ኢ.ፕ.ድ.) አዲስ አበባ፡- በሰው ሰራሽና በተፈጥሮ አደጋ ጉዳት ለደረሰባቸው ከ8 ነጥብ 617 ሚሊዮን በላይ ዜጎች ከ6 ነጥብ 5 ቢሊዮን ብር በላይ እንደሚያስፈልግ የብሔራዊ የአደጋ ስጋት አመራር ኮሚሽን አስታወቀ። የኮሚሽኑ ምክትል ኮሚሽነር ዳመነ ዳሮታ፤ ዳሸን ባንክ በአገሪቱ በተለያዩ አካባቢዎች እርዳታ ለሚፈልጉ ዜጎች ያደረገውን የአምስት ሚሊዮን ብር ድጋፍ ትናንት ሲቀበሉ እንደተናገሩት፤ ከእርዳታ ፈላጊዎቹ መካከል ሰባት ነጥብ ስምንት ሚሊዮን የሚሆኑት በድርቅ፣ በመሬት መንሸራተት፣ በጎርፍና ተያያዥ የተፈጥሮ አደጋ ክስተቶች ለችግር የተጋለጡ ሲሆን፤ የተቀሩት በሰው ሰራሽ ግጭት ለእርዳታ የተዳረጉ ናቸው፡፡ ከዳሸን ባንክ የተሰጠው ገንዘብ በሰው ሰራሽና በተፈጥሮ አደጋ ለተጎዱ ዜጎች ለምግብና ለማቋቋሚያ እንደሚውል ምክትል ኮሚሽነሩ ጠቁመው፤ በሰው ሰራሽ የሚፈጠሩት ሁሉም ግጭቶች በመነጋገር መፍታት እየተቻለ ባለመስከን ዜጎችና አገር ዋጋ እየከፈሉ ነው ብለዋል። መንግሥት ችግሩ ከመከሰቱ በፊት የመከላከል ሥራ እንደሚሰራ ምክትል ኮሚሽነሩ ተናግረዋል፡፡ ሆኖም ችግሮች ተከስተው እርዳታና ድጋፍ የግድ ሲሆን ከውጭና ከአገር ውስጥ ለጋሾች ለዜጎች እርዳታ ይደረጋል። እርዳታ የማይገኝ ከሆነ መንግሥት የጀመራቸውን ፕሮጀክቶች አቁሞ የዜጎች ሕይወት ላይ አደጋ እንዳይደርስ እንደሚሰራም ነው የተናገሩት። ምክትል ኮሚሽነሩ እንዳሉት፤ ዳሸን ባንክ ያደረገው ድጋፍ ሕዝባዊ ወገንተኝነትን ነው፡፡ ሌሎች ድርጅቶችም የዳሸን ባንክ ፈለግ ሊከተሉ ይገባል፡፡ ባንኩ ያደረገው ድጋፍ ለተረጂዎች በአግባቡ መድረሱን ባንኩ እንዲያረጋግጥ ይደረጋል፡፡ የዳሸን ባንክ ፕሬዚዳንት አቶ አስፋው ዓለሙ፤ ባለፉት 22 ዓመታት ባንኩ አገልግሎት ሲሰጥ ሕዝቡ የኋላው ደጀን እንደነበር ተናግረዋል፡፡ የሕዝብን ደጀንነት በማሰብ በየዓመቱ ለሕዝብ ድጋፍ እንደሚያርግ ጠቁመው፤ ዘንድሮ ካለፉት ዓመታት በተለየ በተለያዩ አካባቢዎች ዜጎች እርዳታ ስለሚያስፈልጋቸው ባንኩ በታሪኩ በአንድ ጊዜ ትልቅ ዕርዳታ ለማድረግ በባንኩ ዳይሬክተሮች ቦርድና ማኔጅመንት በማስወሰን ስጦታው ተበርክቷል ብለዋል። ባንኩ ከተመሰረተ ጊዜ ጀምሮ ለቀይ መስቀል፣ ለልብ ህሙማን ማዕከል፣ ለካንሰር ህሙማን፣ ለመቄዶንያ፣ ለሙዳይ በጎ አድራጎት ድርጅት፣ በጣና ላይ የእምቦጮ አረምን ለማጥፋትና ሌሎች የበጎ አድራጎት ድርጅቶች እስከ 49 ሚሊዮን ብር የሚደርስ ገንዘብ በልገሳ መስጠቱ ተመልክቷል፡፡