Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

“ፈረሱም”፣ “ጋሪውም” ይስከን…

0 1,682

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

“ፈረሱም”፣ “ጋሪውም” ይስከን…

                                                       ዋሪ አባፊጣ

ይህ ሁሉ ተጎታች “ጋሪ” በአንድ ዓይነት አስተሳሰብ ህዝብን ማረድ፣ ዘራፊነትንና ውንብድናን ሰልጥኖ ወይም “ሰይጥኖ” ተሰማርቷል ብሎ መደምደም እንደምን ይቻላል?..እርግጥ ከመሃሉ እምቢተኛ መኖሩ ተፈጥሮአዊና ባሀሪያዊ ነው። የሰው ልጅ በአፈጣጠሩ ማመዛዝን የሚችል ህሊና ያለው ፍጡር ነው። በተለይ ኢትዮጵያዊያን ግብረገብነትን ተላብሰን ያደግን በመሆናችን፣ በእንዲህ ዓይነት አሳፋሪና ሌላው ዓለም በሚሳለቅብን ተግባር ውስጥ ተዘፍቀን ለመገኘት ሞራላዊ እሴቶቻችን (Moral Values) አይፈቅዱልንም። እናም ‘እነዚህ ሰዎች እነማን ናቸው?’…

 

ምን ላይ እንዳነበብኩት ለጊዜው ትዝ አይለኝም። ግና ታሪኩ እንዲህ ነው።…ጊዜው የፊውዳሉ ስርዓት በገነገነበት በንጉሱ የስልጣን ዘመን የመጨረሻዎቹ ዓመታት ገደማ ነው። በዚያን ወቅት አንድ ሙሴ ጋሌብ የሚባል አርመናዊ ባለሃብት ወደ ኢትዮጵያ ይመጣል። አመጣጡ ፋብሪካ ከፍቶ በመስራት ትርፋማ ለመሆን ነው። እናም ከንጉሳውያኑ መሪዎች ፈቃድ ካገኘ በኋላ ጥሬ ዕቃው ከሀገር ውስጥ የሚገኝ አዋጪ የሆነ መጠነኛ ፋብሪካ ይከፍታል።

ፋብሪካው የተከፈተው ኢትዮጵያዊያኑ ጭሰኞች እነ ሩጋ መንደር አቅራቢያ ነው። ሚስተር ጋሌብ ጭሰኞቹን እነ ሩጋን ወዛደሮች በማድረግ በአነስተኛ ገንዘብ ለማሰራት አሰበ። እናም የአካባቢውን ዋነኛ ተሰሚ ግለሰብ አቶ ሩጋ ባልቻን በአስተርጓሚ አነጋገረው። አብዛኛው ጭሰኛ የራሱ መሬት የሌለው በመሆኑ፤ አቶ ሩጋ የአካባቢው ሰው ትንሽ ስልጠና ከተሰጠው ሊሰራ እንደሚችል አረጋገጡለት። “በጭሰኝነት ሰርተንና ለባለርስቱ ሰጥተን የሚተርፈን ነገር ያንተ የተሻለ ከሆነ ፋብሪካ ውስጥ ገብተን ለመስራት ዝግጁ ነን።” የሚል ምላሽ ለሚስተር ጋሌብ ይሰጠዋል—የመንደሯን አባወራዎች ካነጋገረ በኋላ።…በዚህ ስምምነትም እነ ሩጋ ጭሰኝነታቸውን ትተው የፋብሪካ ሰራተኛ ሆኑ። ስራውንም ለመዱት። ፋብሪካውም ትርፋማ ሆነ። ሙሴ ጋሌብም ቢጠሩት የማይሰማ ዲታ ሆነ። ታዲያ የሰው ልጅ በባህሪው ሁሌም የተሻለን ነገርን ፈላጊ ስለሆነ፤ እነ ሩጋ ጥያቄ ማንሳት ጀመሩ።…

ጥያቄያቸውም “ደመወዝ ይጨመርልን” የሚል ነበር። ለዚህ ያቀረቡት ምክንያትም “ሙሴ ጋሌብ በእኛ ጉልበት እጅግ ሃብታም ሆኗል። እኛ ባንኖር ኖሩ ፋብሪካው አትራፊ አይሆንም ነበር። ስለዚህ አሁን የሚከፍለን ገንዘብ ትንሽ በመሆኑና ከቀለብና ከልጆቻችን ልብስ ወጪ አይተርፈንም። ስለዚህ ገንዘብ ይጨመርልን” የሚል ነው። ሙሴ ጋሌብ በበኩላቸው፤ “የለም። እኔ ከሀገሬ ካፒታል ይዤ ባልመጣ፣ ለፋብሪካ መስሪያ የሚሆን ቁሳቁሶችን ከውጭ ባላስገባና ፋብሪካውን ባልገነባ እናንተ ጭሰኞች ሆናችሁ ትቀሩ ነበር። ምን ዓይነት ስራ እንደሚያዋጣኝ አዕምሮዬን በማሰራቴና ገንዘቤን በማውጣቴ ሃብታም ልሆን ችያለሁ።” የሚል ሃሳብ ያራምዳሉ። በዚህ መሃከል ጭቅጭቅ ይነሳልና እነ ሩጋ ደመወዝ እንዲጨምርላቸው ለሀገራቸው ፍርድ ቤት “አቤት!” ይላሉ። ፍርድ ቤቱም እነ ሩጋን “አርፋችሁ ስሩ፣ እምቢ ካላችሁ ባለርስት ፈልጉና ወደ ጭሰኝነታችሁ ተመለሱ” የሚል ብይን ይወስንባቸዋል። ውዝግቡም በዚህ ተቋጨ። እነ ሩጋም የፋብሪካ ስራቸውን ማከናወን ጀመሩ።  

እዚህ ላይ ማንሳት የፈለግኩት ‘የወቅቱ ፍርድ ቤት ውሳኔ ትክክል ነው ወይስ አይደለም?’ የሚል ጥያቄን ለማንሳት አይደለም— ለዚህ ፅሑፍ አንባቢ አንድ ጥያቄን ማንሳት እንጂ። ጥያቄው እውነትን የተመለከተ ነው። እውን ሙሴ ጋሌብ ነው ወይስ እነ ሩጋ ናቸው እውነት እውነትንስ እንደዴት ነው የምንመለከተው?….በእውነቱ የዚህ ፅሑፍ አንባቢ ሊወያይበት ይገባል።… ያም ሆኖ በእኔ እምነት፤ ሙሴ ጋሌብም ትክክል ነው፤ እነ ሩጋም ትክከል ናቸው። እዚህ ላይ ‘ሁለት እውነት ሊኖር አይችልም’ የሚል መከራከሪያ ሊነሳ ይችላል። ሆኖም መከራከሪያው ከአንፃራዊ መለኪያ አኳያ መታየት ይኖርበታል ባይ ነኝ።

እውነት አንፃራዊ ነው። ለእኔ እውነት የሆነ ጉዳይ፤ ለሌላው ሰው ላይሆን ይችላል። ለእኔ ሐሰት የሆነ ደግሞ ለሌላው ሰው ቅልጥ ያለ አውነት ሊሆን ይችላል። እውነትና ውበት እንደተመልካቹ ነው ማለትም የሚቻል ይመስለኛል። ሙሴ ጋሌብ ጭንቅላታቸውን አሰርተው፣ ፋብሪካ ከፍተው ሃብታም መሆናቸው እውነት ነው። እነ ሩጋም በርሳቸው ፋብሪካ ውስጥ በመስራታቸው እርሳቸውን ሃብታም ማድረጋቸውም እውነት ነው።

ዳሩ ግን በአንድ በሚያግባባ ሶስተኛ እውነት መመራት የግድ ነው። ሶስተኛው እውነት የእነ ሩጋ ስራ መልቀቅ አሊያም በተሰጣቸው ደመወዝ አሜን ብሎ መስራት ነው። ሶስተኛው የፋብሪካው ባለንብረት የሆነውንና “ፈረሱን” አሊያም በወቅቱ የስራው ተጠሪ ወይም “ጋሪ” የሆኑትን እነ ሩጋን ማግባባት አለበት። በዚህ እውነት ውስጥ ሁለቱም ወገኖች አማራጮቻቸውን ፈትሸው ውሳኔ ላይ ይደርሳሉ ማለት ነው። ምናልባት ሰከን ብለው ከተነጋገሩ፤ በእውቁ ፈላስፋ፤ በአሪስጣጣሊስ አማካይ የእውነት ቦታ (The Golden Mean) ላይ ተገናኝተው ሊስማሙ ይችላሉ። ለዚህም ነው “ፈረሱም”፣ ጋሪውም ይስከኑ የሚባለው።

በእኔ እምነት፤ ከመሰንበቻው በቡራዩና አካባቢው በዜጎች ላይ ዘግናኝ ጭፍጨፋ አቀነባባሪዎቹ “ፈረሶቹም” ይሁኑ በማወቅም ሆነ ባለማወቅ የተጎተቱት “ጋሪዎቹ” እንደ ዜጋ ሰከን ብለው ማሰብ አለባቸው። ትናንት የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን በሰጠው መግለጫ፤ በቡራዩና በአካባቢው ለተፈፀመው የህይወት ማጥፋት፣ የዘረፋ፣ የአስገድዶ የመድፈርና የማፈናቀል ተግባር ውስጥ አንዳንድ የፖለቲካ ሃይሎችና የውጭ አካላት በሀገሪቱ ውስጥ በታቀደ መልኩ ብሔርን ከብሔር የማጋጨት እንዲሁም የሃይማኖት ጦርነት የማስነሳት ተግባርን ለመከወን እየሰሩ ናቸው።

“የውጭውን ኃይል” ለጊዜው እንተወውና ፖሊስ በስም ባይጠቅሳቸውም (አለመጥቀሱ ትክክል ይመስለኛል) አንዳንድ የፖለቲካ ሃይሎች እንዲህ ዓይነቱን አሳዛኝ ድርጊት እንዲፈፀም ከኋላ ሆነው የመሩት ከሆነ አደብ መግዛት አለባቸው። ፓርቲዎቹ ምናልባትም በስም ያልተገለፀውን “የውጭ ሃይል” እሳቤን ይዘው በወገናቸው ህይወትና ስቃይ ትርፍ ለማግኘት ካሰቡ በእርግጥም ተደምረዋል ለማለት አይቻልም። ወይም “ተደምረን በሰለማዊ ትግል ለመንቀሳቀስ ነው ወደ ሀገር ቤት የገባነው” የሚሉት ነገርም ከተረትነት ሊያልፍ የሚችል አይመስለኝም። እናም ከፌዴራል ፖሊስ መግለጫ እንደተረዳሁት፤ “ፈረስ ያደርሳል እንጂ አይዋጋም” በሚል ስሌት አንዳንድ የፖለቲካ ሃይሎች ጉዳዩን ከፈፀሙት እኔ በበኩሌ በእነርሱ ቦታ ሆኜ ለማፈር እገደዳለሁ።

እኔ እስከሚገባኝ ድረስ፤ ወደ ሀገር ቤት የመጡት የፖለቲካ ድርጅት አመራሮች በእድሜ የደረጁና ብዙ የትግል ልምድ ያላቸው ናቸው። ወደ ሀገር ቤት ሲመጡም ያላቸውን የፖለቲካ መስር በሰላማዊ መንገድ ለህዝባቸው አስረድተውና በምርጫ አሸንፈው ሀገር ለመምራት ነው። ይህን የሚያደርጉት ደግሞ ህዝብ ሲኖር ነው። ህዝብ ከሌለ፤ በባዶ መሬት ላይ ሊወዳደሩና ስልጣን ሊይዙ አይችሉም። የህዝባቸው ስቃይ ሊያማቸው ይገባል። ህዝባቸው ሲጎዳ ራሳቸው እንደተጎዱ መቁጠር አለባቸው። ህዝብን ለመጥቀም እሰራለሁ ከሚል የፖለቲካ ድርጅት የሚጠበቀው እንዲህ ዓይነቱ ህዝባዊ ወገንተኝነትን የተላበሰ አስተሳሰብ ነው። እናም ወጣቶችን ኢትዮጵያዊ እሴት ላልሆነ እኩይ ዓላማ ለማሰማራት እንደ ፈረስ ተሸክመው ክፋትን የሚያሰራጩ ከሆነ፤ ቢያንስ እንደ ዜጋ ደግመው ደጋግመው ሊያስቡ ይገባል።

ያም ሆኖ እዚህ ሀገር ውስጥ የተጀመረው ለውጥ በዚህ ዓይነት ሁኔታ ሊቀለበስ እንደማይችልም መገንዘብ ያባት ነው። አርቆ አስተዋይነትም ጭምር ይመስለኛል። ምክንያቱም የለውጡ ባለቤት መላው የኢትዮጵያ ህዝብ ስለሆነ ነው። ለውጡን ለመቀልበስ የሚደረግ ማንኛውም እኩይ ምግባር ባለቤቱ የሆነው ህዝብ እስካለ ድረስ ግቡን ሊመታ አይችልም። ስለሆነም ለውጡን ለመቀልበስ “በፈረስነት” እየሰሩ ያሉ አካላት ይህን እውነታ ተገንዝበው ወደ ውስጣቸው ማየት ያለባቸው ይመስለኛል። “ፈረሱ” ከሚጎትተው “ጋሪ” ቀድሞ የሚገኝ ስለሆነም ቀዳሚውን የጥሞና አየር ሰዓት ወስዶ ማገናዘብ ይኖርበታል።

በሌላ በኩልም፤ በማወቅም ይሁን ባለማወቅ አሊያም በጥቅም ተደልለው “በፈረሱ” ሴራ አስታጣቂነት ወደ ጥፋት ተልዕኮ ተጎትተው የገቡት “ጋሪዎችም” ህሊናቸውን ሊያሰሩ ይገባል። እነዚህ ተጠርጣሪ ወገኖች ከአዲስ አበባና ከቡራዩ አካባቢ የተያዙ ናቸው። ቁጥራቸውም ከ700 እንደሚልቅ ፌዴራል ፖሊስ ነግሮናል። መቼም ይህ ሁሉ ሰው አንድ ዓይነት የተዛባ አስተሳሰብ ያለው ነው ለማለት አያስደፍርም።

ይህ ሁሉ ተጎታች “ጋሪ” በአንድ ዓይነት አስተሳሰብ ህዝብን ማረድ፣ ዘራፊነትንና ውንብድናን ሰልጥኖ ወይም “ሰይጥኖ” ተሰማርቷል ብሎ መደምደም እንደምን ይቻላል?..እርግጥ ከመሃሉ እምቢተኛ መኖሩ ተፈጥሮአዊና ባሀሪያዊ ነው። የሰው ልጅ በአፈጣጠሩ ሊያመዛዝን የሚችል ህሊና ያለው ፍጡር ነው። በተለይ ኢትዮጵያዊያን ግብረገብነትን ተላብሰን ያደግን በመሆናችን፣ በእንዲህ ዓይነት አሳፋሪና ሌላው ዓለም በሚሳለቅብን ተግባር ውስጥ ተዘፍቀን ለመገኘት ሞራላዊ እሴቶቻችን (Moral Values) አይፈቅዱልንም። እናም ‘እነዚህ ሰዎች እነማን ናቸው?’ ብለን ለመጠየቅ እንገደዳለን።

በእኔ እምነት፤ እነዚህ ሰዎች “በቦይ ውሃነት” የሚመሰሉ ናቸው። የቦይ ውሃ ታውቃላችሁ?…በተቀደደለት የቦይ መስመር ብቻ ዝም ብሎ ይፈሳል። ከመስመሩ አይወጣም። ቦዩ ወደ ታች ከተቀደደ ወደ ታች ቀጥ ብሎ ይነጉዳል፤ ከመስመሩ ሊወጣ የሚችልበት ባህሪያዊ ተፈጥሮ የለውም—“የቦይ ውሃው”።

ተጎታቹ “ጋሪ” ወይም “የቦይ ውሃው” ግዑዝ ነገር አይደለም። ሰው ነው። እንደ ሰው ያስባል። እንደ ሰው ክፉውንና ደጉን ይለያል። ክፋትና ጥቃት መሸሸጊያ እንደሌላቸው ያውቃል። ችግር ካለም በመታበይ ሳይሆን በህግ አግባብ ማቅረብን ያውቃል። በፊውዳሉ ዘመን ከነበሩት ከእነ አቶ ሩጋ በተሻለ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ሁኔታ ውስጥ የሚገኝ ነው። እናም በሰለጠነ ዘመን ውስጥ እየኖረ ከእነ አቶ ሩጋ በታች እያሰበ ህግንና የበላይነቱን ካላወቀ፤ በእውነቱ የህይወት መርሁ ዝም ብሎ መጎተት ብቻ ነው የሚሆነው። እናም ተጎታቹ “ጋሪ” አሳፋሪ ነው።

ለውጥ ቀልባሽ ሃሳቦችን እያስታጠቀ ፊት ለፊት የሚመራው “ፈረሱንም” ይሁን ተጎታቹን “ጋሪ” ህግ ግልፅነት በተሞላውና የህዝቡን ሰላም ሊያረጋጋ በሚችል መልኩ መዳኘት ይኖርበታል። ተጠርጣሪዎች ከሌላ ፕላኔት የመጡ አይደሉም። ይህ ህዝብ አቅፎና ደግፎ የያዛቸው፤ አሳድጎም ለአቅመ- “ፈረስነትና ጋሪነት” ያበቃቸው ናቸው። የህዝቡ ወኪል ደግሞ መንግስት ነው። መንግስት የህግ የበላይነትን ማስከበር ይኖርበታል።

አጥፊዎችን ያለ አንዳች ማቅማማት ወደ ህግ አቅርቦ በማስቀጣት የደረሰበትን ድምዳሜም ለህዝቡ ግልፅነት በተሞላውና ተዓማኒ በሆነ መንገድም ማሳወቅ አለበት። ማንኛውንም ጉዳይ ለህዝቡ የሚያሳውቁ አካላት፤ በህዝቡ የሚታመኑ እንዲሁም አሳማኝ ጉዳዩችን ማንሳት የሚችሉ ብቃት ያላቸው አስፈፃሚ አካላት መሆን አለባቸው። አስፈፃሚዎቹ እውነትን ይዘው ቢመጡ እንኳን ህዝበ በሚገባው ቋንቋ የማስረዳት ብቃት ከሌላቸው ወይም ሙያዊ አቅምን ያተካነ ማብራሪያ ካቀረቡ አመኔታ የሚባል ነገር እንደ ማዕድን ቢቆፈርም የሚገኝ አይመስለኝም።

ያም ሆኖ በቡራዩና አካባቢው የተፈጠረውን ችግር ለመፍታትና ይህን መሰሉን ህዝብን ከህዝብ ለማጋጨት የሚደረግን ጥረት፤ መንግስት ተግባሩን እንደ ደዌ በመቁጠር አስቀድሞ የመከላከል መንገድን መከተል ይኖርበታል። አንድ ክዋኔ ከተፈፀመ በኋላ፤ የአባሮሽ ዓይነት ስትራቴጂ የትም አያደርስም። የመንግስት መዋቅር ሩቅ ዓላሚ ሆኖ የሚመጡ ችግሮችን ማሽተት ይኖርበታል። ይህም እንደ ቡራዩው ዓይነት አሳዛኝና አሳፋሪ ድርጊት እንዳይፈፀም ያግዛል፤ “ፈረሱም”፣ “ጋሪውም” እንዲሰክንም ያደርጋል።   

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy