Artcles

ዴሞክራሲ የሚጎለብተው  በእነርሱ ነው!

By Admin

September 11, 2018

ዴሞክራሲ የሚጎለብተው  በእነርሱ ነው!

ወንድይራድ ኃብተየስ

 

አዲስ ዓመትን በአዲስ መንፈስ፣ በአዲስ አስተሳሰብ፣ በአዲስ አቀራረብ ልንቀበለው ይገባል። ከትላንት ልንማር ይገባል። ትላንት በርካታ መልካም ነገሮችን እንዳከናወን ሁሉ ድክመቶችም እንደነበሩብን ካወቅን ትምህርት አገኝተናል፤ ታርመንበታል ማለት ነው። የትላንት ስኬትም ሆነ ድክመት የጋራችን መሆኑን ልንተማመን ይገባል። በአዲሱ ዓመት የጥላቻ ግንብ ሙሉ ለሙሉ  ሊወገድ እንዲሁም የንትርክ ፖለቲካ ሊቆም ይገባል። የአብሮነት፣ የፍቅርና የአንድነት ድልድይ ሊጎለብት ይገባል። ይህ ድልድይ የሚጎለብተውና የሚጠናከረው ደግሞ በይቅርታና በሆደ ሰፊነት ብቻ ነው።

 

ዴሞክራሲ የሚጠነክረውና  የሚጎለብተው በዋነኝነት የዴሞክራሲ ተቋማትን  ማጠናከር ሲቻል ብቻ ነው። መንግስት ዕቅድን ወደ ተግባር መለወጥ አቃተው እንጂ  በሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዘመን የዴሞክራሲ ስርዓቱን ለማጠለቅ የተለያዩ ተግባራትን ለማከናወን አቅዶ እንደነበር ዕትዕ ሁለት ላይ መመልከት ይቻላል።  ከእነዚህ ተግባራት መካከል በዓለም ዓቀፍ ደረጃ የዴሞክራሲ ተቋማት ተብለው የሚታወቁትን የተወካዮች ምክር ቤቶች፣ ምርጫ ቦርድ፣ የሰብአዊ መብት ኮሚሽን፣ የህዝብ እንባ ጠባቂ ተቋም እና የዋና ኦዲተር መስሪያ ቤቶችን በሰው ሃይልና በቁስ ማሟላት ለዴሞክራሲ መጠናከር ከፍተኛ አስተዋጽዖ ይኖረዋል።  

ከላይ ለመጥቀስ እንደተሞከረው በአዲሱ ዓመት መንግስት  የዴሞክራሲ ስርዓትን በዋነኝነት ያጎለብታሉ ተብለው የሚታወቁትን  ተቋማት ለአብነት የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤቶች፣ የፌዴሬሽንና የብሄረሰቦች ምክር ቤቶች፣ የብሔራዊ የምርጫ ቦርድ፣ የሰብዓዊ መብት ኮሚሽን፣ የኢትዮጵያ እንባ ጠባቂ ተቋም፣ የዋና ኦዲተር መ/ቤቶች አሰራር  በማዘመን የዴሞክራሲ ስርዓቱን የበለጠ ማጠናከር ዋንኛ አቅጣጫ መሆን መቻል አለበት። ዴሞክራሲ ባህል ነው። እለቱን ሊጎለብት አይችልም። በመሆኑም የዴሞክራሲ ባህል ከማዳበር አኳያ ትምህርት ቤቶች ያላቸው ሚና  እጅግ የጎላ በመሆኑ መንግስት በአዲስ ዓመት የትምህርት ስርዓቱን ከዜጎች ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች በደንብ የተቃኙበት እንዲሆን ማድረግ ተገቢ ነው።

የዴሞክራሲ ስርዓት የሚጎለብተው  የህዝብ ቀጥተኛ ተሳትፎ ሲታከለበት በመሆኑ ህብረተሰቡ መብቱንና ግዴታውን ጠንቅቆ እንዲያውቅና መብቱን  እንዲጠየቅ እንዲሁም ግዴታውን መወጣት እንዳለበት ማወቅ ይኖርበታል። የዴሞክራሲ ስርዓት መጎልበት የሰጪና የተቀባይ አካሄድ ሳይሆን ሁሉም በጋራ ተረባርቦ የሚያሳከው ጉዳይ  በመሆኑ ህብረተሰቡ ከመንግስት ጎን በመሰለፍ የድርሻውን ሊወጣ ይገባል ባይ ነኝ። አገራችን በየዘርፉ  የጀመረችውን የህዳሴ ጉዞ  ስኬታማ ማድረግ የምትችለው ዜጎች የተደራጀና ንቁ ተሳትፎ  ማድረግ ሲችሉ በመሆኑ በአዲሱ ዓመት መንግስት ሁኔታዎችን ማመቻቸት ይኖርበታል።   

ከላይ ለማንሳት  እንደተሞከረው ዴሞክራሲን ለማጎልበት የህዝብ ተወካዮችን አቅም ማሳደግ የተቋማቱን አሰራር  ማዘመን ተገቢ ነው። አገራችን ያልተማከለ የአስተዳደር ስርዓትን የምትተገብር አገር በመሆኗ   በፌዴራል ደረጃ ብቻ ሳይሆን በክልል፣ በዞን፣ በከተማ፣ በወረዳ እና በቀበሌ ደረጃ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤቶች ህግ የማውጣትና አስፈጻሚውን የመቆጣጠር ሥልጣናቸውን በብቃት እንዲወጡ ማድረግ  ተገቢ ነው።

የህዝብ ተወካዮችን አቅምና አደረጃጀት ከማጠናከር  ባሻገር በአዲሱ ዓመት የአገራችንን የዴሞክራሲ ስርዓትን ለማጠናከር የሰብአዊ መብት ኮሚሽንና የእንባ ጠባቂ ተቋማትን ማዘመን  ተገቢ ነው። የእነዚህን ተቋማት አቅም ማጎልበት የዴሞክራሲ ስርዓትን መሰረት ማሲያዝ ማለት በመሆኑ መንግስት ትኩረት ሰጥቶ ሊገነባቸው ይገባል።  የሰብአዊ መብት ኮሚሽን ከህብረተሰቡ ከሚያገኘው ጥቆማ እንዲሁም ራሱ ከሚያካሂዳቸው ጥናቶች በመነሳት የዜጐችን ሰብዓዊ መብቶች እንዲከበሩ ለማድረግ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በቅርበት በመስረት  ለዴሞክራሲ መጎልበት ሃላፊነቱን ሊወጣ ይገባል።

ሌላው  በዓለም ዓቀፍ ደረጃ  የዴሞክራሲ ተቋማት ተብለው ከሚጠቀሱት መካከል  ደግሞ የእንባ ጠባቂ ተቋም ነው። ይህ ተቋም ዜጐች የአስተዳደር በደል እንዳይደርስባቸው እና ደርሶ ሲገኝም አስፈላጊውን የማስተካከያ እርምጃ እንዲወሰድ በማድረግ የዴሞክራሲያዊ ስርዓቱን ለማጠናከር በህገ-መንግስቱ መሰረት የተደራጀ የዴሞክራሲ ተቋም ነው፡፡ የእንባ ጠባቂ ተቋም  ከዜጐች የሚደርሱትን ጥቆማዎች በማጣራትና ትክክል ሆነው በተገኙት የማስተካከያ እርምጃ እንዲወሰድ፣ ከዚህ አልፎ ያልተስተከከሉትን ደግሞ ወደ ህዝብ ተወካዮች ም/ቤት በማቅረብ መፍትሄ ማፈላለግ ነው። ተቋሙ ተልዕኮውን በላቀ ሁኔታ መወጣት እንዲችል ተቋማዊ አቅሙን የማጠናከር ጉዳይ በመንግስት  ቅድሚያ ትኩረት ሊሰጠው ይገባል።

ሌላው በዓለም ዓቀፍ ደረጃ  የዴሞክራሲ ተቋማት ተብለው ከሚጠቀሱት መካከል  የሚጠቀሰው ዋና ኦዲተር ነው። የፌዴራል ዋና ኦዲተር እንዲሁም  የክልል ኦዲት ቢሮዎች መጠናከር ለዴሞክራሲ ሥርዓቱ መጠናከር ያላቸውን ሚና  ትልቅ ነው። ምክንያቱም እነዚህ ተቋማት በመንግስት አሰራር ግልጽነትና ተጠያቂነት እንዲንግስ  ትልቅ አስተዋጽዖ አላቸው። እነዚህ ተቋማት የመንግስት ፋይናንስና ንብረት እንደዚሁም የሰው ሃይል ያለ ብክነት በአግባቡ ለታለመለት የህዝብ ጥቅም መዋሉን  የሚያረጋግጠው ይህ ተቋምን ማጠናከር ተገቢ ነው።

በአገራችን  ዜጎች በወኪሎቻቸው አማካኝነት ከሚያደርጉት ተሳትፎ በተጨማሪ በቀጥታ በተደራጀ መልኩ የሚያደርጉት ተሳትፎ ለዴሞክራሲ ሥርዓቱ መጠናከር ትልቅ ሚና አለው፡፡ በመሆኑም ህገ-መንግስቱ በደነገገው መሠረት ዜጎች በነፃነት ተደራጅተው አጀንዳቸውን እንዲያራምዱ ለማድረግ ያለው ምቹ ሁኔታ ተጠናክሮ እንዲቀጥል መንግስት  በአዲሱ ዓመት መስራት ይኖርበታል።

ለአገራችን የዴሞክራሲ ሥርዓት መጠናከር የማሕበራትና የበጐ አድራጐት ተሳትፎ ወሳኝ በመሆኑ መንግስት ለእነዚህ ተቋማት መጠናከርም ትኩረት ሰጥቶ መስራት ይኖርበታል።  የብዙሃንና የሙያ ማህበራት እንደዚሁም የበጎአድራጎት ድርጅቶች  ግልፅነትና ተጠያቂነት የሰፈነበት አሠራርን ተከትለው ለአገሪቱ ልማትና የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ የበኩላቸውን ሚና ማበርከት ይጠበቅባቸዋል። ሚዲያውም ለዴሞክራሲ ስርዓት መጎልበት ያለው ሚና ወሳኝ በመሆኑ  መንግስት በአዲሱ ዓመት ትኩረት ሊሰጠው የሚገባ ዘርፍ ነው።