Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

መስህበ ዲፕሎማሲ

0 1,328

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

መስህበ ዲፕሎማሲ

                                                    እምአዕላፍ ህሩይ

የዲፕሎማሲ ስራ በዋነኛነት በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ከፍተኛ አመራሮችና ሰራተኞች የሚፈፀም ተግባር ቢሆንም፤ እያንዳንዱ ዜጋ የሀገሩ አምባሳደር ሆኖ ኢትዮጵያን የማስተዋወቅና ገፅታዋን የመገንባት ስራን ማከናወን የሚጠበቅበት ዘርፍ ነው። ዲፕሎማሲ፤ ለሀገር ውስጥ ሰላም፣ ልማትና ዴሞክራሲ የሚጫወተው ሚና የላቀ መሆኑን ለመገንዘብ ሩቅ መሄድ የሚያስፈልግ አይመስለኝም። ሌላውን ሁሉ ትተን፤ በቅርቡ የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ባለፉት ስድስት ወራት በጎረቤት ሀገሮችና በመካከለኛው ምስራቅ ሀገራት ያደረጉት ጉብኝቶች በሀገራችን ውስጥ ምን ያህል ለውጥ እንዳመጡ ግልፅ ነው።

ርግጥ ነው—ዲፕሎማሲው ለ20 ዓመታት ያህል በኢትዮጵያና በኤርትራ መካከል ተሰንቅሮ የነበረውን የጥላቻ ግንብ በማፍረስ አዲስ የወንድማማችነትና የጋራ ተጠቃሚነት ፈር መቅደድ ችሏል። ይህም በሁለቱ ሀገራት ውስጥ ሁለንተናዊ ግንኙነት እንዲደረጅ ምክንያት ሆኗል። ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ፤ ከመካከለኛው ምስራቅ ሀገራት ውስጥ ያደረጉት ጠንካራ ዲፕሎማሲያዊ ጥረቶች፤ በታሪካችን ሰምተን የማናውቀው ቢሊዮን ዶላሮች ወደ ካዝና እንዲገቡና ኢንቨስትመንትም ኢትዮጵያ ውስጥ እንዲስፋፋ ምክንያት ሆኗል ማለት ይቻላል። በዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ዘንድም፤ የሀገራችን ተፈላጊነት እንዲጨምር በማድረግ ረገድም ዲፕሎማሲው ጉልህ፣ ሊታይና ሊጨበጥ የሚችል ውጤቶችን አስመዝግቧል፤ እያስመዘገበም ነው።

በእኔ እምነት፤ እነዚህ በግልፅ የሚታዩ ውጤታማ ዲፕሎማሲያዊ ጥረቶች፤ ሀገሮች በእኛ ላይ እምነት አድሮባቸውና አብረውን እንዲሰሩ መስህብ እየሆኑ መጥተዋል። ርግጥ በርካታ ሀገሮች በተለይም ካለፉት ስድስት ወራት ወዲህ አብረውን ለመስራት ፍላጎት ለምን እንደሚያድርባቸው ጥቂት ነጥቦችን ማንሳት ይቻላል። እንዳልኩት፤ ዋነኛው ጉዳይ የሀገራችንን ተጨባጭ ሁኔታ የማስተዋወቅና ገፅታዋን የመገንባት ስራን፤ ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ በውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዶክተር ወርቅነህ ገበየሁና በሌሎች የመስሪያ ቤቱ ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎችና ቆንስላዎች እንዲሁም እያንዳንዱ ዜጋ በሚያደርገው ርብርብ፤ ሀገራት ከእኛ ጋር አብሮ ለመስራት ፍላጎት እንደሚያድርባቸው አይካድም። ባለፉት ስድስት ወራት ኢትዮጵያ ውስጥ እያታየ ያለው አንፃራዊ ሰላም፣ ሀገራችን በምስራቅ አፍሪካ ጂኦ-ፖለቲካ ውስጥ ያላት ጉልህ ስፍራና በቀጣናው ውስጥ እየገነባች ያለችው ተሰሚነት እንዲሁም ሊያሰሩ የሚችሉ ምቹ የኢንቨስትመንት አሰራሮችና ሊሰራ የሚችል በቂ የሰው ኃይል ኢትዮጵያን በሌሎች ሀገሮች ተፈላጊ እንድትሆን አድርጓታል።        

የስሎቬኒያ ልዑክ በብሔራዊ ቤተ- መንግስት፤

እዚህ ላይ በማሳያነት፤ ሰሞኑን የስሎቬኒያ ፕሬዚዳት ቦሩት ፓሆርና ከእርሳቸው ጋር አብሮ ወደ ኢትዮጵያ የመጣው የልዑካን ቡድን ለሶስት ቀናት በሀገራችን ያደረጉት ጉብኝት ተጠቃሽ ሊሆን የሚችል ይመስለኛል። በዋና ከተማዋ ጁብልጃና እና በሌሎች አካባቢዎች የታሪክ መስህቦችን ያቀፈችው አውሮፓዊቷ ሀገር ስሎቬኒያ በአፍሪካ ውስጥ ለሚኖራት እንቅስቃሴ ኢትዮጵያን እንደ መሸጋገሪያ ለመጠቀም ማሰቧ በፕሬዚዳንቷ አማካኝነት መነገሩ፤ ሀገራችን በሌሎች ሀገራት ምን ያህል ተፈላጊ መሆኗን የሚያመላክት ነው።

በኢትዮጵያ ይፋዊ ጉብኝት ያደረጉት ፕሬዚዳንት ፓሆር ከኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ዶክተር ሙላቱ ተሾመ ጋር ባደረጉት ውይይት፤ ሀገራቸው ኢትዮጵያ ውስጥ ኤምባሲ ለመክፈት ያላትን ፍላጎት ጠቁመዋል። በኢንቨስትመንት፣ በንግድ፣ በእውቀትና ልምድ ሽግግር አንዲሁም በከፍተኛ ትምህርትና ስልጠና ረገድ ሰፊ ትብብር ለመፍጠር ብሎም ከሁለትዮሽ ትብብር ባሻገር በባለ ብዙ ወገን መድረኮች በጋራ መስራት በሚቻልበት ሁኔታዎች ላይ ያተኮረው የሁለቱ ፕሬዚዳንቶች ምክክር፤ እነዚህ ሁሉን አቀፍ ጉዳዩች የሀገራቱን ግንኙነት ወደ ተሻለ ስፍራ ከፍ የሚያደርግ መሆኑ አይካድም።

ዓለማችን በምትገኝበት የሉላዊነት (Globalization) ዘመን የትኛውም ሀገር ያለ ትብብርና መደጋገፍ ለብቻው ተነጥሎ መኖር አይችልም። ፕሬዚዳንት ዶክተር ሙላቱና የስሎቬኒያው አቻቸው፤ በተለይ የኢኮኖሚ ትብብርን በማጎልበት፣ ኢንቨስትመንትንና ንግድን በማስፋፋት እንዲሁም በቴክኖሎጂ ሽግግር ትብብሮች ላይ ልዩ ትኩረት ሰጥተው በጋራ ለመስራት የተስማሙትም ለዚሁ ይመስለኛል።

ርግጥ አውሮፓዊቷ ሀገር ስሎቬኒያ የምትታወቅበትን ዘመናዊ የንብ እርባታና ውጤታማ የማር አመራረት ተሞክሮና ቴክኖሎጂ በኢትዮጵያ ተግባራዊ በማድረግና በዘርፉ ያለውን የወጣቶች ተሳትፎ ለማሳደግ በሁለቱ ሀገራት መካከል የተደረሰው ስምምነት የጋራ ተጠቃሚነትን የሚያሰፋ ከሞኑም በላይ፤ የሀገራችን ወጣቶች በዘርፉ ልምድ ቀስመው ውጤታማ ስራ እንዲያከናውኑ የሚያደርጋቸው ነው። ይህም ለወጣቶቻችን የስራ ዕድልን ከመፍጠር አኳያ የሚሰጠው አበርክቶ አሌ የሚባል አይደለም። የዲፕሎማሲ መስህብ ይህን መሰሉን የሀገራችንን የስራ ዕድል ፈጠራ እንደሚደግፍ ልብ ይሏል!

ኢትዮጵያና ስሎቬኒያ የተስማሙበት ሌላኛው ጉዳይ፤ ሰላምንና ፀጥታን እንዲሁም የአየር ንብረት ለውጥንና የስደት ጉዳይን የተመለከተ ነው። የሀገራቱ የጋራ ፍላጎት በሆኑት አካባቢያዊና ዓለም አቀፋዊ ጉዳዮች ላይ የአውሮፓ ህብረትንና የተባበሩት መንግስታት ድርጅትን ጨምሮ በባለ ብዙ ወገን መድረኮች ደረጃም በጋራ ለመስራት ተግባብተዋል። ይህ የጋራ ትብብር፤ ሁለቱንም ሀገሮች ይበልጥ ተጠቃሚ የሚያደርግ ከመሆኑም በላይ፤ አንዱ ለሌላው የሚያደርገው ድጋፍ፤ የእኩልነት መንፈስንና የሁለትዮሽ ተጠቃሚነትን ሊያደረጅ እንደሚችል ይታመናል። በተለይ ስሎቬኒያ በኢትዮጵያ ውስጥ የራሷን ኤምባሲ ስትከፍት ሁለቱ ፕሬዚዳንቶች በትብብር ለመስራት የተስማሙባቸው ጉዳዩች ይበልጥ መጎልበታቸው የሚቀር አይመስለኝም። እናም ሀገረ-ስሎቬኒያ ኤምባሲዋን በሁሉም መስኮች ተሰሚ እየሆነች በመጣችው የሀገራችንና የአፍሪካዊያን መናኸሪያ በሆነችው አዲስ አበባ ውስጥ በመክፈት የሁለቱንም ሀገራት ተጠቃሚነት ወደ መሬት እንዲወርድ ታደርገዋለች ብዬ አምናለሁ።

በብሔራዊ ቤተ-መንግስት ለስሎቬኒያው መሪ የተበረከተ ስጦታ (ሰዓሊ ለማ ጉያ)

የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ሙላቱ ተሾመ ለስሎቬኒያው አቻቸው ባደረጉት  የራት ግብዣ ላይ፤ የሀገራቱን የጋራ ተጠቃሚነት ለማሳለጥ ሀገራቸው ፍላጎት እንዳላት አስታውቀዋል። የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አቶ መለስ ዓለም በበኩላቸው፤ ኢትዮጵያ በአፍሪካ ውስጥ ያላትን ጉልህ አስተዋፅኦ ለማሳየት፤ የቀድሞው የደቡብ አፍሪካ ፕሬዚዳንት ኔልሰን ማንዴላ ሀገራቸውን ከአፓርታይድ ስርዓት ነፃ ለማውጣት ኢትዮጵያ የተጫወተችውን ሚና አውስተዋል። በዚህም ሀገራችን በአፍሪካዊያን ነፃነት ውስጥ የነበራትን ጉልህ ተሳትፎና ድጋፍ እንዲሁም አሁንም በቀጣናዊና በዓለም አቀፍ የሰላም ማስከበር ተልዕኮ እያበረከተች ያለችውን ወሳኝ አስተዋፅኦ አመላክተዋል።

በጥቅሉ፤ የዲፕሎማሲ ስራ፤ ማንነትን በማስተዋወቅ ለሰላም የሚደረግ ጥረትን የሚያጎላ፣ ልማትን የሚስብና ለዴሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታ የሚደረግ ትግልን የሚደግፍ ነው። በመግቢያዬ አካባቢ ለመግለፅ እንደሞከርኩት፤ ስራውን በዋነኛነት የሚመራው የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መስሪያ ቤት ቢሆንም ቅሉ፤ የተግባሩ ፈፃሚዎች ጠቅላይ ሚኒስትሩንና ፕሬዚዳንቱ ጨምሮ ሁሉም ዜጋ ነው። እናም ሀገርን የማስተዋወቅና ገፅታዋን የመገንባት ስራ የሁላችንም በመሆኑ፤ የዲፕሎማሲው መስህብ እንዲጨምርና እንደ ስሎቬኒያ ሁሉ ሌሎች ሀገሮችም የለውጥ ሂደታችን ደጋፊ እንዲሆኑ ሁሉም ዜጋ በያለበት ቦታ ሁሉ የሀገሩ አምባሳደር ሆኖ መስራት ይኖርበታል እላለሁ።             

           

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy