Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

“አላማጣ ውዬ፣ አሁንም አላማጣ…”

0 10,341

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

8“አላማጣ ውዬ፣ አሁንም አላማጣ…”

                                                     እምአዕላፍ ህሩይ

 

“…ከትናንት የማይማር ህይወት የሌለው ግዑዝ አካል ብቻ ነው። እሳት የሚያቃጥል መሆኑን የማያውቅ ዜጋ አለ ብዬ አላስብም። ጠባሳውም የማይሽርና እስከ መጨረሻው ምልክት ሆኖ እንደሚቀርም…”

 

ያደግኩበት ቤት ሁሌም ማታ…ማታ ፀጥ-ረጭ ይላል። በዚያ ፀጥታ ውስጥ መርፌ እንኳን ቢወድቅ፤ የከበሮ ድምፅ ያህል የሚሰማን ይመስለኛል። የፀጥታው መንስኤ፤ ባለ ክራሩ አጎቴ ነው—የእናቴ ወንድም። እኛ ቤት ውስጥ ማታ…ማታ የማይሰበሰብ የመንደር ሰው የለም— የአጎታችንን የክራር ቅኝት ከመረዋ ድምፁ ጋር ለመስማት። ጎረምሳው፣ አባወራው አዛውንቱ ባልቴቱ…ወዘተርፈ. ቡና ሳይጠሩ ምሽት ላይ ከቸች የሚሉ ወዳጆቻችን ናቸው። አጎቴ፤ ክራሩን ቃኝቶ፣ የሚጫወተው ያለ መግረፊያ ነው። አምስቱን የክራር ክሮቹን በአምስቱ ጣቶቹ ብቻ እየነካካ፤ አምባሰልን፣ ትዝታን፣ ባቲን፣ አንቺ ሆዬ ለእኔን…ሲጫወት አፍ ያስከፍታል። በጣቶቹ ብቻ ክሮቹን በሰውኛ ቋንቋ ያናግራቸዋል። በተለይ ለስለስ ባለ ክራራዊ ቅኝቱ፤ “አላማጣ ውዬ፣ አሁንም አላማጣ፤ በበሽታዬ ላይ በሽታ ላመጣ” እያለ፣ አንዲት የአላማጣን ልጅ የወደደን ሰው ተመስሎ ይጫወት የነበረው የፍቅር ጥዑም ዜማ ከአዕምሮዬ ጓዳ የሚፋቅ አይደለም።

በመሃል ላይም፤ ትግርኛውን፣ ኦሮሚኛውንና አፋርኛውን በዚያ ባማረ ቅላፄው ሲያቀነቅን፤ ‘ምነው እኔም እንደርሱ እነዚያን ቋንቋዎች ሁሉ ባወቅኩኝ ኖሮ?!’ ያስብላል። እኛ ቤት የሚመጡት ጎረቤቶቻን፤ አማራዎች፣ ትግሬዎች፣ አፋሮች፣ ደቡቦች…እና አሁን የማላስታውሳቸው ሌሎች ብሔረሰቦች በመሆናቸው ሁሉም ለአጎቴ ልዩ ፍቅር አላቸው። ዛሬ ላይ፤ ‘ምናልባትም በየራሳቸውን ቋንቋ ስለሚያዜምላቸው ይሆን እንዲህ የሚወዱት?’ ብዬ እንዳላስብ፤ ለሁሉም ለዘፈኖቹ ሁሉም እኩል ፍላጎት ያላቸው መሆናቸው ደግሞ ግራ ያጋባኛል። በወቅቱ የዘጠነኛ ክፍል ተማሪ የነበርኩት እኔ እንኳ፤ ዙረቴን ትቼ የማታውን የቤታችንን “የአንድ ሰው ኦርኬስትራ” በመናፈቅ በጊዜ ወደ ቤቴ እሰበሰባለሁ—ጓደኞቼን በማስከተል።

በእውነቱ አጎቴ የማታውን የቤታችንን የቡና ስነ ስርዓት ነፍስ ይዘራበታል። በክራሩ እያጀበ ያንን ተስረቅራቂና ማራኪ ቀጭን ድምፁን ወደ እያንዳንዳችን ጆሮ እንደ ጥሩ ጠላ ያንቆረቁራል። ታዲያ ያን ሁሉ የመንደር ሰው ዛሬ ላይ ወደ ኋላ መለስ ብዬ ሳስበው፤ የሰው ልጅ የሙዚቃ ፍላጎት፣ የመግባባት መጠንና አብሮ የመኖር ትስስር ምን ያህል ስር የሰደደ እንደነበር በእጅጉ ይደንቀኛል። ታዲያ ከዚያ ሁሉ የመንደር ጎረምሳ አጀብ ውስጥ አንዳችንም የእርሱን ፈለግ ሳንከተል በየፊናችን እንደ ጨው መበተናችንም ሳያስገርመኝ አልቀረም።

ዳሩ ግን፤ ሁላችንንም ያሰባስበን የነበረው ኢትዮጵያዊ ፍቅር እንደነበር አሁን ላይ ተከስቶልኛል። ኢትዮጵያዊነትን ከኢትዮጵያዊ የመስማት ጉጉት። አጎቴ የመሰባሰባችን ሰበብ ነበር ማለት ነው። በእውነቱ፤ ኢትዮጵያዊ ፍቅር ምን ያህል እንደሚያሰባስብ ያ ክስተት ሁነኛ ማሳያ ይመስለኛል። እናም ሳናውቀው በኢትዮጵያዊነት ሱስ ተጠምደን ነበር ማለት እችላለሁ። ዛሬም ይኸው ኢትዮጵያዊ አንድነታችንን ሊያጠናክር በሚችል የለውጥ ሃዲድ ላይ ነን። ኢትዮጵያዊነት ፍቅር መሆኑን በዶክተር አብይ አህመድ የሚመራው “ቲም ለማ” በአዲስ የአንድነት መንገድ እያደሰው ነው። በግጭት ማዕበል ሳይመታ በሰላም የለውጥ ጎዳና ላይ ሳይደናቀፍ እንዲጓዝ እያደረገው ነው። እጅ ለእጅ ተያይዘን አዲሲቷን ኢትዮጵያ በፍቅር ተሳስረን እንድንገነባ ፈር እየቀደደ ነው—“ቲም ለማ”። ለዚህም ሳይሆን አይቀርም—የኦሮሚያው ፕሬዚዳንት ኦቦ ለማ መገርሳ “ኢትዮጵያዊነት ሱስ ነው” የሚለው ንግግራቸው ሁሌም በውስጣችን የሚመላለሰው።

አላማጣን የማውቃት በአጎቴ ክራር ነው። በፍቅር ከተማነቷ ነው። “አላማጣ ውዬ፣ አሁንም አላማጣ፤ በበሽታዬ ላይ በሽታ ላመጣ” እያለ የሚያዜመው አጎቴ ግጥም የሚያስረዳው፤ አንድ ኢትዮጵያዊ በአንዲት የአላማጣ ሴት ፍቅር ተነድፎ እርሷኑ ለማየት እንደ ውሃ ቀጂ እየተመላለሰ ወደ አላማጣ የሚሄድ መሆኑን ነው። ከዚህ በፊት እንደያዘው ፍቅር ዓይነት፣ ዛሬም የሌላ ተጨማሪ ፍቅር ሰለባ ሆኛለሁ ለማለት ነው። የአጎቴ ግጥም ባይነግረንም አፍቃሪው ሰውዬ ‘ወይ እዳዬ…አበሳዬ!’ እያለም በውስጡ ሳያንጎራጉር የቀረ አይመስለኝም።

አዎ! አላማጣ የፍቅር ሀገር ነው። የፍቅር ከተማ ነው። አላማጣን ባሰብኳት ቁጥር ወደ አዕምረዬ ጓዳ የሚመላለሰው ፍቅሯ ብቻ ነው። በፀብ ከተማነት እንኳን በውኔ ላስባት በህልሜም ላያት አልፈቅድም—አላማጣ እንዲያ አይደለችምና። ይሁንና ሰሞኑን በተለያዩ ሚዲያዎችና ማህበራዊ ድረ ገፆች ስለ አላማጣ የምሰማው ነገር በአያሌው ቅሬታ ውስጥ ከትቶኛል። በፍቅር በማውቀው ከተማ ውስጥ፤ ሰዎች በግጭት ሳቢያ ሲሞቱና ሲጎዱ መስማቴ ከፍቶኛል። ምንም እንኳ ግጭቶች በየትኛውም ማህበረሰብ ውስጥ ሊኖሩ የሚችሉ ነባራዊ ክስተቶች ቢሆኑም፤ በተፈጠሩ ግጭቶች ሳቢያ ክቡሩ የሰው ልጅ ህይወት እንደ ዋዛ ሲያልፍ መስማት ልብ ይሰብራል። ያሳቅቃል።

እዚህ ሀገር ውስጥ ማንኛውንም ጉዳይ ህገ መንግስታዊና ሀጋዊ በሆነ መንገድ መፍታት እየተቻለ ዜጎች በየቦታው የሚሞቱበት ምክንያት ለእኔ የማይገባኝ እንቆቅልሽ ነው። ትናንት የትግራይ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት የኮሙኒኬሽን ጉዳዩች ቢሮ ባወጣው መግለጫ፤ አላማጣ ከተማ ውስጥ ሶስት ሰዎች መሞታቸውን ሰምተናል። የፀጥታ ሃይሎችም መጎዳታቸውን እንዲሁ። በእውነቱ እንዲህ ዓይነቱ ነገር አንድ ቦታ መቆም አለበት። ‘እገሌ ከተማ ውስጥ ይህን ያህል ሰው ሞተ፣ ተጎዳ፣ ተፈናቀለ…’ ከሚለው አሳዛኝ ዜና የምንላቀቅበት ጊዜ መኖር አለበት።

ሁሌም እንደምለው፤ ኢትዮጵያዊ ፍቅርና አንድነት እየጎለበተ ባለበት የለውጥ ሂደት ውስጥ የምንገኝ ህዝቦች ነን። እንዲህ ዓይነት ህዝብ ማደርጀትና ማጎልበት ያለበት፤ ግጭትንና ሞትን እንዲሁም ቁርሾንና መፈናቀልን አይደለም። ድርጅቱና ጉልበታው ስለ መለያየትና ስለ ሞት መሆን የለበትም። ልንናፍቃቸው የሚገቡን ጉዳዩች፤ ኢትዮጵያዊነት፣ አንድነት፣ ፍቅርና ጠንካራ ወዳጅነትን ነው። እነዚህን አስተሳሳሪ ገመዶች አጥብቀን መቋጠር ይኖርብናል። አዎ! ለእነዚህ የተቀደሱ ሃሳቦች የከፍታ ማማ አበጅተንላቸው እነርሱው ላይ ተመልሰን ለመውጣት መታተር አለብን። ፍቅራችንና ወዳጅነታችን እየጨመረ ሲሄድ አንድነታችን ጠንክሮ የጋራ ቤታችን የሆነችውን ኢትዮጵያን ለመገንባት የሚያስችሉን ድራችን ናቸውና።

በአንድ ወቅት ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ እንደናገሩት፤ አንድነታችን ከልዩነታችን ይበልጣል። ያንን አንድነት ማስቀጠልና በጠንካራ መሰረት ላይ እንዲቆም ማድረግ የዜጎች ድርሻ ነው። ርግጥ አንድነትን የማጠናከርና በሁሉም ህዝቦች ውስጥ የማስረፅ ስራ የመንግስት ብቻ ሊሆን አይገባም—የሁሉም ዜጋ የየዕለት ተግባር እንጂ። እኛ ኢትዮጵያዊያን በሁሉም ህዝቦች ዘንድ ተቀባይነት ያላቸው የተንሰላሰሉ እሴቶች ባለቤቶች ነን። እነዚህ እሴቶቻን ህግና ስርዓትን የሚያከብሩ ናቸው። እሴቶቻችን ግጭቶችንና መጠላለፍን የሚሰብኩ አይደሉም—የሚጠየፉ እንጂ። እሴቶቻችን፤ የህግ የበላይነትን የሚፃረሩ አይደሉም—የሚያከብሩ እንጂ። እሴቶቻችን፤ የተናጠል ጉዞን የሚገልፁ አይደሉም—አብሮነትንና አንድነት የሚያንሰላስሉ እንጂ።

እናም ሁሉም ዜጋ እነዚህን እሴቶቹን የየዕለት ስንቁ ማድረግ ይኖርበታል። ከግጭት አባባሾችና ከተግባሮቻቸው መራቅ አለበት። የዓለም ህዝቦች ‘አንድ እንሁን፣ ድንበር አያሻንም’ በሚሉበት 21ኛው ክፍለ ዘመን፤ እኛ “ጠብ ያለሽ በዳቦ” እያልን በጎጥና በመንደር እየተቧደንን የምንጋጭበትና ህይወታችንን የምናጣበት ምክንያት አሳፋሪ ነው። ያሸማቅቃልም። ስልጡን ከሆነ አስተሳሰብ ርቀን የኋሊት ሸርተቴ ተጫዋቾች ለመሆን ማሰባችን የትኛውንም ዜጋ የሚያሸማቅቅ ነው። በተለይ በየማህበራዊ ሚዲያው ዘርንና ቡድንን እየለዩ ‘ጀግናዬ በለው!’ ዓይነት እጅግ አሳፋሪ ተግባሮችን የሚፈፅሙ ወገኖች በራሳቸው ማዘን ያለባቸው ይመስለኛል። እነዚህ ወገኖች፤ ኢትዮጵያዊነትን የማይገልፁ ጉዳዩችን እየመዘዙ በደም ፍላት የሚወረውሯቸው አላስፈላጊ ቃላቶችና የፈጠራ ትረካዎች “ቤንዚን” ሆነው ግጭትን ከማባባስና የዜጎቻችንን ህይወት ከመቅጠፍ በስተቀር የሚያስገኙልን አንዳችም ጠቀሜታ የለም። እናም አስተሳሰባችንም ይሁን ተግባራችን የሰፋና ዘመኑን የሚዋጅ መሆን ይኖርበታል እላለሁ።

አላማጣ ወይም ራያ የማንም ይሁን የማን ህገ መንግስቱ እንዲህ ዓይነት ጉዳዩችን የሚፈታበት የራሱ ህግና ስርዓት ስላለው እዚያ ውስጥ ገብቼ መፈትፈት አልፈልግም። አስፈላጊም አይደለም። የለውጡ አካላት የሆኑት የትግራይም ይሁን የአማራ ክልሎች ተገቢ ያልተገባ እንካ ሰላንቲያ ውስጥ መግባት አለባቸውም ብዬም አላምንም። ኢትዮጵያዊ አንድነትን ለማጎልበት ይህን መሰሉ ተራ ሙግት ምንም ዓይነት ፋይዳ የለውምና። ይሁን እንጂ፤ በየማህበራዊ ሚዲያው የራሳቸውን ግብ አንግበው “በጥላቻ ንግግር” (Hate Speech) ነገሮችን የሚያቀጣጥሉ እንዲሁም በአንዳንድ የመንግስትና የግል ሚዲያዎች ውስጥም በተመሳሳይ መልኩ ጉዳዩችን የሚያጋግሉ ወገኖች ከድርጊታቸው መቆጠብ አለባቸው ብዬ አምናለሁ።

ፌስ ቡክን በመሳሰሉ የትስስር መረቦች አላስፈላጊ የነገር ድሪቶን እየጎተቱ ዜጎችን ወደማይገባ ብጥብጥ ውስጥ ለመምራት የመሞከር ፍላጎት “ብስራተ-ዜና”ው ሊሆን የሚችለው የዜጎች ሞት፣ አካል መጉደልና መፈናቀል መሆኑን ከቅርብ ጊዜ ኑባሬያዊ ጉዟችን ልንማር ይገባል። ከትናንት የማይማር ህይወት የሌለው ግዑዝ አካል ብቻ ነው። እሳት የሚያቃጥል መሆኑን የማያውቅ ዜጋ አለ ብዬ አላስብም። ጠባሳውም የማይሽርና እስከ መጨረሻው ምልክት ሆኖ እንደሚቀርም ሁላችንም የምንገነዘብ ይመስለኛል። እናም እሳትን ያለቦታው ከመጠቀምና ከማቀጣጠል በመቆጠብ ሁሉም ዜጋ ለኢትዮጵያዊ አንድነት መስራት ይኖርበታል። ፍቅር፣ መቻቻልና አብሮነት ትርፍ እንጂ ኪሳራ የላቸውም። የያዝነው የለውጥ መንገድ ሳይደናቀፍ የሁላችንም ሀገር የሆነችውን ኢትዮጵያን የምንገነባው በፍቅርና በአንድነት ተደምረን እንጂ በየመንደሩ የሚቆሰቆሱ እሳቶችን ወደ እቶን ቋያነት እየቀየርን አይደለም።

ስለሆነም “የግጭት ምንቸት ግባ፤ የሰላም ምንቸት ውጣ” የሚሉ የጠብ አለቆችን ቢቻል በመምከር፣ ካልተቻለም በማውገዝ ጭምር ምክንያታዊ ያልሆነ የግጭት ምዕራፍ በሀገራችን ውስጥ እንዲዘጋ መጣር አለብን። ይህን ሳናደርግ በነገር ሾተል እየተወጋጋን ለውጡን ልናፋጥነው የምንችል አይመስለኝም። የአላማጣ ወይም የራያ ጉዳይም ከዚህ አኳያ መታየት ይኖርበታል። አላማጣ እንደ ማንኛውም የኢትዮጵያ ከተማ ሁሉ በፍቅር ደምቃና በአንድነት አምራ እንጂ የግጭትና የቋያ እሳት ተምሳሌት ሆና ፈፅሞ ላያት አልሻም። ዛሬም እንደ ትናንቱ አላማጣን የማስባት አጎቴ ይቀኝላት በነበረው የፍቅር ሀገርነቷ ነው። አዎ! ዛሬም “አላማጣ ውዬ፣ አሁንም አላማጣ፤ በበሽታዬ ላይ በሽታ ላመጣ” እያልን በፍቅር ሃሳብ የምንመላለስባት ከተማ እንድትሆን እመኛለሁ። ሁሌም ፍቅር ያሸንፋልና ይህ እንደሚሆንም ቅንጣት ያህል አልጠራጠርም። ሰላማችን ይብዛ። ሰናይ ጊዜ።    

 

                 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy