Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

የዲፕሎማሲው ስኬት እስከየት?

0 6,419

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

5የዲፕሎማሲው ስኬት እስከየት?

የኢ... መንግስት ለከፍተኛ አመራሮች እና የአዲሱ የካቢኔ አባላት ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትሩ በተገኙበት ሰሞኑን በተለያዩ ርዕሶች ዙሪያ ስልጠና ሰጥቷል፡፡ ለመጪው ሁለተኛ የሩብ ዓመት ወይም በወቅቱ እንደተገለፀው 100 ቀናት ውስጥ 20ዎቹ ሚኒስትር መስሪያ ቤቶች በመጪዎቹ ቀናት የሚጠበቅባቸው ዋና ዋና ተግባር ተቀምጦላቸዋል፡፡ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴርም ከተሰጠው ስልጣንና ኃላፊነት አንፃር ከጎረቤት እንዲሁም ከሌሎች ስትራቴጂካዊ አጋር ከሆኑ አገሮች ጋር ወዳጅነት የማጠናከር፣ የዳያስፖራውን ተሳትፎ በሙያም ሆነ በሌሎች አገራዊ ጉዳዮች ዙሪያ የማጎልበት፣ የአገሪቱን ገፅታ የመገንባት የዲፕሎማቶችን ስምሪት ማሻሻል እና ሌሎች ተግባሮች ይጠበቅበታል፡፡

ይህ ተግባር የሚጠቀምበት የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ከአገራችን ከአንጋፋ የመንግስት ተቋማት አንደኛው ነው፡፡ በአፄ ሚኒሊክ ዘመን ነው የተቋቋመው ። እ.. 1887 የተመሰረተው ይህ ተቋም በኢትዮጵያ የውጭ ግንኙነት እና የዲፕሎማሲ መስኮች በወርቅ የተፃፈ ታሪክ አለው፡፡ ክቡር / ወርቅነህ ገበየሁ 27ኛው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ናቸው፡፡ ከመንግስታቱ ማህበር እሰከ የተባበሩት መንግሰታት ድርጅት፤ ከአፍሪካ አንድነት ድርጅት እስከ የአፍሪካ ህብረት፣ ከገለልተኛ አገሮች እስከ ኢጋድ የተቋሙ አመራሮች እና ሠራተኞች ለአገር ጥቅም ዘብ፤ ለክብሯ ዋልታ ሆነው ሰርተዋል፡፡ ቀሪውን ለታሪክ ፀሀፊዎች ልተወው፡፡

የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በመጪዎቹ አንድ መቶ ቀናት የሚያከናወናቸው ተግባራት እንዳሉ ሆነው አዲሱ አመራር ወደ ኃላፊነት በመጣባቸው 200 ቀናት ብቻ ብንወስድ 1001 ስኬቶችን አሳይቶናል፡፡ ይህን ለማለት ያነሳሳኝ በኃይሉ  ሚደክሳ ፍስሃፅዮን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር  ምን እያለን ነው?” በሚል ርዕስ በድሬቲዮብ ያቀረቡት ይህን ስኬት የሚያሳንስ መጣጥፍ ካደመጥኩ በኃላ እኔም እንደ ዜጋና የውጭ ጉዳይ እና ዲፕሎማሲያችንን በተመለከተ ሰፊ ዘገባ እንደሰራ ጋዜጠኛ የሚከተለውን ብያለው፡፡

ይህ የአቶ የኃይሉ ፅሁፍ ዜጎች በአገራችው የውጭ ግንኙነት ዙሪያ ውይይት  እንዲያደርጉ በር የሚከፍት በመሆኑ ሊበረታታ ይገባል፡፡ የመጀመሪያ አዎንታዊ ጎኑ ይኸው ነው፡፡ ሁለተኛ የኢ... የውጭ ጉዳይ ፖሊሲው አሁን ከተፈጠሩ አላማዊ፣ አህጉራዊ እና አከባቢያዎ ጉዳዮች ጋር አየታየ እየተፈተሸ መሄድ ይገባዋል የሚለውም ሌላኛው ነው፡፡ ፀሃፊው እንዳላት ብዙ የተለወጡ አገራዊም አካባቢያዊና ዓለማዊም ጉዳዮች ስላሉ መሻሻል አለበት። ከዚያ ውጭ ፅሁፉ ብዙ መሰረታዊ ስህተቶች አሉበት፡፡ የፅሁፌ አላማ በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር እየታዩ ሰላሉ ጥሩ እርምጃዎች ብቻ መናገር ባለመሆኑ አቶ በኃይሉ ባነሷቸው ውስንነቶች ላይ ግን የተወሰነ ነገር ልበል፡፡

አንደኛ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ከሳምንታት በፊት በሰጠው መግለጫ የአገሪቱን የሁለትዮሽና የባለብዙ ወገን ዲፕሎማሲ እንቅስቃሴ ውጤታማ ለማድረግ እንዲሁም ይህ ዕድሜ ጠገብ መስሪያ ቤት የዕደሜውን ያህል እንዲያፈራ የመዋቅር ማሻሻያ እና የሰራተኛ ድልድል አደርጋለው ብሏል፡፡ ትክክል ። ይሁን እንጂ ሁለት ጊዜ በተሰጡት መግለጫዎች ላይ መስሪያ ቤቱ አንድም ጊዜ እደግመዋለው አንድም ጊዜ ሰራተኞቼንና ዲፕሎማቶቼን ከሁሉም ኤምባሲዎች ወደ አዲስ አበባ ጠርቼአለው አላለም፡፡ ፀሀፊው ከየት አመጡት? መስሪያ ቤቱ ያለው አዲስ መዋቅር ተግባራዊ ይሆናል፤ በዋናው መስሪያ ቤትም ሚሲዮኖችም የሰራተኛ ድልድል ዳግም ይካሄዳል ነው፡፡ ፀሀፊው ለሁሉም ሰራተኛ ወደ አዲስ አበባ እንዲመለሱ ጥሪ ቀርቧል የሚሉትም ስህተት ነው፡፡ የተጠሩት 4-25 ዓመታት በአገልግሎት ዘርፍ ሲሰሩ የነበሩ ሰራተኞች ብቻ ናቸው፡፡

ሁለተኛ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ስራተኞችን በመመደብ ብቻ ሪፎርም አድርጌያለው ይላል ሲሉም ፀሀፊው ተናግረዋል፡፡ ሌላው ስህተት። ማን አለ? የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር እያደረገ ያለው የሰራተኛ ዳግም ድልደላ እያካሄደ ካለው  ለውጥ እና ማሻሻያ ውስጥ አንደኛው ሰበዝ ብቻ ነው፡፡ የማሻሻያ ዕርምጃው ብዙ ነገሮችን ያካተተ ነው። ከመስሪያ ቤቱ የሰው ሃብት ድልድልም ባለፈ በድርጅቱ አወቃቀር፣ አሰራር፣ የመሰረተ ልማት ግንባታ፣ የጥናት እና ምርምር ስራዎች ላይ ያተኩራል፡፡ በመሆኑም ሪፎርሙ ከሰው ምደባ በላይ ነው፡፡

በቀረበው ፁሁፍ ላይ ብዙ ማለት ይቻላል፡፡ ተጨማሪ ስንክሳር ሳላወጣ አንድ የፀሀፊውን የመረጃ ስህተት ማስተካከያ ሰጥቼ ወደ የመስሪያ ቤቱ ዋና ዋና ስኬቶች ልግባ፡፡ በኢትዮጵያና ኤርትራ መሀከል በቅርቡ ስምምነቱ የተፈረመው ሳዑዲ አረብያ ሪያድ ሳይሆነ ጄዳ ውስጥ ነው።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ያላፉት አንድ እና ሁለት ዓመት ስራ ስኬታማ ነበር ማለት ይቻላል፡፡ በመጀመሪያ ለዲፕሎማሲ ስራ የአገር ሰላም ወሳኝ ነው። በትርምስ ውስጥ ዕድገት፤ በሁከት ውስጥ ሰለ ገፅታ ግንባታ ማውራት አይቻልም፡፡ ይሁን እንጂ ይህ ውጤታማ የዲፕሎማሲ ስራ ባለፉት ጥቂት ወራት የተከናወነው አገራችን በችግር ውስጥ እየተናጠች በነበረችበት ወቅት ብቻ ሳይሆን በአፍሪካ ቀንድና የቀይ ባህር አካባቢ አዲስ ጆኦፖለቲካዊ መሳሳብ በተፈጠረበት ሁኔታ ነው፡፡  በእነዚህ ተግዳሮቶች ውስጥ የኢትዮጵያ የውጭ ግንኙነት በጥንቃቄ፣ በብስለት እና በረቀቀ መንገድ በመካሄዱ የአገርን ጥቅም ማስከበር ተችሏል፡፡ በጣም ቀላሉ ምሳሌ በባህረሰላጤው ጎራ የለየ ውዝግብ ውስጥ እንደ አገር ሳንላላጥ ያለፍንበት ዲፕሎማስያዊ መንገድ ይጠቀሳል፡፡

ባለፉት ጥቂት ወራት ሌላው እንዲየውም ዋነኛው የውጭ ግንኙነት እና የዲፕሎማሲ ስራ ስኬታማ መገለጫ የሆነው ከኤርትራ ጋር 20 የዘለቀውን ችግር የፈታው የሰላም ውሳኔ ነው፡፡ ከተባበሩት መንግስታት እስከ የአፍሪካ ህብረት በአጠቃላይ የዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ታክቶት እና ደክሞት ትቶት የቆየ ጉዳይ ነበር፡፡ ይሄ በተዓምር፣ ምትሃት ወይም በዕድል አልተፈታም፡፡ የመሪዎች ብቃት ውጤት ነው፡፡ዓለም ይህን ስናደርግ በአይኑ በብረቱ ታዝቧል፡፡ ይሄ ስኬት የአፍሪካ ቀንድን ጂኦፖለቲካዊ ሁኔታ ፍፁም የቀየረ ነው፡፡ ፋይዳው ለሁሉም የአፍሪካ ቀንድ አገሮች ተርፏል፡፡

ባለፈው አንድ ዓመት የስንት አገራት መሪዎች ወደ አገራችን መጡ?  2009 እና 2010 . 30 መሪዎች ለጉብኝት አዲስ አበባ መጥተዋል ። በዲፕሎማሲው ያልተነገረ ካልሆነ ያልተሰራ ነገር የለም፡፡ ምን አይነት የትብብር መግባባቶች ደረስን፣ ምን ያህል የልማት ድጋፍ አገኘን፡፡ ድርሳናት ማገላበጥ አይጠይቅም። የትናንት ታሪክ ነው፡፡ የኢ.ፌ.ዲ.ሪ ፕሬዝዳንት፣ ጠቅላይ ሚኒስትር፣ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር በስንት አገሮች ጉብኝት አደረጉ? ይታወቃል፡፡ የመሪዎች እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ጉብኝት ታስቦ፣ ታቅዶ እና ታልሞ የሚካሄድ ነው፡፡ የሁሉም ጎረቤቶቻችን፣ የብዙዎቹ የመካከለኛው ምስራቅ፣ የአውሮፓ እና ኤስያ አገራት መሪዎች፣ ንጉሶች አልጋ ወራሾች እና ሚኒስትሮች ወደ አገራችን መጥተው ወዳጅነታችሁን እንፈልጋለን ብለዋል፡፡የአሜሪካ እና ሩስያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች በአንድ ቀን በአንድ ጣሪያ ስር እዚሁ አዲስ አበባ መቆየታቸው ይታወሳል። የምትሻገሩት ፈተና እንዳለ ሆኖ የአከባቢው የሠላም ማማ፤ የመረጋጋት ካሰማ በመሆናችሁ አብረን እንሰራ ብለዋል፡፡ ውጤቱም ብዙ ቅፅ፤ በርካታ ገፅም ሊፃፍበት ይችላል፡፡ አበው የማታድርበት ቤት አታመሽበት እንዲሉ፤ በዲፕሎማሲ ደግሞ አትወዳጀበት አገር አትሄድበት ነው ነገሩ፡፡

የአገራችን ዲፕሎማሲ በነፃነት፣ በመልካም ጉርብትና፣ በጋራ ተጠቃሚነት ላይ የተመሰረተ በመሆኑ ከጎረቤቶቻችን ጋር ጥሩ ወዳጅነት እየተፈጠረ ነው፡፡ያለው ትስስር፣ በቀጠናው ሰላም እንዲመጣ ኢትዮጵያ የምታደርገው አስተዋፅኦ፣ ዜጎቻችን ከየታሰሩበት አገር የሚፈቱበት ሁኔታ፣ የውጪ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንት ከመሳብ አኳያ የተኬደበት ርቀት ግሩም የሚባል ነው፡፡ መከራከርም መሞገት ይቻላል። በሰሜን አሜሪካ አውሮፓ እና በመላው ዓለም የሚገኙ ወንድሞችና እህቶቻችን በአገራቸው ጉዳይ ተሳታፊ እንዲሆኑ የተጀመረው ጥረት እና የተገኘው የእሰካሁን ውጤት በ50 ዓመት ውስጥ ያልታየ ነው። የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ድርሻውን ሲያስቀምጥ ሚዛን የሚደፋ ሌላ ስራ ነው፡፡

ከሌሎች አገሮች ጋር ባለፉት ጥቂት ወራት የተከናወኑ ስራዎችን በተመለከተ ብዙ ማለት ቢቻልም ወደ የባለብዙ ወገን ዲፕሎማሲ (Multilateral Diplomacy) ልለፍ፡፡ በፀጥታ ምክር ቤት ያለን እና በሚቀጥለው ወር የሚጠናቀቀው የተለዋጭ አባልነት ተሳትፎና አስተዋፅኦ ሌላ ወርቃማ የአገራችን ስኬት ምሳሌ ነው፡፡ የራሳችንን ጥቅም ብቻ ሳይሆን የአፍሪካውያንን ፍላጎት ያረጋገጠንበት 30 ዓመት ያህል የተገኘ ዲፕሎማሲያዊ ድል ነው፡፡ ይሄ የዲፕሎማሲው ማሽቆልቆል እንዴት ይሆናል? በየትኝውም ወገን ወቀሳና እርግማን የማያደበዝዝ ትውልድ የሚያስታውሰው ስራ ነው፡፡ ምክንያቱም ነገሩ የአዋጁን በጆሮ ነውና፡፡ ዓመቱ ብዙ መስሪያ ቤቶች በወቅታዊ ችግር ተተብትበው ድምፃቸው ባልነበረበት ሁኔታ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቀና ብሎ የሄደበት ነበር፡፡ ወረቅ ስራ ተሰርቷል፤ ስኬቱ ስለራሱ ይናገራል።

ብዙ ዲፕሎማሲያዊ ድል ቢመዘገብም፤ ሁሉም ነገር አልጋ በአልጋ ግን አልነበረም፡፡ የዲፕሎማሲ ስራው የስኬታማነቱን ያህል ብዙ ተግዳሮቶች ገጥመውታል፡፡ በአገር ውስጥ የነበረው የቁለቁለት ጉዞ፣ የአካባቢያችን የመረጋጋት እጦት፣ ጂኦፓለቲካዊ ሁኔታ፣ አሁንም ከድህነት ያለመውጣታችን የስደት ችግር መፍትሄ አለመገኘት፣ የዓለም የንግድ ስርዓት ታዳጊዎች ላይ ፍትሃዊ አለመሆኑ ይጠቀሳሉ፡፡

 

የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ተዘናግቶ በቀጣይ ሊሄድ አይችልም። ብዙ ይጠበቅበታል። በእስካሁን ስኬቶች ላይ ተመርኩዞ 21ኛው ክፍለ ዘመን የሚመጥን ተቋም መሆን ለነገ የሚባል ወይም አማራጭ አይደለም፡፡ በመጪው ጊዜ ከወዳጆቻችን ጋር ያለንን ግንኙነት የማጎልበት፣ አዳዲስ ወዳጆችን የማበረከት፣ ጠላትና የስጋት ደመና  የመቀነስ የአገርን በጎ ገፅታ የመገንባት እና ዜጋ ተኮር ዲፕሎማሲው የማረጋገጥ ኃላፊነት የእስካሁኑን ውጤት ባሰመዘገበው አመራር እና ዲፕሎማት ጫንቃ ላይ የተጫነ ኃላፊነት ነው፡፡ መቼም አታሳፍሩንም።

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy