Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

‘አይ አለማወቅ…!’

0 8,584

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

‘አይ አለማወቅ…!’

                                                      እምአዕላፍ ህሩይ

 

“…በዋዜማውና በመባቻው፤ በተለያዩ ማህበራዊ ሚዲያ የትስስር መረቦች የነገር አንካሴዎች ሲጣሉበትና ሲነሱበት፣ መላ-ምቶች ሲወነጨፉበት፣ ለያዥና ለገናዥ ሲያስቸግሩበት እንዲሁም ከወዲያ ወዲህ አስገራሚ የሃሳብ ደርዞች ሲላተሙበት የሰነበተው…”

 

ከጉባኤው በፊት፤ ‘እንቶኔና እንቶኔ ፓርቲዎች በአንድ ወገን፣ እገሌና እገሌ ደግሞ በሌላ በኩል ጎራ ለይተው ይፋለማሉ፤ እገሌ ቦታውን ሊለቅ ነው’ ከሚለው ምናብ ወለድ ሃሳብ ጀምሮ፤ ‘ኢህአዴግ ይህ ጉባኤው የመጨረሻው ነው፤ በቃ! አከተመለት፤ ይበታተናል!’ እስከሚሉ ድፍረት የተሞላባቸው ትረካዎች ድረስ አድምጠናል። አንዳንዶች በሚደንቅ ሁኔታ ‘ጉባኤው በአታካራ ተሞልቶ ያለ ስምምነት ይበተናል’ በማለት የሀገሪቱን መፃዒ ዕድል ለመተንበይ ሲከጅሉ ታዝቤያለሁ።

ነገሩን ዳር ሆነን ስንመለከት የነበርነው ገለልተኛ ወገኖች ግን፤ እነዚህ መላ ምቶችና ምኞቶች እንደ ሃሳብ የሚከበሩ መሆናቸውን ብናውቅም፤ ሃሳቦቹ ግን የኢህአዴግን ተፈጥሮና የመጣበትን መንገድ ካለማወቅ የመነጩ መሆናቸውን ሳንገልፅ አላለፍንም። አብዛኛዎቹ ሃሳቦች በስሜት የተዋጡ፣ ከግላዊ አሊያም ከድርጅታዊ እምነት በሚነሱ ፍላጎቶች በመሆናቸው ሰሚ አልባ ሆንን እንጂ።

ያም ሆኖ፤ በዋዜማውና በመባቻው፤ በተለያዩ ማህበራዊ ሚዲያ የትስስር መረቦች የነገር አንካሴዎች ሲጣሉበትና ሲነሱበት፣ መላ-ምቶች ሲወነጨፉበት፣ ለያዥና ለገናዥ ሲያስቸግሩበት እንዲሁም ከወዲያ ወዲህ አስገራሚ የሃሳብ ደርዞች ሲላተሙበት የሰነበተው የኢህአዴግ 11ኛ ጉባኤ ትናንት ማሳረጊያውን አግኝቷል።

ዛሬ ደግሞ፤ በጉባኤው የኢህአዴግ ሊቀመንበር ሆነው በድጋሚ የተመረጡት ዶክተር አብይ አህመድ ባደረጉት ንግግር የማሳረጊያው ማሳረጊያ ስነ ስርዓት ተከናውኗል—ሀዋሳ ከተማ ላይ፤ መስከረም 26 ቀን 2011 ዓ.ም። በማሳረጊያው ማሳረጊያ ላይ የድርጅቱ ሊቀመንበር ዶክተር አብይ አክመድ፤ ሰላምን ለማረጋገጥ ህዝቡ ከጎናቸው እንዲቆም፣ የማያሰሩ ህጎች ካሉ እንደሚሻሻሉ፣ በቀጣዩ ዓመት የሚካሄደው የሀገሪቱ አጠቃላይ ምርጫ ነፃ፣ ፍትሐዊና ገለልተኛ እንደሚሆን እንዲሁም ተፎካካሪ ፓርቲዎች ማሸነፍ ብቻ ሳይሆን መሸነፍም እንዳለ ተገንዝበው ራሳቸውን እንዲያዘጋጁ የድርጅታቸው ጉባኤ ውሳኔ ማሳለፉን ገልፀዋል። በተጨማሪም፤ ግብርና፣ ኢንቨስትመንትና መስኖ ልማት እንዲጠናከሩ እንዲሁም ቱሪዝም ቀጣዩ የትኩረት አቅጣጫ መሆኑንና ድርጅታቸውም ውስጣዊ አንድነትን በማጠናከር የኢትዮጵያውያን አንድነት ለመጠበቅ እንደሚሰራ አስታውቀዋል። ይህም በቅድመና በድህረ ኢህአዴግ ጉባኤ ከሀገር ውስጥም ይሁን ከውጭ በአንዳንድ ወገኖች ሲሰነዝሩበት የነበረው አስተያየት በተቃራኒ ድርጅቱ ውስጣዊ አንድነቱን በመጠበቅ የጋራ አቋም ይዞ ጉባኤውን ስለ መደምደሙ አንድ ማሳያ ይመስለኛል።

እኔ በግሌ፤ ጓድ ዶክተር አብይ አህመድና ጓድ አቶ ደመቀ መኮንን በሊቀመንበርነትና በምክትል ሊቀመንበርነት የተመረጡበት የትናንቱ ዕለት፣ በድርጀቱ የታሪክ ድርሳን ተከትቦ መቀመጥ ያለበት ክስተት ይመስለኛል። ምክንያቱም ይህኛው የገዥው ፓርቲ ጉባኤ፤ ከምንግዜውም በላይ የህዝብን ቀልብና ስሜት የሳበና የተለያዩ ሃሳብ ወለድ መላ-ምቶችን ያስተናገደ ብዬ ስለማምን ነው—ምንም እንኳን ኢህአዴግ የራሱ የአሰራር መንገድ ያለው ቢሆንም።  

አዎ! ገዥው ፓርቲ ያደረገው የሶስት ቀናት ጉባኤ፤ መነሻውም ይሁን መድረሻው፤ ባለፉት ጊዜያት ኢህአዴግ ያስቀመጣቸው የጥልቅ ተሃድሶ ውሳኔዎች ናቸው። ‘በጥልቅ ተሃድሶው ወቅት ድርጅቱ ለህዝቡ የገባው ቃል እንደምን ተፈፀመ?’ የሚለው የግምገማ መነሻ፤ የጉባኤው ገዥ ሃሳብ እንደሚሆን ጉዳዩን ከስረ-መሰረቱ ስንከታተል ለነበርነው ሰዎች ብዙም እንግዳ ጉዳይ አልነበረም። ድርጅቱን በበጎ ጎን የሚመለከቱትም ይሁን የራሳቸው የፖለቲካ አተያይ ያላቸው ወገኖች ያራመዷቸው ሃሳቦች የኢህአዴግን ድርጅታዊ ተክለ-ቁመና ካለማወቅ የመነጩ ነበሩ። እናም ‘አይ አለማወቅ…!’ እንድንል አድርጎናል።

እንደ እውነቱ ከሆነ፤ ኢህአዴግ በውስጡ ችግር ቢፈጠርበት እንኳን በመከባበር ላይ የተመሰረተ የመገማገም፣ የሂስና የግለ ሂስ መድረኮችን የሚጠቀምና ይህንንም ባህል ዘለግ ላሉ ዓመታት ያዳበረ ድርጅት ነው። ማናቸውንም ችግሮች በብልሃትና በሰከነ መንገድ መወጣት የሚችል ልምድን ከልጅነቱ እስካሁን ድረስ እያጎበተ የመጣ ነው።

እናም ምናልባት በውስጡ ብቅ ጥልቅ እያሉ የሚታዩ እንቅፋቶች ካሉም፤ ግላዊና ቡድናዊ ምልከታዎችን ወደ ጎን በማለት፤ ለሀገርና ለህዝብ ሲሰራ የመጣ የፖለቲካ ድርጅት መሆኑን ‘የዚህም ይሁን የዚያ ወገን ሰዎች’ የሚያውቁት ይመስለኛል። እንኳንስ በአሁኑ ህዝባዊ ተደማጭነትን በተጎናፀፈበት ወቅት ቀርቶ፤ ያኔ በከፍተኛ ችግር ውስጥ በነበረበት ጊዜም ቢሆን፤ ከነ ችግሩም ቢሆን ከተግዳሮት የመውጫ ቀዳዳዎችን በአሻጋሪ አጮልቆ ሲመለከትና ውሳኔ ሲያስተላልፍ እንደነበር እናስታውሳለን።   

በጉባኤው ላይ ድርጅቱ ቀደም ሲል ባስቀመጠው አቅጣጫ መሰረት የተለያዩ አንኳር ጉዳዩችን አንስቷል። የተያዙ ዕቅዶች በምን ዓይነት ሁኔታ እንደተፈፀሙም በስፋት ተወያይቶባቸዋል። ባለፉት ስድስት ወራቶች የተከናወኑትን ሀገራዊና ዲፕሎማሲያዊ ሁኔታዎችን በጥልቀት ገምግሞም፤ ድርጅታዊ አቋሙንም አሳውቋል። ይህን ሲያደርግ ታዲያ፤ ምንም ዓይነት የሃሳብ ፍጭት አልነበረም እያልኩ አይደለም። ሲጀመር፤ የሃሳብ ፍጭት የሌለበት ፓርቲ አምባገነናዊ ብቻ ሳይሆን፤ በአንድ ሰው ፈላጭ ቆራጭነት የሚመራ ድርጅት ጭምር ነው።

ታዲያ ኢህአዴግ ውስጥ ግን እንዲህ ዓይነቱ ኢ-ዴሞክራሲያዊ አሰራር ቦታ የሌለው ከመሆኑም በላይ፤ አራቱም አባል ድርጅቶች የየራሳቸው ነፃነትና አሰራር ያላቸው ናቸው። አንዱ አባል ድርጅት ከሌላው በጎ የሚለውን ትምህርት ከመውሰድ በዘለለ፤ በሌላኛው ድርጅት የውስጥ አሰራር ጣልቃ የሚገባበት ኢህአዴጋዊ ደንብና አሰራር የለም። አባል ድርጅቶች በውስጣዊ አሰራርም ይሁን በአመዳደባቸው ነፃነትን የተላበሱ ናቸው።

ይህ ማለት ግን ‘ኢህአዴግ ውስጥ መተጋገል የለም’ እያልኩ አለመሆኑ ሊታወቅልኝ ይገባል። አዎ! በድርጅቱ ውስጥ የሃሳብ ፍጭት የሚጠበቅና በስተመጨረሻም እውነታን በያዝ ሁኔታ በአብላጫ ድምፅ የሚጠናቀቅ ነው። ‘ብዙሃን ይመውኡ’ (ብዙሃን ያሸንፋሉ) እንዲል መፅሐፉ፤ በዴሞክራሲ ሂደት ውስጥም ጥቂቶች ለብዙሃን ሃሳብ ተገዥ ይሆናሉ። ብዙሃን ያቀረቡትን ሃሳብ ባይስማሙበትም እንኳን ተቀብለውት ይወጣሉ።

በገዥው ፓርቲ አሰራር ውስጥ ተፈፃሚ እየሆነ የመጣውና የሆነውም ብሎም ወደፊትም የሚሆነው ይኸው ዋነኛ የዴሞክራሲ የብዙሃን ድምፅ (The Majority Vote) ፅንሰ-ሐሳብ አተገባበር ነው። በድጋሚ ሙሉ በሙሉ በሚባል ሁኔታ የድርጅቱ ሊቀመንበር ሆነው የተመረጡት ዶክተር አብይ አህመድ በጉባኤው መቋጫ ላይ፤ “ኢህአዴግ ከመቼውም ጊዜ በላይ አንድ ሆኖ ጉባኤውን አጠቅቋል” ያሉትም ለዚሁ ይመስለኛል።

አባል ድርጅቶችን ወይም የሚመሯቸውን ግለሰቦች ስም እየጠቀሱ፤ ‘እገሌ ቦታውን ለእገሌ ሊለቅ ነው፤ እገሌ የተሰኘው ድርጅት ያለው አቋም የተለየ ስለሆነ ጉባኤውን ያደናቅፋል…ምንትስ’ እየተባሉ በተረክነት ሲሰነዘሩ የነበሩት እሰጥ አገባዎች፤ ምንም ዓይነት መሰረት የሌላቸውና የማህበራዊ ሚዲያ ማዳመቂያ ከመሆን የዘለሉ እንዳልነበሩ በገሃድ ታይተዋል። ለዚህም በአስረጅነት ዶክተር አብይ 177 ከሆነው አጠቃላይ ጉባኤተኛ ውስጥ የ176ቱን ድምፅ ማግኘታቸው (ቀሪው አንድ ድምፅ የርሳቸው መሆኑን ልብ ይሏል!)፤ ሲወራ የነበረው የኢህአዴግን አንድነት የሚያብጠለጥለው ‘ፍየል ወዲህ፣  ቅዝምዝም ወዲያ’ እሳቤና ትክክለኛው የጉባኤው ድባብ ‘አልተገናኝቶም’ እንዲሉት ዓይነት ለመሆኑ ሁነኛ ማረጋገጫ ስለሆነ ነው።

የማህበራዊ ሚዲያው ‘አፈ-ንጉሶች’፤ እየፈጠሩ ‘የስብሰባው ተሳታፊ የሆነ ሰው የነገረኝ ነው’ በማለት “አራምባና ቆቦ” የሚረግጡ የአንድ ወገን ትንታኔ ያልሆኑ ትንታኔዎችን ሲሰጡ መመልከት፤ በሀገራችን ውስጥ የፖለቲካ ግንዛቤ፣ ሞራልና ግብረ-ገብነት ምንኛ በስሜት የታጨቀ፣ ያሻው ሁሉ ላዩ ላይ ቁጭ ብሎ እንደ ሌጣ ፈረስ የሚጋልበው አውድ መሆኑን እንድንታዘብ ሳያደርገን የቀረ አይመስለኝም። “ለምን?” ቢሉ፤ ይሰጡ የነበሩት አስተያያቶች፤ በትክክል የድርጅቱን ነባራዊ ሁኔታ ካለመገንዘብ፣ በውስጣዊ ፍላጎት ግፊትና አመክንዩ አልባ መላ-ምታዊ እሳቤዎችን ተንተርሰው የሚሰነዘሩ ስለነበሩ ነው።

እናም እነዚህ ወገኖች ሃሳባቸውን በነፃነት የመግለፅ መብታቸው እንደተጠቀ ሆኖ፤ ስለ ኢህአዴግም ሆነ ስለሚገልፁት ማናቸውም ጉዳዩች፤ ከግንዛቤ እጥረት ወይም ከአላዋቂነት የሚያነሷቸው ጭብጦች፤ ‘ምን ያህል በዕውቀትና በተጨባጭ እውነታ ላይ የተመረኮዙ ናቸው?፣ ምን ያህልስ ከመንጋ አስተሳሰብ፣ ከአሉባልታና ከጥላቻ የፀዱ ናቸው?’ ብለው ማመዛዘን ያለባቸው ይመስለኛል። ከሁሉም በላይ ደግሞ፤ ‘ጭብጦቹ ምን ያህል ኢትዮጵያዊ አንድነትን ያጠናክራሉ?’ የሚል ሃሳብን የማይሰርቅ ሚዛን ላይ በማስቀመጥ፤ ሃሳቦቹ ያላቸውን ኢትዮጵያዊ ፋይዳ በልኬታቸው በመመዘን ሊገልጿቸው ይገባል እላለሁ። ይህም በትንሹ፤ እንደ እኔ ዓይነቱ ተራ ገለልተኛ ወገን ‘አይ አለማወቅ…!’ ብሎ እንዳይታዘባቸው ያደርጋል። በትልቁ ደግሞ፤ መላው የሀገራችን ህዝብ በትግሉ ያመጣውንና ‘መፃዒ ህይወቴን ይለውጥልኛል’ በሚል እሳቤ እንደ ዓይኑ ብሌን የሚመለከተውን ለውጥ በማገዝ በትክክለኛው ጎዳና መጓዝ እንዲችል ድጋፍ እንዲሰጡ ያስችላቸዋል። ሰናይ ጊዜ።    

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy