Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

ደህና ሁኚ “ኦህዴድ”…?

ደህና ሁኚ “ኦህዴድ”…?

0 9,768

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

ደህና ሁኚ “ኦህዴድ”…?

                                                    እምአዕላፍ ህሩይ

አንድ ፓርቲ ስሙን ሲቀይር ወይም “በአዲስ መልክ ስራ ጀምረናል” ሲል፤ ‘ደህና ሁኚ’ ይባል እንደሆን አላውቅም። ምናልባት ለመጀመሪያ ጊዜ ከሆነም፤ ይህ የእኔ ሃሳብ ቀዳሚ ተደርጎ ይወሰድልኝ። አዎ! ላለፉት 27 ዓመታት በኢትዮጵያ የፖለቲካ ምህዳር ውስጥ እጅግ የሚበዛውን ህዝብ ወክላ ትንቀሳቀስ የነበረችው ኦህዴድ፤ አሮጌ ስሟንና አርማዋን እንዲሁም 14 የሚሆኑ ጉምቱ ፖለቲከኞቿን ይዛ ተሰናብታለች።

ስንብቷ ግን የምር አይደለም። ቀደም ሲል ከነበሯት 66 ነባር አመራሮች ውስጥ 16 ብቻ አስቀርታ ሌሎቹን በክብር ሸኝታለች። (እዚህ ላይ ላገለገለ ክብር የሚሰጥ እርሱም ክብር ይገባዋልና እነሆ ለአዲሱ አመራር በአክብሮት ከመቀመጫዬ ተነስቼ ባርኔጣዬን አንስቻለሁ!) ታዲያ “ኦህዴድ” እንዲሁ “መንገዱን ጨርቅ ያድርግልሽ” ተብላ አልተሸኘችም። መጠሪያዋንና አርማዋን ብትቀይርም ቅሉ፤ አርአያ ሊሆኑ በሚችሉ ወጣቶች ተደራጅታለች።

ነገርዬው ባይለይልትም፤ በአዲስ ርዕዩተ ዓለምም ብቅ ለማለትም ያሰበች ትመስላለች። አዲስ የስያሜ ጃኖ ለብሳ ብቅ እንዳለች፤ ሊቀመንበሯ ዶክተር አብይ አህመድ ለውጥን አስመልከተው፤ በደርግ ጊዜ የተካሄደው ለውጥ እንዲሁም በ1983 ዓ.ም ኢህአዴግ ያደረገው ለውጥ አለመሳካቱን መናገራቸው፤ ፓርቲያቸው በተለየ መንገድ ለመሄድ ማሰቡን ፍንጭ ይሰጣል የሚሉ ወገኖች በርካታ ናቸው። ምክንያቱም ኢህአዴግ በደርግ ላይ ያደረገው የትግል ለውጥ ካልተሳካ፤ በውስጡ የነበረችው ኦህዴድም ትከተለው የነበረው ሂደት ትክክል ስላልሆነ አሁን አዲስ መንገድ ልትቀይስ ትችላለች የሚል እምነት በብዙዎች ዘንድ ስላደረ ነው። ያም ሆኖ፤ “ኦህዴድ” ‘ደህና ሁኚ’ ተብላ፣ ነገር ግን በቅሪትነት የያዘችው ነገር በመኖሩ ሽኝቷን ሙሉዕ የሆነ አይመስለኝም። ወይም ኦህዴድ ተሸኝታለችም፣ አልተሸኘችምም ማለት የሚቻል ይመስለኛል።

ርግጥ ነው— ኦህዴድ ስሟን ወደ “ኦሮሞ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ” (ኦዴፓ) ቀይራለች። አርማዋንም በአዲስ መልክ አሳምራ ፅድት አድርጋ አቅርባለች። ዘጠኝ ነባርና አዳዲስ የስራ አስፈፃሚ ኮሚቴዎችንም መርጣለች። የዚህ ፅሑፍ አቅራቢ ጥሎበት እጅግ የሚወደው አቶ ታዬ ደንደአ የሚገኝበት 45 ማዕከላዊ ኮሚቴዎችንም መርጣለች—አዲሷ “ኦዴፓ”። ስብጥሩ “ይበል!” የሚያሰኝ ነው። በዶክተር አብይ አህመድ ሊቀመንበርነትና በክቡር ዶክተር ለማ መገርሳ ምክትል ሊቀመንበርበት የምትመራው እንዲሁም እነ ዶክተር ወርቅነህ ገበየሁን በስራ አስፈፃሚነት ያየዘችው ብሎም አቶ ታዬ ደንደአን የመሳሰሉ ትንታግ ተንታኝ ወጣቶችን ያቀፈችው “ኦዴፓ”፤ ኦሮሞን፣ ኢትዮጵያን፣ ቀጣናውንና አፍሪካን የመገንባት ራዕይ ሰንቃለች። ዶክተር አብይ የገዳ ስርዓትን ለዓለም ያበረከተው የኦሮሞ ህዝብ፤ አዳዲስ መንገዶችን ለሀገራችን፣ ለምስራቅ አፍሪካና ለአፍሪካ ያቀርባል ማለታቸው ለዚሁ ይመስለኛል። አዎ! ይህ የኦዴፓ ቅርብና ሩቅ ራዕይን የሰነቀ አላሚነት (far sighted outlook) ከተሰናባቿ “ኦህዴድ” ለየት የሚያደርጋት ይመስለኛል። የአዲሱ ትውልድ ነፀብራቅና ወኪል ሆናም አግኝቻታለሁ። ዘመኑን የምትመጥንና ከዓለም ተለዋዋጭ ሁኔታ ጋር አብራ መጓዝ የሚችል ቁመናም ይዛለች። እናም “እንኳን ደህና መጣሽ ኦዴፓ!” ልላት እፈልጋለሁ።      

ግና ከአራት ዓመት በፊት የነበረችው ከአራት ላመት በፊት የነበረችውን “ኦህዴድ” ዛሬም ሳስባት አንድ ተረት ታስታውሰኛለች። ተረቱ እንዲህ ነው።…”አባትና ልጅ በቅሏቸውን እየነዱ ይሄዳሉ። ታዲያ በመንገድ ላይ የሚያገኛቸው ሰው፤ “እነዚህ ምን ዓይነት ሰዎች ናቸው በቅሏቸውን ባዶዋን እየነዱ እነርሱ በእግራቸው የሚሄዱት” ይሏቸዋል። አባትየውም ልጁን “ልጄ መቼም የሰው ነገር አስቸጋሪ ነውና በል አንተ በቅሎዋ ላይ ውጣ” ብለው መንገዳቸውን ይቀጥላለ። ይህን የተመለከቱ ሰዎችም “አይ ጊዜ! አይ ዘመን!…ምን ዓይነት ወቅት ላይ አደረስከን አምላኬ!፤ ልጁ ሽማግሌ አባቱን በእግራቸው እያስኬደ እርሱ በቅሎዋ ላይ ተቀምጧል” ይላሉ። ልጁም “አባዬ ሰዎቹ ልክ ናቸው አሁን ደግሞ ና አንተ በቅሎዋ ላይ ውጣ” ይላቸዋል። አባትም በቅሎዋ ላይ ይቀመጡና ጉዟቸውን ይቀጥላሉ። ትንሽ እንደተጓዙ ሰዎች ያገኟቸዋል። ሰዎቹም “ምናለበት አባትየው በእግሩ ቢሄድ?!” ሲሉ ይሰማሉ።

“አሁን አባትና ልጅም ነገሩ ግራ ገብቷቸው ቁጭ ብለው መመካከር ያዙ። “አሁን ያለን አማራጭ ሁለታችንም በቅሎዋ ላይ ወጥተን መሄድ ነው” ይባባላሉ። እናም በቅሎዋ ላይ ተቀምጠው ሲሄዱ ዕለቱ የገበያ ቀን በመሆኑ ሰካራሞች ያገኟቸዋል። “እንዴ?! አየሃቸው እነዚህ ሰዎች የእግዚሐብሔር ፍጡር የሆነችውን እንስሳ ለሁለት ተቀምጠውባት ሊገሏት ነው እኮ!” በማለት አባትና ልጅን በዱላ ሊወቋቸው አሯሯጧቸው። በቅሎዋም ደንግጣ በረገገች። በስተመጨረሻም በቅሏቸው ጠፍታ ሲፈልጓት ቆይተው እኩለ ለሊት ላይ አግኝተዋት ወደ ቤታቸው ገቡ” ይባላል።

ከዚህ ተረት የምንማረው ትልቁ ቁም ነገር፤ በሌሎች ሳይሆን በራስ ሃሳብ መመራትን ነው። አንድ ቡድን ወይም ድርጅትም በሌሎችን ሃሳብ የሚዘወር ከሆነ በስተመጨረሻ የሚገጥመው በተረቱ ላይ ያየናቸው አባትና ልጅ እጣ ፈንታ ነው። ለህዝቡ ይዞት የተነሳውን አጀንዳም ሊፈፅም የሚችል አይመስለኝም። እናም ያቺ “ኦህዴድ” ራስን ከመሆን አንፃር በሁለት እግሯ ቆማ ነበር ለማለት የሚያስደፍር አይመስለኝም።

የሰው ልጅ እንደ መልኩ ሁሉ ሃሳቡም ዥንጉርጉር ነው። በአንድ ጉዳይ ላይ አንድ ዓይነት አቋም ሊይዝ አይችልም። እናም የያኔዋ “ኦህዴድ” ያበረከተቻቸው በጎ ነገሮች ቢኖሩም ቅሉ፤ ራሷን ሆና የህዝቧን ጥቅሞች በትክክል ባለማስከበሯ ዋጋ የከፈለች ይመስለኛል። ይህም የኦሮሞን ህዝብ ነፃነት የተሟላ እንዳይሆን ያደረገው ከመሆኑም በላይ፤ ኢ-ህገ መንግስታዊነትን የተላበሱ ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች በጠራራ ፀሐይ እንዲፈፀሙበት በር ከፍቷል። በእኔ እምነት፤ ከዛሬ አራት ዓመት የነበረችው “ኦህዴድ” በሶስት ተከፍላ ትታየኛለች። አንደኛው፤ እስከ 1994 ዓ.ም ድረስ የነበራት እንቅስቃሴ፣ ሁለተኛው፤ እስከ አቶ መለስ ዜናዊ ህልፈተ ህይወት ድረስ ያለው ሲሆን፤ ሶስተኛው ደግሞ፤ በአቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ ጠቅላይ ሚኒስትርነት ዘመን እስከ 2008 ዓ.ም ድረስ ያለው ጉዟዋ ነው።

“ኦህዴድ” በእነዚህ ሶስት ጉዞዋ፤ እንደ በተረቱ ላይ እንደተመለከትናቸው አባትና ልጅ በሌሎች እየተዘወረች በቅሎዋ ላይ ስትወጣና ስትወርድ ነው ጊዜዋን የፈጀችው። ድርጅቷ የምታስተዳድረው ክልል ለፌዴራል መንግስት ስልጣኑን ቆርሶ መስጠቱን ዘንግታ፤ ፌዴራል መንግስቱ አዲስ አበባ ላይ ሲያስነጥስ፤ ማሃረብ ይዛ ትቀርብ ነበር ብል ማጋነን አይሆንብኝም። ይህ የራሷንና የህዝቧን መሰረታዊ ጥቅሞች ያላስከበረ አካሄድ የኋላ ኋላ የኦሮሚያን ወጣት ወደ ነፃነት ትግል እንዲያመራ አድርጎታል።

ለሶስትና ለአራት ዓመታት በዋነኛነት በኦሮሚያ ውስጥ የተካሄደው ትግል፤ “ቲም ለማ” የሚሰኙትን ዶክተር አብይ አህመድን፣ ኦቦ ለማ መገርሳንና ሌሎች የለውጥ ሃይሎች ወልዶ ነጥረው እንዲወጡ አደረጋቸው። የዚህ ፅሑፍ አንባቢ ይህን ወቅት እንደ አራተኛ “የኦህዴድ” ጉዞ አድርጎ ሊቆጠረው ይችላል። “ቲም ለማ” የያኔዋን “ኦህዴድ” ከነፃነትና ከመብት አኳያ በአዲስ መልክ አደራጅቷት የተንቀሳቀሰው በዚህ ወቅት ነው ማለት ይቻላል። እናም በሌሎች ሃሳብ እየተመራ፣ በቅሎዋ ላይ መውጣትና መውረድን እርግፍ አድርጎ በመተው፣ የለየለት ትግል ውስጥ ገባ። ትግሉ በህዝቡ ይደገፍ ስለነበርም በመስዕዋትነት ድልን ተቀዳጅቷል።

በአዲስ አስተሳሰብና አመለካከት እንዲሁም ህዝባዊ ጎዳና በራሱ መንገድ እየተመመ “ኦዴፓ”ን ትናንት “እንካችሁ” ብሎናል። የኦሮሞ ህዝብ ባህል የሆነውን አቃፊነትን በመያዝና ዴሞክራሲን ወደ ላቀ ምዕራፍ ለማሸጋገር፤ ደህና ሁኚ “አህዴድ” ያለ ይመስላል። ርግጥ እንዳልኩት አንድ ያልለየለት ነገር ይቀራል— የርዕዩተ-ዓለም (Ideology) ጉዳይ። ታዲያ ይህን እውነታ በቅርቡ ሀዋሳ ላይ ከሚካሄደው 11ኛው የኢህአዴግ ጉባኤ የምናውቅ ይመስለኛል። እስከዚያው ግን በድጋሚ “ኦዴፓ”ን እንኳን ደህና መጣሽ እላለሁ። ሰናይ ጊዜ።            

 

   

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy