ግንኙነቱና አንድምታው
እኔም በዚህ ፅሑፍ ላይ የጠቅላይ ሚኒስትሩን ማብራሪያ በመንተራስ፤ ስለ ኢትዮ-ቻይና እንዲሁም ስለ ቻይና-አፍሪካ የትብብር ፎረምና ስለ ግንኙነቱ አንድምታ ለአንባቢያን ጥቂት ሃሳቦችን ለማቅረብ እሞክራለሁ። በቅድሚያ ከኢትዮ-ቻይና ስትራቴጂካዊ ግንኙነት ልነሳ።
ግንኙነቱና አንድምታው
እምአዕላፍ ህሩይ
የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ክቡር ዶክተር አብይ አህመድ በቻይና-አፍሪካ የትብብር ፎረም ላይ ለመገኘት ወደ ቤጂንግ ከማቅናታቸው በፊት ከሲ ጂ ቲ ኤን ቴሌቪዥን ጋር ቆይታ አድርገው ነበር። የጠቅላይ ሚኒስትሩ ቆይታ በኢትዮ-ቻይና ጠንካራ ግንኙነት እንዲሁም በቻይና-አፍሪካ ትስስር ላይ ያጠነጠነ ነበር። በዚህም ዶክተር አብይ የኢትዮጵያና የቻይና ግንኙነት ለዘመናት በቆየ ስልጣኔ ላይ የተመሰረተ ጥልቅና ስትራቴጂያዊ እንደሆነ እንዲሁም በባህልና በታሪክ የተሳሰሩት ሁለቱ ሀገራት ጠንካራ የኢኮኖሚ ግንኙነት እንዳላቸው አንስተዋል።
ከዚህ በተጨማሪ ቻይና ራዕይ ይዛ በ“ ዋን ሮድ ዋን ቤልት” በተሰየመ የትብብር ማዕቀፍ አፍሪካን፣ አውሮፓን እና እስያን ለማስተሳሰር እየሰራች ያለችው መልካም ሃሳብ መሆኑንም ጠቅሰዋል። በሃሳቡም አፍሪካ የመሰረተ ልማት፣ የኢንቨስትመንት፣ ንግድና አገልግሎትን የመለዋወጥ እድል እንደምታገኝ ተስፋ እንዳላቸው አስታውቀዋል። የቻይና አፍሪካ ግንኙነት እኩል ተጠቃሚነትን ለመፍጠር ፋይዳው ከፍተኛ መሆኑንም አንስተዋል።
እኔም በዚህ ፅሑፍ ላይ የጠቅላይ ሚኒስትሩን ማብራሪያ በመንተራስ፤ ስለ ኢትዮ-ቻይና እንዲሁም ስለ ቻይና-አፍሪካ የትብብር ፎረምና ስለ ግንኙነቱ አንድምታ ለአንባቢያን ጥቂት ሃሳቦችን ለማቅረብ እሞክራለሁ። በቅድሚያ ከኢትዮ-ቻይና ስትራቴጂካዊ ግንኙነት ልነሳ።….
መረጃዎች እንደሚጠቁሙት፤ ኢትዮጵያና ቻይና ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት የጀመሩት እ.ኤ.አ በ1970 ዓ.ም ነው። የሁለቱ ሀገራት ግንኙነት በጋራ የስልጣኔ እሴቶች ላይ የተመሰረተና ረጅም ዕድሜን ያስቆጠረ ታሪካዊ ቁርኝት ያለው በመሆኑ፤ ትብብራቸውን ሲያስቡ ጥንታዊ ስልጣኔያቸውንና ረጅም የታሪክ ባለቤትነታቸውን ከግምት ውስጥ ባስገባ መልኩ ነው። ለዚህም ነው— ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ የሀገራቱን ግንኙነት አስመልክተው፤ “…በዘመናት በቆየ ስልጣኔ ላይ የተመሰረተ ጥልቅና ስትራቴጂካዊ ነው” ሲሉ የገለፁት። ታዲያ ታዲያ ይህ የዘመናት ቀመር የወለደው ጥልቅና ስትራቴጂካዊ ቁርኝት በርካታ ፖለቲካል-ኢኮኖሚ ግንኙነቶችን እንዲመሰርቱ አስችሏቸዋል። ቁርኝቱም በዶክተር አብይ አህመድ ጉብኝት ይበልጥ በመተሳሰር ቻይና እና ኢትዮጵያ በተጠናከረ መንፈስና የጋራ ተጠቃሚነትን መርህ ተከትሎ መደርጀቱ አይቀርም።
ይህ ሁኔታም ዛሬ ለደረሱበት በጋራ ተጠቃሚነት ላይ ለተመሰረተው፣ አንዱ በሌላኛው ሀገር የውጥ ጉዳይ ጣልቃ ለማይገባበትና ሰላማዊ ትብብር ለጎለበተበት ከፍተኛ የሁለትዮሽ ትስስር መሰረት መጣሉን መካድ አይቻልም።
በሁለትዮሽ ግንኙነት ዓመታት ውስጥ የትዮጵያ ጠቃሚ የልማት አጋር መሆኗን አስመስክራለች። ኢትዮጵያ ውስጥ ለሚከናወኑ የልማት ስራዎችና ለተገኘው ዕድገት ዋነኛ አጋር ነበረች። ዶክተር አብይም ላለፉት 27 ዓመታት በሀገራችን ለነበረው ዕድገት የቻይናን ሚና በማውሳት ለሀገሪቱ ባለስልጣናት ገልፀዋል። ርግጥ ኢትዮጵያና ቻይና በአሁኑ ወቅት የደረሱበት የግንኙነት ደረጃ የግንኙነቱን ጥንካሬ አመላካች ይመስለኛል።
ምን ይህ ብቻ። ኢትዮጵያና ቻይና በተለያዩ ወቅቶች በከፍተኛ ባለስልጣኖቻቸው ደረጃ የሚያደርጉት ግንኙነት እንዲሁም ጠቃሚ የሁለትዮሽ ጉዳዮች ዙሪያ የሚፈራረሟቸው ስምምነቶች የግንኙነቱን ጥንካሬና የሀገራቱን የተፈላላጊነት ደረጃ የሚያሳዩ ለመሆናቸው አስረጅ መፈለግ የሚያሻው አይደለም— እስከ ዛሬ ድረስ የተከናወኑት ተግባራት በይፋ የሚናገሩ ናቸውና።
ኤስያዊቷ ሀገር ቻይና በሀገራችን ውስጥ የነዳጅ ዘይትን በማውጣት፣ ፖታሽን በማልማት፣ እንዲሁም ልዩ የኢኮኖሚ ዞኖችን በማልማትና በማስተዳደር ረገድ ከሀገራችን ጋር በትብብር እየሰራች ነው። በእኔ እምነት፤ ይህ ግንኙነት ኢትዮጵያ የምዕራቡን ዓለም ብቻ ሳይሆን፣ የምስራቁን ልዕለ-ኃያል የኢኮኖሚ የሆነችውን ቻይናንም ጭምር ምን ያህል ቀልብ የሳበች ሀገር መሆኗን የሚያረጋግጥ ነው።
ቀደም ባሉት ጊዜያት ኢትዮጵያና ቻይና በመሰረተ-ልማት፣ በቴክኖሎጂ ሽግግር እና በህዝብ-ለህዝብ ግንኙነቶች በጋራ ለመስራት ስምምነት ላይ ደርሰዋል። እንዲህ ዓይነቱ በገራ ተጠቃሚነት ላይ ሊመረኮዝ የሚችል ግንኙነት ለሁለቱም ሀገራት የሚኖረው ፋይዳ በቀላሉ የሚታይ አይደለም።
ይህን ፋይዳ የሚያሳዩ ጥቂት እውነታዎችን ማንሳት ይቻላል። ቀደም ሲል ሀገራቱ እ.ኤ.አ ከ2015 እስከ 2024 የሚቆይ የአስር ዓመቱ ሁሉን አቀፍ ስትራቴጂካዊ የትብብር ስምምነት ማዕቀፍ ተፈራርመዋል። በዚህም የድሬዳዋ-ደወሌ የባቡር መስመር ዝርጋታን መከወን፣ የወልቃይት ስኳር ፋብሪካን የመደገፍ እንዲሁም ከወለድ ነፃ የሆነ ከ150 ሚሊዮን ብር ስምምነት ማድረጋቸው የሚታወስ ነው። ከዚህ ሃቅ ጀርባ ያለው የሚታይ ነገር ቢኖር በኢትዮጵያ ልማት ውስጥ ቻይና ያላት ተሳትፎን ነው።
እንዲሁም እ.ኤ.አ ከ2014 እስከ 2017 የሚቆይ የባህል ትብብር ማካሄጃ ፕሮግራም፣ በሲቪል አና በንግድ ጉዳዩች ላይ የሚያተኩሩ የጋራ የህግ መደጋገፍ፣ የኢትዮ-ቻይና የኢኮኖሚና የንግድ ትብብር ዞኖች፣ የቻይና ኩባንያዎች የኢንዱስትሪ ፓርኮችን ኢትዮጵያ ውስጥ ማቋቋም እና ሌሎች በጋራ ፍላጎት ላይ የተመሰረቱ ጉዳዮችን እያከናወኑ ሆናቸውን መረጃዎች ያስረዳሉ።
ርግጥ እነዚህን ክንዋኔዎች የሚመለከት ማንኛውም ሰው፤ አንድ አንድ በገሃድ የሚታይ እውነታን መደንዘቡ አይቀርም። እርሱም ኢትዮጵያ ከቻይና ጋር የምታከናውናቸው የሁለትዮሽ ትብብሮች፤ ቻይና የዓለም ኢኮኖሚን በሁለተኛ ደረጃ የምትመራ ከመሆኑም በላይ፣ በፖለቲካውም ረገድ በዓለም አቀፍ ደረጃ ተሰሚነት ያላት ስለሆነ ፋይዳው ብዙ ነው።
ምንም እንኳን የትኛውም ሀገር በራሱ የውስጥ እምቅ አቅም መተማመንና ይህንንም አጎልብቶ ማደግ ያለበት መሆኑ የሚታወቅ ቢሆንም፤ ከራሱ አቅም ውጭ የሆነን ነገር ከሌሎች ጋር ተባብሮ በመስራት ኢኮኖሚውን በማሳደግ ዜጎቹን ተጠቃሚ ማድረግ ይኖርበታል። የግንኙነቱ አንድምታ ከዚህ ዓለማዊ ሁኔታ አኳያ መታየት ያለበት ይመስለኛል።
ባለፉት አራት ወራቶች ኢትዮጵያ ውስጥ የተገኘው አንፃራዊ ሰላም ቻይናን ያበረታታት ነው ማለት ይቻላል። በለውጡ ምክንያት የተገኘው ሰላም ሀገሪቱ ከኢትዮጵያ ጋር ጠንካራ ግንኙነትን ዳግም ለማደስ ያስቻላት ይመስለኛል። ይህ ሃቅም ሁለቱ ሀገራት ሰሞኑን በቤጂንግ በተፈራረሟቸው በርካታ ስምምነቶች በሚገባ ታይቷል። ወደፊት የሀገራቱ ግንኙነት የጋራ ተጠቃሚነትን ይበልጥ በሚያሻሽል ሁኔታ ገቢራዊ ሊሆን የሚችል ነው።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ በመግቢያዬ ላይ ከጠቀስኩት ቴሌቪዥን ጋር ባደረጉት ቆይታ ያነሱት የቻይና-ኢትዮ “የዋን ሮድ ዋን ቤልት” የትስስር ሃሳብ ቀናነት ያለውና አፍሪካንም የሚጠቅም መሆኑን አንስተዋል። ይህ ሁኔታም በየሶስት ዓመቱ በመሪዎች ደረጃ በሚካሄደው ጉባኤ ላይ ተረጋግጧል። ምክንያቱም የአፍሪካ ሀገራት ከቻይና ጋር ባላቸው የምጣኔ ሃብት፣ የመሰረተ ልማት እና የማህበራዊ ዘርፎች ላይ ምክክር ሲያደርጉ የቻይና ፍላጎት እነዚህን ጉዳዩች ለማሳካት ያለመ መሆኑ ስለተገለፀ ነው።
ያም ሆኖ የቻይና- አፍሪካ የትብብር ፎረም ላይ የአፍሪካ ሀገራት ከቻይና ጋር ያላቸው ሁለትዮሽ ግንኙነትና የትብብራቸውን ቁልፍ ትኩረት ላይ መሪዎቹ ተወያይተዋል። የቻይና እና የአህጉራችን ግንኙነት የነበሩትን ልዩነቶች ያጠበበና ተግባብቶ ለጋራ ተጠቃሚነት መስራትን ማዕከል ያደረገ ነው ማለት ይቻላል። የትብብር መንፈስ የተጠናከሩበት መሆኑም እንዲሁ።
በፎረሙ ላይ የአፍሪካን የትብብር ፍላጎት በግልፅ በማስቀመጥ ውይይቱን ወደ እኩል ተጠቃሚነት መለወጥ ተችሏል። ይህም አፍሪካዊያን ለልማትና ለዕድገት እንዲተጉ በማድረግ ያላቸውን ሃብት በአግባቡ እንዲጠቀሙ የሚያደርግ ስለሆነ አፍሪካዊያን ከሁለተኛዋን የኢኮኖሚ ልዕለ ሃያል ሀገር ጋር አብረው ለመስራት መጠንከር ይኖርባቸዋል እላለሁ።