነበር፡፡ ጥቃቱ በተፈጸመበት ወቅትም ሆነ ከዚያ በኋላ ሁሉም ተረባርቦ እሣቱን ለማጥፋት እንቅስቃሴ በማድረጉ ተገታ እንጂ የታቀደው ነገር በጣም ዘግናኝ ነበር፡፡

የኮልፌ ክርስቲያን ማህበር ወጣቶች የወሰዱት እርምጃ፤ ክፉች ያሰቡት ተቀጣጣይ ነገር አለመኖሩን እና ኢትዮጵያውያን በሐይማኖት ልዩነት ሳቢያ ከሚመጣ አደጋ ራሳቸውን ለመጠበቅ የሚችሉ ብልህ ህዝቦች መሆናቸውን የሚያረጋግጥ ነው፡፡ እነዚህ ወጣቶች፤ ወደ ኢትዮጵያ የሚመጡ ጎብኝዎች ሁሉ በተለየ የአድናቆት ስሜት የሚጠቅሱትን እና የሐገራችን ህዝብ ልዩ መገለጫ የሆነው እሴት ከጥቃት ለመጠበቅ መንቀሳቀሳቸው በትውልዱ ተስፋ እንድናሳድር የሚያደርግ ነው፡፡ ዘመናትን ያስቆጠረው የሁለቱ ሐይማኖቶች ምዕመናን ሰላማዊ ግንኙነት፤ ከፖለቲካ ነጋዴዎች መሰሪ ጥቃት ክፍ ብሎ፤ ዛሬም እንደ ትናንቱ በክብር ተይዞ ለመጪው ትውልድ የሚተላለፍ ቅርስ መሆኑን በጉልህ የሚያመለክት ነው፡፡

በአሁኑ ጊዜ፤ የሁለቱ ሐይማኖቶች ተከታይ የሆኑ ምዕመናን ለዘመናት ይዘውት ለዘለቁት እና ለዓለም ህዝብ በአስተማሪነት ሊቀርብ ለሚችለው ልዩ መስተጋብር ተገዳዳሪ የሚሆን ዓለም አቀፋዊ ክስተት መኖሩን በማሰብ ለሚጨነቁ ሁሉ እፎይታ እንዲሰማቸው የሚያደርግ ነው፡፡ ለዓለም ህዝብ በአስተማሪነት ሊቀርብ የሚችለውን የሁለቱ ሐይማኖቶች ተከታዮች ልዩ መስተጋብር የሚፈታተን ዓለም አቀፋዊ ሁኔታ መፈጠሩን በመጥቀስ፤ ‹‹እናንት ኢትዮጵያውያን ይህን አኩሪ እሴት መጠበቅ መቻል አለመቻላችሁ የሚፈተንበት ጊዜ መጥቷል›› የሚል አስተያየት የሚያቀርቡ ወገኖች አሉ፡፡ ከግሎባላዊው ስርዓት መጠናከር፤ ከኢንተርኔት አገልግሎት መስፋፋት እና ከፖለቲካ ነጋዴዎች ሴራ ጋር አያይዘው በማሰብ ለሚጨነቁ ወገኖች ሁሉ፤ ኢትዮጵያውያን ከተጠቀሱት ሁኔታዎች ጋር ተያይዞ የሚደቅነውን አደጋ ተሻግሮ ለመሄድ የሚያበቃ የአስተሳሰብ እና የሞራል ከፍታ ይዘው መገኘታቸውን በሚያመለክት አግባብ በወጣቶቹ የተከናወነው አብነታዊ የበጎ ፈቃደኝነት ሥራ፤ እጅግ የምንሳሳለት ድንቅ ባህላዊ እና ታሪካዊ እሴታችን በዘመኑ ወጣቶች ተጠብቆ ለመጪዎቹ ተከታታይ ትውልዶችን እንደሚሻገር የሚያረጋግጥ ተግባር ነው፡፡

እንደሚታወቀው፤ ኢትዮጵያ ሁለቱ ሐይማኖቶች ለመጀመሪያ ፊት ለፊት የተገናኙባት ምድር ናት፡፡ ከነቢዩ መሐመድ ዘመን ጀምሮ የተፈጠረ ሰላማዊ ግንኙነት ጠብቃ መዝለቅ የቻለች ሐገር ናት፡፡ ከመካ ቀጥሎ የእስልምና ሐይማኖት የተተገበረባት የመጀመሪያዋ አፍሪካዊት ሐገር ናት፡፡ ከነቢዩ መሐመድ ጋር ጥብቅ ቁርኝት ያላት ናት፡፡ በእርሳቸው ዓይን ሞገስ ያገኘች ሐገር ናት፡፡

ነቢዩ መሐመድ በ610 ዓ.ም በተነሱ ጊዜ፤ የገዛ ዘመዶቻቸው በተከታዮቻቸው ላይ ጥቃት ሲሰነዝሩ፤ ‹‹ሐበሻ (ኢትዮጵያ) የእውነት አገር ናት፤ በውስጧም ሰውን የማይበድል፤ በእርሱም ዘንድ አንድም የማይበደል ንጉሥ አለና፤ ወደዚያ ብትሄዱ መልካም ነው›› በማለት ተከታዮቻቸውን ሁለት ጊዜ ወደ ኢትዮጵያ ልከዋቸዋል፡፡ በመጀመሪያ፤ የነቢዩ ሴት ልጅ፣ ኸሊፋው ዑስማን እና የአጎታቸው ልጅ ጃዕፈር የሚገኙባቸው 16 ስደተኞች ወደ ኢትዮጵያ መጥተዋል፡፡ ከዚያም ከመቶ በላይ የሚሆኑ የሐይማኖት ጥገኞች ወደ ኢትዮጵያ መጥተው 15 ዓመት በመልካም ግኑኝነት ተቀምጠዋል፡፡

ሙስሊሞች ሐይማኖታቸውን እንዳይተገብሩ የማይከለክላቸው ከሆነ፤ እስላማዊ ባልሆነ ሐገር ወይም መንግስት ውስጥ ከሌሎች ጋር በሰላም መኖር እንደሚችሉ አስረጅ ሆኖ የሚጠቀስ ታሪክ ያላት ሐገር ናት፡፡ በዛው በነቢዩ ዘመን በነበረው ክርስቲያናዊ ንጉስ ትተዳደር የነበረችው ኢትዮጵያ ብቻ ሳትሆን፤ ከዛ ወዲህ ያለችውም ኢትዮጵያ ባልተቋረጠ ሁኔታ የአብሮ መኖር መርህን ለዓለም እያሳየች ዘመናትን ዘልቃለች፡፡ አሁንም ታሪክ በአድናቆት የሚዘክረውን ይህን ልዩ የአብሮ መኖር ባህል ጠብቀው መቆየት የሚችሉ ወጣቶች እንዳሏት አረጋግጣለች፡፡

ታሪክ እንደሚመሰክረው፤ ከምድረ – አረቢያ የተወለደውን እስልምና ከተቀበሉ፤ በነቢዩ መሐመድ ዙሪያ ከነበሩ ጥቂት የቅርብ ሰዎች ውጪ፤ ከኢትዮጵያውያን ቀድሞ እስልምና የተቀበለ ህዝብ አይገኝም፡፡ በመካ የነበሩ የቁረይሽ ገዢዎች ስደተኞቹ ተላልፈው እንዲሰጡአቸው ሲጠይቁ ‹‹አልሰረቁም – አልገደሉም፤ አሳልፌ አልሰጥም›› በማለት፤ ስደተኞቹን በቀና መንፈስ ተቀብሎ፤ ያለ ሥጋት እምነታቸውን በነፃነት እንዲተገብሩ ከመፍቀድ የሚልቅ ኢስላማዊ ተግባርም አይኖርም፡፡ የኢትዮጵያውያንን ምግባር አልቆ እና አተልቆ የሚያወድስ አዲስ አረባዊ የሥነ- ጽሑፍ ዘውግ እንዲፈጠር ያደረገውም ይህ ድንቅ ተግባር ነው፡፡

በዚህ የተነሳ፤ ኢትዮጵያ ክርስቲያኖች እና ሙስሊሞች ለመጀመሪያ ጊዜ፤ በአንድ መንግስት ሥር በሰላም የኖሩባት እና እምነታቸውን በነፃነት የተገብሩባት ድንቅ ሐገር ሆናለች፡፡ በነቢዩ የትውልድ ሐገር እምነታቸውን በነፃነት መተግበር ያልቻሉ ሰዎች፤ በነቢዩ ትዕዛዝ በስደት የመጡባት ኢትዮጵያ፤ የእስልምና እምነትን ምትክ እናት ሆና የጠበቀች ሐገር ናት፡፡ በዚህም የተነሳ እንግሊዛዊው የታሪክ ፀሐፊ ኤድዋርድ ጊቦን፤ ‹‹ኢትዮጵያ ለአንድ ታላቅ ማህራዊ አብዮት መስፋፋት ምክንያት ሆናለች›› በማለት ይወቅሳታል፡፡ ጊቦን ያለ አንዳች ማለባበስ፤ ‹‹ኢትዮጵያ ወደ እርሷ የሸሹ ሙስሊሞችን ባታስጠጋ እና ባትጠብቃቸው ኖሮ እስልምና አይስፋፋም ነበር›› ይላል፡፡

 

የኢትዮጵያ መንግስት ከነቢዩ መሐመድ መነሳት ሦስት መቶ ዓመታት ገደማ ቀደም ብሎ የክርስትና እምነትን የተቀበለ በመሆኑ፤ እንዲሁም በአንዳንድ የአረቢያ ጉዳዮች ላይ ተሳትፎ ያደርግ ስለ ነበር፤ ኢትዮጵያ የ‹‹አንድ አምላክ›› እምነት የሚተገበርባት ክርስቲያናዊ ሐገር እንደ ሆነች፤ ነቢዩ መሐመድ እና የዘመናቸው ሰዎች ያውቁ ነበር፡፡ በአረብኛው ቃል፤ አል-ሐበሻ  ወይም አል- አሕባሽ በሚል የሚጠሩት የኢትዮጵያ ህዝቦች፤ ከቀይ ባህር ማዶ የሚኖሩ አፍሪካዊ ጎረቤት ህዝቦች መሆናቸውን ጥንታዊኑ የአረቢያ ህዝቦች ያውቁ ነበር፡፡  

ገና ከእስልምና ፅንስ ጀምሮ፤ ለመላው ሙስሊም ልዩ ትርጉም ያላት ሐገር ሆና እስከ ዛሬ የዘለቀችው ኢትዮጵያ፤ ሙስሊሞችን ከጥቃት የጠበቀው የፍትሐዊው እና የክርስቲያኑ ንጉስ አልነጃሽ ሐገር ኢትዮጵያ፤ ‹‹የመጀመሪያው ሂጅራ›› (እኤአ 615-616 ዓ.ም) ምድር የሆነችው ኢትዮጵያ፤ በወቅቱ ጠቅላላውን የሙስሊም ማህበረሰብ አቅፋ – ደግፋ መጠጊያ በመስጠቷ፤ በዓለም ሙስሊም ህዝብ ዘንድ የፍትሕ ምድር ተደርጋ የመታየት የማይደበዝዝ ልዩ የታሪክ ግርማን አግኝታለች፡፡

ኢትዮጵያ እና የአፍሪካ ቀንድ አካባቢ እምነቱ ያለ ጦርነት የተስፋፋባቸው ሐገሮች ናቸው፡፡ ኢትዮጵያውያን ሙስሊሞች፤ ኢትዮጵያዊነታቸውን እና ብሔረሰባዊ  ማንነታቸውን ከሐይማኖቱ እኩል የማንነታቸው መገለጫ አድርጎ የማየት ልዩ ዝንባሌ ያላቸው ናቸው፡፡ ይህም ከሌሎች ህዝቦች ለየት ያደርጋቸዋል፡፡ እስልምና ብቻ ሳይሆን ክርስትናም በኢትዮጵያ የተለየ ባህርይ ይዞ ማደጉን ምሁራን ይናገራሉ፡፡ በኢትዮጵያ ክርስትና የታየው ባህርይም በኢትዮጵያ እስልምናም ታይቷል፡፡ ሁለቱም እምነቶች ከሌላው የመነጠል፣ ራስን ችሎ የመቆም ባህርይ እንደሚታይባቸው የሚገልፁት ምሁራን፤ በሌሎች ሀገሮች እንደታየው፤ በኢትዮጵያ የአረብኛ ቋንቋ ከእስልምና ጋር ተዳብሎ አልገባም፡፡ አረብኛ፤ በኢትዮጵያ የሚነገር ቋንቋ ሆኖ አያውቅም፡፡ ኢትዮጵያውያን ሙስሊሞች የቁርዐን ጥቅሶችን እና ፀሎቶችን በአረብኛ ያውቋቸዋል እንጂ አረብኛ ተናጋሪ አይደሉም፡፡

የ‹‹ኢትዮጵያ እስልምና›› የምንለው፤ የኢትዮጵያ ሙስሊሞች ለእምነታቸው መሠረት የሚሆን ከሌሎች የተለየ ነገር አላቸው ለማለት አይደለም፡፡ ሆኖም እስልምና በምድረ አረቢያ ተወልዶ በዓለም ሲስፋፋ፤ በየሐገሩ የገጠመው የተለያየ ታሪክ እና ባህል መኖሩን ታሳቢ በማድረግ ነው፡፡ እስልምና በዚህ ሐገር በምን ሁኔታ ተስፋፋ? የመስፋፋቱ ሂደት ምን ዓይነት ሂደት ነበረው? በሚል የሚቀርብ ጥያቄን ከማየት የሚነሳ ስያሜ ነው፡፡ ይሄ ብቻ አይደለም፡፡ ከእስልምና በፊት ከነበረው ባህላዊና ማህበራዊ ሁኔታዎች ጋር እንዴት ተዛመደ ብለን ስንመረምር የምንደርስበት መደምደሚያ ጭምር ነው፡፡

ኢትዮጵያ፤ እምነቱ በሰላማዊ መንገድ የተስፋፋባት የመጀመሪያዎቹ ሙስሊሞች የኖሩባት እና የተቀበሩባት፤ በእስልምና ታሪክ ውስጥ ልዩ ሥፍራ ያላት ሀገርም ነች፡፡ ከኢትዮጵያ የተወሰዱ ቃላት በቅዱስ ቁርዓን ውስጥ እንደሚገኙ የሐይማኖት ሊቃውንት ይናገራሉ፡፡

በኢትዮጵያ የእስልምና ሐይማኖት መስፋፋት ሂደት ትኩረት ሊሰጠው የሚገባ አንድ ሐቅ አለ፡፡ እስልምና ለኢትዮጵያ አንድነት መፈጠር ያደረገው አስተዋፅዖ ትልቅ ሆኖ ይታየኛል፡፡ እንደሚታወቀው፤ በአማራ – ትግራይ ክርስቲያኖች ዘንድ ያለው ተዋረዳዊ ማህበራዊ አወቃቀር እና ማህበራዊ እሴት፤ ለዓለም አቀፍም ሆነ ለአካባቢያዊ ንግድ፤ እንዲሁም ለዕደ-ጥበብ ሥራ ዝቅተኛ ስፍራ የሚሰጥ በመሆኑ፤ የንግድ ሥራ በአብዛኛው በኢትዮጵያውያን ሙስሊሞች የተያዘበት ሁኔታን ፈጥሯል፡፡

የደገኛው አስተሳሰብ፤ ወታደርነትን፣ አርሶ አደርነትን፣ አስተዳዳሪ እና ቄስ መሆንን አብልጦ የሚያይ ነው፡፡ የንግድ መስመሮቹም በእስላማዊ ሀገራት የሚያቋርጡ በመሆናቸው፤ ኢትዮጵያውያን ነገስታት የንግድ መስመሮቹን ተከትለው በየቦታው የሚዘዋወሩ የኢስላም ምሁራንን (ብዙዎቹ ከአረብና ከየመን) በትዕግስት እንዲመለከቷቸው ያደረጉ ምክንያቶች ናቸው፡፡ ኢትዮጵያውያን ነገስታት የሚፈልጉትን ንግድ የሚያካሂዱላቸውን ሙስሊሞች ከመቃወም ተቆጥበዋል፡፡ እስልምና ይበልጡን በቆላማ እና በጠረፍ አካባቢዎች በሚኖሩ አርብቶ አደር ማህበረሰቦች ዘንድ በርካታ ተከታዮችን መሳብ የቻለ ሲሆን፤ ዝግ ባለ ሂደት ወደ መሐል ሀገር ዘልቋል፡፡ የስርጭቱ ቅርጽ በመልከአ ምድር፣ በቋንቋ፣ በብሄረሰባዊ ማንነት ያልተወሰነ ነበር፡፡ የታወቁ ኢስላማዊ ማዕከላትም በሐረር፣ በምፅዋ፣ በዘይላ፤ በኋላ ደግሞ በጅማ ተፈጥረዋል፡፡

የኢትዮጵያ እስልምና ይበልጡን ወደ ውስጥ ተመልካች ሆኖ ተነጥሎ ብቻውን የኖረ ነው – እንደ ክርስትናው ሁሉ፡፡ ለእንዲህ አይነት ሁኔታዎች መፈጠር፤ ከመልክአ ምድራዊ ሁኔታዎች በተጨማሪ ስነልቦናዊና ባህላዊ ምክንያቶች የየራሳቸው ሚና ሳይኖራቸው አይቀርም፡፡ ከብዙዎች ሀገራት ታሪክ እንደምናየው የእስልምና ኃይማኖት መለያ መልክ ተደርጎ የሚታየው የአረብኛ ቋንቋ ከእምነቱ ጋር አብሮ ይወሰዳል፡፡ ሆኖም፤ በኢትዮጵያ (በአጠቃላይ በምሥራቅ አፍሪካ) እንዲህ ያለ ሁኔታ አልተከሰተም፡፡ አረብኛ በኢትዮጵያ የሚነገር ቋንቋ ሆኖ አያውቅም -(አሁን በኤርትራ ከሚገኙ በቁጥር እጅግ ጥቂት ከሆኑ ጎሳዎች በስተቀር)፡፡

በሰላማዊ መንገድ የመስፋፋት ዕድሉ እና አስፋፊዎቹ ነጋዴዎች የመሆናቸው ነገር ነባሩን ባህል በመናድ የመሄድ ዝንባሌን አስቀርቷል፡፡ በተጨማሪም፤ እስልምናን ከአረብኛ ቋንቋ ጋር እንዲቀበሉ የማስገደድ ፍላጎት ቢኖር እንኳን ነገሩ የኃይል እርምጃን የሚጠይቅ መሆኑ የማይቀር ነው፡፡ የማስተዳደር ሥልጣኑን የያዘው ክርስቲያናዊ ንጉስ ባለበት ሁኔታ ይህን ማድረግም የማይታሰብ ነው፡፡ የኃይል እርምጃው ሌላ ግጭትን የሚያስከትል መሆኑ ሳይታለም የተፈታ ነው፡፡ እናም የመስፋፋት ሂደቱ ነባሩን ነቅሎ፤ አዲሱን እንደመትከል ያለ ሂደት አልተከተለም፡፡ መስፋፋቱ ይህን የማይፈቅድ ሁኔታ ባለበት የተከናወነ ነው፡፡ ስለሆነም እስልምና በዝግተኛ ሂደት ሲስፋፋ፤ ከነባሩ ባህል ጋር እየተመቻመቸ መሆኑ ግድ ነው፡፡ ከነባሩ ባህል ጋር እየተዋሀደ የራሱን ልዩ መልክ ማበጀቱ የማይቀር ነው፡፡

በመስፋፋቱ ሂደት አዲሱ (እስልምና) እና ነባሩ (የየብሄረሰቡ ባህል) ስሙር ገጥመው እየተጣመኑ መሄዳቸው፤ የቁርአንን  ጥቅስ በአረብኛ አንብቦ በየራሳቸው ቋንቋ ትምህርት እና ትንታኔ የሚሰጡበትን ሁኔታ አስከትለዋል፡፡ በብዙ ምክንያቶች ሃይማኖታዊ ማንነት ከብሔረሰባዊና ክልላዊ ማንነት ጋር የሚፎካከር እንጂ ለብቻው የሚነግስ አይደለም፡፡ በኢትዮጵያ የእስልምና እምነት በሁሉም ብሔረሰቦች የመሰራጨቱ ዕድልም ክልልና ብሔረሰብን ማዕከል አድርጎ እንዳይቀመጥ አድጎታል፡፡ በምስራቅ፣ በምዕራብ፣ በሰሜን እና በደቡብ እስልምና አለ፡፡ እንዲያው በደፈናው ደጋማው ክፍል ይበልጥ ክርስቲያን ሆኖ ቆላማው በአብዛኛው የእስልምና እምነት ተከታይ ነው ማለት ይቻል ይሆናል፡፡ ከዚህ ሌላ ኢትዮያዊያን ሙስሊሞች ከአረብ የዘር ግንዳቸውን የሚስቡ አይደሉም፡፡

የአረብ ተወላጅ የሆኑ ነጋዴዎችና መምህራን በኢትዮጵያ ውስጥ ኖረው ከኢትዮጵያውያን ጋር የተጋቡ ቢሆንም ቁጥራቸው በጣም ውስን ነው፡፡ ስለሆነም እስላምም ሆነ ክርስትና የብዙ ብሄሮች ቅንብር ከሆነ ኢትዮጵያዊ የባህል መደብ ላይ ሥር ሰደው የቆሙ ናቸው፡፡ በኢትዮጵያዊ ርዕዮታዊና ሃይማኖታዊ ማዕቀፍ ላይ የተመሰረቱ ናቸው፡፡ በመሆኑም በሁለቱ ሃይማኖቶች መካከል ጠንካራ ቁርኝት አለ፡፡ የኢትዮጵያን ክርስትና ወይም እስልምና ለመረዳት አንዱን ካንዱ በመነጠል ከተሄደ እውነቱ መረዳት አይቻልም፡፡ እንደውም አንድ ነገር ልንገራችሁ፡፡ የኢትዮጵያን መልከአ ምድራዊ፣ ባህላዊና ቋንቋዊ መበጣጠሶችን በአንድነት አያይዞ በህብር ማንነት ያጌጠ ኢትየጵያዊ ባህል በጥብጦ እና ለውሶ ለንቁጦና ጠፍጥፎ መልክ እንዲይዝ ያደረገው ኢትዮጵያዊው ሙስሊም ነጋዴ ነው፡፡ አንዱን ካንዱ ነጥሎ መረዳት አይሞከርም ያልኩት ለዚህ ነው፡፡

እርግጥ ነው፤ በተለያየ ጊዜ ኃይል የቀላቀለ መቀናቀን እና መፋጠጥ በእስላምና በክርስቲያኑ ኢትዮጵያውያን መካከል መከሰቱ አይታበልም፡፡ ይሁንና በተለይ ባለፉት 300 ዓመታት በዕለታዊ ኑሮ በተግባር በተገለጠ የአብሮ መኖር እና የትብብር ህይወት (modus vivendi) እየጎለበተ ስር ሰዶ ጸንቶ ቆሟል ኢትዮያውያን ነገስታት ቸል ያሉትን፤ ከፈለግንም የተሸነፉበትን ወይም ያልተጨነቁበትን እና ያልደከሙበትን ወይም ያልቻሉበትን ይህን (modus vivendi) ህብር የፈጠረው የኢትዮጵያዊው ሙስሊም ነጋዴ ነው፡፡

ኢትዮጵያ የተሰራችው ከሰኞ ገበያ፣ ከማክሰኞ ገበያ፣ ከረቡዕ ገበያ፣ ከሐሙስ ገበያ ወዘተ ገበያዎች ነው፡፡ በአፋር፣ በኦሮሞ በትግራይ በአማራ በቤኒሻንጉል፣ በጋንቤላ በሚገኙ ገበያዎች ትስስር የተፈጠረች ሀገር ነች፡፡ ይህን ትስስር የፈጠረው ደግሞ ኢትዮጵያዊው ሙስሊም ነጋዴ ነው፡፡ ይህ (modus vivendi) የተተከለው እና ስር ሰዶ የበቀለው ከኢትዮጵያዊ ሙስሊም ኢኮኖሚያዊ ክንዋኔዎች ነው፡፡

ሙስሊሙ ነጋዴ ገበያ በሌለባቸው ሀገሪቱ አካባቢዎች ንግድን እያስተዋወቀ ገበያ እየቆረቆረ፤ ለቆሙ ገበያዎች ደግሞ አዳዲስ ምርቶችን እና ሸቀጦችን እያስተዋወቀ ህዝቡ በአንድ አይነት ሸቀጥ የሚጠቀም እና በንግድ የተሳሰረ እንዲሆን አድርጎ የኢትዮጵያን ህዝቦች ያቆራኘ ነው፡፡ ከኢትዮጵያ ድንበር ተሻግሮ ደግሞ ሀገሪቱን ከውጪው ዓለም ጋር ያስተሳሰረ ነው፡፡ የኢትዮያ ህዝብ እርስ በእርሱ እንዲተዋወቅ በዚህም ሂደት ህብረ ብሄራዊ የጋራ እሴቶች እንዲያቆጠቁጡና እንዲለመልሙ ያደረገ ነው፡፡ እይታው በወንዘኝነት ያልታጠረ ሆኖ ተመሳሳይ ዕይታ እንዲፈጠር ምክንያት የሆነው ኢትዮጵያዊው ሙስሊም ነጋዴ ነው፡፡

እስልምና ኢትዮያዊነትን በመፍጠር ረገድ ትልቅ ሚና እንደ ተጫወተ ከዚህ መረዳት ይቻላል፡፡ ኢትዮያዊ ሙስሊም ደግሞ የኢትዮጵያ ማህበረሰቦችን የጋራ እሴቶች ሸማኔ ሆኖ በህብረ ቀለም አንቆጥቁጦ የሰራው እርሱ ነው፡፡ የሀገሪቱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር እና አምባሳደርም ነበር፡፡

ልብ አድርጉ፤ ነገስታቱ በኃይል የግዛት አንድነት መፍጠር ሲያቅታቸው ወይም ድንበራቸው አንዴ ሲሰፋ ሌላ ጊዜ ሲጠብ፤ እንዲሁም በፖለቲካ ረገድ የህዝቡን ግንኙነት ማጽናት ሲሳናቸው፤ በደጉም ሆነ በክፉ ዘመን፤ በመዛልም ሆነ በብርታት ዘመን ኢትዮጵያዊነት ሳይቋረጥ ትስስሩ ጸንቶ አንዲቆም ያደረገው ኢትዮጵያዊው ሙስሊም ነጋዴ ነው፡፡ ከባህል አንጻር፤ ኢትዮያዊነት በየቦታው በየዕለቱ ከሚቆሙ ገበያዎች ተሰርቶ የወጣ ሸማ ከሆነ ሸማኔው ኢትዮጵያዊው ሙስሊም ነጋዴ ነው፡፡ በሌላ አገላለፅ ዘመን ሲቀየር እና ነገስታት ሲለዋወጡ የማይቀየር እና የማይለወጥ የአንድነት መንፈስ የፈጠረ እርሱ ነው፡፡

ይህ እውነታ እንደ ተጠበቀ ሆኖ፤ ዛሬ ኢትዮጵያውያን ከውጭ ዓለም ጋር እንደ ልብ እየተገናኙ ነው፡፡ ይህ ግንኙነት ግሎባላይዤሽን በሚሉት ክስተት እና በመገናኛ ዘዴ ቴክኖሎጂ ዕድገት እና መስፋፋት የሚታገዝ ነው፡፡ ስለዚህ፤ ኢትዮጵያውያን ሙስሊሞች ከውጪው ዓለም ጋር በሰፊው መገናኘት በመቻላቸው፤ ከዓለም አቀፍ የእስልምና እንቅስቃሴዎች ጋር የሚተሳሰሩበት ሁኔታ መፈጠሩ የማይቀር ነው፡፡  ይህ እውነት ነው፡፡ ስለዚህ የኢትዮጵያውያን የአብሮ መኖር ባህል እንዳይሸረሸር የሚሰጉ ወገኖች አሉ፡፡ የኮልፌ ወጣቶች እና የአንዋር መስጊድ ሙስሊሞች ለዚህ ስጋት ምላሽ የየሚሰጥ ነው፡፡

እርግጥ የግሎባላይዤሽን ክስተት መፈጠሩ እና የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ መስፋፋቱ አዲስ የማህበራዊ ህይወት ዘዬ እንዲጠናከር እያደረገ ነው፡፡ ይህ ሁኔታም የአስተሳሰብ እና የአኗኗር ዘዬ ለውጥ እያስከተለ ነው፡፡ በመሆነም አዲስ አመለካከት እና አስተሳሰብ የሚያቀነቅኑ እና ነባሩን ነገር ለመገዳደር የሚሞክሩ ማህበራዊ ቡድኖች መነሳታቸው እና  ፍልሚያ ውስጥ መግባታቸው የማይቀር ነው፡፡ አንዳንድ ማህበራዊ ቡድኖች እና የሲቪል ማህበራት ድንበር ተሻጋሪ ህብረት ለመፍጠር መፈለጋቸው የማይቀር ይሆናል፡፡ ይህን ፍላጎታቸውን ለማሳካት የሚያግዝ የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ስርዓት መፈጠሩ፤ እንቅስቃሴዎቻቸውም ዓለም አቀፍ ይዘት እያገኘ መምጣቱ፤ ኢትዮጵያውያንም በዚህ የትስስር መረብ ውስጥ መግባታቸውና መሳባቸው ወዘተ እስከ ዛሬ ፈጽሞ ወደ ውጭ የማማተር ዝንባሌ ባለማሳየት የሚታወቁት የኢትዮጵያ የክርስትና እና እስልምና ሐይማኖቶች ምዕመናን ዓለም ዓቀፍ በትስስር ውስጥ የገቡበበት ሁኔታ እንዲፈጠር አድርጓል፡፡

ከዚህ በመነሳት፤ የኢትዮጵያ እስልምና ወይም ክርስትና ሌሎችን ያገለለ ማህበራዊ ማንነትን ለሚፈጥር ፖለቲካዊ ወይም ማህበራዊ እንቅስቃሴ ማዳወሪያ ሆኖ ሊያገለግል ይችላል-አይችልም? የሚል ጥያቄ ቢነሳ የሚገርም አይደለም፡፡ በበርካታ የአፍሪካ ሐገራት የታየው ሁኔታ፤ በኢትዮጵያ ሊፈጠር ይችላል- አይችልም? ብሎ መወያየትም ተገቢ ነው፡፡  በማላዊ፣ በሱዳን እና በናይጄሪያ፤ በእስልምና እና በክርስትና እምነት ተከታዮች ዘንድ የሚታየው አብሮ የመኖር ባህል፤ በአሁኑ ጊዜ እያቆጠቆጡ ባሉ የአክራሪነት አስተሳሰቦች ሳቢያ አዲስ መልክ ሲይዝ እያየን ነው፡፡ ስለዚህ፤ ‹‹በተጠቀሱት የአፍሪካ ሀገራት እንደታየው ያለ ሁኔታ በኢትዮጵያም ይፈጠር ይሆን?›› የሚል ጥያቄ ለሚያነሱ ምሁራን፤ በአንዋር መስጊድ እና በኮልፌ ወጣቶች ክርስቲያን ማህበር አባላት መካከል የታየው ትብብር የወደፊቱን ሁኔታ ሊያመለክታቸው የሚችል አንድ ክስተት ነው፡፡

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy