Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

‘ዶክተር አብይ—እጅ ወደ ላይ!’

0 9,670

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

‘ዶክተር አብይ—እጅ ወደ ላይ!’

                                                        እምአዕላፍ ህሩይ

“…ለዚህ የሀገር ባለውለታ የለውጥ ኃይል የከድር ሰተቴው ‘…እጅ ወደ ላይ!’ ፈፅሞ አይመጥነውም። አዎ! የዚህች ሀገር መፃዒ ተስፋ ያለው በለውጥ ኃይሉ እጅ እንደመሆኑ መጠን፤ እኛ ማለት ያለብን፤ ‘ዶክተር አብይ—ከሁሉም በላይ!’ ነው። እኛ ማለት ያለብን፤ ‘ቲም ለማ፣ ከጎንህ ነን ሀገር ስታለማ!’ ነው። እኛ ማለት የሚገባን፤ ‘በለውጡ የመጣ፤…”

 

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ በብዕር ስም እንደፃፉት የሚነገረው “ሰተቴ” የተሰኘ መፅሐፍ እጄ አልገባም። ግና ዋና ገፀ ባህሪው በጅማ ይኖር በነበረ ከድር ሰተቴ የተባለ ሰው ግለ-ስብዕና ላይ የሚያጠነጥን መሆኑን አንድ ወዳጄ አጫውቶኛል። የከድር ሰተቴ ነገረ- ‘መቼት’ የሚያጠነጥነው፤ በደርግ ስርዓት ወቅት በጅማ ከተማ ላይ እንደሆነም አውግቶኛል። ከድርን የሚያውቀው ወዳጄ፤ ውልደቱም ሆነ ዕድገቱ ኢሉባቡር ውስጥ ነው፤ መቱ ከተማ። እናም ጅማን፣ አጋሮን፣ ቴፒን፣ ሶኮሩን፣ ጎሬንና በዚያ መስመር የሚገኙትን ከተሞች የእጁን ጣቶች ያህል አሳምሮ ያውቃቸዋል። ስለ ከድር ሲያወራ ቢያድር የሚሰለቸው ሰው አይደለም።

ወዳጄ፤ ከድር ሰተቴን ብዙዎች “አውቆ አበድ” እንደሚሉት አልሸሸገኝም። እርሱም በእነዚህ ሰዎች ብያኔ የሚያምን ሳይሆን አይቀርም—ከአነጋገሩ እንደተረዳሁት። ከድር ሰተቴ “ተዓምረኛ ሰው” እንደሆነ ይነገርለታል። በዚያን ማንኛውም ዓይነት ፈርድ በባለስልጣናት ብቻ በሚበየንበት ዘመን፤ ሰውዬው በሚናገራቸው ነገሮች ሳቢያ በደርግ ሰዎች እንደ ጥጃ ሲታሰርና ሲፈታ የኖረ ነው። ተግባሮቹ የ“እብድኛ” ይሁኑ እንጂ፤ የ“አውቆ አበዱ”ን ሰው ምግባር፤ ከኢህአፓ የፖለቲካ ተልዕኮ ጋር የሚያያይዙ ብዙ እንደነበሩ ገልፆልኛል—ይኸው ወዳጄ።

እዚህ ላይ ወዳጄ ስለ ከድር ሰተቴ ያወጋኝን አንድ አስገራሚ ነገር ላጫውታችሁ። በአንድ ወቅት፤ ከድር “ከፋ” እየተባለ የሚጠራው ክፍለ ሀገር የኢሰፓ ባለስልጣን የነበሩትን ሰው ህዝብ በተሰበሰበበት ቦታ እንዲህ አደረገ።…የከፋ ክፍለ ሀገር የኢሰፓ ዋነኛ ባለስልጣን የነበሩት አቶ ተሰማ በላይ ህዝብ በተሰበሰበበት ስቴድየም በደማቅ ክብረ በዓል ላይ በክብር ታድመዋል። ታዲያ ከድር ሰተቴ ወደ እርሳቸው ጠጋ ይልና ድምፁን ከፍ በማድረግ፤ “ተሰማ በላይ—እጅ ወደ ላይ!” ይላል። ታዲያላችሁ የኢሰፓው ባለስልጣን ጠባቂዎች ወዲያውኑ ሰውዬውን እንደ ሻንጣ አንጠልጥለው ወህኒ ቤት ውስጥ ይከረችሙበታል። ከድር ሰተቴም የወህኒ ቤት ኑሮውን ቀጠለ።…ከዕለታት አንድ ቀን፤ ባለስልጣኑ አቶ ተሰማ በላይ በወህኒ ቤት ያለውን የእስረኞች አያያዝ ሁኔታን እየጎበኙ ሳሉ ከድር ሰተቴ በአትኩሮት ይመለከታቸዋል። እናም አንገቱን ከታሰረበት ፍርግርግ ውስጥ አውጥቶና ድምፁን ጎላ አድርጎ፤ ትናንት “ተሰማ በላይ— እጅ ወደ ላይ!” ያላቸውን ባለስልጣን፤ “ተሰማ በላይ—ከሁሉም በላይ!” እያለ መጮህ ይጀምራል። የክፍለ ሀገሩ ኢሰፓ ከፍተኛ ባለስልጣንም በአባባሉ ይገረሙና “ይህ ሰው እስካሁን ድረስ እዚህ ነው እንዴ?!…ፍቱት እንጂ!” የሚል ቀጭን ትዕዛዝ ያስተላልፋሉ። እናም በወቅቱ የማንኛውም እስረኛ ውሳኔ የሚሰጠው በግለሰብ ባለስልጣን እንጂ በህግ አለመሆኑን የሚያውቀው ከድር ሰተቴም፤ በዚህ አስቂኝና አስገራሚ ድርጊቱ ከደርግ እስር ቤት ለመፈታት በቃ።     

የከድር ሰተቴን “…እጅ ወደ ላይ!” እና “…ከሁሉም በላይ!” የሚሉ በተለያዩ ወቅቶች የተገለፁ፣ ነገር ግን ሁለት የሚቃረኑ ይዘት ያላቸውን አስተሳሰቦች እዚህ ላይ ያነሳሁት ያለምክንያት አይደለም። አዎ! አስተሳሰቦቹ ዛሬም እንደ ወራጅ ውሃ ያለምክንያት በሚነዱ አንዳንድ ወገኖች አማካኝነት እየተስተዋሉ ነው። ትናንት በምክንያታዊነት “ከሁሉም በላይ!” ያልነውን ዛሬ በአሉባልታ እየተነዳን “እጅ ወደ ላይ!” የማለት አባዜ የተጠናወተን ይመስላል። በእውነቱ ሚዛናዊነታችንን ማን እንደወሰደብን አላውቅም።

ርግጥም አንዳንድ ወገኖች ኢትዮጵያችን ውስጥ አንድ ነገር ሲፈጠር ያለ አንዳች አስረጅ እንዲሁም ምክንያታዊ ባልሆነ አስተሳሰብ ላይ ተመስርተው፤ በዶክተር አብይ አህመድ የሚመራውን እንዲሁም ሀገሪቱን በለውጥ ጎዳና ውስጥ አስገብቶ በጥቂት ወራቶች ውስጥ በሁሉም መስኮች በፍጥነት እያስወነጨፋት የሚገኘውን “ቲም ለማ”ን በውሸት ወሬና በስሜታዊነት እየተናጡ ‘…እጅ ወደ ላይ!’ የሚሉ ዓይነት ስሞታን በየማህበራዊ ሚዲያው የሚለፍፉ ጥቂት ወገኖችን እየተመለከትን ነው።  

እንዲያውም እነዚህ ወገኖች ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ታችኛው የስልጣን እርከን ድረስ ወርደው ይሰሩ ይመስል፣ እንዲሁም እየተከተልን ያለነው ስርዓት፤ ክልሎች ከራሳቸው ስልጣን ቆርሰው በሰጡት ስልጣን ሀገርን የሚያስተዳድረው ፌዴራላዊ ስርዓት መሆኑን ዘንግተው፤ ‘ዶክተር አብይ—እጅ ወደ ላይ!’ ለማለትም የሚከጅላቸው ናቸው። ‘እጅ ወደ ላይ እጅ ወደ ታች’ ማለት መብት ነው። አስገራሚው ነገር ግን፤ የእነዚህን አካላት ፍላጎትና ዓላማ መንግስት እያከናወነ ያለውን አኩሪ ተግባር እያዩና እየተመለከቱ በ‘አሉሽ…አሉሽ’ ብቻ እንደ ቦይ ውሃ ለመፍሰስ የሚሞክሩ ወጣቶችን አልፎ…አልፎ ማጋጠማቸው ነው— ጨበየማህበራዊ ሚዲያው። ትናንት “ዶክተር አብይ—ከሁሉም በላይ!” ይሉ የነበሩ ጥቂት ወጣቶች እዚህ ሀገር ውስጥ በተለያዩ ‘ለውጥ-ጠል’ አካላት የሚከናወኑት አስፀያፊ ድርጊቶችን በውል የተገነዘቡ አይመስለኝም። አሊያም ጉዳዩን በውል ሳያጣሩ በየትስስር ድሩ “እልል በቅምጤ” እያሉ ነው ማለት ይቻላል። እናም ወጣቶች ‘ማን ምን እያደረገ ነው? ዓላማውስ ምንድነው?’ የሚሉ ጥያቄዎችን በማንሳት እውነታውን ሊመረምሩ ይገባል እላለሁ። እናም ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ በቅርቡ እንዳሉት፤ ወጣቶች የአንዳንድ አካላት መጠቀሚያ እንዳይሆኑ ራሳቸውን መጠበቅ እንደሚኖርባቸው ደግሜ ላስታውሳቸው እወዳለሁ።

አዎ! የመንግስትን ፈጣንና አኩሪ ተግባሮች በጥቁር መጋረጃ ለመሸፈን የሚፈልጉት አካላት ፍላጎታቸው ከማንም የተሰወረ አይመስለኝም። የእነዚህ ወገኖች ፍላጎትና ዓላማ፤ በዚህም…በዚያም ብለው ‘መንግስት የመምራት አቅም ስለሌለው መቀየር ይኖርበታል’ የሚል ቀቢፀ-ተስፋን በመያዝ፤ ለውጡ እያስገኛቸው ያሉትን ሁለንተናዊ ጠቀሜታዎች በአሉባልታ ናዳ ለማደናቀፍ መሞከር ነው። ዳሩ ግን፤ እነዚህ “ጦር ከፈታው፤ ወሬ የፈታው” በሚል ባረጀና ባፈጀ ብሂል የሚጓዙት ወገኖች፤ አዲሱን ትውልድ በአሮጌ አስተሳሰብ ለመምራት የሚከጅሉ መሆናቸውን መገንዘብ ይገባል። ታዲያ እንዲህ ዓይነቱ አስተሳሰብ 21ኛውን ክፍለ ዘመን በ14ኛው ክፍለ ዘመን እሳቤ ለማስተዳደር የመሞከር ያህል ነው። እናም ነገሩ “ላም አለኝ…” መሆኑን ማወቅ ያስፈልጋል—መቼም የማይሆን።

ርግጥ ወጣቱም ይሁን ሌላው የህብረተሰብ ክፍል፤ የሚጨበጥንና የሚዳሰስን መንግስታዊ ተግባር እየተመለከተ ስለሆነ፤ እንደ እነርሱ ‘ዶክተር አብይ—እጅ ወደ ላይ!’ በሚል እሳቤ ውሰጥ አለ እያልኩ አይደለም። ምክንያቱም ወጣቱን ጨምሮ ሁሉም የህብረተሰብ ክፍል በለውጡ የተቀዳጀውን ነፃነትና እኩልነት እንዲሁም የአንድነት መንፈስ በሚገባ የሚገነዘብ ስለሆነ ነው። ያም ሆኖ ግን፤ አሁንም ወጣቱ ከእነዚህ ሃይሎች ራሱን በማራቅና ፍንትው ብለው የሚታዩ ሀገራዊ ለውጦችን በመገደፍ እንደ ሁሌው ከዶክተር አብይ ጎን መሰለፍ ይኖርበታል። በዶክተር አብይ የሚመራው “ቲም ለማ” ስራ ላይ መሆኑንና ለማንኛው አሉባልታ ጊዜ የሌለው ባተሌ መሆኑን ማወቅ አለበት።          

እንደ እውነቱ ከሆነ፤ “ቲም ለማ” ክምንግዜውም በላይ ወደፊት እየገሰገሰ ነው። ግስጋሴው ከመጀመሪያዋ የፓርላማ ንግግር እስካሁን ድረስ የቀጠለ ነው። ባተሌ ሆኗል። በተለይ በአሁኑ ወቅት ፍጥነቱ ልኬታ የሌለው እየሆነብኝ ነው። የለውጡ ፍጥነት በሀገር ውስጥ የሚፈጠሩ ችግሮችን አስቀድሞ በመከላከል ረገድ እመርታ እየታየ ነው። ህግና ስርዓት በተከተሉ አፋጣኝ መፍትሔዎችም እየተሰጡ ነው። ሊያሰራ የሚችል መዋቅር ተዘርግቶም ከመቶ ቀናት ተጠባቂ ግቦች ጋር ለሁሉም አስፈፃሚ አካላት “እንካችሁ” ተብሏል።

ሁሌም እንደምለው፤ ዶክተር አብይ ስትራቴጂካዊ አመራር በመሆናቸው፤ ማድረግ የሚችሉት አቅጣጫ በመስጠት ፈፃሚዎቹ አካላት እንዲሰሩ ማድረግ ነው። ታች ድረስ ወርደው ቴክኒካዊ ጉዳዩችን ሊፈፅሙ አይችሉም። እናም የተሰጠውን አመራርና ግብ መፈፀምና በተጨባጭ መሬት ላይ አውርዶ የማሳየት ተልዕኮ የታችኛው አካል መሆኑን መገንዘብ ተገቢ ይመስለኛል። ያም ሆኖ፤ አሁን ባለው ሁኔታ፤ ሰላምን አማክሎ የተቋቋመ ሚኒስትር በመኖሩ፤ ግጭቶች እንዳይከሰቱ አቅም በፈቀደ መጠን አስቀድሞ መከላከል የሚቻልበት አሰራር የተዘረጋ ይመስለኛል። ችግሮች ከተፈጠሩም በኋላ ቢሆን፤ ብዙ ጉዳት ሳያስከትሉ በቁጥጥር ስር ለማዋል የሚቻልበት ሁኔታም ተመቻችቷል ማለት ይቻላል። ይህም የለውጡ ባለቤት የሆነው “ቲም ለማ”፤ እንደ ፈጣኑ ለውጥ ሁሉ፤ ከትናንት ዛሬ እየተሻለና ነገሮችንም ከነባራዊ ሁኔታችን ጋር እያዛመደ ራሱን በማጠናከር ሀገራዊ ተልዕኮውን በብቃት እየተወጣ መሆኑን የሚያመላክት ነው።

ምን ይህ ብቻ! የዲፕሎማሲ ስራውን የሚሰራው የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መስሪያ ቤትን ብንመለከት እንኳ ፋታ የሚያገኘው መቼ እንደሆነ አግራሞትን የሚያጭር ነው። ሌላውን ክንዋኔዎች ትተን የሰሞኑን የቀናት ፍፃሜዎች ብንመለከት፤ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዶክተር ወርቅነህ ገበየሁ እንዴት ዓይነት ስራዎችን እየከወኑ እንደሆነ ልብ ያለው ልብ የሚል ይመስለኛል። ርግጥ ስራው ቅንጅታዊ ነው። ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሰባቱንም ቀናት እየሰሩና ሌሎችን እያሰማሩ በማሰራት ምን ያህል ባተሌ መሆናቸውን እየተመከትናቸው ያሉት የቀናት ተግባራዊ ፍፃሜዎች ብቻ አፍ አውጥተው የሚናገሩ ናቸው። “ቲም ለማ”፤ ጧት ሞቃዲሾ ቆይቶ ሳያርፍ ደግሞ አስመራ ነው። ወዲያውኑ ደግሞ የአሜሪካ ድምፅ አገልግሎት ኃላፊዎችን ተቀብሎ አነጋግሮ በማግስቱ ለጉባኤ ወደ ሌላ ሀገር ማቅናት…ወዘተ. ነው። እነዚህ ጉዳዩች በሁለት ቀናቶች ብቻ የተፈፀሙ ናቸው። ታዲያ ተግባሮቹ በማንኛው ሀገር ወዳድ ዜጋ ልብ ውስጥ ኩራትን የሚጨምሩና የ“እኛነትን” ካባ የሚደርቡ መሆናቸው አሌ የሚባል አይመስለኝም።

ታዲያ የእዚህ በማሳያነት ያነሳኋቸው የቀናት ተግባሮች ባለቤት እንዲሁም የሀገር አለኝታ የሆነን “ቲም” መሪን፤ ‘ዶክተር አብይ—እጅ ወደ ላይ!’ በሚል ዓይነት ስሜት በፌስ ቡክ ላይ አሉባልታ ሀገራዊ ስራን ለማኮስመን የሚደረግ ጥረት ከራሱ ጋር የተጣላ ሰው ምግባር አሊያም እንደ ከድር ሰተቴ “አውቆ አበድ” የሆኑ አካላት ምግባር ከመሆን አይዘልም—ለእኔ። ርግጥም ሰው ለሀገሩ እንቅልፍ አጥቶ ሌት በቀን ሲሰራ ከጎኑ ሆኖ ‘አይዞህ በርታ!’ እያሉ ድጋፍ መስጠት እንጂ፤ በጥራትና በብቃት የሚሰሩ እጆችን ከስራ ላይ እንዲነሱ በገደምዳሜው መንገር ነውረኝነት ከመሆን አያልፍም።

አዎ! ሀገርን ከውርደትና ከብተና ያዳነን እንዲሁም ዜጎቿን ከተበታተነ ሁኔታ ደምሮ ወደ አንድነት እያመጣ ያለን ቡድንንና መሪን የተግባሮቹ ምርኩዝና ድጋፍ ልንሆነው ይገባል። ለዚህ የሀገር ባለውለታ የለውጥ ኃይል የከድር ሰተቴው ‘…እጅ ወደ ላይ!’ ፈፅሞ አይመጥነውም። አዎ! የዚህች ሀገር መፃዒ ተስፋ ያለው በለውጥ ኃይሉ እጅ እንደመሆኑ መጠን፤ እኛ ማለት ያለብን፤ ‘ዶክተር አብይ—ከሁሉም በላይ!’ ነው። እኛ ማለት ያለብን፤ ‘ቲም ለማ፣ ከጎንህ ነን ሀገር ስታለማ!’ ነው። እኛ ማለት የሚገባን፤ ‘በለውጡ የመጣ፤ እቆጥረዋለሁ ዓይኔን እንዳወጣ!’ ነው። እናም ወጣቱ የአሉባልታ ነፋስ ወደሚያዘምበት አቅጣጫ ባለመሄድ፤ ሁሉም ህዝቦች በትግላቸው ያመጡትን ለውጥ፤ “ብሌኔ…ብሌኔ” እንዳለው ዘፋኙ፤ እርሱም ዘብ ሆኖ እንደ ዓይኑ ብሌን በንቃት ሊጠብቀው ይገባል እላለሁ—የአሉባልተኞቹ ስብከት “ለወሬ የለውም ፍሬ” እንዲሉት ዓይነት ነውና። ሰናይ ጊዜ።

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy