Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

“ተው ስማኝ ሀገሬ!…”

0 7,464

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

“ተው ስማኝ ሀገሬ!…”

                                                     እምአዕላፍ ህሩይ

 

“እናትም ብትሞት በሀገር ይለቀሳል፣ አባትም ቢሞት በሀገር ይለቀሳል፣ ወንድም፣ እህትና ዘመድ አዝማድ ቢሞት በሀገር ይለቀሳል፤ ሀገር የሞተ እንደሆን ወዴት ይደረሳል?” በማለት የሀገርን ጠቀሜታ የሚናገር ጃሎታ ባለቤት ሆኖ ሳለ፤ እንደምን በዚህ ዓይነቱ ኢ-ኢትዮጵያዊ የሞራል ክስረት ውስጥ ሊገባ ይችላል?…”

 

ጀግንነት እንዳይባል፤ የድኩማኖች ሃሳብ ነው። ሞኝነት እንዳይባልም፤ ራስን በራስ የማጥፋት ያህል ነው። ብልጥነት እንዳንለውም፤ አንዱ ተዋጊ ሌላው ተወጊ ሆኖ ፍዳውን የሚያይበት የእርኩሰት ሜዳ ነው። ሰላማዊነት እንዳይባልም፤ አያያዙ ሲታይ፤ ልክ እንደ ድንጋይ፤ ገጀራንና ሌሎች ራስን የማጥፊያ መንገዶች ሁሉ የሚጠቀም ሰው-ጠል እንዲሁም አፍቃሪ አርዮስ ተግባር ነው። የተግባሩ ፈፃሚዎች ሰይጣን እንኳን የሚቀናባቸው የሰዎች ሁሉ መጨረሻ ናቸው—ከሰውነት ተራ ወጥተው ወደ አውሬነት የተለወጡ።

እንግዲህ ልብ በሉ!— ሰይጣን የሚቀናበት ሰው ምን ዓይነት ፍጡር ሊሆን እንደሚችል። በክርስትናም ይሁን በእስልምና እምነቶች ውስጥ ሰይጣን የተኮነነ ፍጡር ነው—መፅሐፉ “ውግዝ ከመ አርዮስ” ያለው። ታዲያ ይህን ፈጣሪ “ዓይንህን ለአፈር” ያለውን እኩይ ፍጡር ተክተው የሚሰሩት በሩህሩሁ አምላክ የተፈጠሩትና “ሰብዓዊ” መሆን የሚጠበቅባቸው የእኛዎቹ ጉዶች አርዮሱን ሰይጣን በልጠውና አስር እጅ አስከንድተው ሲገኙ እጃችንን ከፍ አድርገን በማውጣት መናገራችን የግድ ሆኗል…“ተው ስማኝ ሀገሬ!…” እያልን።

ታዲያ የሰው ልጅ ከሰይጣን የተሻለ ብቃት እንዳለው ሳስብ፤ አንድ ወዳጄ ያጫወተኝ ተረት ትዝ አለኝ። ተረቱ ምን መሰላችሁ?…ከዕለታት በአንዱ ቀን አንዲት ባለትዳርና እግዚሐብሔርን አማኝ ሴት ንሰሃ ለመግባት ወደ ፃድቁ አቦዬ ጋር ትሄዳለች። ፃድቁ አቦዬ ገብረመንፈስ ቅዱስ፤ ያኔ በአንድ እግራቸው ቆመው ለዓለም ህዝቦች ሁሉ ድህነት እየፀለዩ ነበር አሉ።…ታዲያላችሁ ሴትየዋ ወደ ፃድቁ አቦዬ እየሄደች ሳለ፤ አንድ የቀድሞ ወዳጇ የሆነ ሰው መንገድ ላይ ይገጥማታል። ሰላምታ ከተለዋወጡ በኋላ፤ ስለ ድሮ ፍቅራቸው ማውጋት ያዙ። ጨዋታ ጨዋታን ወለደና ሰውዬውና ሴትየዋ ወደ አንዱ ጫካ ጎራ ብለው ያው እንደ ድሯቸው “አመላቸውን” ይፈፅማሉ።

ሰይጣንም እነዚህ ምን ዓይነት አሻጥረኛ ሰዎች ናቸው ብሎ ተደብቆ ይመለከታቸው ነበር። ሴትየዋም መንገድ ላይ ያጋጠማትን የድሮ ወዳጇን ትሰናበተውና ጉዞዋን ወደ አቦዬ ገብረ መንፈስ ቅዱስ ታደርጋለች። ዓላማዋ ንሰሃ ለመግባት ቢሆንም ቅሉ፤ ከባለቤቷ ውጭ ከቀድሞ ወዳጇ ጋር ከአልጋ ወድቃለች። ያም ሆኖ፤ ንሰሃ መግባት አለብኝ ብላ አቦዬ ፃዲቁ ጋር ተደርሳለች። አቦዬም “ልጄ ወደ እኔ ምን አመጣሽ?” ሲሉ ይጠይቋታል—ሴትየዋን። እርሷም “አቦዬ አመጣጤ ንሰሃ ለመግባት ነበር፤ ሆኖም መንገድ ላይ ሰይጣን አሳሳተኝና ሃጠያት ሰራሁ” ትላቸዋለች። አቦዬም “እግዚሐብሔር መሃሪ ነው፤ አይዞሽ ልጄ!” ከማለታቸው፤ ለካስ ሰይጣኑ ሲከታተሏት ኖሮ፤ “አቦዬ ፈፅሞ እንዳይሰሟት። ይህችን ሴት ፈፅሞ አልቀረብኳትም። ሁሉንም በራሷ ፍላጎት የፈፀመችው ነው። እኔ ራሴ ለካስ እንዲህ ዓይነት ነገርም አለ እንዴ? ብዬ ቀንቼባታለሁ” በማለት ‘ከደሙ ንፁህ ነኝ’ ይላል። አቦዬም በቅድሚያ ሰይጣኑን “ሂድ አንተ ከይሲ፤ እዚህ ምንድር ትሰራለህ!” ብለው ገስፀው ካባረሩት በኋላ፤ ሴትየዋን በእርጋታ እንዲህ አሏት—“የሰው ልጅ አንዳንዴ በሚፈፅማቸው ዘግናኝ ተግባራት ከሰይጣን እንደሚበልጡና እንደሰማሽውም ሰይጣንን ራሱ ከማስገረም አልፈው እርኩሱ ፍጥረት የሰው ልጅ የክፋት መጠን ከእርሱ ልቆ ሲያገኘው እንደሚያስቀናው አስገንዝበዋት፤ “ለሰራሽው ሐጢያት እግዚሐብሔር ይፍታሽ” ብለው በሰላም አሰናበቷት ይባላል።     

ታዲያ ይህ ተረት የሚያስገነዝበን ነገር ቢኖር፤ የሰው ልጅ ክፋት ምን ያህል ሰይጣንን ሊያስከነዳ እንደሚችል ነው። ሰይጣን ራሱ በቅናት እስኪናውዝ ድረስ የሚፈፀሙ የሰው ልጆች የክፋት ልኬታ ወደር የለውም። በምድር ላይ እርስ በርሱ የሚጠፋፋው የሰው ልጅ፤ “ሰይጣን አስንቄ” ምግባሮቹን የሚፈፅመው በተለያዩ ምክንያቶች ነው። በተለይም አሁን በምንገኝበት ወቅት፤ ፖለቲካዊ አስተሳሰቦች ምን ያህል የሰውን ልጅ በግፍ እንደሚያስገድሉ፣ እንደሚያስደፍሩ፣ አካል የሚያስጎድሉና ንብረት እንደሚያወድሙ እየተመለከትን ያለነው እውነታ ነው።

ሰሞኑን በተለያዩ የሀገራችን ክፍሎች ውስጥ የሚታዩት የህይወት መጥፋቶችና መፈናቀሎች የዚህ ክፋት መገለጫዎች ናቸው። ርግጥ እየተመለከትናቸው ያሉት ተታችለንና በኢትዮጵያዊ መንፈስ መኖር ስንችል በመከፋፈል የምንፈፅማቸው ጉዶች፤ “ተው ስማኝ ሀገሬ…” የሚያስብሉ ናቸው* እናም እኔም “ተው ስማኝ ሀገሬ!…” ለማለት ወደድኩ። አዎ! “ተው ስማኝ ሀገሬ!…” እላለሁ።

ታዲያ “ተው ስማኝ ሀገሬ!…” የምለው እንዲሁ ከመሬት ተነስቼ አይደለም— በአሁኑ ወቅት የምመለከታቸውና የምሰማቸው ጉዳዩች ምሬትንና ሐዘንን የሚያጭሩ ስለሆኑብኝ እንጂ።…ነገሩ የኦዴፓው ምናባዊው ወዳጄ አቶ ታዬ ደንደአ እየደጋገመ ‘በባንዴራ ለመጣላትም መጀመሪያ ሀገር መኖር አለበት’ እንደሚለው ዓይነት ስለሆነብኝ እንጂ። ርግጥ ነው— ከመሰንበቻው ከየቦታው የሚሰማው ነገር አሳዛኝ ነው። ግና ለማዘንም ቢሆን አስቀድሞ ‘የእኔ’ የምንለው ሀገር ሊኖረን ይገባል።
ሰሞኑን በኦሮሚያ ክልልና በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ከማሺ ዞን የሚኖሩ 44 ንፁሃን ዜጎች በታጣቂዎች ተገድለዋል። ከ70 ሺህ በላይ ዜጎችም ከሁለቱም ክልሎች ተፈናቅለዋል። ከአንድ ሺህ 560 በላይ የአርሶ አደር ቤቶችም ተቃጥለዋል። ቁጥሮቹ ከዚህ ሊያሻቅቡ እንደሚችሉ የቤኒሻንጉል ክልል የመንግስት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዩች ቢሮ ኃላፊ ሲናገሩም አድምጠናል።…ልብ እናድርግ!— የክፋታችንና የጭካኔያችን ደርዝ አሳዛኝነትን፤ ሰይጣን የሚቀናባቸው አሳፋሪ ወገኖቻችን እኩይ ሴራቸው እስከየት ድረስ የሚዘልቅ መሆኑን። ኧረ ራሳችንን አናጥፋ፤ ኧረ ወገን ከጥፋታችን እንቆጠብ!…ኧረ ተው ስማኝ ሀገሬ!…
ከምዕራብ ወደ ምስራቅ ስናመራም፤ በድሬደዋ ከተማ አስተዳደር 01 ቀበሌ በተለምዶ “መልካ ጀብዱ” እየተባለ በሚጠራው አካባቢ፤ መስከረም 21 ቀን 2011 ዓ.ም ምሽት ላይ በአንድ ግለሰብ ላይ የደረሰ ጉዳት ወደ ብሔር ግጭት ተቀይሮ፤ ሁከትና ረብሻ የተከሰተ ሲሆን፤ በዚህም አንድ ሰው በደረሰበት ድብደባና የስለት ጉዳት ህይወቱ ማለፉን መገናኛ ብዙሃን ዘግበዋል። አንድ ሌላ ሰውም በጥይት ተመቶ ህይወቱ ማለፉ የተነገረ ሲሆን፤ ተጨማሪ አንድ ሰውም እግሩ በጥይት ቆስሎ በህክምና ላይ እንደሚገኝ ተገልጿል።
በመጀመሪያ ደረጃ በየትኛውም መልኩ ቢሆን ግጭት ሲፈጠር የሚሞተው፣ የሚቆስለውና የሚፈናቀለው ወገኔ ነው ብሎ ማሰብ ያስፈልጋል። የጥንካሬያችን ምንጭ አንድነታችን እንጂ መለያየታችን አይደለም። አንድ ሰው ሲሞት ሲጎዳ “እገሌ የእኔ ብሔር ነው” ከማለት ይልቅ፤ “ኢትዮጵያዊ ነው እንድረስለት” ማለት ያስፈልጋል። ይህን ማድረግ ካልቻልን፤ እንደ ሀገር በሁለት እግራችን ቆመን ለመጓዝ መቼም ቢሆን ርግጠኛ መሆን አንችልም።
ምን ይህ ብቻ! ባለፉት ሶስት ቀናት በከፋ ዞን ከ15 የማያንሱ ሰዎች በአሰቃቂ ሁኔታ መገደላቸውን፤ እንዲህ ዓይነት የግጭት ዜና ከሚመቸው ኢሳት የተሰኘው ጣቢያ ትናንት አድምጫለሁ። እንግዲህ እነዚህ ማሳያዎች ሀገራችን ውስጥ በሁሉም የስራ ዘርፎች ማለት በሚቻል ሁኔታ ሰይጣንን አስር እጅ የሚያስከነዱ ሰዎች የገዛ ዜጎቻቸውን ለመግደል፣ ለማጥቃትና ለማፈናቀል አሰፍስፈው መገኘታቸው ነው። ሰዎቹ “ሀገር ጃርት ያበቅላል” እንደሚባለው፤ በእሾሃማ ክንፋቸው ሀገራቸውንና ህዝባቸውን የሚወጉ ናቸው። አወጋጋቸው ደግሞ እየለየ በመሆኑ ሀገርን የሚያፈርስ ነው። ሀገር ከፈረሰስ ወዴት እንገባ ይሆን?…የሶሪያ የየመን የሊቢያ…ወዘተ. ዕጣ ፈንታ እንደማይደርስብን በምን ርግጠኛ መሆን እንችላለን?…
የሀገራችን ሰው፤ “እናትም ብትሞት በሀገር ይለቀሳል፣ አባትም ቢሞት በሀገር ይለቀሳል፣ ወንድም፣ እህትና ዘመድ አዝማድ ቢሞት በሀገር ይለቀሳል፤ ሀገር የሞተ እንደሆነ ወዴት ይደረሳል?” በማለት የሀገርን ጠቀሜታ የሚናገር ጃሎታ ባለቤት ሆኖ ሳለ እንደምን በዚህ ዓይነቱ ኢ-ኢትዮጵያዊ የሞራል ክስረት ውስጥ ሊገባ ይችላል?…እናም የሀገሬ ሰው አስቀድሞ የገዛ ወንድሙንና ራሱን እየገደለ፣ ለጥቆም ሀገሩን እንዳይገድል ቆም ብሎ ከአንዴም ሁለት ሶስቴ…አራት አምስቴ…ስድስት ስባቴና ስምንት ዘጠኜ…እየደጋገመ ማሰብ ያለበት ወቅት አሁን ይመስለኛል።
እስቲ እንዲያው አንድ ነገር ላንሳ። እዚህም…እዚያም የሚታዩትና ብሔርን ማዕከል አሊያም ምክንያት ያደጉት ግጭቶች መጨረሻቸው ምን ይሆናሉ? ብለን እናስብ። በእኔ እምነት፤ የሀገሬ ሰው መጪውን አደገኛ ሁኔታ እስካላሰበ ድረስ፤ በዚሁ ከቀጠልን ወደ ሀገር ብተና ላለመግባታችን ምንም ዓይነት ማስተማመኛ የለንም። የብጥብጥና የሁከት ሀገር ማደሪያው ተደራራቢ መቃብሮች ብቻ ናቸውና። ዳሩ ግን እነዚህን መቃብሮች የሚፈልጋቸው ዜጋ አለ ብዬ አላስብም—ማንም ቢሆን ከመሞት መሰንበትን ይመኛልና። እናም በለውጥ ሂደት ላይ ያለን ህዝቦች በመሆናችን መፃዒ ዕድላችንን አሳፋሪ በሆነ የልየታ ግድያ አንግታው። ለውጡ እንዳይደናቀፍ የሰለጠኑ ሰይጣኖችን በየአካባቢያችን ወዳላስፈላጊ ሁከት እንዳይወስዱን ግራ ቀኙን እንመልከት። በሰከነ አዕምሮ በአንድነት “ከቲም ለማ” ጋር በመሆን ኢትዮጵያችንን ለመገንባት እጅ ለእጅ እንያያዝ።
ፖለቲካና እምነት ለየቅል ናቸው። ፖለቲካ ውስጥ “ለሰራኸው/ሽው ሐጢያት እግዚሐብሔር ይፍታህ/ሽ” ብሎ ነገር የለም። የሚዳኘው በምድራዊ ህግ ነው። ምድራዊውን ህግ የሚገዛው ደግሞ መንግስት ነው። መንግስት ብቻውን ምንም ማድረግ አይችልም። ስለ ሀገሩ የሚያስብና የሚያንጎራጉረው ህዝባችን ከሰይጣን በላይ የሰለጠኑበትን የሰላም ቀበኞችን ወደ ፍትህ ደጃፍ ማድረስ አለበት። ሀገሩ እንዳይሞት ለማድረግ የሚከውነው ትልቅ ተግባር ይኸው ነውና።   
እናም አሁን ያለንበት አሳዛኝ ወቅታዊ ሁኔታ “ተው ስማኝ ሀገሬ!…” የምንልበት ነው። ሁላችንም ለራሳችንና ለሀገራችን ስንል ከሰይጣን በላይ ሰይጣን የሆኑ ሰዎችን በያለንበት አደብ ልናስገዛቸው ይገባል። ይህን ሀገራዊ ኃላፊነታችንን እንደ ዜጋ መወጣት ካልቻለን፤ ቁጭ ብለን እንኳን ሐዘናችንን የምንወጣበት ሀገር ሊኖረን እንደማይችል ማወቅ አለብን። እኔ በበኩሌ ሀገሬና ህዝቤ ከሰማኝ እነሆኝ “ተው ስማኝ ሀገሬ!…” ብያለሁ። የእኔ አምሳያዎችም በፊናቸው እንዲጮሁም እሻለሁ። ለዛሬው ግን፤ መጪው ጊዜ ለህዝባችንና ለሀገሬ ሰናይ ይሆን ዘንድ ተመኘሁ።     

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy