Artcles

ነገረ-ፊንፊኔ ወ ‘ኢሳት’

By Admin

September 28, 2018

ነገረ-ፊንፊኔ ወ ‘ኢሳት’

                                                          ዋሪ አባፊጣ

ሰሞኑን አቧራው ጨሷል። ድንገት አምስት የኦሮሞ አመራሮች በቴሌቪዥን መስኮት ብቅ ብለው አቋማቸውን አሳወቁ—በኦቦ በቀለ ገርባ አንባቢነት፤ በብዙ ጉዳዩች ላይ። የጨሰው አቧራም መብነን ያዘ። በተለይ አዲስ አበባንና ኢሳትን በተመለከተ የሰጡት አስተያየቶች፤ የአቧውን ብናኝ ወደ እኛ እንዲነፍስም አደረገው። ማህበራዊ ሚዲያው እንደ ዱላ ቅብብል  ሩጫ ከወዲያ ወዲህ ሲቀባበለው ከረመ። አጎነው፤ አጦዘው። የጡዘቱ የውሃ ልክም በእያንዳንዱ የማህበራዊ ሚዲያ ገበያተኛ እሳቤ የታቃኘ ነበር።

‘የእውነት መለኪያው ምንድነው?’ እስከሚያስብል ድረስ፤ ሁሉም በየፊናው ተብሰከሰከ። በድንጋጤም ታመሰ። “እኛም ምን ያስደነግጣል?” አልን። በተለይ ከ‘አዲስ አበባ የኦሮሞ ናት፣ አሁን ባለው ተጨባጭ ሁኔታ ግን የብሔር ብሔረሰቦች መኖሪያ ናት’ እስከ ‘አዲስ አበባ የሁሉም ኢትዮጵያዊያን ከተማ ናት’ እንዲሁም ‘ኢሳት የኦሮሞና የትግራይ ህዝብ ጠላት ነው’ እስከ ‘ኢሳት የኢትዮጵያ ህዝብ ዓይንና ጆሮ ነው’ የሚሉ ትርክቶች ማድመጣችን የመልስ ምት እንዲከተል አደረገ—በአንድ ግለሰብ አማካኝነት። የመልስ ምቱም እንዲህ የሚል ነበር።…“በፊንፊኔ ጉዳይ ሁሉም የኦሮሞ ልሂቃን አቋም አንድ ነው፤ ፊንፊኔ የኦሮሞ ስለመሆኗ ምንም ዓይነት ልዩነት የላቸውም” አሉ። እኚህ ሰው አክቲቪስትና የኦሮሞ ሚዲያ ኔት ወርክ ስራ አስኪያጅ አቶ ጃዋር መሐመድ ናቸው።

በየማህበራዊ ሚዲያው ይላተም የነበረው ይህኛውና ያኛው በድን ጎራ ለይቶ የልቡን ተናገረ። በተለይ በድንጋጤ የታጀበውና በአንደነት መንፈስ የሚሰራው አካል አዲስ አበባ ላይ ይኖረኛል ብሎ ያሰበውን ነገር የተቀማ ያህል በአፈ-ቀላጤዎቹ አማካኝነት ብዙ አለ ወይም አስባለ። የኦሮሞ የፖለቲካ ፓርቲዎችና አክቲቪስቶች ግን አቋማቸውን አንዴ አሳውቀዋልና ከዚያ በኋላ ያሉት ነገር የለም። አሊያም እኔ አልሰማሁም።

ያም ሆኖ፤ አዲስ አበባ (ፊንፊኔ) የኦሮሞ ናት ስለተባለ አሊያም ኢሳት የኦሮሞና የትግራይ ህዝቦች ጠላት ነው በመባሉ እውነታውን ለማስረዳት መሞከር እንጂ፤ ድንጋጤ ውስጥ ገብቶ “አራምባና ቆቦ” እንደሚባለው ዓይነት ተግባር መፈፀሙ ተገቢ ሆኖ አላገኘሁትም። እናም በዛሬው ፅሑፌ፤ በአዲስ አበባውም ይሁን በኢሳት ጉዳይ ላይ የድንጋጤውን ምክንያቶች በመጠኑ እንዲህ ለመመልከት እሞክራለሁ።

አምስቱ የኦሮሞ የፖለቲካ ፓርቲዎችም ይሁኑ አክቲቪስት ጃዋር “አዲስ አበባ የኦሮሞ ናት” ማለታቸው ዝም ብሎ ከመሬት የተነሳ ሃሳብ አይመስለኝም። ቀደም ሲል ‘የሽግግር መንግስት…ምንትሴ ማቋቋም ያስፈልጋል’ የሚል ስሜት ያለውን ሰላማዊ ሰልፍ ያደረጉ አካላት “ኦሮሞ ከአዲስ አበባ ይውጣ” ላሉት ሚዛናዊነት የጎደለው መፈክር ምላሽ ነው።

ትናንት “ኦሮሞ ከአዲስ አበባ ይውጣ” ሲል የነበረ አካል፤ ዛሬ ሌሎች “ፊንፊኔ የኦሮሞ ናት” በማለታቸው ሊደግጥ አይገባም። እንዲያውም መደንገጥ የነበረበት፤ ማንም ይሁን ማን ከሚኖርበት ከተማው “ውጣ!” በተባለበት ወቅት ነበር። መደንገጥ ያለበት፤ የጠቅላይነትና የአግላይነት አካሄድ ነው። ልንደነግጥ የሚገባን፤ ከአዲስ አበባም ይሁን ከማንኛውም የሀገሪቱ ክፍል ዜጎች እንዲወጡ በሰላማዊ ሰልፍ ጭምር ሲጠየቁ ነው። እናም በእኔ እምነት፤ አይደለም ኦሮሞ የትኛውም ኢትዮጵያዊ ከየትኛውም የሀገሩ አካባቢ እኩልነቱ ተረጋግጦና ተከብሮ መኖር አለበት እንጂ ፈፅሞ “ውጣ!” የሚል ሃሳብን ሊያደምጥ አይገባም። ኧረ እንዲያውም መታሰቡ ብቻ ነውረኛ መሆኑን መግለፅ የነበረባቸው ይመስለኛል።

ከዚህ አንፃር ለእኔ የኦሮሞ ልሂቃን በአያሌው ትክክል ናቸው። ያነሱት ነገር የባለቤነት ጉዳይ ብቻ አይደለም። ፊንፊኔ የብሔር ብሔረሰቦች መኖሪያ መሆኗን ከመግለፅ ባሻገር፤ የትኛውም ህዝብ መብቶቹ ተጠብቆለት መኖር እንደሚችልም አስታውቀዋል። ይህ “ውጣ” ከሚለው የጠቅላይነትና የአግላይነት አስተሳሰብ በእጅጉ የተሻለ ብቻ ሳይሆን፤ የሌሎችንም መብቶች ያከበረ ተቀባይነት ያለው እሳቤ ነው። አሃዳዊነት ሁሌም የመጠቅለልና የኃይል አገዛዝን መሰረት ያደረገ በመሆኑ ለእንዲህ ዓይነቱ ዴሞክራሲያዊ አስተሳሰብ ቦታ አይሰጥም። አሃዳዊነት ከእርሱ በተቃራኒ የሚከሰቱ ነገሮችን መስማት አይፈልግም። ድንገት የሰሙት ነገር የሚያስደነግጣቸው ምክንያት ለዚሁ ይመስለኛል። ነገረ- ፊንፊኔን ከዚህ አኳያ መመልከት ተገቢ ነው።

ነገረ-‘ኢሳት’ም ከዚህ የተለየ አይደለም። በዚህ ፅሑፍ ላይ የኢትዮጵያ ሳተላይት ቴሌቪዥን (ኢሳት) ባለቤትነትን ማንሳት አልሻም። ምክንያቱም ነገሩ “ምግባርህን ንገረኝና ማንነትህን እነግርሃለሁ’ እንዲሉ ጃፓኖች፤ ከዘገባው በመነሳት ዝማሜው ወዴት እንደሆነ ለመገመት ስለማይከብድ ነው። ያም ሆኖ ግን አንድ እውነታን ማንሳት እወዳለሁ። እርሱም ‘የኢትዮጵያ ዓይንና ጆሮ የተባለው ኢሳት ለሁሉም እኩል የመስራት፤ ሁሉንም ኢትዮጵያዊ ሃሳቦች አክብሮ የማስተናገድ ባህል አለው’ ብሎ ለማመን ማስቸገሩ ነው።

ሀገራችን ውስጥ የተለያዩ ሃሰቦች አሉ። ልሙጡን ባንዴራ ይዞ ከወጣው አሃዳዊ እሳቤ እስከ ህገ መንግስታዊው የፌዴራሉ ባንዴራን የሚያውለበልቡ ወገኖች መኖራቸውን ተመልክተናል። ታዲያ ‘ኢሳት’ እንደ ሚዲያ የየትኛውንም ወገን በእኩልነት ሳያዳላ ሽፋን መስጠት ይኖርበታል። አንድን ወገን ብቻ በመደገፍ ሌላውን ማብጠልጠል ስራዬ ብሎ መያዝ የለበትም። አንዱን ጥሎ ሌላውን አንጠልጥሎ መሮጥ ያለበት አይመስለኝም።

‘ኢሳት’ ከዚህ ቀደም በሰሜን አሜሪካ የሚኖሩ የትግራይ ተወላጆች ከሚዲያ ስነ ምግባር ያፈነገጠና የትግራይ ህዝብን የሚያጥላላ ተግባርን እየፈፀመ ነው በማለት ክስ እንደቀረበበት አስታውሳለሁ። አሁን ደግሞ ወደ አንድ የፖለቲካ እሳቤ ያጋደለ ሆኖ፤ ሌላውን ወገን በአክራሪነት እየፈረጀና ለእነዚህን ወገኖች ሃሳብ የአፀፋ ምላሽ ሲሰጥ እየተመለከትነው ነው—እንደ አንድ የፖለቲካ ድርጅት። ኢሳት ግን መገናኛ ብዙሃን እንጂ፣ የፖለቲካ ደርጅት አይደለም። በእኔ እምነት፤ እንዲህ ዓይነቱ አሰራር የጋዜጠኝነት ሙያን ስነ ምግባር (Journalistic Ethics) የተከተለ አይመስለኝም።

ሌላውን ትተን ሰሞኑን አምስቱ የኦሮሞ ድርጅቶች ‘ኢሳት የኦሮሞ ጠላት ነው’ ካሉ፤ እንደ ሚዲያ ‘ለምን እንዲህ ልትሉን ቻላችሁ?፤ የትኛውን የመገናኛ ብዙሃን ስነ ምግባር ስለጣስን ነው እንዲህ እንዲህ ልንፈረጅ የቻልነው?’ ብሎ እንኳን ለመጠየቅ አልደፈረም። ሚዲያ ግን ማድረግ ያለበት ይህንኑ ነበር። ‘ኢሳት’ ግን፤ ‘የተባልነው በዚህ ምክንያት ነው’ በሚል በመላ ምት ላይ በተመረኮዘ ትንታኔ አምስቱን ድርጅቶች ማብጠልጠል ነው የመረጠው። በዚህም አምስቱን የኦሮሞ ድርጅቶች “እርስ በርሳቸው የማይግባቡ” በማለት ልዩነታቸውን እንደ ፖለቲካ ፓርቲ ማስፋት ነው የወደዱት። በእውነቱ ይህ የመገናኛ ብዙሃን ኃላፊነትና ተግባር ነው ብዬ አላስብም።   

‘አምስቱም ፓርቲዎች በእኛ ሚዲያ ላይ ተስተናግደዋል’ ማለትም በቂ አይመስለኝም። ርግጥ አምስቱም ፓርቲዎች ‘ኢሳት’ ከተመሰረ ጀምሮ የዘገባው ደንበኛው ሊሆኑ ይችላሉ። በዚያ ወቅት ይህ ሁኔታ ትክክል ሊሆን ይችላል። አሁን እየተባለ ያለው ግን፤ ‘ኢሳት’ ሁሉንም ሃሳቦች ካለማስተናገዱ ባሻገር፤ እንደ ጠላት ሌሎችን እየፈረጀ ስለመሆኑ ነው። በግልፅ ለመናገር፤ ‘ኢሳት’ እየተባለ ያለው፤ አሃዳዊውን ሃሳብና አቀንቃኞቹን እያሽሞነሞነ እንዲሁም ፌዴራሊዝምን የሚከተሉትን እያገለለ ብሎም በሌላ ዘውግ ፈርጆ እየኮነነ እየሰራ ነው። ሚዲያው ይህን ‘አላደረኩም’ ወይም ‘አድርጌያለሁ’ ብሎ የራሱን ሃሳብ ማቅረብ እንጂ የአንድ ወገን ልሳን ሆኖ መስራት አይመስለኝም።

እየደጋገመ ‘ሚዲያ አለኝ ብሎ ማንም የፈለገውን መናገር የለበትም’ የሚለው ‘ኢሳት’ )አቶ ጃዋርን ለማለት ይመስለኛል)፤ ከእርሱ በላይ ይህን ጉዳይ በዋነኛነት ሲፈፅም አተመለከትኩም። ርግጥ አቶ ጃዋር የሚመራው ሚዲያ የኤዲቶሪያል ቀመር እንዳሻው ሊመራው ይችላል—ግላዊ የባለቤትነት መብቱ ይፈቅድለታልና። ‘ኢሳት’ ግን ‘የኢትዮጵያ ህዝብ ዓይንና ጆሮ ነኝ’ ስላለ ተጠሪነቱ ለሁሉም ኢትዮጵያዊ ነው። ኦሮሞ ደግሞ የራሱ መለያ ያለው ኢትዮጵያዊ ነው። ለዚያውም እጅግ የሚበዛ የህዝብ ቁጥር ጭምር ያለው ነው፤ ኦሮሞ።

እናም ‘ኢሳት’ ይህን ህዝብ ሳያቅፍ በአግላይነት መጓዙ ለጣቢያውም ቢሆን የሚጠቅመው አይመስለኝም። የኦሮሞን ህዝብ በሚወክሉ የፖለቲካ ድርጅቶች እንደ ጠላት እስኪቆጠር ድረስ መስራቱም ተገቢ ነኝ ብዬ አላምንም። ያም ሆኖ ግን፤ አንድ ተግባር አንዱ ሲፈፅመው የተሳሳተ፤ እርሱ ሲከውነው ግን ትክክል የሚሆንበት አመለካከት ‘እኔ ብቻ ትክከል ነኝ’ የሚል የጠቅላይነት እሳቤ ስለሆነ ተቀባይነት ሊኖረው እንደማይችል መገንዘብ ተገቢ ይመስለኛል።