Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

የአሜሪካውን ድል በፍራንክፈርትም?

0 6,522

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

የአሜሪካውን ድል በፍራንክፈርትም?

                                                   እምአዕላፍ ህሩይ

አንድ አባት ነበር—ቀርከሃ ነጋዴ። ሁል ጊዜ ከስሩ የማይጠፋውን ልጁን “ዞር በል፣ ቀርከሃ ይመታሃል” እያለ ከአጠገቡ ገለል እንዲል ይነግረው ነበር። ልጁም፤ “አባዬ ቀርከሃ እኮ ውስጡ ባዶ ስለሆነ ቢመታኝም አያመኝም” እያለ ይመልስለታል። አባትየውም፤ ልጁ በቀርከሃ እንዳይመታ በማሰብ፤ ከአካባቢው ዞር የሚልበትን መላ መዘየድ ጀመረ። አውጥቶ…አውርዶ ያገኘው ነገር ቢኖር፤ ልጁ በቀርከሃ እንዲመታ ማድረግ ብቻ ነበር። እናም በመጀመሪያው ቀን፤ ሁለት ቀርከሃዎችን በአንድነት አስሮ ልጁ እግር ላይ ቀስ ብሎ እንዲያርፍ አደረገ። ልጁም በትንሹ አመመው። ሆኖም “አባዬ ቀርከሃው እግሬ ላይ ቢወድቅም ጣቴን አላሳመመኝም” አለው።

በሁለተኛው ቀን፤ አባትዬው አራት ቀርከሃዎችን በአንድነት አስሮ አስቀመጠና ልጁ ጠጋ ሲለው፤ ቀስ ብሎ እግሩ ላይ ጣል አደረገው። ልጅየውም፤ “እንዴ አባዬ ቀርከሃ እንደዚህ በሃይል ያማል እንዴ?” ሲል ይጠይቀዋል። አባትም፤ “እንዴታ ልጄ! ቀደም ሲል ነግሬህ ነበር እኮ!” ይለዋል። ልጁ፤ አሁን በዛ ብለው የታሰሩ ቀርከሃዎችን መፍራት ጀመረ። በሶስተኛው ቀን፤ አባትዬው ስድስት ቀርከሃዎችን በአንድነት አስሮ አስቀመጠ። ልጅየውም እንደለመደው ወደ አባቱ ጠጋ አለ። አባትም ልጁ እንዳይጎዳ በማሰብ፤ ቀስ ብሎ እግሩ ላይ የታሰሩትን ቀርከሃዎች ወረወራቸው። ልጁም ቀርከሃዎቹ ብዙ ስለሆኑ በጣም አሳመሙት። እሪ ብሎም አለቀሰ። ጮኸ። ዳግመኛም ወደ ቀርክሃ ነጋዴ አባቱ ጠጋ ብሎ መቆም እጅጉን ፈራ። አባቱ ጋ ሲሄድም፤ በርቀት ሆኖ ሊያነጋግረው እንጂ፤ እንደ በፊቱ አጠገቡ ሆኖ ላያስቸግረው ቃል ገባ ይባላል።…

ይህን የቀርከሃ ነጋዴና የልጁን ተረት ያነሳሁት በምክንያት ነው። ነጠላና ብዙ ስንሆን ለእኛ የሚሰማን ነገር፤ የተለያየ መሆኑን ነው ለማሳየት ነው— ተረቱን ‘እንካችሁ’ ያልኩት። ምንም የሌለው ባዶ ነገር ለብቻው ሲሆን፤ የማይፈራ፣ የማይከበርና አድማጭም የሌለው መሆኑ ግልፅ ነው። እንደ ቀርከሃው ባዶ የሆነ ነገር በአንድነት ልጥ ሲታሰር፤ የሚፈራ፣ የሚከበርና የሚደመጥ ይሆናል። አንድነት ሃይል መሆኑ በገሃድ ይገለፃል። “ድር ቢያብር፣ አንበሳ ያስር” የሚለው ብሂል ይገዝፋል። “ሃምሳ ሎሚ ለአንድ ሰው ሸክሙ፣ ለሃምሳ ሰው ግን ጌጡ ነው” የሚለው ይትብሃልም ነፍስ ዘርቶ ይታያል። በአንድነት ውስጥ እኛነታችን ክብር፣ ግርማና ሞገስ ያገኛል። በነጠላ “እኔነት” ያለገኘነውን ሞገስ በብዙው “እኛነታችን” እንጎናፀፈዋለን። ይህ አንድነታችንም፤ ነገአችን እንደ ጠራ ሰማይ ብሩህ እንዲሆን ያደርገዋል።

የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ፤ የፈረንሳይ ፕሬዚዳንትና የጀርመኗ መራሄ መንግስት አንጌላ መርክል ባደረጉላቸው ጥሪ መሰረት ዛሬ ወደ አውሮፓ ተጉዘዋል። የመጀመሪያውን የአውሮፓ ጉብኝታቸውንም ዛሬ ጧት በፈረንሳይ መዲና ፓሪስ ከተማ ጀምረዋል። በውቢቷ ፓሪስ ከተማ፤ ከሀገሪቱ ፕሬዚዳንት ኢማኑኤል ማክሮን ጋር በሁለትዮሽ፣ በቀጣናዊና በዓለም አቀፋዊ ጉዳዩች ዙሪያ ይመክራሉ። የተለያዩ ስምምነቶችንም ያደርጋሉ። በጀርመን በሚያደርጉት ጉብኝትም፤ ከሀገሪቱ መራሄ መንግስት ወይም ቻንስለር አንጌላ መርክል ጋር ተመሳሳይ ውይይትና ስምምነቶችን እንደሚያደርጉ ይጠበቃል። በጀርመኗ ፍራንክፈርት ከተማ ከ20 ሺህ ለሚበልጡ ኢትዮጵያዊያንና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን ንግግር ያደርጋሉ፤ ይወያያሉ—“አንድ ሆነን እንነሳ፣ ነገን እንገንባ” በሚል መሪ ቃል።

ከተለያዩ የአውሮፓ ሀገሮች የሚወከሉ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጋር የሚያደርጉት ውይይት፤ ስለ ሀገራቸው መፃዒ ዕጣ ፈንታ፣ ስለ መንግስታቸው ዕቅድና ክንውን እንዲሁም አሁን በተጀመረው የለውጥ እንቅስቃሴ ውስጥ ስለሚኖራቸው አስተዋጽኦ፤ ያላቸውን ጥያቄዎች፣ ፍላጎታቸውንና ራዕያቸውን የሚያቀርቡበት እንዲሁም ፊት ለፊት ሃሳብ የሚለዋወጡበት ይሆናል። ዶክተር አብይ አህመድ ለሁሉም የአውሮፓ ቆንስላዎች አማካይ በሆነችውና በርካታ ኢትዮጵያዊንና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን በሚገኙባት በፍራንክፈርት ከተማ፤ “አንድ ሆነን እንነሳ፣ ነገን እንገንባ” በሚል ቃል ከዳያስፖራው ጋር የሚያደርጉት ውይይት፤ በኢትዮጵያዊ አንድነት መንፈስ ነገን ብሩህ ሊያደርግ ይችላል ተብሎ የታመነበት ነው።

ዶክተር አብይ አህመድ ቀደም ሲል በአሜሪካ ከዳያስፖራው ጋር “ግንቡን እናፍርስ፣ ድልድዩን እንገንባ” በሚል መሪ ቃል ከኒውዮርክ እስከ ሚኒሶታ ባደረጉት ጉብኝት፤ በውጭ የሚኖረውን ኢትዮጵያዊ የሀገሩ የለውጥ ሂደት ባለቤት እንዲሆን እንዳደረጉትና በጉብኝታቸውንም በስኬት እንደከወኑት ሁሉ፤ ዛሬም አንድነትንና ነገን በሚያመላክት መንፈስ በአውሮፓ ከሚገኙት ዳያስፖራዎች ጋር ተመሳሳይ ድል ያመጡ ይሆን? የሚል ጥያቄ የሚያነሱ አካላት በርካታ ናቸው። እነዚህ አካላት፤ በሁሉም ቦታዎች ያሉት ዜጎቻችን (ለዚያውም ኢትዮጵያዊ) መሆናቸውን ከግምት ውስጥ ያስገቡ አይመስሉም። ኢትዮጵያዊ የትም ይሁን የት፤ ያው ኢትዮጵያዊ ነው። ሊቀየር አይችልም። ቅዱሱ መፅሐፍ፤ “ነብር ዥንጉርጉርነቱን እንደማይቀይረው ሁሉ ኢትዮጵያዊም ማንነቱን አይቀይርም” እንዳለው፤ የሀገሬ ዜጋ አውሮፓም ይሁን አሜሪካ፣ አውስትራሊያም ይሁን አንታርቲካ፣ ኤሽያም ይሁን አፍሪካ…ወይም ሌላ ስፍራ፤ ኢትዮጵያዊ ባህሪውንና ስነ ልቦናውን አይቀይርም። ለዚህም ነው—በአንድ ወቅት ዶክተር አብይ “የትም ሀገር ብትሄዱ፣ ኢትዮጵያን ይዛችኋት ነው የምትዞሩት” በማለት የተናገሩት። ይህም ኢትዮጵያዊነት የቦታ ርቀት የማይገድበውና በውስጡም የወል ስነ ልቦናዊ ባህሪን የተላበሰ የተቆራኘ ማንነት መገለጫ መሆኑን የሚያመላክት ይመስለኛል።

የአውሮፓው የጠቅላይ ሚኒስትራችን ጉብኝት፤ በዳያስፖራው ሀገራዊ አንድነት ላይ የሚያጠነጥንና ነገን ብሩህ ለማድረግ ዜጎች በጋራ መሰለፍ እንደሚገባቸው ለማስረዳት ያለመ ነው። ርግጥ በውጭ የሚገኘው ኢትዮጵያዊ አንድነትን በሚገባ የሚገነዘብ ይመስለኛል። ተነጥሎና ከሀገሩ ተለይቶ በግሉ የሚያደርጋቸው እንቅስቃሴዎች፤ ልክ ከላይ እንደጠቀስኩት አንድ ቀርከሃ በህፃን ልጅ እንኳን የሚፈራና የሚከበር አይሆንም። እናም አውሮፓ ውስጥ ያለው ዜጋችን አንድነት በመፍጠር የሀገሩን መፃዒ ዕድል እንደ ሌላው የሀገሬ ሰው ብሩህ ማድረግ ይኖርበታል። ይህን የሚያደርግበትም በርካታ ዕድሎች አሉት። ለምሳሌ ያህል፤ እዚህ ሀገር ውስጥ፤ “የዳያስፖራ ትረስት ፈንድ” ተቋቁሟል። በዚህ ትረስት ፈንድ ውስጥ ቀጥተኛ ተሳታፊ በመሆን ሀገሩን ሊጠቅም ይችላል።

ለዳያስፖራው ኢትዮጵያ ዞሮ መግቢያው ናት። ከሞትና ከሀገር የሚቀር ወገን የሚኖር አይመስለኝም። ኢትዮጵያ ውስጥ በርካታ ሊያሰሩ የሚችሉ የኢንቨስትመንት መስኮች አሉ። የውጭ ሀገር ሰዎች አዋጭነቱን አምነው ሀገራችን ውስጥ ኢንቨስት እያደረጉ ነው። በዚህም ራሳቸውን ጠቅመው ሀገራችንንና ህዝባችንን እየጠቀሙ ነው። ዳያስፖራው እንኳንስ በንግድና በኢንቨስትመንት ቢሰማራ የሚያዋጣ ሀገር እያለው ቀርቶ፤ ባያዋጣውም እንኳ፤ ኢትዮጰያ ሀገሩ ስለሆነች መዋዕለ ነዋዩን ሀገር ቤት መጥቶ ማፍሰስ የግድ የሚለው ይመስለኛል። በእኔ እምነት ይህ ተግባሩ፤ አንድም፤ ዳያስፖራው እንደ ሰው፤ ያለውን ሃብት በትርፍ ለማዳበር ያግዘዋል፤ ሁለትም፤ እዚህ ሀገር ውስጥ ለሚገኙ ወንድሞቹና እህቶቹ የስራ ዕድል ይፈጥራል። የስራ ዕድል በመፍጠሩም፤ የዜጎችን የነፍስ ወከፍ ገቢ እንዲጨምርና በሀገሪቱ አጠቃላይ ምጣኔ ሃብት እመርታ ላይ አዎንታዊ ሚናን እንዲጫወት ያደርጋል። በዚህም በሀገሩ ውስጥ ወገግ ያለ ብርሃናዊ ፀዳል በማብራት የሀገሩንና የህዝቡን ተስፋ ይገነባል። አዎ! ከዚህ በላይ ለህዝቡ የሚያስብ ዳያስፖራ የትም ተፈልጎ አይገኝም።

ታዲያ ይህ ይሆን ዘንድ፤ የአንድነትን አስተሳሰብ ማጠንከር ያስፈልጋል። አንድነትን ያላጠነከረ ህዝብ፤ ተመሳሳይ ግብና ራዕይ ሊኖረው አይችልም። ተመሳሳይ ግብና ራዕይ የሌለው ደግሞ፤ ቢያወራ እንኳ፤ የገደል ማሚቶም ቢሆን ድምፁን አያስተጋባለትም። እንዲያው ለነገሩ አስተጋብቶለታል ተብሎ ቢታሰብ እንኳ፤ የሚስተጋባው ነገር፤ የሰለለና አቅም የለሽ ሆኖ ይዋጣል። ታዲያ ይህ እንዳይሆን፤ በቅድሚያ አንድነታችንን ማጥበቅ የአማራጮች ሁሉ አማራጭ ነው። ከተለያዩ የአውሮፓ ሀገሮች ወደ ጀርመን ፍራንክፈርት የሚመጣው ዳያስፖራ፤ ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጋር የሚደርገው ውይይት፤ እነዚህን እውነታዎች ከግምት ውስጥ በማስገባት የሀገሩን ነገ ለመገንባት በገሃድ ተደምሮ የለውጡ አካልና ባለቤት መሆን የሚጠበቅበት ይመስለኛል። ችግሮች ቢኖሩም እንኳ፤ ራሱን የመፍትሔው አካል አድርጎ በመቁጠር፤ አንድነትን ሊያመጡ በሚችሉ ጉዳዩች ላይ በጋራ መክሮ የነገ ራዕይውን መሰነቅ ይኖርበታል። ያም ሆኖ፤ በአውሮፓ የሚገኘው ወገኔ፤ ጥላቻን፣ መናቆርንና ቅሬታን ወደ ጎን በማለት፤ አንድነትን ይቅርታንና ፍቅርን ሰንቆ፤ ልክ እንደ አሜሪካው ሁሉ ለጋራ ሀገሩ ዋልታና ማገር እንደሚሆን በርግጠኝነት መናገር የሚቻል ይመስለኛል። ሰናይ ጊዜ።     

 

            

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy