‘ካልቻለ ይልቀቅ…?’
እምአዕላፍ ህሩይ
“የምርት ዘርን እንደ ሃሳብ፤ ተቀባይነትን ደግሞ እንደ ቡቃያ ብንወስደው፤ የእኛ ሀገር የሴራ ፖለቲከኞች ልክ በተረቱ ላይ እንደተመለከትነው ገበሬ ሁሉ፤ እነርሱም ለከርሞ የሚዘሩት ዘር እንዲሁም ሊያበቅሉ የሚችሉት ቡቃያ አላቸው ብሎ ለመናገር የሚያስደፍር አይመስለኝም። ኧረ እንዲያውም ራሳቸውም ቢሆኑ ‘ሃሳብም ሆነ ተቀባይነት የለንም!’ ብለው ሳይደመድሙ የቀሩ አይመስልም። ለዚህም ሳይሆን አይቀርም…”
አንድ ዕድሜ ጠገብ ተረት አለ።…በአንድ ሀገር ውስጥ የሚኖር ገበሬ ነበር። ይህ ገበሬ ያመረተው እህል ይበላሽበታል። በዚህም ምክንያት ቤተሰቡ አደጋ ላይ ይወድቃል። እጅግም ይጨነቃል። በተለይ ለሚቀጥለው ዓመት ምርት የሚዘራው ዘር እጁ ላይ ባለመኖሩ የጭንቀቱ መጠን እጥፍ ድርብ ሆነ። ታዲያ ሁሌም ሲቸግረው ወደ ላይ…ወደ ፈጣሪው ይማፀናል። ዛሬም ያደረገው እንዲያ ነው።…እናም ለፈጣሪው እግዚሐብሔር ደብዳቤ ይፅፍ ዘንድ ውስጡን አንዳች ስሜት አነሳሳው። እንዲህም ሲል በመፃፍ ብዕሩን ከወረቀት ጋር አገናኘው።…
“ውድ አምላኬ ሆይ! ክብርህ በሰማይና በምድር ይስፋ። ጌታዬ ሆይ! በዚህ ዓመት የተበላሸብኝን ሰብል አይተሃል። በጎርፍና በተምች ምክንያት ባዶዬን ቀርቻለሁ። ለዚህ ዓመት የተራረፈውን ለቅሜም ቢሆን ክረምቱን እወጣዋለሁ። ሆኖም እንዳየኸው ለሚቀጥለው ዓመት ሰብል የምዘራው ዘር የለኝም። ይህ ደግሞ ቤተሰቤን ረሃብ ላይ የሚጥል ነው። ስለዚህ እባክህ ዘር የምገዛበት ገንዘብ እንድትልክልኝ በምትወዳት እናትህ በድንግል ማርያም ስም እማፀንሃለው።” በማለት ፈርሞ በደብዳቤው ላይ የተቀባዩን አድራሻ ‘ለፈጣሪያችን እግዚሐብሔር’፤ የላኪውን ደግሞ የራሱን ስም ያደርግና በአቅራቢያው ወዳለው የወረዳ ፖስታ ቤት ፖስታውን ያስገባል። የተቀባዩን አድራሻ ያዩት የወረዳው ፖስታ ቤት ሰራተኞችም ይገረሙና በቀጥታ ወደ ሀገሪቱ ዋና ፖስታ ቤት ደብዳቤውን ይልኩታል።
የዋናው ፖስታ ቤት ሰራተኞችም እጅግ በጣም ተገረሙ። የሰው ፖስታ መክፈት ስለማይቻልም፣ ፖስታውን ለኃላፊያቸው አስረከቡ። ፖስታው ተቀድዶ ሲነበብ፤ ገበሬው የፃፈው አስገራሚ መልዕክት ብቅ አለ። ኃላፊውና ሰራተኞቹ ገበሬው በፈጣሪው ላይ ያለው እምነት እጅግ አስደመማቸው። ይህ እምነቱ እንዳይሸረሽርም በማሰብም ‘አንድ ነገር ማድረግ አለብን’ ብለው መመካከር ያዙ። ከሰራተኞቹ አንዱ ‘ለዚህ ሰው የሚያስፈልገው የዘር መግዣ ገንዘብ ነው፤ እናም ያለንን አዋጥተን በእግዚሐብሔር ስም እንላክለት’ የሚል ሃሳብ አቀረበ። ሃሳቡ ተቀባይነት በማግኘቱም ቁጥራቸው የሚበዛው የዋናው ፖስታ ቤት ሰራተኞች ያላቸውን አምስትም…አስርም ብር አዋጥተው ለዘር መግዣ ከሚያስፈልገው በላይ ገንዘብ እንዲሁም “ልጄ ሆይ! እኔ ሁሌም ካንተ ጋር ነኝ። ለአሁኑ የዘር መግዣ የሚሆንህን ገንዘብ ልኬልሃለሁ። በሌላ ጊዜም ሲቸግርህ ፃፍልኝ። ፈጣሪህ እግዚሐብሔር” የሚል አጭር ደብዳቤ ፅፈው በአድራሻው ይልኩለታል።
ገበሬውም ደብዳቤው ደረሰው። ፈጣሪውን በእጅጉ አመሰገነ። ‘ከቶ ላንተ ምን ይሳንሃል?!’ ሲልም ወደ ላይ አንጋግጥጦ ምስጋና አቀረበ። ክብርም ሰጠ። ሆኖም ገንዘቡን ተቀብሎ ዝም ማለት ስላልቻለና ምስጋናውንም ጭምር ለመግለፅ በማሰቡ እንዲህ ሲል የመልስ ደብዳቤ ለፈጣሪው ፃፈ።…”ውድ ፈጣሪያችንና መድሃኒታችን እየሱስ ክርስቶስ ሆይ!…ላንተ የሚሳንህ ነገር የለም። ሰማይ መቀመጫህ፣ ምድርም መረገጫህ ናት። አምላኬ ሆይ! እጅግ አድርጌ አመሰግንሃለሁ። የላክልኝ ብዙ ገንዘብ ደርሶኛል። ዘሩንም ገዝቻለሁ። የተረፈኝንም ለልጆቼ ጥብቆ አለበስኩበት። ለወደፊቱ ገንዘብ ስትልክልኝ ግን፤ የፖስታ ቤት ሰራተኞች ፖስታ እየቀደዱ ገንዘብ ስለሚሰርቁ በካህናት አማካኝነት እንድትሰድልኝ ይሁን። ያንተው ፍጡር።” ብሎ ስሙን አስፍሮ በመፈረም ደብዳቤውን ላከ ይባላል።…
እንግዲህ ከዚህ ተረት መሰል ቁም ነገር ትረካ የምንማረው ነገር ቢኖር፤ “ወርቅ ላበደረ፤ ጠጠር” እንደሚባለው፤ ፖስታ ቤት ሰራተኞቹ በሰሩት ቅንነት የተሞላው በጎ ምግባር ያተረፉት በገበሬው በሌብነት መጠርጠራቸው ነው። ይህም አንዳንዴ ቅን በማያስቡና ተንኮልን በተካኑ ሰዎች ዘንድ ሊፈጠር የሚችል ክስተት ነው። ታዲያ ይህ “ወርቅ ላበደረ ጠጠር” ሁኔታ በእኛ ሀገር ፖለቲካ ውስጥም ከሰሞኑ እየታየ ነው። ለዚህች ሀገር ሰላምና ልማት በአምስት ወራት ውስጥ ወርቅ ላበደሩን መሪ ምላሹ ‘ካልቻለ ይልቀቅ!’ የሚል የጠጠር ሃሳብ መሆኑ እጅግ የሚያዛዝንና የሚያስገርም ነው። “ላም ባልዋለበት፣ ኩበት ለቀማ” እንዲሉት ዓይነትም ነው።
አዎ! ከመሰንበቻው አንዳንድ ማህበራዊ ሚዲያዎች ላይ የሚሰፍሩና ኢ-ህገ መንግስታዊ የሽግግር መንግስትን የሚመኙ አካላት ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድን ‘ካልቻለ ይልቀቅ!’ የሚል የቁራ ጩኸት ሲያሰሙ እየተመለክትናቸው ነው። ያሳፍራል። የዚህ ሃሳብ ባለቤቶች በምርጫ ተወዳድረው ማሸነፍ እንደማይችሉ ከወዲሁ የተገነዘቡ ናቸው ማለት ይቻላል። ምክንያቱም ሆን ብለው ግር…ግር በመፍጠርና ህዝብን የሚያስቆጣ ተግባር በመፈፀም ‘ጠቅላይ ሚኒስትሩ ስላልቻሉ የጋራ የሽግግር መንግስት እንመስርት’ በማለት የስልጣን እርካብን ለመቆናጠጥ ያለሙ በመሆናቸው ነው።
ታዲያ የዚህ ፅሑፍ አቅራቢ፤ ‘እውን ዶክተር አብይ አልቻሉንም?’ የሚል ጥያቄን ማንሳት ግድ ይለኛል። በርግጥም ጥያቄውን አነሳለሁ፤ ምላሹንም በማውቀው መጠን እሰጣለሁ። “ለምን?” ከተባለ፤ የራሳቸውን የሴራ ንድፈ ሃሳብ (Conspiracy Theory) ቀምረውና በሺህዎች የሚቆጠሩ የውሸት የፌስ ቡክ አካውንቶችን ከፍተው በየማህበራዊ ሚዲያው የሚያሰራጩ አንዳንድ ‘አፍቃሬ የሽግግር መንግስት’ ልሂቃኖች ስለ አለመቻል የሚያራምዱት አስተሳሰብ ትክክል ያልሆነ ብቻ ሳይሆን፤ ወርቅን በጠጠር የመለወጥ ያህል የውሸት አመክንዩ ያያዘም ጭምር ስለሆነ ነው።
በእኔ እምነት፤ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ የማይችሉት አለመቻልን ብቻ መሆኑን በተግባር ያሳዩን መሪ ናቸው። እንዲያውም በሀገራችን ታሪክ ተቃዋሚውም፣ ደጋፊውም፣ መሃል ሰፋሪውም በአንድነት የዘመረላቸውና እየዘመረላቸው ያሉ ብቸኛ መሪ ዶክተር አብይ ብቻ ናቸው። ታዲያ ይህ ተቀባይነትና የይሁንታ ዝማሬ እንዲያው ዝም ብሎ የተገኘ አይደለም። ማንም ቢያልመውም እግሩ እስኪላጥ ድረስ ቢዞርና ያሻውን ሚሊዩን ብሮች ቢመድም ከቶም ሊያገኘው አይችልም። ዶክተሩ በህዝብ የተጎናፀፉት ተፈላጊነትና ፍቅር የመጣው ሌት ተቀን ሴራን እየጠነሰሱ ስላደሩና ሚሉዮን በሮችን ስለረጩ አይደለም— በብቃታቸው ባከናወኑት ስራና ለህዝብ ካላቸው ጠንካራ ፍቅር አሊያም ህዝባዊ ወገንተኝነት የተገኘ እንጂ።
ዶክተር አብይ አህመድ ሀገራችንን በፍቅር፣ በይቅርታ፣ በመደመር፣ በአንድነትና በሰላም ለመምራት ቀደም ባሉት ጊዜያች በአሸባሪነት ጭምር የተፈረጁ ድርጅቶችን ጭምር በሆደ ሰፊነትና በትዕግስት ወደ ሀገራቸው እንዲገቡ ተደጋጋሚ ጥሪ ያቀረቡት፣ ከነበርንበት የጥላቻ ፖለቲካ ወጥተን ስለ ኢትዮጵያ በጋራ እንድንዘምር ያደረጉትና ከጎረቤቶቻችን ጋር የጥርጣሬን መንፈስ በማስወገድ ወደ ልማት ማማ ላይ ይዘውን የወጡት የመቻላቸውን ልኬታ ማሳያ ነው። የሁሉንም የፖለቲካ ፓርቲዎች ፍላጎት በአንድነት ለመምራት ያላቸውን ብቃት የሚያሳይ መሆኑም እንዲሁ። ዶክተር አብይ በፖለቲካው ብቻ ሳይሆን በማህበራዊ መስክም በክርስትናም ይሁን በእስልምና ሃይማኖቶች ውስጥ የነበረውን መከፋፋል በማስቀረት እዚህ ሀገር ውስጥ ፍቅርን ማንገስ የቻሉ መሪ ናቸው። እነዚህ ሁሉ ክንዋኔዎች ሊፈፀሙ የሚችሉት ብቃት ባለው የአመራር ክህሎት እንጂ በሴራ ፖለቲካ አለመሆኑን ማንኛውም የዚህ ፅሑፍ አንባቢ እንደሚገነዘበው አምናለሁ።
እናም ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ፤ በ“እነ ማር አይጥሜ” ‘ካልቻለ ይውረድ!’ የሚባሉ መሪ አይደሉም—ዕድሜና ጤና የምንለምንላቸው እንጂ። ዶክተር አብይ ላለፉት ሶስትና አራት ዓመታት እዚህ ሀገር ውስጥ የተፈጠረውን ትርምስ በአምስት ወራት ውስጥ ብቻ አንፃራዊ ሰላም መፍጠር ችለዋል። በቀጣናው ሀገራት ውስጥ የጋራ ተጠቃሚነትን በማስፈን የትብበርና ተያይዞ የማደግ ፍላጎትን ማምጣት የቻሉ በሳል ኢትዮጰያዊ ናቸው። ከኤርትራ ጋር የነበረንን የ20 ዓመታት “ሞት አልባ ጦርነት” ሁኔታን ቀልብሰው ወደ ልማትና መተጋገዝ የቀየሩ የሰላም አርበኛ ናቸው።
ዛሬ ከኤርትራ በዛላምበሳ-አዲግራት በኩል እንደ ባቡር ተቀጣጥሎ የሚፈሰው ያ ሁሉ የመኪና ወጀብ፣ የድንበር አካባቢ ዜጎች የንግድ ልውውጥ፣ የህዝቦች የተጠናከረ አንድነት የተገኘው፤ በተረቱ ላይ እንደተመለከትነውና የፖስታ ቤት ሰራተኞቹን በጎ ምግባርንና ወርቅ የተላበሰ በሳል አስተሳሰብን በጠጠር ለመቀየር እንደሞከረው ገበሬ፤ ስራን ሳይሆን ሴራን በተካኑት አንዳንድ ፖለቲከኞች አማካኝነት አይደለም—ብቃት ባላቸውና የኢትዮጵያ መድን በሆኑት በዶክተር አብይ አህመድ አማካኝነት እንጂ።
ኢትዮጵያ ከራሷ አልፋ ኤርትራና ጂቡቲ በራስ ዱሜራ ኮረብታዎችና ሃይቆች ሳቢያ የተፈጠረውን ችግራቸውን ፊት ለፊት ተገናኝተው እንዲፈቱ ያደረገችው በዶክተር አብይ አህመድ ብቃትን የተላበሰ አቅም አማካኝነት ነው። በኢትዮጵያ፣ በኤርትራና ሶማሊያ መካከል የሶስትዮሽ ግንኙነት ተፈጥሮ ሀገራቱ ያላቸውን የተፈጥሮ ፀጋ በጋራ ለመጠቀም የተስማሙት በእኚሁ በሳል መሪያችን አማካኝነት መሆኑን “እነ ወርቅ ለምኔ” ይዘነጉታል ብዬ አላስብም። ምክንያቱም የዶክተር አብይ የአምስት ወራት ስራ ማንም ቢሆን በአምስት ዓመት እንኳን ሊፈፅመው እንደማይችል “እነ አያ እንቶኔ” ጠንቅቀው ስለሚያውቁት ነው።
ሀገራችን በውጭ ምንዛሬ ድርቅ ስትመታና ከውጭ የሚገቡ መድሃኒት መግዣ ጭምር አጥተን ዜጎቻችን በሞት አፋፍ በነበሩበት ወቅት፤ ዶክተር አብይ ያካበቱትን እምቅ አቅም ተጠቅመው፣ ለምነው ጭምር ያበሉንና ከሞት የታደጉን መሪ ናቸው። በታሪካችን በብሔራዊ ባንክ ተቀምጦ የማያውቀውን ቢሊዮን ዶላሮችን እንድናስቀምጥ እንዲሁም መካከለኛው ምስራቅ፣ ምዕራቡም ይሁን ምስራቁ ዓለም በእኩል እይታ ሀገራችንን እንዲቀበሏት ያስቻሉም የአመራር ክህሎትን የተላበሱ የሀገራችን ብርቅዬ ሰው ናቸው። ይህ የጠቅላይ ሚኒስትሩ በጎረቤቶቻችንም ይሁን በተቀረው ዓለም ያላቸው ተቀባይነት የተገኘው፤ ባካበቱት በብስለትና አስተዋይነት የተሞላበት የዲፕሎማሲ ክህሎት መሆኑን ለሴራ ፖለቲከኞች መንገር ከእኔ የሚጠበቅ አይመስለኝም። ያም ሆኖ፤ ‘ለምንትስ ማር አይጥማት’ እንደሚባለው፤ የሴራ ፖለቲከኞች ይህን ዘንግተው አሁን ላይ የሚያራምዱትን ‘ካልቻለ ይልቀቅ!’ የሚለውን አፈ ታሪክ ወደ ኋላ መለስ ብለው ቢያስቡት በአስተሳሰባቸው መልሰው ማፈራቸው የሚቀር አይመስለኝም።
የምርት ዘርን እንደ ሃሳብ፤ ተቀባይነትን ደግሞ እንደ ቡቃያ ብንወስደው፤ የእኛ ሀገር የሴራ ፖለቲከኞች ልክ በተረቱ ላይ እንደተመለከትነው ገበሬ ሁሉ፤ እነርሱም ለከርሞ የሚዘሩት ዘር እንዲሁም ሊያበቅሉ የሚችሉት ቡቃያ አላቸው ብሎ ለመናገር የሚያስደፍር አይመስለኝም። ኧረ እንዲያውም ራሳቸውም ቢሆኑ ‘ሃሳብም ሆነ ተቀባይነት የለንም!’ ብለው ሳይደመድሙ የቀሩ አይመስልም። ለዚህም ሳይሆን አይቀርም— በስመ ሽግግር መንግስት የስልጣን ኮርቻን በቅርብ ርቀት በማለም በየማሀበራዊ ሚዲያው ‘ካልቻለ ይልቀቅ!’ የሚል ዲስኩርን በስማ በለው አማካኝነት የሚያሰሙን። በአስረጅነትም በቅርቡ የአፍሪካ መዲና እና የዓለም አቀፍ ተቋማት መናኸሪያ በሆነችው አዲስ አበባ የብሔር ግጭት ለማስነሳት በማሰብ፤ ‘ኦሮሞ ከአዲስ አበባ ይውጣ’ የሚል አይን አውጣና አስቂኝ መፈክርን መጥቀስ የሚቻል ይመስለኛል። እንዲሁም በዕለቱ ‘ዶክተር አብይ ወይ ፍረድ፣ ወይ ውረድ!’ የሚለው አስቂኝ ዲስኩራቸው ያው የፈረደበት የሽግግር መንግስት ተረታቸው መገለጫ ነው ማለት ይቻላል። ያም ሆኖ፤ የህዝብ ወገንተኛ የሆኑትና የስራቸው ሁሉ አልፋና አሜጋ ማጠንጠኛ ህዝብ የሆነው ዶክተር አብይ፤ ምን ዓይነት አኩሪ ተግባር እየፈፀሙ እንደሆነ፤ ሁሌም ሚዛናዊ እይታ የማይለየው የሀገራችን ህዝብ ጠንቅቆ የሚያውቀው እውነታ ነው።
ዶክተር አብይ የአዲሱ ትውልድ መገለጫና መሪ ናቸው። ኢትዮጰያንና ምስራቅ አፍሪካን ብሎም አፍሪካን የመገንባት ራዕይን ሰንቀው የተነሱ ብቃት ያላቸው መሪ ናቸው። ሰሞኑን ለንባብ የበቃው አንድ የናይጄሪያ ጋዜጣ፤ በሀገሩ ውስጥ ያለውን ውጥንቅጥ በማተት እንዲሁም ዶክተር አብይ ያላቸውን ብቃት፣ ክህሎትና ችሎታ በመግለፅ ናይጄሪያ ከጠቅላይ ሚኒስትራችን ትምህርት ልትወስድ እንደምትችል በሰፊው የዘገበውም ከዚህ በመነሳት ለመሆኑ በርግጠኝነት መናገር ይቻላል።
ታዲያ እዚህ ላይ ጥቂት ጥያቄዎችም ማንሳት ይቻላል። እርሱም ‘ካልቻለ ይልቀቅ!’ የሚለው የሴራ ፖለቲከኞች “ፍየል ወዲህ ቅዝምዝም ወዲያ” ተረክ አራማጆች፤ የተደመሩት የሽግግር መንግስት ለመመስረት ነው እንዴ?’፣ የሴራ ፖለቲከኞች ለስልጣን ካላቸው ጉጉት “ጅራፍ ራሱ ገርፎ ራሱ ይጮሃል” እንደሚባለው፤ ራሳቸው አንድ ነገር ፈጥረው ሲያበቁ፤ መልሰው ‘መምራት ስላልቻለ ይውረድ!’ የሚል ከነባራዊው እውነታ ጋር አብሮ የማይሄድ ልቦለድ እየቀመሩ እንደምን የጋራ ሀገርን ልንመራ እንችላለን?፣ እንደምንስ ህዝብን አክብሮ መንቀሳቀስ ይቻላል?…ኢትዮጵያ የሁላችንም በመሆኗ፣ ፖለቲከኞች ለስልጣን ያላቸውን የተሳሳተ ግንዛቤ ወደ ጎን በማለት ለዘላቂው ሀገራዊ አንድነትና ለህዝባቸው ተጠቃሚነት በቅንነት መስራት ይኖርባቸዋል። እናም አዲሱ ትውልድ ዘመን ባለፈበት አሮጌ የሴራ አስተሳሰብ ሊመራ ስለማይችል፤ ዘመኑን የሚዋጅና 21ኛውን ክፍለ ዘመን የሚመጥን ፖለቲካን በማቀንቀን ቀና መንገድን ሊከተሉ ይገባል እላለሁ።