Artcles

የብዝሃነት (Pluralism) በህብረ-ብሄራዊ (Mulitinational) የፌዴራል ስርዓት!

By Admin

September 18, 2018

የብዝሃነት (Pluralism) በህብረ-ብሄራዊ (Mulitinational) የፌዴራል ስርዓት!

( Ewnetu Bilata ,2011)

የህብረ-ብሄራዊነት ዋነኛ መገለጫዎች ከሆኑ አበይት ጉዳዮች የብሄር፤የቋንቋ ፤የሀይማኖት እና የባህል ብዝሃነት ግንባር ቀደም ተጠቃሾች ናቸው፡፡ ብዝሃነት በህብረ-ብሄራዊ የፌዴራል ስርዓት ውስጥ በሂደት የግድ መፈጠር የሚገባው ነው፡፡ ብዝሃነት ልዩነቶችን በሚያስተናገድ ሥርዓት ውስጥ ከህብረ-ብሄራዊ ውበትነት አልፎ የስርዓቱ ዋልታና ማገር እንዲሁም ማሶሶ ሆኖ በልዩነት ወስጥ ያለውን አንድነትን ያጠናክራል፡፡ ብዝሃነት በተሻለ ደረጃ ግልጽነትን ስለሚፈጥር ለኪራይ ሰብሳቢነት፤ለጥበትና ትምክህት እንዲሁም ለፀረ ሰለም ኃይሎች መደበቂያ ዋሻ ለመናድ ምቹ ሁኔታዎችን የመፍጠር እድሉ ከፍተኛ ነው፡፡ የዘርፋ ጠቢባን ብዝሃነት ከባድና አድካም ማህበራዊና ፖለቲካዊ ሂደት ውስጥ ታልፎ የሚገኝ ወይም የሚደረስ መሆኑን ለማስረዳት ሲሉ ኅብረ ብሄራዊነትን እንደ ድፍድፍ ነዳጅ ሲገልጹት ብዝሃነትን ደግሞ እንደ ተጣራ ነዳጅ እና እንደነጠረ ወርቅ ወይም ውድ መዓድን ይመስሉታል፡፡ ብዝሃነትን የሚያስተናግድ የአመለካከት የበላይነት ባልሰፈነበት ወቅትም ህብረ-ብሄራዊነትን በህግና በመመርያ ደረጃ መተግበር የሚቻል ሲሆን ብዝሃነት ግን የህብረ-ብሄራዊነትን የአመለካከት ልዕልና ማረጋገጥን ይጠይቃል. ሀገራችን ብዙህነትን ማስፈንና ማክበር ይቅርና በተፈጥሮ ብቻ በውስጧ ያለውን ልዩነት እንኳን ማስተናገድ ተስኗት ነበር፡፡ ህብረ-ብሄራዊት የሆነችው ሀገራችን በውስጧ ያሉትን ልዩነቶች አምና መቀበል ተስኗት ለበርካታ አስርት ዓመታት በእርስ በእርስ ጦርነት ስትናጥና የኋልዮሽ ጉዞ ሽምጥ ስትጋልብ ኖራ ለመናድ ጥቂት እርምጃ ሲቀራት ብረ-ብሄራዊነትን ለመጀመሪያ ጊዜ የተቀበለችው በሽግግሩ ዘመን ቻርተር ኋላም በ1987 በኢፌዴሪ ህገመንግስት ነው፡፡ ሀገራችን ልዩነቶችን አምና ለመቀበል ረጅም ዘመናትና መራራ ትግል ቢጠይቃትም አሁን ግን ከዚያ ሁሉ አስከፊ የጨለማ ዘመን አልፋ ብዙህነትን በተግባር ለማረጋገጥ ረጅሙን ጉዞ በቁርጠኝነት ጀምራለች፡፡ ብዙህነት መረጋገጥ እንደ እኛ ባለ ህብረብሄራዊ ሀገር የሰላም ፤የልማትና የዴሞክራሲ ማስፈኛ ወሳኝ መሰረት ስለሆነ በሚገባ አውቀን የበኩላችንን ድርሻ የመወጣት ለሀላፊነት አለብን፡፡ በሀገራችን ብዙህነትን አውን ለማድረግ ከሚሰሩ ስራዎች የመጀመሪያዎቹ በህብረብሄራዊ የፈዴራል ስርዓቱ ላይ በቂ ግንዛቤ ፤መግባባት እና የአመለካከት የበላይነት በሁሉም ደረጃ ማረጋገጥ ያስፈልጋል፤፤ በህብረ-ብሄራዊ የፌዴራል ስርዓታችን ውስጥ በተፈጥሮ ያለው ልዩነት በሥራና በሂደት ወደ ብዙህነት ሲያድግ፤ ህብረብሄራዊነታችን በተግባር፤በሥራ ሲረጋገጥ ሀገራዊ ውበታችንና ኩራታችን ይሆናል፡፡ ለብዙህነት መሰረት በሆነው የፌዴራል ሥርዓቱ ላይ በቂ ግንዛቤ ሳይኖር የሚሰራ ስራ ለአንድ የፖለቲካና የኢኮኖሚ ማህበረሰብ ግንባታ፤ለሰላም፤ ለዴሞክራሲና ልማት የሚኖረው በጎ አስተዋፅዎ ባይኖርም አላስፈላጊ የገንዘብ ፤የጊዜ፣ የዕውቀትና የጉልበት ብክነት ማስከተሉ አይቀርም፡፡ ስለ ብዝሃነት መስረታዊ መነሻና መድረሻ በአግባቡ መረዳትና ማስረዳት ሚና ወሳኝ ነው:: በመጀመሪያ ደረጃ ብዙህነት ማለት በተፈጥሮ የሚገኝ በዓይነት ወይም በልዩነት ላይ የተመሰረተ የቁጥር ብዙነት ብቻ ሳይሆን ሙሉ አቅማችንን ተጠቅመን በልዩነቶቻችን ውስጥ ያለውን አንድነት የውበትና የጥንካሬ ምንጭ ለማድረግና ለማጎልበት በቁርጠኝነት በመስራት የሚረጋገጥ የጥምረት እና የጥረት ውጤት የሆነ ህብር ነው፡፡ ብዙህነት የሚሠራበትና በአብሮነት ሂደት ልናሳካውና ልናጎለብተው የምንችል የመስተጋብር ውጤት ነው፡፡ብዙህነት ማለት በሀይማኖቶችና ተቋሞቻቸው እንዲሁም በብሄር/ብሄረሰሰቦች/ህዝቦች መካከል ሊኖር የሚገባውን ግንኙነት በመቻቻል፤ በመከባበርና በመረዳዳት ላይ የተመሰረተ ጠንካራ ህብረት እንዲሆን ለማድረግ በሚፈጠረው መልካም ግንኙነት የሚረጋገጥ የአብሮነት ውጤት ነው፡፡ ብዙህነት እንደ ልዩነት በተፈጥሮ ብቻ የሚገኝ ሳይሆን በተጨባጭ እንዲኖርና አንዲረጋገጥ ለማድረግ ስራን እና ጥረትን የሚፈልግ ጉዳይ ነው፡፡ በዚህም አኳኋን ሲገነባ በህብረብሄራዊ ስርዓት ውስጥ ያለው ልዩነት የውበትና የአብሮነት ማሳያ/መገለጫ ይሆናል፡፡ በሁለተኛ ደረጃ ስንመለከት ብዙህነት ማለት መቻቻል ማለት ብቻ ሳይሆን ልዩነቶቻችንን በፈጠሩት እሴቶች እና ለልዩነታችን መኖር ምክንያት በሆኑ ማንነቶቻችን ላይ መግባባት እና የጋራ ግንዛቤ (መረዳዳትን) መፍጠር ነው፡፡ መቻቻል ለአብሮነት የሚያስፈልግ የጋራ እሴት ቢሆንም ተቻችሎ ለመኖር ግን አንዱ የሌላውን እምነት ምንነት እና ማንነት በጥልቀት ማወቅ አስገዳጅ አይደለም፡፡ የማንነት እና የሀይማኖት ጥንቅሯ ብዙ በሆነባት አለማችን ውስጥ መቻቻል ብቻውን ቁንፅል የሆነ እና ጨለምተኝነትንና ቅድመ-ቅኝት (Stereotypes) ለማስወገድም በራሱ ብቻውን በቂ አይደለም፡፡ በተለያዩ ማንነቶች እንዲሁም ሀይማኖቶች መሀል ሊወገድ የሚገባው ጨለምተኝነት እስካለ እና እስካልተወገደ ድረስ ጊዜያትን ቆጥሮም ቢሆን በአሉታዊነቱ ዋጋ የሚያስከፍል እዳ ሊሆን ይችላል፡፡ ጨለምተኝነት ደግሞ መወገድ የሚችለውና የሚገባው ባማሩ ቃላት ብቻ ሳይሆን በተግባር በተረጋገጠ ቁርጠኝነት እና የስራ ውጤት ወይም መስዋዕት ነው፡፡ በሦስተኛ ደረጃ ብዙህነት ማለት በተለያዩ ሁኔታዎች በአጋጣሚ የሚፈጠር አንፃራዊነት (relativism) እና እንደየሁኔታው የሚለያይ/የሚቀያየር ሳይሆን በማንኛውም ሁኔታ እንዲኖር ለማድረግ የግድ ዋጋ ወይም መስዋዕት የሚከፈልለት/የሚከፈልበት ነው፡፡ ብዙህነት ዋጋ የሚከፈልለት እንደመሆኑ መጠን በአሁኑ ወቅት ብዙህነትን አስመልክቶ ያለ የአቅጣጫ ምልከታና እርምጃ የማንነት መገለጫዎቻችንን እንድንተው የሚጠይቅ አይደለም፡፡ ይህ ማለት ለአብሮነታችን ሲባል በሀይማኖቶች/በብሄር/ብሄረሰሰቦች/ህዝቦች ወይም ማንነቶች መሀል ያሉ ልዩነቶቻችንን መተው ወይም መካድ ሳያስፈልግ የጋራ በሆኑ ጉዳዮቻችን ላይ ግንኙነቶችን በመፍጠርና በማጠናከር አንድነትንም ጭምር ማረጋገጥ ማለት ነው፡፡ በመጨረሻም ብዙህነት የውይይት፤ድርድር እንዲሁም የሰጥቶ መቀበል ባህል መጎልበት ውጤት ሆኖ እናገኛለን፡፡ ብዙህነት ሰጥቶ መቀበልን መሠረት ያደረገ ድርድርን፤ የጋራ መረዳዳትን እና ግንዛቤ የሚፈልግ ሂደት (ሥርዓት) ነው፡፡ ውይይት የተሳታፊዎች ሁሉ መስማማት ማለት ሳይሆን ለውይይቱና ድርድሩ መሳካት ከመነሻው አንስቶ የሚደረግን ቅን እና ፅኑ ፍላጐትን ጨምሮ መልካም የሆኑ የመወያያ ሃሳቦችን እንዲሁም ጥሩ ንግግርን የሚያሰተናግድ ነው፡፡ ይህንንም ለማሳካት ሁለት ነገሮች (ሃሳቦችን) መረዳት ይፈልጋል፡፡ በአንደኛ ደረጃ ልዩነታችንን አክብረን በአንድነት ለመኖር የሚጠቅሙን አስተሳሰቦችንና ግንኙነቶችን ማዳበር አለብን፡፡ በሁለተኛ ደረጃ ደግሞ በዕለት ተዕለት ህይወታችን ውስጥ አንዱ ከሌላው ጋር የሚጋራቸው መደበኛ ያልሆኑ መግባቢያዎች ጭምር ህብረብሄራዊነትን የሚያከብሩና የሚያንፀባርቁ መሆን ይገባቸዋል ( Ewnetu Bilata ,2011)