Artcles

በፍቅር ተደምረን፣ በይቅርታ ለመሻገር∙∙∙

በፍቅር ተደምረን፣ በይቅርታ ለመሻገር∙∙∙

By Admin

September 10, 2018

በፍቅር ተደምረን፣ በይቅርታ ለመሻገር∙∙∙

ስሜነህ

የጳጉሜ ወር የተለየ የዘመን አቆጣጠር ለምንከተለው ኢትዮጵያውያን ብዙ ተግባራትን መከወኛ ወር ተደርጋ ትቆጠራለች። የዘንደሮው የጳጉሜ ወርም “በፍቅር እንደመር፤ በይቅርታ እንሻገር” በሚል መሪ ሃሳብ የተለያዩ የበጎ አድራጎት ስራዎችን በማከናወን እየተከበረ ይገኛል። ከነዚህም መካከል የጽዳት ስራ፤ ኑሯቸው በዝቅተኛ ደረጃ ለሚገኙ ህጻናት የመማሪያ ቁሳቁስ በማሰባሰብና አረጋውያንን በመደገፍ መላው ህብረተሰብ የመንግስትና የግል ተቋማት ተሳትፎ እያደረጉ ይገኛሉ።

የጳጉሜ ወር ቂም በቀልና ጥላቻን ለማስወገድና ያለፈውን ይቅር የምንባባልበት እንዲሆንም መርህ ወጥቶ እየተሰራበት ነው። በዚህ መሰረት ጳጉሜ 1 የሰላም ቀን፤ ጳጉሜ 2 የፍቅር ቀን፤ ጳጉሜ 3 የይቅርታ ቀን፤ ጳጉሜ 4 የመደመር ቀን፤ ጳጉሜ 5 የአንድነት ቀን ተብሎ የተሰየመበትና በዚሁ አግባብ ቀናቱ ትርጉም ባለው መልኩ ስራ ላይ የዋሉት በአዲሱ አመት ሁሉም በመደመር እንዲሰራ፤ በዚህም ዘመናትን በስኬት እንዲሻገር የሚያስችል ተስፋ ለመሰነቅ መሆኑ አያጠያይቅምና ፤ በአዲሱ አመት በፍቅር ተደምረን ዘመናትን ለመሻገር በሚያስችሉን ጉዳዮች ላይ በዚህችው በዿግሚት መነጋገር ተገቢ ይሆናል።  

መጪው አዲስ አመት ‘በፍቅር እንደመር በይቅርታ እንሻገር’ በሚል መሪ ቃል ከ25 ሺህ በላይ ህዝብ በሚገኝበት በሚሊኒየም አዳራሽ በድምቀት የሚከበር መሆኑን የተመለከተው የመንግስት ኮሙዩኒዩኬሽን ጉዳዮች ጽ/ቤት መረጃ የውይይታችን መነሻ ቢሆን ተገቢና ልክ ይሆናልና ከዚያው እንነሳ።  

መንግስት በአገሪቱ ተስተውሎ የነበረውን ቀውስ በትክክለኛ መንገድ በመፍታት በህብረተሰቡ ሁለንተናዊ ድጋፍና ትብብር የሪፎርም ስራዎችን በመስራት የለውጥ፣ የአንድነትና የይቅርታ ሂደት በመጀመሩ መጪውን አዲስ አመት በደማቅ ሁኔታ ለመቀበል ማስፈለጉ ምክንያታዊና ይልቁንመ ባይፈልገው በገረመን በነበር።

ከዚህ መረጃ ተነስተን በመንግስት ደረጃ መጪውን አዲስ አመት በደማቅ ሁኔታ ለማክበር የተፈለገበትን መሰረታዊ ምክንያት ብንሻ ምላሹ ቀላል ነው።ይኸውም ካሳለፍናቸው  ሶስት የጨለማ ዓመታት ጋር የተያያዘ እና ከነዚህ የከፉ የጥላቻ አመታት አንጎበር ለመላቀቅ እንዲቻለን የመሆኑ እውነታ ነው መሰረታዊው መነሻ።ወደ አዲሱ አመት በምነሻገርበት ዋዜማ ላይ በውጭ አገር ከሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ጋር የነበረውን ችግር መፍታት መቻሉ፣ የፖለቲካ ምህዳሩን በማስፋት በትጥቅ ትግል ሲንቀሳቀሱ የነበሩ የፖለቲካ ድርጅቶች ወደ አገር ቤት ገብተው በሰላማዊ ሁኔታ ለመስራት መወሰናቸው፣ እንዲሁም የሀይማኖት መሪዎች የነበራቸውን ልዩነት ወደ አንድነት የቀየሩበት ይቅርታና አንድነት በተግባር የታየበት ወቅት መሆኑ በራሱ መጪውን አዲስ አመት በላቀ የመደመር ጥበብ በስኬት ለመሻገር ያስችለናልና በድርብርብ የደመቁ የአዲስ አመት ሁነቶች ማክበሩ ተገቢና እዚያው ሳለም አዲሱ የለውጥ አመራር ስራውን እየሰራ የበለጠም ወደህዝብ እየቀረበ መሆኑን የሚያጠይቅ ነው።

ባሳለፍናቸው ሶስት የከፉ አመታት  ውስጥ በገዥዎች የሚፈጸሙት ግፍና በደሎች አስቆጥተውት ሕዝቡ በከፊልም ቢሆን ጠንካራ ተቃውሞዎቹን አድርጓል። እነዚህ መነሳሳቶች በአዲሱ ዓመት ውስጥ ጎልተው ተስፋፍተውና ርስ-በርስ ተሳስረው መላውን የኢትዮጵያ ህዝብ  በፍቅር ደምረው በይቅርታ ሊያሻግሩት ግድ ይሆናል።

ከ2010 ዋዜማ ጀምሮ እስከመጋቢት መባቻ በነበሩት ወራት  ነባርና አመርቃዥ እንዲሁም አዳዲስ ችግሮች የኢትዮጵያውያን ሕዝብ ክፉኛ ተፈታትነውት የነበረ መሆኑ የማይዘነጋ እና አሁንም ከአንጎበሩ ያልተላቀቅን መሆኑ እሙን ነው። ግፍና በደሎች በዝተው መላውን ሕዝብ አንገሽግሸውታል። በተወሰኑ የሀገራችን ክፍሎች ውስጥ በተለይም ወጣቶች ቆርጠውና ደፍረው ገዥዎቻችንን በመጋፈጣቸው እብሪተኞቹ ገዥዎች እንዲርበተብቱ አድርገዋል። ስለሆነም ዐመቱ የማይረሳ ሕዝቡ በራስ-ተነሳሽነት ብርቱ ትግል ያደረግበት ታሪካዊ ዐመት ሆኖ ነው የሚኖረው። ግፈኞቹ ገዥዎች በሠላማዊ ሠልፈኞች ላይ የፈጸሙት ጭፍጨፋ፣ ግድያና ድብደባ፣ በገፍ ማሠርና ማሠቃየት፣ ለአሥር ወራት የቀጠለ በአስቸኳይ-ጊዜ ዓዋጅ ሥር የተፈጸመ የረገጣ-አገዛዝ፣ በቅሊንጦ እስር-ቤት ውስጥ የተፈጸመው ግድያ፤ በዒሬቻ-በዓል ላይ የተፈጸመ የግፍ ጭፍጨፋ፣ በቆሻሻ ናዳ መደርመስ የተፈጸመ ዕልቂት፣ ∙∙∙∙ምኑ ቅጡ።

ይሁን ብሎ በርካታውን ህዝብ ርስ-በርስ የማጋጨት ተንኮል፣ መሬት ነጠቃና ባለቤቶቹን የማፈናቀል ተግባር፣ ጭምልቅ-ያለ ሙስና፣ የሕግ-የበላይነት አለመኖርና የፍትህ ዕጦት፣ የኑሮ -ውድነት፣ ዐይን ያወጣ አድላዊነትና ብልሹ አስተዳደር፣ ወጣት ዜጎች ሀገራቸው-ውስጥ ሰርቶ በሠላም የመኖር ተስፋ-እያጡ ወይንም ለህይወታቸው ከመስጋት እየተሰደዱ በየምድረ-በዳው፣ በየባህሮቹ ዉስጥ በባእዳን ሀገሮች ዉስጥ ለመሠቃየት፣ ለመማቀቅ ለመደፈርና ለዕልቂት እንዲዳረጉ በሚያደርጉ፣ … ሁኔታዎች  ወዘተ ሲታወስ ይህን አዲስ በመደመር እና በይቅርታ የተዋጀ አመት በደማቁ አለማክበር ምናልባት አጋንኜው እንዳይሆን እንጂ መንግስታዊ ወንጀል ይሆናል።

እኒህ ብቻ አይደሉም የተደረመሱት ሌሎችም አዳዲስ ድሎች የመጡበት የመደመር ዘመን ነው። በኢኮኖሚው መስክ የነበረውን የውጭ ምንዛሬ እጥረት ኢንቨስትመንት በመሳብና የዳያስፖራ ትረስት ፈንድ በመቋቋም ችግሩን በፍጥነት ማስወገድ ተችሏል።   በዲፕለማሲው በኩል ከጎረቤት አገራት ጋር በተለይ ከኤርትራ ጋር የነበረውን ሻካራ ግንኙነት በመፍታት ወደ እርቅና ሰላም የተመጣበትም ጊዜ ነው ።

ለረዥም አመታት ታስረው የነበሩ የፖለቲካ እስረኞችንም በመፍታት አገራዊ መግባባት የተፈጠረበትና በይቅርታ የተሻገርንበት፤ የዘመነ ፍዳን ድልድይ ሰብረን የዘመነ ፍስሃን የፍቅር ግንብ የገነባንበት ዘመን ነው። ስለሆነም በአጭር ጊዜ ውስጥ የመጣውን የለውጥ ሂደት በመጪውም አመት በአዲስ ተስፋና በተጠናከረ ሁኔታ ለማስቀጠል ቃልን የማደስ መርሀ ግብር ማክበር እጅግ ከበቂ በላይ የሆነ ምክንያታዊነት ነው።  

እንደመንግስት በዚህ ደረጃ ዝግጁነት ካለ እንደህዝብ በፍቅር ተደምረን በይቅርታ ለመሻገር የምንሻ ከሆነ ባሳለፍናቸው የጨለማ አመታት ለመለወጥ ባለን መሻት ልክ ውስጣችን ያመነ፣ አቋማችን የሰከነ፣ እርምጃችን የተካነ ያልነበረ መሆኑን ከማመን መጀመር የግድ ይሆናል፡፡ ባሳለፍናቸው የጨለማ አመታት በማወቅም ይሁን ባለማወቅ ነፍሳችን በሃሳዊ ኩራት የረጋች፣ በግለኝነት የተዘጋች፣ በምንቸገረኝነት የተወጋች ቁስለኛ የነበረች መሆኑንም ማመን በፍቅር ተደምሮ በይቅርታ ለመሻገር መደላድል ይሆናል፡፡ በፍቅር ተደምሮ በይቅርታ ለመሻገር ከሞላ ጎደል ስለ ሃገራችን ከከንፈር ያለፈ ትኩረት፣ ከልብ የገዘፈ ህብረት ያልነበረን መሆኑንም መቀበል ይጠይቃል ፡፡ አንድነታችን የዕድር፣ በጀታችን የብድር ነበረ፡፡ ይህም አብሮ ከመተለቅ አብሮ ማለቅን ስውር ግብ ባደረገው ህይወታችን ለሽሚያ እንጂ ለቅድሚያ፣ ለመኳተን እንጂ ለመተንተን ልግመኞች በመሆናችን ውስጥ ተስተውሎ የነበረ መሆኑንም ማስታወስ በፍቅር ተደምሮ በይቅርታ ለመሻገር ይበጃል፡፡ እርስበርሳችን በጋራ የምንኖር ባለጋራዎች ነንና አቋራጫችን የረዘመ፣ መፍትሔያችን የቆዘመ እንደነበር አለ፡፡ ከመተላለፍ መቆላለፍ አሁንም በላያችን እንደነገሰ ነው፡፡ ከመደናነቅ መተናነቅ እንዳከባበረን ከዛሬ ደርሰናል፡፡ በዘመናችን ተመሳስሎ ማደር እንጂ ተለያይቶ መደራደር፤ ሲያሳጣ እንጂ ሲያዋጣ ተመልክተን ስለማናውቅ፣ የብሔር እንጂ የሀሳብ ልዩነት ዛሬም የገባን አይመስልም፡፡ በአንድ አቅጣጫ ፈጠን፣ በአንድ ሩጫ ተመስጠን ቀርተናል፡፡ ንግግራችን የፍራቻ ምግባራችን የዘመቻ ነው፡፡ ከመወያየት መተያየት፣ ከመኮረጅ መፈረጅ ይቀለናል፡፡ ለመውደድ አደብ፣ ለመጥላት ሰበብ የለንም፡፡ ውንጀላችን ያለቦታው፣ ውዳሴያችን ያለጌታው እንደሆነ ከዛሬ ላይ ደርሰናል፡፡ በዚህ ሁሉ ምስቅልቅል ውስጥ ግን ይህን የሚያመክን አዲስ የለውጥ ስርአት ፈጥረናል።አዲሱ አመታችን ደግሞ ከፈጠርነው ስርአት በመለስ በፍቅር ተደምረን በይቅርታ መሻገር የሚያስችሉንን ተግባራት መፈጸም ግድ ይሆናል።

በዚህ አዲስ አመት በለውጡ አመራር ታግዘን  አዲስ የመደመርና የይቅርታ ማንነት መቀመር አለብን፡፡ ከአቧራ ምኞት ከአቧራ ህይወት ለመውጣት ከላይ ከተመለከተው ምስቅልቅል አኳያ የተገናዘበ ትጋት ግድ ይለናል፡፡ የቤታችን ሰላምታ፣ የስራ ቦታችንም እንቢልታ በፍቅር ተደምረን በይቅርታ መሻገርን ታሳቢ ያደረገ ይሁን፡፡ በዚህ አዲስ አመት ወደ ብርሃን በመውጣት ጥበብ እንካፈል፣ ግኝት እንፈልፍል፡፡ ህሊናችንን እናድስ፣ ኑሮን እናወድስ፡፡ በዚህ የመደመር አዲስ ዓመት ለመናቆር ሳይሆን ለመፋቀር ቦታ እንስጥ፡፡ እንደ ግለሰብ መቋሚያ የሚያሲዝ እምነት ብቻ ሳይሆን እንደ ማህበረሰብ መቋቋሚያ የሚሆን እውነት እንጨብጥ፡፡  በርቀት መነቋቆር ሳይን በቅርበት መነጋገር ባህል ይሁን፡፡ በዚህ አዲስ ዓመት ከአሮጌ ማንነት እንውጣ!!