Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

‹‹ለስርዓት አልበኝነት መፍትሄ – ከኢህአዴግ ጉባኤ›› • ምሁራንና ፖለቲከኞቹ

0 1,087

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

ባለፉት ሁለት ሳምንታት የኢህአዴግ እህት ድርጅቶች በተለያዩ ርዕሰ ጉዳዮች ላይ ሲመክሩ መቆየታቸው ይታውሳል፡፡ሌሎቹ ጉባኤያቸውን ሲያጠናቅቁ ፣ደኢህዴን ዛሬ እንደሚያጠናቅቅ ይጠበቃል፡፡ ከአባል ድርጅቶቹ መካከል ከንቅናቄነትና ከድርጅትነት ወደ ፓርቲነት የተለወጡ፣አርማ የቀየሩም ይገኙበታል፡፡

ነባር አባላት በክብር የተሰናበቱበት አግባብና ሌሎች ትልልቅ ውሳኔዎችም የተከናወኑበት ጉባኤ ነው ያካሄዱት ፡፡

በነገው እለት ደግሞ በሐዋሳ ከተማ‹‹አገራዊ አንድነት፤ ለሁለንተናዊ ብልፅግና››በሚል መሪ ሐሳብ የግንባራቸውን ጉባኤ ማካሄድ ይጀምራሉ፡፤ ይህን 11ኛውን የኢሕአዴግ ድርጅታዊ ጉባኤን በተመለከተ አዲስ ዘመን ያነጋገራቸው ምሁራንና ፖለቲከኞች ከጉባኤው በርካታ ጉዳይ እንደሚጠበቅ ይናገራሉ፡፡

ከእነዚህም መካከል በዋናነት ቅድሚያ ሊሰጠው የሚገባው ጉዳይ ሰላም መሆኑን በመጥቀስም፣ ስርዓት አለበኝነት አደብ እንዲገዛ ጉባኤው በትኩረት መምከር እንዳለበት ነው ምሁራኑና ፖለቲከኞቹ ያስረዱት፡፡

የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ፕሮፌሰር ጣሰው ወልደሃና እንደሚሉት፤በሀገሪቱ ባለፉት አስርና አስራ አምስት ዓመታት እድገት መመዝገቡ አይካድም፡፡በተመሳሳይም ድክመቶች መኖራቸው ይታወቃል፡፡በመሆኑም ከኢህአዴግ የሚጠበቀው ጠንካራ ጎኖቹን ማስቀጠልና ለስርዓት አልበኝነት መፍትሄ ማበጀት ነው፡፡ዋናው ነገር የአገሪቱ እድገትና ሰላም የሚረጋገጥበት አካሄድ ላይ ትኩረት ማድረግ ይገባል፡፡የኢትዮጵያን አንድነት የሚያጠናክርና ሁሉም ዜጋ እኩል የሚሆንበት ጉዳይ ላይ ትኩረት አድርጎ መምከር አለበት፡፡

‹‹ከምንም በላይ አሁን ላይ ህብረተሰቡ ሰላም፣ሥራ ያጣውም ወጣት ሥራ ማግኘት ይሻላልና ኢኮኖሚው የሚጠናከርበት ሁኔታ መፈጠር ይኖርበታል፡፡›› ያሉት ፕሬዚዳንቱ፣እህት ድርጅቶቹ ስለ ክልላቸው ሁኔታ ብቻ በመመካከር ሊጠመዱ ይችሉ ይሆናል፤ኢህአዴግ ግን ኢትዮጵያዊነትን ማጠናከርና ክልሎችም ለየብቻቸው ሳይሆን በጋራ በመሆን አንድነትን የሚያጠናክሩበት አግባብ ላይ ማተኮር ይኖርበታል፡፡›› ሲሉ ያስገነዝባሉ፡፡በብሄርና በብሄር መካከል ያለ አለመግባባት የሚወገድበትና እኩልነት የሚሰፍንበት አካሄድን ሊከተል እንደሚገባውም ያመለክታሉ፡፡

‹‹ከኢህአዴግ ጉባኤ የሚጠበቀው ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ጉዳዮች ላይ ለውጥ ማምጣት ቢሆንም፤ በአስቸኳይ ትኩረት ሊደረግበት ይገባዋል ብዬ የማምነው ግን ፖለቲካው ላይ ነው›› ሲሉ የኮተቤ ሜትሮፖሊታን ዩኒቨርሲቲ መምህር ግደይ ደገፉ ይናገራሉ፡፡
‹‹በግንባሩ መካከል ያሉ አባላት ግንኙነት መሻከር እየታየበት ነው፡፡ የርዕዮተ ዓለም አንድነትም በመለወጥ ላይ ነው፡፡ አሁን ላይ እየመጣ ያለው ርዕዮተ ዓለማዊ ሳይሆን ክልላዊ አስተሳሰብ ነው፡፡››ሲሉ ጠቁመው፣ የአገሪቱ አንድነት የሚጠበቀው በምን መልክ ነው በሚለው ላይ መምክር ይኖርባቸዋል ይላሉ፡፡
የአገሪቱን አንድነት ለመጠበቅ የሰላም ጥያቄ መመለስ እንደሚኖርበትም ያስገነዝባሉ፡፡ ከሰላም ጋር ተያይዞ ደግሞ የዜግነት ጥያቄ አብሮ ይመጣልና በዚህ ጉዳይ ላይ ማተኮር የግድ ይላል፡፡ዜጎች በተለያየ ስፍራ የመኖር መብታቸው ሲጣስ መስተዋሉ ይታወቃል፡፡ ክልልዊ አስተሳሰብ ከዜግነት አስተሳሰብ የሚቃረን በመሆኑም ይህ ትኩረት የሚሻ ጉዳይ ነው ብለዋል ፡፡

በህዝቡ ውስጥ ያለው የኢኮኖሚ ጥያቄ በርካታ መሆኑን ይጠቅሱና ፍትሃዊ የሆነ የኢኮኖሚ ክፍፍል ባለመኖሩ እዚህ ላይ ትኩረት ተደርጎ ቢመከርበት ይሻላል ብለዋል፡፡ በሌላ በኩል ማህበራዊ ግንኙነቱም በጣም የተበላሸ ነው ማለት እንደሚቻል ጠቅሰው፤ ኢትዮጵያዊ እሴቶች ላይ ትኩረት በማድረግ ኢትዮጵያዊነትን ማጎልበት እንደሚያስፈልግ አስረድተዋል፡፡

ፖለቲከኛ ዶክተር ጫኔ ከበደ በበኩላቸው፤ ጉባኤው አገር የሚያስተዳድር እንደመሆኑ የሰከነ አካሄድን መከተል እንዳለበት ያመለክታሉ፡፡በተለይ ጉባኤው ግጭቶች የማይከሰቱበትን አቅጣጫ በመያዝ በቀጣይ ህዝቡ ወደ ተሻለ ልማት የሚገባበትን አካሄድ መከተል ይኖርበታል ይላሉ፡፡

ዶክተር ጫኔ እንዳሉት፤ከምንም በላይ ኢትዮጵያዊነትን ማጠናከር ለምርጫ የሚቀርብ ጉዳይ ባለመሆኑ እዚህ ላይ በትኩረት መምከር ይኖርበታል፡፡ የህግ አከባበሩ ጉዳይ ልዩ ትኩረት ሊሰጠው ይገባል፡፡ ሲሰበክ የቆየው ልዩነት ያመጣው ፈተና አለና በእርቅና በብሄራዊ መግባባት የሚፈታበት ሁኔታ ላይም መምከር ያስፈልጋል፡፡የቅራኔ ምንጭ የሆኑ ነገሮች መነሻቸውን በአግባቡ ማጤንና መፍትሄም መስጠት ከጉባኤው እንደሚጠበቅም ይናገራሉ፡፡

‹‹አብዛኛዎቹ እህት ድርጅቶች ስያሜያቸውን መቀየራቸው ልምድ እያካበቱ መምጣታቸውን ያሳያል›› ያሉት ዶክተር ጫኔ፣ወደፓርቲ ደረጃ መድረሳቸውም አንድ እርምጃ መሄዳቸውን እንደሚያመለክት ይገልጻሉ፡፡

እንደ ዶክተር እህት ድርጅቶቹ ወደ ፓርቲነት ከተቀየሩ አንድ አገራዊ የሆነ ህብረብሄራዊ ፓርቲ የመመስረት እድላቸው ይሰፋል፡፡ህወሓት ባይቀይርም ሁለትም ሦስትም ሆኖ ይህን መመስረት እንደሚቻልና ለቀጣይም ቢሆን ህብረብሄራዊ ፓርቲን የመመስረት ጉዞን መያያዛቸውን አመላካች ነው›› ይላሉ፡፡

ፖለቲከኛ ትዕግስቱ አወሉ እንደሚሉት፤ከጉባኤው የሚጠበቀው የተጀመረውን የለውጥ እንቅስቃሴ ማስቀጠል ነው፡፡ ህጋዊነት የሚከበርበት ሁኔታ ላይ መምከር አለበት፡፡ በጎበዝ አለቃ የሚካሄድ የመንጋ እንቅስቃሴ መቆም አለበት፡፡ ትናንት መንግሥት ይፈራ ነበር፤ ዛሬ ግን ይህን እያደረገ ያለው ቡድን ሆኗልና ይህ ሊታሰብበት ይገባል፡፡

‹‹ከሁሉም በፊት ግን መጀመሪያ እርስበእርሳቸው መደመር አለባቸው፡፡ እነርሱ ላይ ተግባራዊ ያላደረጉትን መደመር ህዝቡ ላይ መጫን ከባድ ነው፡፡ ለራሷ ያልተነሳች ልታቋቁም ሄደች እንዳይሆን መምክር አለባቸው›› ሲሉ ይገልጻሉ፡፡ ለቀጣዩም ምርጫ ዝግጅታቸው ጠንካራ መሆን እንዳለበት ይናገራሉ፡፡

እርሳቸው እንደተናገሩት፤ከምንም በላይ ለሰላም ትኩረት መስጠት አለባቸው፡፡ በመጀመሪያ የርዕዮተ ዓለም ለውጥ ሳይሆን ሰላም ነው የሚያስፈልገው፡፡ አጀንዳቸው ሰላም መሆን አለበት፤ ህዝቡንም በሰላማዊ ሁኔታ ለምርጫ ማዘጋጀት አለበት፡፡ ይህን ካላደረገ ራሱም ምርጫ ላይ የመድረሱ ነገር አጠያያቂ ይሆናል፡፡

አስቴር ኤልያስ
ዜና ሐተታ

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy