Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

የ‘ትጥቅ ፍታ!’—‘አልፈታም!’ ነገር…

1 4,585

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

የ‘ትጥቅ ፍታ!’—‘አልፈታም!’ ነገር…

                                                   እምአዕላፍ ህሩይ

 

…“የእብድ ገላጋይ ድንጋይ ያቀብላል” እንዲሉ አበው፤ የተፈጠሩትን የተቃርኖ ሃሳቦች ሁለቱንም ወገኖች ሊያስማማ፣ ሀገርንና ህዝብን ሊጠቅም ወደሚችል ወርቃማው አማካይ ቦታ (The Golden Mean) አምጥቶ አስታራቂ ሃሳብን ማቅረብ እንጂ፤ በስሜታዊነት መንግስትን ወይም ኦነግን ‘ፍለጠው፣ ቁረጠው!’ እያልን አባባሽና እሳት ጫሪ…”

 

ሰሞኑን አንድ እሰጥ-አገባ የትስሰር ድራችንን አጨናንቆት ሰንብቷል። ከዚህም…ከዚያም የነገር አንካሴዎች ሲወነጨፉ ተመልክተናል። እሰጥ-አገባውን እየሰማን ያለነው፤ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ በውጭ ሀገር ትጥቅ አንግበውም ይሁን በሰላማዊ መንገድ ለሚንቀሳቀሱ እንዲሁም በሀገር ውስጥ ለሚገኙ ሁሉም ተፎካካሪ ፓርቲዎች ያቀረቡትን የሰላም ጥሪ ተከትሎ፤ የትጥቅ ትግል ሲያደርግ ከነበረበት የኤርትራ በረሃዎች ወደ ሀገር ቤት ሰላማዊ ትግል ለማድረግ የመጣው የኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ) /ከእንግዲህ በኋላም በአህፅሮተ ቃል “ኦነግ” እያልኩ በምጠራው ኃይል/ እና በኢፌዴሪ መንግስት መካከል ነው።

ታዲያ ይህ በሰላማዊ ጥሪ አቅራቢውና ጥሪውን ተቀብሎ ወደ ሀገር ውስጥ በገባው ኃይል መካከል የምናደምጠው የሚዲያ መመላለስ፤ በአብዛኛው የሀገራችን ህዝብ ውስጥ ጥሩ ስሜት የፈጠረ አይደለም። ብዙዎች ‘ከተጀመረው የፍቅር፣ የሰላም፣ የይቅርታና የአንድነት እንዲሁም በመደመር መንፈስ በጠረጴዛ ዙሪያ ችግሮችን የመፍታት የ21ኛው ክፍለ ዘመን የሰለጠነ የመግባቢያ ቋንቋ ወጥተን፤ ዳግም ወደ ተሳሳተውና ጊዜው ወዳለፈበት የጠብ-መንጃ አፈሙዝ ንግግር እንገባ ይሆን?’ ሲሉ ስጋታቸውን ይገልፃሉ። ይህን ስጋት የዚህ ፅሑፍ አቅራቢም እንደ ዜጋ የሚጋራው ነው።   

የስጋቱ መነሻ፤ በአንድ በኩል፤ የኦነግ መሪ የሆኑት አቦ ዳውድ ኢብሳ “በስምምነታችን ውስጥ ትጥቅ ስለመፍታት የተነሳ ነገር የለም። ስለዚህ ትጥቅ አንፈታም፤ ትጥቅ የያዘው አካል እያለ እኛ ለምን ትጥቅ እንፈታለን?” የሚል ሃሳብ በመገናኛ ብዙሃን ማራመዳቸው ነው። በሌላ በኩል መንግስትም፤ ‘ትጥቅን የመፍታት ሁኔታ በስምምነቱ ላይ ያልተነሳው ለሰላማዊ ትግል ትጥቅ እንደማያስፈልግ ግልፅ ስለሆነ ነው፤ በአንድ ሀገር ውስጥ ሁለት መንግስት ሊኖር አይችልም፤ ኦነግ ትጥቁን መፍታት ይኖርበታል፤ የያዘውንም አቋም ያስተካክላል ብለን ተስፋ እናደርጋለን፤ ሆኖም የህግ የበላይነትን ለማስከበር ሲባል መከላከያ ሰራዊቱ በህጉ መሰረት ትጥቅ የማስፈታት ስራን ያከናውናል’ የሚል መግለጫ አውጥቷል።

ርግጥ እነዚህ ሁለት የሚደመሩ ሳይሆን የሚቃረኑ ሃሳቦች ብዙዎቻችንን ማሳሰባቸውና መነጋገሪያችንም ሆነው መዝለቃቸው የሚደንቅ ጉዳይ አይመስለኝም። ምክንያቱም፤ ከሁሉም በላይ፤ ስጋታችን እውን ሆኖ፤ ላለፉት ስድስት ወራት ገደማ ያገኘነው አንፃራዊ ሰላምና ሁሉን አቀፍ የተስፋ ፀዳላዊ ብርሃን እንዳይደበዝዝ ካለን ፍላጎት የተነሳ ስለሆነ ነው። ምንም እንኳን ቀደም ሲል የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ከቅን ሀገራዊ እሳቤ በመነሳት፤ “ኦነግ ትጥቅ አልፈታም ማለቱ ምናልባት የአፍ ወለምታ እንዳይሆን ማረጋገጥ ያስፈልጋል፤ በቅርቡ ስለምናገኛቸው በመነጋገር ችግሩን እንፈታለን፤ የሚያሳስብ ነገር አይደለም” በማለት ለመገናኛ ብዙሃን ቢገልፁም፤ ከርሳቸው ገለፃ እንዲሁም መንግስት በይፋ ከሰጠው መግለጫ በኋላ፤ የኦነግ መሪ ኦቦ ዳውድ ኢብሳ፤ “ትጥቅ አንፈታም” በማለት ቀደም ሲል የተናገሩትን ሃሳብ አጠናክረዋል።

ይህ የ‘ትጥቅ ፍታ!’—‘አልፈታም!’ ነገርን ተመርኩዞ አንዳንድ ወገኖች በቅንነት፣ ሌሎች ደግሞ፤ ከራሳቸው ፖለቲካዊ ፍላጎት በመነሳት ‘እንዲህ ቢሆን ጥሩ ነው’ የሚል ሃሳቦችን እየሰነዘሩ ነው። ሆኖም፤ በምንገኝበት የፍቅርና የይቅርታ እንዲሁም የመደመር ዘመን ‘በለውና ውቃው’ ከሚል ነፋስ ጋር አብረን መንፈስ የለብንም። “የእብድ ገላጋይ ድንጋይ  ያቀብላል” እንዲሉ አበው፤ የተፈጠሩትን የተቃርኖ ሃሳቦች ሁለቱንም ወገኖች ሊያስማማ፣ ሀገርንና ህዝብን ሊጠቅም ወደሚችል ወርቃማው አማካይ ቦታ ላይ (The Golden Mean) አምጥቶ አስታራቂ ሃሳብን ማቅረብ እንጂ፤ በስሜታዊነት መንግስትን ወይም ኦነግን ‘ፍለጠው፣ ቁረጠው!’ እያልን አባባሽና እሳት ጫሪ መሆን ተገቢ አይመስለኝም። ነገሮችን ከውጤታቸው አኳያ እየመዘኑ መመልከት የአንድ ጥሩ ዜጋ ባህርይ ነው ብዬ አስባለሁ።

 

ታዲያ ይህን የምለው እዚህ ሀገር ውስጥ ተነጋግረን መፍታት የምንችላቸው ጉዳዩች የአንድም ሰው ህይወት ማጥፋት የለባቸውም ከሚል ፅኑ እምነቴ በመነሳት ነው። ርግጥ ለሀገሩ ሰላም የሚያስብና ‘የነገሮች መፍቻ ሁሉ ጠብ-መንጃ ነው’ የሚል ዝማሬን የማያቀነቅን ማንኛውም ዜጋ፤ ሁሌም ከሃይል ርምጃ በፊት ሰላማዊውን የንግግር አውድ ማሰብ ይኖርበታል። እናም እኔም ሆንኩ ‘የሰላም ጠቀሜታን እገነዘባለሁ’ የሚል ማንኛውም ወገን፤ መቼም ቢሆን ጠብ-መንጃ ሊናፍቀው አይገባም። አዎ! ይህን መሰሉ ዜጋ በሚያገኘው አጋጣሚ ሁሉ መመስከር ያለበት፤ ስለ ሰላም ጣፋጭነትና ስለ ጠብ-መንጃ አፈሙዝ እሬት…እሬት ባይነት ነው። የጠብ-መንጃ ፍቅር ባፍንጫችን ይወጣ ዘንድ ለሰላም መትጋት ይኖርብናል።

ከስሙ እንደምንረዳው ጠብ- መንጃ፤ የጠብ ማስፈፀሚያ ወይም ማካሄጃ እንጂ፤ የፍቅር አሊያም የመደመሪያ መሳሪያ አይደለም። በጠብ-መንጃ አፈሙዝ ውስጥ የሰላም መንገዶች ከቶም ሊኖሩ አይችሉም። ቢኖሩም፤ በሃይል ቃታ አማካኝነት ተደፍጥጠው መጥፋታቸው አይቀርም። ርግጥ የሃይል ቃታ የትኛውንም ወገን ዋጋ ማስከፈሉ አይቀሬ ነው። እናም በዚህ ስልጡን ዘመን፤ መነጋገርን የመሰለ ፍቱን መድሃኒት እያለልን፤ ስለምን ከጠብ መንጃ አፈሙዝ ጋር በፍቅር እንወድቃለን?፣ ስለምንስ ሰዋዊውን ፍቅርንና ይቅርታን ረግጠን ለአጥፊያችን የጠብ-መንጃ ብርታት እንንበረከካለን?፣ ስለምን ጊዜ ባለፈበት አስተሳሰብ ውስጥ ሆነን እርስ በርሳችን ለመጨራረስ እንዛዛታለን?—ወገኔ ሆይ! ይህ ጠብ-መንጃን የሚጠየፈው የአዲሱ ትውልድ ዘመን የሁላችንም ነው። ዘመኑ፤ የተወሰኑ አካላት ወይም ቡድኖች ብቻ አይደለም። ሊሆንም አይችልም። ያለንበት የለውጥ ሂደት በዜጎቻችን ህይወት፣ ደምና አጥንት ፍላፃ የመጣና የተገነባ ነው።

በአሁኑ ወቅት ተጨማሪ ሰላምና ፍቅር እንጂ፤ ተጨማሪ መስዋዕትነት፣ አካል መጉደልና መፈናቀል አያስፈልገንም። አያሻንም። መንግስትም የልማትና የዴሞክራሲ ስራውን ትቶ፤ ሁሌም የተቀደደውን ቦታ እየሰፋ የሚኖር ባተሌ አካል ልናደርገው አይገባም። እናም ለጠብ-መንጃ አፈሙዝ ብርታት መረታት ማለት፤ እነዚያን የለውጡን ቀንዲሎች መዘንጋት መሆኑን ለአፍታም ከአዕምሯችን ጓዳ ሊወጣ አይገባም። እናም እኔ በበኩሌ፤ የጠብ-መንጃ አፈሙዝ የማይናፍቀኝ ይህን ስለማስብ ነው። እናንተስ?

ያም ሆኖ፤ ከናፍቆተ- ጠብ-መንጃ ለመውጣት እሰጥ- አገባውን ከኦነግም ይሁን ከመንግስት አንፃር በየልኬታው ሚዛናዊ ሆኖ መመልከት ይገባል። ኦነግ፤ ከኤርትራ ወደ ሀገር ውስጥ በትግራይ-ዛላንበሳ በኩል ሲገባ፤ አንድ ሺህ 300 ታጣቂዎቹን ትጥቃቸውን አስፈትቶ ነው። ያ ባይሆን ኖሮ ወይም እንዲያ ዓይነት ስምምነት ቢኖረው ኖሮ፤ ሰራዊቱን ከነ ጠብ-መንጃው ወደ ሀገር ውስጥ ሲያስገባ በተመለከትነው ነበር። ያ ግን አልሆነም። የሆነው ነገር፤  ሰራዊቱ የድርጅቱን ባንዴራ ይዞ ባዶ እጁን ወደ ሀገር ቤት መግባቱን ነው። ይህም ኦነግ ወደ ሀገር ቤት የገባው፤ ተተንትኖ የተደራጀ ፖሊሲዎቹን፣ ስትራቴጂዎቹንና ስልቶቹን ‘እወክለዋለሁ’ ለሚለው ህዝብ በማስረዳት እየሰፋ ባለው ሰላማዊ የፖለቲካ ምህዳር ውስጥ ተወዳድሮ ለማሸነፍ የመጣ መሆኑን የሚያሳይ ይመስለኛል። ሌላ ምንም ዓይነት ትርጓሜ ሊሰጠው የሚችል አይደለም።

ታዲያ በሰላማዊ መንገድ ለመታገል ትጥቁን ፈትቶ ሀገር ውስጥ የገባ አካል፤ እዚህም…እዚያም በስሙ የታጠቁ አካላትን ትጥቅ ማስፈታት እንዳለበት ሊነገረው የሚገባ አይመስለኝም። ምክንያቱም ኦነግ ትጥቁን በኤርትራ በረሃዎች ውስጥ ጥሎ ወይም አስረክቦ የመጣው፤ የቀረበለትን የሰላም ጥሪ ተቀብሎ እንጂ፤ እዚህ ሀገር ቤት ውስጥ አዲስ የጦርነት አውድማ ከፍቶ የረሳነውን የጦርነት ቋያ እሳት ሊያስታውሰን ስላልሆነ ነው።

እናም በእኔ እምነት፤ ኦነግ እዚህ ሀገር ውስጥ ማራመድ ያለበት ትግል፤ የጠነከረ ሰላማዊ ሃሳብን እንጂ፤ ጠብ-መንጃን ምርኩዝ ያደረገና ለማንም የማይጠቅም አስተሳሰብን አይመስለኝም። አዎ! ትናንት ዛሬ ባለመሆኑም፤ የፖለቲካ ድርጅቱ፤ እንደ ትናንቱ ሁሉ ዛሬም በትጥቅ ትግል ማመን ይገባዋል ብዬ አላስብም። እንዳልኩት ትጥቁ መሆን ያለበት ዓላማውን የሚያሳካበት የተጠናከረና ጥልቀት ያለው ፖለቲካዊ ሃሳብ ብቻ ነው። አሁን ባለንበት ዘመን በትጥቅ ትግል ምንም መፈየድ የሚቻል አይመስለኝም—ጊዜው ያለፈበትና ዘመኑን እንዲሁም ትውልዱን የማይመጥን አስተሳስብ ነውና። ይህ የግል ምልከታዬ፤ እንኳንስ በትጥቅ ትግል ውስጥ ከ40 ዓመት በላይ የሚጠጋ ዕድሜን ላስቆጠረው የሀገሬ ድርጅት ኦነግ ቀርቶ፤ ለማንም ቢሆን ግልፅ የሚሆን ይመስለኛል—የፖለቲካ “ሁሁ” ነውና።

እናም ኦነግ ለሀገሩና ለህዝቡ እንደሚያስብ አንድ የፖለቲካ ድርጅት፤ ከሁሉም በላይ ለሰላም ቅድሚያ በመስጠት በኦሮሚያ ክልል ውስጥ በስሙ የሚንቀሳቀሱ ታጣቂዎችን ትጥቅ ማስፈታት አለበት ብዬ አስባለሁ። ይህን የምለው ታዲያ፤ በድርጅቱ ሳቢያ የአንድም ወገን ደም መፍሰስ እንደሌለበት በጥብቅ ስለማምን ነው። ደም በመቃባት፤ የዜጎችን ህይወት ከመቅጠፍና የተጀመረውን ለውጥ ከማደናቀፍ በስተቀር የምናገኘው ምንም ትርፍ የለም። እናም ይህ እንዳይሆን ድርጅቱ፤ ሞራላዊ፣ ሀገራዊና ህዝባዊ ኃላፊነት ያለበት ይመስለኛል። ኦነግ የሰላም ጥሪን ተቀብሎ እንደመጣው ሁሉ፤ ችግሮች ቢኖሩም እንኳን ስልጡንና ሁሉንም አሸናፊ (win-win) የሚያደርግ የሰላም መፍትሔን በመከተልና ለህግ ልዕልና ቅድሚያ በመስጠት እንዲሁም የያዘውን “ትጥቅ አንፈታም” የሚል አቋሙን ዳግም በመፈተሽ፤ ነገሮችን በጠረጴዛ ዙሪያ ተቀምጦ በሰላማዊ መንገድ መፍታት ይጠበቅበታል እላለሁ።

በእኔ እምነት፤ ድርጅቱ የራሱን አባላት ትጥቅ ማስፈታቱ ሁለት ጠቀሜታዎችን ያስገኙለታል ብዬ አስባለሁ። አንደኛው፤ በኦሮሚያ ክልል በታጣቂዎች አማካኝነት ግጭት በተፈጠረ ቁጥር ስሙ ሲነሳ፤ “እጄ የለበትም፤ ፈፃሚዎቹንም አላውቃቸውም” በማለት የሚሰጠው አስተያየት፤ ስጋና ደም ለብሶ እንዲሁም ትክክለኛ ሆኖ ህዝቡ እንዲያይለት ዕድል ይሰጠዋል። ሁለተኛው ደግሞ፤ ከኤርትራ በረሃዎች የመጣበትን ሰላማዊ ትግል የማካሄድ ፍላጎቱን በአጠቃላይ ለኢትዮጵያ ህዝብ፤ በተለይ ደግሞ ለሚታገልለትና ሁሌም ሰላምን ለሚሻው የኦሮሞ ህዝብ የሚያረጋግጥበት አንድ መንገድ ሊሆን ይችላል ብዬ እገምታለሁ። እናም ትጥቅ መፍታቱን ቢያንስ ከእነዚህ ጠቀሜታዎች አኳያ ሊመዝናቸው ይገባል እላለሁ። እኔ በበኩሌ፤ ኦነግ የጠብ-መንጃ አፈሙዝ አይናፍቀኝም ወደሚል ሰላማዊ አውድ ይመጣል ብዬ አምናለሁ—ለሰላምና ለህዝብ ዋጋ ይሰጣል ብዬ አምናለሁና።  

መንግስትም ቢሆን፤ ስለ ሰላም ሲል እስካሁን እያደረገ እንደመጣው ሁሉ፤ ጉዳዩን በትዕግስትና በአርቆ አሳቢነት መያዝ እንዳለበት ይሰማኛል። እንደ ሁል ጊዜው፤ ቀዳሚ ምርጫውን ለውይይት መስጠት አለበት። ርግጥ ዶክተር አብይ በቅርቡ “…ከኦነግ ጋር እንወያያለን” ማለታቸው የዚህ አባባሌ አስረጅ ነው። ውይይቱ፤ የሰላም ኣራጮች ሁሉ እስኪሟጠጡ ድረስ መከናወን ይኖርበታል እላለሁ። የሰው ህይወት እንዳያልፍም፤ የህዝብን ሰላምና የመኖር ዋስትናን በሚያረጋግጥ መልኩ፤ መንግስት የሚችለውን ያህል መንገድ ሁሉ ርቆ መጓዝ ይኖርበታል ብዬ አስባለሁ።

እዚህ ላይ ግን፤ መንግስት በተለያዩ የኦሮሚያ አካባቢዎች በኦነግ ስም የሚንቀሳቀሱ ታጣቂዎች ለዜጎች መሞት፣ አካል መጉደልና መፈናቀል ምክንያት መሆናቸውን መግለፁን ዘንግቼው አለመሆኑ ሊታወቅልኝ ይገባል። ለእነዚያ ወገኖቼ ያለኝ ሃዘኔታም እጥፍ ድርብ ነው። መቼም ከውስጤ የሚወጣ አይደለም። ዳሩ ግን እነዚያ አሳዛኝ ድርጊቶች፤ ዳግም እንዳይከሰቱም የዘወትር ፀሎቴ ከመሆኑም በላይ መንግስት ህዝቡ የጣለበትን ኃላፊነትና ግዴታ እንዲወጣም እጠይቃለሁ። ርግጥ በዶክተር አብይ የሚመራው የለውጥና የሰላም አመራር፤ የዜጎቹን ሰላምና ደህንነት የማስጠበቅ ኃላፊነትና ግዴታ እንዳለበት ከመንም የሚሰወር እውነታ አይደለም። መንግስት፤ በሀገሩ ውስጥ የህግ የበላይነትን የማስከበር ተግባሩ፤ አማራጭ የሌለውና ለድርድር የማይቀርብ ጉዳይ መሆኑንም አላጣሁትም። ያም ሆኖ ግን፤ የህዝቡን ሰላም እያስጠበቀ፤ የሰላም አማራጮችን ሁሉ አሟጦ መጠቀም እንደሚኖርበትም አምናለሁ።

የዚህ ፅሑፍ አቅራቢ፤ ስለ ሰላም፣ ስለ ፍቅርና ስለ አንድነት እንጂ፤ አንድም ጊዜ ቢሆን የጦርነትን ጠቃሚነት ለማንም ነግሬ ወይም ለማስረዳት አስቤ አላውቅም። እንደ ማህበራዊ ሚዲያ ነገር የጠማቸው ባለሟሎች፤ “ጀግናዬ በለው!” በሚል ቀረርቶ፤ መንግስትንና አንድን ትንሽ ታጣቂ ቡድን ላወዳድርም አልፈልግም። ምክንያቱም ውድድሩ፤ ሚዛን የሚደፋ ካለመሆኑም በላይ፤ በሰላማዊ አውድ የሚፈቱ ጉዳዩች የአንድንም ዜጋ ህይወት እንዳይቀጠፉ ስለማልሻ ነው። ያም ሆኖ፤ ምንም እንኳን መንግስት ከትዕግስተኝነት ባለፈ በጥቂት ጊዜ ውስጥ ታጣቂዎችን አደብ የማስገዛት አቅምና ብቃት እንዳለው ባውቅም፤ ሁሉንም አካላት በአባትነት አቻችሎ እንደሚመራ ተቋም፤ ዛሬም እንደ ትናንቱ፤ ከትዕግስቱ ጨመር፣ ከሃይል ርምጃው ቀነስ በማድረግ መንቀሳቀስ አለበት ብዬ አምናለሁ። ይህም የትኛውም ወገን ከደም መፋሰስ እንዲድን ያደርገዋል። በተለይም፤ ይህም መሰሉ ትዕግስትን የተላበሰ ተግባር፤ ሁሌም የግጭቶች ሰለባ የሚሆነው ምስኪኑን የሀገራችንን ህዝብ መታደጉ አሌ አይባልም።

ርግጥ ይህ ቀናዒ ሃሳቤ እኔ ስለተመኘሁት ብቻ እውን ሊሆን የሚችል አይደለም። ለሰላም ዝግጁ የሆነና የጠብ- መንጃ አፈሙዝ አይናፍቀኝም የሚል አካል ከሌለ፤ በቃ! ሃሳቤ ሃሳብ ብቻ ሆኖ ይቀራል። እናም ኦነግ በስሙ የሚንቀሳቀሱ ታጣቂዎች በዜጎች ላይ የሚያደርሱትን ሰቆቃና እንግልት ለማስቆም ለሀገሩና ለህዝቡ ሰላም ሲል በቀናነት ተባባሪ ሆኖ መገኘት ያለበት ይመስለኛል። እነዚያ ታጣቂዎች በአንዳንድ አካባቢዎች ችግር በፈጠሩ ቁጥር ስሙ ሲነሳ፤ “ከደሙ ንፁህ ነኝ አላውቃቸውም” የሚለውን ምላሹን ዜጎች በይሁንታ እንዲቀበሉትና መንግስትም ከኦነግ ውጭ ያሉ ፀረ ሰላም ኃይሎችን ከህዝቡ ጋር ሆኖ እንዲታገላቸው፤ ‘የእኔ ናቸው’ የሚላቸውን ታጣቂዎች ትጥቅ በማስፈታት ለሰላም ያለውን ቁርጠኝነት ማሳየት እንዳለበት ይሰማኛል። ምክንያቱም ይህ የድርጅቱ ተግባር፤ ሀገራችን ውስጥ የህግ የበላይነት ይከበር ዘንድ የድርሻውን እንዲወጣ ያስችለዋል ብዬ ስለማስብ ነው። ከዚህ ውጭ በመገናኛ ብዙሃንና በማሀበራዊ ሚዲያዎች ላይ የሚካሄዱ እንካ ሰላንቲያዎች ትርጉም ይኖራቸዋል በዬ አላምንም።  

ታዲያ ሁሌም ሰላማዊ ዕድል ሊያመልጠን አይገባም። ወደ ግጭትና ጦርነት የሚወስዱንና አረንቋ መንገዶች በሰላም አስፓልት ልንቀይራቸው ያለንበት ስለጡን ዘመን ያስገድደናል። አባጣ ጎርባጣ የሌለበትን የሰላም አስፓልት፤ በመነጋጋር፣ መቻቻል፣ ሰጥቶ መቀበል እንዲሁም በፍቅር በመደመር ይበልጥ ውብ ማድረግ የሁሉም ዜጋ የቤት ስራ ነው። ይህ የቤት ስራ፤ ለመንግስትም፣ ለኦነግም፣ ለተራ ዜጋው ለእኔም፣ ለእርሶም፣ ለአንቺም፣ ለአንተም…ወዘተርፈ. የተቸረን የእኩል ዕድል መንገድ ነው። እናም ይህን የሰላምና የእኩልነት ዕድል፤ የትኛውም ወገን በህዝባዊ የኃላፊነት መንፈስ ሳይጠቀምበት ቢቀርና ወደ ማይፈለግ የኃይል ርምጃ ቢገባ፤ የምንፀፀተው ሁላችንንም መሆናችንን ማወቅ አለብን። ስለሆነም ሁላችንም ጠብ-መንጃ እንደማይናፈቀን በተግባራችንና በተባባሪነታችን ልናሳይ የምንችልበት ወቅት አሁን መሆኑን ነጋሪ የሚያሻን አይመስለኝም። ግና ይህ ሳይሆን ቀርቶ፤ ነገሮች ሁሉ ከእጃችን ካመለጡን በኋላ፤ እንደለመድነው “የፈሰሰ ውሃ አይታፈስ” የሚል ተረት ብናወራ፤ በራሳችን ላይ እንደተሳለቅን መቁጠር ይኖርብናል እላለሁ። ሰናይ ጊዜ።    

 

 

   

 

  1. Tess says

    This is a natural, not biased and neutral Article based on genuine comments. In addition, the article is pro-people and pro our country. I like it so much!! I appreciate the way the writer tries to address the issue!

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy