ሀገራዊ አንድነት ለሁለንተናዊ ብልፅግና
ይቤ አብርሃ ከውቤ በረሃ
ያለንበት ወር ከክረምቱ ወደ ብርሃናማው ፀደይ የተሸጋገርበት ነው። ምድራችን በልምላሜ፣ በእንግጫና አበባ የምታጌጥበት የአዲስ ዓመት መባቻ በመሆኑ በኢትዮጵያውያን ዘንድ የተስፋ ጮራ የሚፈነጥቅበት ወቅት ነው።ከነሀሴ ወር አጋማሽ ጀምሮ የተከበሩት በሰሜን የሀገሪቱ አካባቢዎች የአሸንዳ፣ በመሀል የሀገሪቱ አካባቢዎች ደግሞ በወጣቶች የቡሄ፣ በልጃገረዶች የሚካሄዱ የአበባዮሽ ጭፈራዎች የአዲሱ ዓመት ዋዜማ የሚያበስሩ ናቸው። ከዚሁ ጋር የዘመን መለወጫ፣ በሀገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች የተከበረው የደመራና የመስቀል በዓል የአዲሱ ዓመት በዓል አካል በመሆን በድምቀት ተከብረዋል።በተለይ በጉራጌ፣ በጋሞ ፣በወላይታ በመሳሰሉ ብሔረሰቦች የመስቀል በዓል እንደ አዲስ ዓመት ታስቦ የሚከበር ነው።
በኦሮሞዎች በየዓመቱ ከመስቀል በዓል ቀጥሎ ባለው እሁድ የሚከበረው የኢሬቻ በዓልም ከክረምቱ ጨለማ ወደ ፀደይ ብርሃናማ ላሸጋገራቸው ፈጣሪ ምስጋና የሚቀርብበት መሆኑን አባገዳዎች ይናገራሉ።ዘንድሮም ኢሬቻ ሲከበር አረጋውያን ወጣቶችና ልጃገረዶች ለምለም ቄጠማና አደይ አበባ ይዘው ፣በባህላዊ አለባበስ ተውበው በቢሾፍቱ አርሰዲ ሐይቅ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ዜጎች ከሀገራችን አራቱም አቅጣጫ ተሰብስበው ምስጋናና ጭፈራ ያሳዩበት ነበር። በአዲሱ ዓመት መባቻ የተከበረው የዘንድሮው ኢሬቻ ሀገራችን በለውጥ ጎዳና መግቧቷ ፣ የኦሮሞ ህዝብ ሲጠይቅ የነበረው የመልካም አስተዳደር እጦት እልባት ማግኘቱ በዓሉን ልዩ ያደርገዋል።
ምድር በልምላሜና በአበባ በምትውባብት በአዲሱ ዓመት እንስሶች ለምለም ሳር እየነጩ፣ ውሃ እየተጎነጩ የሚፈነጩበት አዕዋፍ ፍሬዎችን አየለቀሙ በደስታ የሚሽከረከሩበትና ዝማሬ የሚያሰሙበት ፣ ንብ አበባ እየቀሰመ ማር የምትጋግሩበት ወቅት በመሆኑ እንኳን ለሰዎች ለእንስሶች የደስታ ወቅት ነው።
በመሆኑም በአዲሱ ዓመት በተጓዳኝ የኢህአዴግ እህት ድርጅቶች ከመስከረም አጋማሽ ጀምሮ ባካሄዷቸው ጉባዔዎች ነባር አመራሮችን በክብር በመሸኘትና በማሰናበት አኩሪ ጅማሬ አሳይተዋል።ቢከፋም ቢለማም ነባር አባላቶች ለአበርክቷቸው ማመስገን ተገቢ ነው።ያገለገሉ ሰዎች እንደ አሬጌ ቁና ለሚወረወሩባት ኢትዮጵያ በምስጋና ማሰናበት በጎ ጅማሬ ነው ማለት ይቻላል። ይህም ዜጎች በመካሄድ ላይ ያለውን የኢህአዴግ ጉባዔ ሂደትና ውሳኔዎች በአዲሱ ዓመት ናፍቆትና በጉጉት እንዲጠብቁ ያደረገ ነው።
የኢህአዴግ እህት ድርጅቶች ከለውጡ በኋላ የመጀመሪያውን ስብሰባቸው በያዝነው አዲሱ ዓመት ሁለተኛ ሳምንት ጀምሮ ሲያካሂዱ ቆይተዋል። በተለያዩ ርዕሰ ጉዳዮች በተካሄዱት በነዚህ ስብሰባዎች የወጣት የአመራሮች ሽግሽግ ተደርጓል።በዚህም በእህት ድርጅቶቹ በተካሄዱት ስብሰባዎች ለረጅም ጊዜ በአመራርነት ያገለገሉ አባላት በክብርና በሽልማት እንዲሰናበቱ ወጣት አመራሮች ደግሞ እንዲካተቱ የተወሰነባቸው ናቸው።
ከእህት ድርጅቶች ስብሰባ በኋላም መስከረም 23 ቀን 2011 ዓ.ም ጀምሮም የኢህአዴግ 11ኛው ጉባዔ በሐዋሳ ከተማ ተከፍቷል። የኢህአዴግ ሊቀ መንበርና የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐብይ አህመድ 11ኛው የኢህአዴግ ድርጅታዊ ጉባኤ መክፈቻ ላይ ባደረጉት ንግግር ሀገሪቱ እና ህዝቧ የለውጥ ምህዋር ውስጥ በገቡበት ወቅት የሚከናወን የኢትዮጵያን መፃኢ ጉዞ የሚወስን ታሪካዊ ጉባዔ መሆኑን አስታውቀዋል።
‟ሀገራዊ አንድነት ለሁለንተናዊ ብልፅግና”በሚል መሪ ቃል እየተካሄደ የሚገኘው የኢህአዴግ ጉባዔ ላይ የግንባሩ አባል ድርጅቶች አመራሮችና አባላት፣ የተፎካካሪ ፓርቲ አመራሮች፣ የወዳጅ ሀገራት ልዑካን እና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል።በንግግራቸው ሀገር የምታድገው በቅብብሎሽ ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ የአዲሱ ትውልድ ከማማረር ይልቅ ያለፈውን ትውልድ በማመስገን ከቀደመው ትውልድ በጎ በጎውን በመውሰድ መማር ያስፈልገዋል ብለዋል።
ኢህአዴግ ባለፈባቸው ሁሉም የትግል ምዕራፎች ባጋጠሙት ፈተናዎች እና መሰናክሎች ተሸንፎ እጅ የሰጠበት እና ጉዞውን ያቆመበት ታሪካዊ አጋጣሚ አልነበረም ያሉት ዶክተር ዐብይ፥ ይልቁንም ያጋጠሙትን ፈተናዎችና መሰናክሎች ፊት ለፊት በመጋፈጥ በአግባቡና በሳይንሳዊ መንገድ በመፍታት ለተጨማሪ ድል እና ጥንካሬ ራሱን በማብቃት ወደ ቀጣይ ምእራፍ መሸጋገሩ የቅርብ ዘመን ትውስታ ነው ብለዋል። ሀገሪቱ አሁን ያለችበት ያለው ሽግግር ቀጣይነት እንዲኖረው ቀና ልብ እና አርቆ አስተዋይ አዕምሮ ይጠይቃል፤ የቀደመው ትውልድም ባካበተው ልምድ እና ዕውቀት የለውጡ ተጋሪ መሆን አለበት ብለዋል።
ሀገር የምታድገው በቅብብሎሽ ነው ያሉት ሊቀመንበሩ፥ ለዚህም የቀደመው ትውልድ ልምድ እና ጥበቡን ተጠቅሞ ለአዲሱ ትውልድ የመሪነቱን በትር ሊያስረክብ እንደሚገባም ገልፀዋል።የአዲሱ ትውልድ ተተኪ መሪዎችም ያለፈውን ባለማማረር እና ባለፈው ትውልድ ላይ ባለማሳበብ፤ ያለፍውን ትውልድ አመስግኖ በማክበር ከቀደመው ትውልድም በጎ በጎውን በመውሰድ የተሻለ መሪ መሆን ይገባል ሲሉ ተናግረዋል።ከትውልድ ወደ ትውልድ የሚደረገው ሽግግር በመሰጋገን እና በመተራረም ላይ የተመሠረተ እንዲሆን የሚያደርግ የፖለቲካ ባህልና ፥ መተካካት የታቀደበት ሂደት እንጂ ድንገተኛ የመበላላት ክስተት እንዳይሆን ሥርዓት መትከል ያስፈልጋል ሲሉም ገልፀዋል።ሊቀመንበሩ ዶክተር ዐብይ አክለውም፥ የአንድ መሪ ስኬታማነት መለኪያ የሱን ሥራ በተሻለ መልኩ ሊያስቀጥል የሚችል መሪ ማፍራት ሲችል መሆኑንም አስገንዝበዋል።
ኢህአዴግ የአራት ድርጅቶች ጥምረት ሆኖ ቢመሰረትም፤ አጋር ፓርቲዎችን ወደ ግንባሩ ለማስገባት ፍላጎት እንደነበረው ይታወቃል ያሉት ዶክተር ዐብይ፥ ለዚህም ጥናት ተጀምሮ እንደነበርና የጥናት ውጤቱ በዚህ ድርጅታዊ ጉባኤ እንዲካተቱ አቅጣጫ ተቀምጦ እንደነበረ ጠቁመዋል።ሆኖም ከ10ኛው ድርጅታዊ ጉባዔ በኋላ በነበረው ሀገራዊ ችግር ይህንን ሊከናወን ባለመቻሉ ጥናቱ ሊጠናቀቅ እንዳልቻለ አስታውቀዋል።ወደፊት ኢህአዴግ አጋር ድርጅቶች የሚካተቱበት ሁሉም ኢትዮጵያዊ የሚሳተፍበት ድርጅት እንዲሆን በፅናት መሥራት ይጠበቅብናል ብለዋል።
ከውጪ ሀገር አቻ ፓርቲዎች መካከልም ከጀርመን፣ ከቻይና፣ ከደቡብ አፍሪካ፣ ከኬንያ፣ ከሱዳንና ከጅቡቲ፣ ከቬትናም ከመሳሰሉ ሀገሮች የመክፈቻው ሥነ ሥርዓት ላይ ተገኝተው ያለቸውን አጋርነት ገልፀዋል።በኢትዮጵያ የተመዘገቡ ዕድገቶችንና የታዩ ለውጦችን እንደሚያደንቁም ተናግረዋል።
ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴው የጥልቅ ተሃድሶውን ተከትሎ የተወሰዱ የለውጥ እርምጃዎች የአመራር ፈጠራ ታክሎባቸው የለውጡ ትሩፋት የሆኑ አመርቂ ውጤቶች መመዝገባቸውን ያረጋገጠ ሲሆን፥ ከአሁን በፊት ውሳኔዎች እየተወሰኑ እና አቅጣጫዎች እየተቀመጡ በአፈፃፀም ድክመት ይታይባቸው የነበሩ ጉዳዮች በፍጥነት መፈፀም በመጀመራቸው በዚህ አጭር ጊዜ ሊመዘገቡ ይችላሉ ተብለው የማይታሰቡ ድሎች መመዝገባቸውን፤ እነዚህ ድሎች የመላ የኢትዮጵያውያንን ድጋፍ ያስገኙና ተስፋውን ያለመለሙ መሆናቸውን በአድናቆት መመልከቱን ነው የገለፀው።
በፖለቲካዊ፣ ዲፕሎማሲያዊ፣ በኢኮኖሚና ማህበራዊ መስኮች መመዝገብ የጀመሩ ለውጦች ጉልህና ይበልጥ ተጠናክረው ሊቀጥሉ የሚገባችው መሆኑንም የገመገመው ኮሚቴው፥ በፖለቲካው መስክ የዲሞክራሲ ምህዳሩን ለማስፋት ታራሚዎችን ከእስር ከመፍታት ጀምሮ፣ የትጥቅ ትግል ያካሂዱ የነበሩ የተለያዩ ድርጅቶች የትጥቅ ትግላቸውን በማቆም በሰላማዊ መንገድ እንዲታገሉ በውይይትና በድርድር መተማመን በመፍጠር ወደ ሀገራቸው እንዲገቡ የተሠሩ ሥራዎች፣ ህዝቡ ያለምንም መሸማቀቅ ሀሳቡን በተለያየ መንገድ በነፃነት ማራመድ የሚችልበት ሁኔታ መፈጠሩ፣ የመንግሥትን ሚዲያን ጨምሮ በሌሎች ሚዲያዎችም የተለያዩ ሀሳቦች በነፃነት የሚንሸራሸሩበት ሁኔታ መጀመሩ፣ ተዘግተው የነበሩ ድረ–ገፆች መከፈታቸው የዲሞክራሲ ምህዳሩን ለማስፋት ዓይነተኛ ሚና መጫወታቸውን ገምግሟል፡፡
ለዜጎች ዋጋና ክብር በመስጠት ከሀገር ውስጥ ባሻገር በጎረቤት ሀገራትና በመካከለኛውምስራቅ ዜጎቻችን ከእስር እንዲፈቱና የነፃነት አየር እንዲተነፍሱ መደረጉ፣ የፖለቲካ ምህዳሩን አጥብበዋል በሚል በተደጋጋሚ ከህዝብ ቅሬታ የሚቀርብባቸውን ህጎች ህዝብንና የመስኩን ሙያተኞች ባሳተፈ መልኩ ለማሻሻል የተጀመረው ሥራ ተጠናክረው መቀጠል ያለባቸው ስኬቶች መሆናቸውን ስራ አስፈፃሚው ካያቸዉ ጉዳዮች አንዱ ነዉ ብሏል በመግለጫው፡፡
በሰብአዊ መብት አያያዝ አስከፊ ችግር የነበረባቸው የማረሚያ ቤቶች እና ሌሎች የፀጥታና ህግ አስከባሪ ተቋማት ሪፎርም ለማድረግ አመራሮቹን ከመለወጥ ጀምሮ እየተሰራ ያለው ሥራ እንዲሁም ህዝብ በተደጋጋሚ ቅሬታ የሚያነሳባቸው ተቋማት ኃላፊዎችን በማንሳት የተጀመረው የአመራር ሪፎርም የተቀመጠውን አቅጣጫ በመከተል የተፈፀሙ እና ውጤትም ያመጡ መሆናቸውን ሥራ አስፈፃሚው እንዳረጋገጠ ነው የጠቆመው፡፡
ለሦስት ቀናት ይቀጥላል ተብሎ በመጠበቀው በኢህአዴግ 11ኛው ድርጅታዊ ጉባዔ ባለፉት ወራት በማህበራዊ፣ በፖለቲዊም ሆነ በዲፕሎማሲያዊ መስኮች የተገኙ ድሎችን በማስቀጠል ላይ እንደሚመክር ታውቋል ።ከዚሁ ጎን ለጎንም ለውጡን ተመርኩዘው በየቦታው ለሚነሱ ግጭቶች የማያዳግም መፍትሔ ለመስጠት፣ የሀገሪቱን ህዳሴና ዕድገት ለማስቀጠል በሚያስችሉ ጉዳዮች ዙሪያ ይወያያል ተብሎ ይጠበቃል።