Artcles

የለውጡ ቀንዲል

የለውጡ ቀንዲል

By Admin

September 05, 2018

የለውጡ ቀንዲል

                                                          ሶሪ ገመዳ

የአገራችን ተጨባጭ ሁኔታ የሚያሳየን ለተከታታይ ሁለትና ሦስት ዓመታት ከቆየንባቸው የሠላም መደፍረስና የዜጎች መፈናቀል ሁኔታ እየወጣን መሆኑን ነው። የምንገኝበት ይህ ወቅት እጅግ ተስፋ ሰጪ ነው። ይህን ተስፋችንን ይበልጥ ማጽናት ይኖርብናል።

ዛሬ በአገራችን ውስጥ አንፃራዊ ሠላምና ጸጥታ የተገኘው ህዝቦች በፍላጎታቸው ባመጡት ለውጥ አማካኝነት ነው። ሠላምና ጸጥታችን አስተማማኝ በሆነ ቁጥር መብቶቻችን ይከበራሉ፣ ተጠቃሚነታችን በሚታይና በሚጨበጥ መልኩ ይረጋገጣሉ፣ የአገራችንም ተሰሚነትና ተቀባይነት ይበልጥ ይጎለብታል።

ታዲያ እነዚህን ሁሉን አቀፍ ፋይዳዎች ላለማጣት የተገኘውን ለውጥ ከሚያውኩ ተግባሮች በመቆጠብና ሌሎችም እንዲቆጠቡ በማድረግ ግንባር ቀደም መሆን ያስፈልጋል። ምሳሌ መሆን ከራስ የሚጀምር በመሆኑ፣ ዜጎች የለውጡ ቀንዲል ሆነው ለሠላምና ፀጥታቸው መስራት ይኖርባቸዋል።

ሰላም ከሌለ ምንም ዓይነት ተግባር መከወን አይቻልም። እንኳንስ በአገር ደረጃ አንድ ነገር ማከናወን ቀርቶ በግለሰብ ደረጃም ቢሆን ወጥቶ መግባት አስቸጋሪ ይሆናል። የሰላምን ጠቀሜታ መለኪያ ከኢትዮጵያ ህዝብ በላይ የሚያውቀው የለም። ይህ ህዝብ የሰላምን ምንነት ጠንቅቆ የሚያውቅ ነው።

የሰላም መደፍረስ ምን ያህል አስከፊ፣ ምን ያህል የሰው ህይወት ቀጣፊ፣ ምን ያህል ንብረት አውዳሚና ትውልድን አሸማቃቂ ጉዳይ መሆኑን ለዚህ ህዝብ መንገር አይቻልም፤ ያውቀዋልና። ዛሬ በሀገራችን ውስጥ አንዳንዴ በሚፈጠሩ ችግሮች ሳቢያ ሰላም ሲታወክ ህዝቡ በግንባር ቀደምትነት የሰላሙ ባለቤት ሆኖ በመቆም በለውጡ አረጋግጧል።

የአገራችን ህዝብ የያኔው አባጣና ጎርባጣ መንገድ ተመልሶ እንዳይመጣ ለሰላሙ ፀር የሆኑ ሃይሎችን በማውገዝ፣ በማጋለጥና ተገቢውን ትምህርት እንዲወስዱ በማድረግ በባለቤትነት መንፈስ እየተንቀሳቀሰ ነው።

የኢትዮጵያ ህዝብ አሁን የተገኘውን ለውጥ ለማምጣት ያደረገው ትግል የሚያስመስግነው ነው። ሰላም ከቁሳቁስ መጥፋትና መውደም ጋር ብቻ እንደማይያያዝ የሚገነዘበው ይህ ህዝብ፤ ነገ የሚገነባው ትልቅ ምጣኔ ሃብት እንደሚኖረው የሚያውቅና ለዘመናት ተነፍጎት የነበረው የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባት ስር እንዲሰድ ይሻል።

ኢትዮጵያ ውስጥ ህዝቡን ከዳር እስከ ዳር የሚያንቀሳቅስ ልማታዊ መንግስት ካለና በዚሁ መሪ አካል አስተባባሪነት ብሎም በህዝቡ የባለቤትነት መንፈስ የሚዘወር ሰላም እስካለ ድረስ፤ ሰርቶ መለወጥና መደግ እንደሚቻል በሚገባ የሚያውቅ ነው።

በሰላም ውስጥ ፍትሐዊ ተጠቃሚነትን ማረጋገጥ ይቻላል። እርግጥ ፍትሐዊ ተጠቃሚነትን የኢትዮጵያ ህዝቦች ካጸደቁት ህገ መንግስት አኳያም መመልከት ያስፈልጋል። ህገ መንግሥቱ አገሪቱ ፍትሃዊ የምጣኔ ሀብት ዓላማዎችን ማራመድ እንዳለባት በግልጽ ደንግጓል። ይህንን ዓላማ ለማረጋገጥ መንግሥት ዜጎች በአገሪቱ የሚገኘውን ሃብት በፍትሃዊነት ተጠቃሚ የሚሆኑበትን አሰራር ቀይሶ እየተንቀሳቀሰ ነው።

ሁሉም ዜጐች ለልማት መሠረት የሆኑ የትምህርትና የጤና አገልግሎቶች፣ የምግብ ዋስትና፣ የንፁህ መጠጥ ውኃ፣ የመኖሪያና የማህበራዊ ዋስትና የማግኘት መብት እንዲኖራቸው ለማድረግም እየሰራ ነው።

በዚህም ዜጐች በየትኛውም አካባቢ ንብረት የማፍራት፣ በመረጡት የሥራ መስክ የመሰማራት መብቶች ተረጋግጠው በነፃ ገበያ ኢኮኖሚ ሥርዓት የሚመራ ፈጣንና ፍትሃዊ ልማት በማምጣት በአጭር ጊዜ ውስጥ ለውጦችን እያመጣ ነው።

ከሁሉም በላይ በአጭር ጊዜ ውስጥ ዘላቂ ሰላም፣ ዴሞክራሲና ልማት ለማምጣት እየሰራ ነው። ሰላም በአስተማማኝ ሁኔታ ከተረጋገጠ የሁሉም መብቶች ተጠቃሚነት ክፍ ይላል። ስለሆነም ሰላምምንና ጸጥታን በሀገር ደረጃ ማረጋገጥ ያስፈልጋል።

የሰላም ቀንዲል የሆኑት ዜጎች በአገራቸው ውስጥ ሰላማቸውን ለማረጋገጥ የሚያደርጉት ስራዎች የኢትዮጵያን ተደማጭነት የሚጨምር ነው። የአገራችን ተሰሚነትና የትብብር ስራዎች የሚጎለብቱት በምንፈጥረው ሰላም ነው። የአገሪቱን የውጭ ግንኙነትና በዓለም አቀፍ ደረጃ ያላትን ስፍራ ለማጎልበት በጥቂት ወራቶች ውስጥ በርካታ ተግባሮች ተከናውነዋል። በአሁኑ ሰዓት ለአገሪቱ ሆነ ለአካባቢው የተረጋጋ የፖለቲካ ሂደት እንዲኖር ግጭቶችና ውዝግቦች በሰላማዊ ጥረት እንዲፈቱ ኢትዮጵያ ጥረት እያደተረገች ትገኛለች።

ኢትዮጵያ በምትከተለው በዚህ የትብብርና የሰላም ዲፕሎማሲ መርህ መሰረት በዓለም ዙሪያ ካሉት አገሮች ጋር ያላት ግንኙነት በጋራ ጥቅም ላይ እየመሰረተች ነው። ዛሬ ኢትዮጵያ ጎረቤት አገሮችንም ሆነ ሌሎችን በጠላትነት የመፈረጅ አካሄድን አትከተልም። ይህም መሰረታዊ ለውጥ አምጥቷል። ተፈላጊነቷም እንዲጨምር አድርጓል።

አገሪቱ ከውርደት፣ ከኋላ ቀርነትና ከተለያዩ የስጋት ምንጮች ነፃ ልትሆን የምትችለው፣ ፈጣን የኢኮኖሚ ልማት እንዲሁም የዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታና መልካም አስተዳደር በተሳካ መንገድ ከተካሄዱ ነው።

እነዚህ ሁኔታዎች እንዲካሄዱም ሰላምና ፀጥታ ወሳኝ ጉዳይ ነው። ሰላምና ጸጥታችን ደግሞ ኢትዮጵያን ወደ ተፈላጊነት ማማ ላይ የሚያወጧት መሆናቸውን በአጭር ጊዜ ውስጥ መመልከት ችለናል።

አገራችን በአጭር ጊዜ ውስጥ የተከተለችው የፖለቲካ ዲፕሎማሲ ለተፈላጊነቷ መጨመር ምክንያት ሆኗል። በአሁኑ ሰዓት ኢትዮጵያ ከተለያዩ ሀገራትና ተቋማት ጋር የምታደርጋቸው ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነቶች ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገና እየጎለበተ መጥቷል።

ኢትዮጵያ በሰጥቶ መቀበል መርህ ከልዩ ልዩ አገሮች ጋር ግንኙነቷን በማጠናከር የኢንቨስትመንት ፍሰት እንዲጨምር እየሰራች ነው። በተለይ ከኤርትራ ጋር በፈጠረችው ሰላም በጋራ ተጠቃሚነት መርህ ለመስራት እየተጋች ነው።

አገራችን የምስራቅ አፍሪካን ሰላም ለማስጠበቅ ብሎም የዓለማችን ጠንቅ የሆነውን አሸባሪነትን በመዋጋት እያከናወነቻቸው ያለችው ተግባራትም ለተፈላጊነቷ መሰረት ሆነዋታል። ይህን ማጠናከርም ያስፈልጋል። ምክንያቱም የጎረቤቶቻችን ሰላም መሆን በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ የእኛም ሰላም ስለሆነ ነው።

ሰላምና ጸጥታችንን በአገር ውስጥ በማስፈን ለጎረቤቶቻችንም ተምሳሌት መሆን አለብን። እኛ ተምሳሌት ስንሆን ጎረቤቶቻችንም ስለ ራሳቸው ሰላም ያስባሉ። ይህ እንዲሆን ግን ዜጎች በአገር ውስጥ ሰላማቸውን በማስጠበቅ ቀንዲል ሆነው መሰለፍ አለባቸው። የሰላም ቀንዲል የሆኑት የአገራችን ህዝቦች ለውጡን በማጠናከር ሰላማቸውን ማጎለበት ይኖርባቸዋል።