Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

“ቆንጆዎቹ” ለምን አልተወለዱም?

0 8,372

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

“ቆንጆዎቹ” ለምን አልተወለዱም?

                                                           እምአዕላፍ ህሩይ

 

“…ሀገራችን ውስጥ “ቆንጆዎቹ” ተወልደዋል። “ቆንጆዎቹ” ከሀገራቸው አልፈው አፍሪካንም “በቁንጅናቸው” ያነጿታል። ያኔም፤ አፍሪካዊ ነፃነት፣ አንድነት፣ ዕድገትና ተምሳሌትነት ከፍ ብለው በዓለም ፊት ይታያሉ።…”

 

የዚህ ፅሑፍ አንባቢያን “ሰርቅ ዳ.”ን የምታውቁት ከሆነ እሰየው ነው። ካላወቃችሁት ግን፤ እኔ ላስተዋውቃችሁ። በብዕር ስሙ “ሰርቅ ዳ.” የሚሰኘውና በትክክለኛ መጠሪያው ዳንኤል ጎበና የሚባለው ደራሲ፤ “ቆንጆዎቹ” እና “የቃየን መስዋዕት” የተሰኙ ሁለት ልቦለድ መፅሐፎችን ለሀገራችን አንባቢያን ያበረከተ ነው። በተለይ የበኩር ስራው የሆነው “ቆንጆዎቹ” የተሰኘው ልቦለድ (የዛሬ 23 ዓመት ገደማ የተፃፈ ነው)፤ የፈጠራ ስራ ይሁን እንጂ፣ ከገሃዱ ዓለም ነፀብራቅነቱ ባሻገር ወደ እውነታው ያጋደለ ይመስለኛል። ምክንያቱም በዚህ መፅሐፍ ላይ የተነሱት አፍሪካዊ ጭብጦች በእውኑ ዓለም የፖለቲካ ዓለም ውስጥ የሚታዩ ስለሆኑ ነው።

እ.ኤ.አ በ1968 ዓ.ም በጋናዊው ዕውቅ ፀሐፊ ኤ.ኬ አርማህ በተሰናዳው “The beautiful ones are not yet born” (ቆንጆዎቹ ገና አልተወለዱም) ልቦለድን እንደ ማንፀሪያ የሚያነሳው “ቆንጆዎቹ” መፅሐፍ፤ ደራሲ አርማህ “ቆንጆዎቹ ገና አልተወለዱም፣ ሲወለዱ ገና ነፃ ያወጡናል” በማለት የሚያነሳውን ጭብጥ ለመቃወም የሚሞክር ነው። ደራሲ ሰርቅ ዳ.፤ በወቅቱ የአፍሪካ ችግር ላይ ይስማማል። በአፍሪካ የውስጥ ጉዳይም የምዕራባዊያን ቀጥተኛና ተዘዋዋሪ ጣልቃ ገብነት መኖሩን ያምናል።

ዳሩ ግን አስተሳሰቡ በጭብጥነት ጠቅለል ተደርጎ ሲታይ፤ ‘ቆንጆዎች አሉን፣ ነገር ግን እነርሱን ማሳደግ አልቻልንም’ የሚል አንድምታን የያዘ ነው። ጉዳዩን ኢትዮጵያ ትናንት ከነበሯት የእነ አክሱምን፣ ላሊበላን፣ ጎንደርን…ወዘተ. የኋላ ታሪካዊ ሃብቶቻችንን አኳያ ተመልክቶም፤ እነዚያን የገናናነታችንን ምኩራብ አስጠብቀን ወደፊት መጓዝ አልቻልንም ይላል። ወደፊት መራመድ አልቻልንም። በዚህም “ሁላችንም ቆንጆዎች ነን” የሚል ሃሳብን ለአንባቢያን ለማስጨበጥ የሞከረ ይመስለኛል።

እኔም በዚህ ሃሳቡ እስማማለሁ። እንዲያውም ሁሉም የየዘመኑ “ቆንጆዎች” አሉት እላለሁ። ደራሲ ኤ.ኬ. አርማህ የአፍሪካ ችግሮች ብሎ ያነሳቸው የውስጥና የውጭ ተግዳሮቶች ትክከል ቢሆኑም፤ “ቆንጆዎቹ ገና ተወልደው ነፃ ያወጡናል” የሚለው አባባል ትክከል ነው ብዬ አላምንም። ሰርቅ ዳ. “ሁላችንም ቆንጆዎች ነን” እንዳለው፤ ሁሉም የየዘመኑ “ቆንጆ” ነው። እናም ይህ ዘመን፤ ከራስ አልፎ ለአፍሪካ በቂ ቀመር የተሰነቀበት ነው ብዬም አስባለሁ። በየዘመኑ ሁሉም የየራሱን “ቆንጆ” ልሂቅ ይወልዳል። እነዚህ በአዕምሮ የጎለመሱ የየዘመናቱ “ቆንጆዎች” ደግሞ ከሀገራቸው አልፈው፤ ለአህጉሪቱ ብሎም ለዓለማችን መፃዒ ዕድል እውነተኛ መሲህ መሆን የሚችሉ ስለመሆናቸው መጠራጠር አይገባም። በፍልስፍና፣ በሳይንስና ቴክኖሎጂ እንዲሁም ሌሎች ዛሬ የምናነሳቸው ወይም የምንጠቀምባቸው ጉዳዩች የትናንት ግኝቶች መሆናቸውን ልብ ማለት ይገባናል።

ታዲያ እዚህ ላይ “ቆንጆዎቹ ለምን አልተወለዱም?” የሚል ጥያቄ ብናነሳ፤ “ቆንጆዎቹ” ለመወለዳቸው ህልቆ መሳፍርት እማኝነትን መጥቀስ ይቻላል። ግና መመልከት ያለብን ከውስጥ ወደ ውጭ በመሆኑ፤ ሩቅ መሄድ የሚያስፈልግ አይመስለኝም። ከዚህችው ቀዳሚ ሀገራችን ተነስተን ወደ አፍሪካችን እናቀናለን። ርግጥ በእኔ እምነት፤ ምናልባትም የሰርቅ ዳ. “ቆንጆዎቹ” መፅሐፍ፤ ከነባራዊ ሁኔታችን አንፃር በ20 ዓመት በላይ የቀደመ ይመስለኛል። ይህም ነገሮችን ከውስጥ ወደ ውጭ ለማየት ዕድል ይሰጠናል ብዬ አስባለሁ።

ታዲያ ሀገራችንን በዚህ የእሳቤ ደርዝ ስንመለከታት፤ በአሁኑ ወቅት ኢትዮጵያችን ውስጥ “በቲም ለማ” አማካኝነት እየተከናወነ ያለው የመደመር ፍልስፍና መነሻው ሀገራዊ ይሁን እንጂ፤ እግሩን ሰድዶ ምስራቅ አፍሪካዊና አፍሪካዊ እንዲሁም ዓለም አቀፋዊ ሆኖ የማይዳረስበት ምክንያት ያለ አይመስለኝም። አዲሶቹ የሀገራችን ስትራቴጂክ አመራሮች ወይም በእኔ እይታ “ቆንጆዎቹ” የምላቸው፤ ዛሬን ብቻ ይዘው የተነሱ አይደሉም። ትናንትን አስታውሰውና እንደ መሰረት ቆጥረው ወደ ቀድሞው ገናናነታችን መመለስ ይኖርብናል እያሉን ነው። በትናንት ላይ ተንደርድረን ወደ ነገ መትመም አለብን እያሉን ነው። አንድ ቦታ ተቸክለን መቆም የለብንምም እያሉን ነው።…

ትናንትን እንደ እርሾ ይዘን፣ ዛሬን ከወቅታዊ ዓለማዊ ሁኔታዎች ጋር እያጣጠምን የነገዋን ውብ ሀገር እንስራ እያሉን ነው። አንድ ሆነን እጅ ለእጅ በመያያዝ የጋራ ቤታችን የሆነችውን ኢትዮጵያን እንገንባ እያሉን ነው። ልዩነት፣ ጥላቻ፣ መናቆርና ክፋት ሀገርን እንደ አረም ተብትቦ የሚይዙ ወረርሽኞች ስለሆኑ፤ እነርሱን ከልተን ፍቅርን፣ አንድነትን፣ ይቅርታንና መቻቻልን በማንገስ ኢትዮጵያዊ ታሪካችንን በአዲስ ብራና ላይ እንፃፍ እያሉን ነው።

ርግጥ ከዚህ በላይ የልዕለ ሃሳብ “ቁንጅና” ከወዴትም የሚመጣ አይመስለኝም።…እናም የዘመናችን “ቆንጆዎች” አጠገባችን ስለሚገኙ፤ “ለምን አልተወለዱም?” ብለን ልንጠይቅ አንችልም። ወይም የመጠየቂያው ዘመናችን አክትሟል። አዎ! እንደ ኤ.ኬ. አርማህ ‘ገና ስለሚወለዱ እንጠብቃቸውና ነፃ ያወጡናል’ ብለን ልናስብ የምንችል አይመስለኝም። ለእኔ በዶክተር አብይ አህመድ የሚመራው “ቲም ለማ” የዘመናችን የአስተሳሰብ ልህቀት “ቆንጆ” ነው—ከሀገር እስከ አህጉር የዘለቀ ፍልስፍና ባለቤት ነውና። እናም ይህን “ቲም” ከመከተል ውጭ ሌላ አማራጭ ሊኖረን የሚችል አይመስለኝም—እኛም ሆንን ሌሎች።

ርግጥ ኢትዮጵያዊ አንድነትን መፍጠር የሚያስችለው የእኛዎቹ “ቆንጆዎች” አዲስ እሳቤ፤ ውስጣዊ አንድነታችንን በማጠናከር የቀጣናው ሀገራትም ወደ አንድነት እንዲመጡ የሚያስችል ነው። የመደመሩ ቀመር የቀጣናው ሀገራት ሁሉንም የሚያበለፅገውን የጋራ የዕድገት ዝማሬ እንዲያቀነቅኑ ከማስቻል በላይ ኢትዮጵያ እንደ ትናንቱ ዛሬም አፍሪካዊ ሚናዋን እንድትወጣ የሚያስችላት ነው። ታዲያ በቅድሚያ እኛ አንድ መሆን ይገባናል፤ ልዩነቶች ቢኖሩም እንኳን በመከባበርና በሰለጠነ መንገድ መፍታት የምንችልበትን ሁኔታን መፍጠር ይኖርብናል፤ “ቆንጆዎቹ ተወልደዋል፤ ወደ ነፃነት መስመርም መርተውናል” የሚል አስተሳሰብን በመያዝ የቀጣናው አርአያነታችንን ቀዳሚው ትኩረታችን ሊሆን ይገባል—እኛ ያልሆንነውን ሌሎች እንዲሆኑ መጠየቅ አሊያም ማግባባት አይቻልምና።

እንደ እውነቱ ከሆነ፤ የሀገሬ የአዲስ አስተሳሰብ “ቁንጅና” ፋና ወጊዎች ወደ ነፃነት መንገድ እየወሰዱን ነው። ትናንት በውስጥም ይሁን በውጭ ተፅዕኖዎች ሳቢያ ያጣነውን ሁለንተናዊ ነፃነታችንን አስመልሰውልናል። ታዲያ ይህ የሀገር ውስጥ ስኬታማ የነፃነት ምልሰት፤ ወደ ቀጣናው ሀገራት እንደ ሰደድ እሳት ቢዛመት ከጦርነትና ከሰቆቃ እንዲሁም ከረሃብና ከድንቁርና የሚያወጣን መላ ለመሆኑ ጥርጥር የለውም።

ደራሲ ኤ.ኬ አርማህ በእነዚያ የቅኝ ግዛት ዓመታት ውስጥ እንዳለው፤ አፍሪካ የቆሻሻና የሙስና መናኸሪያ እንዲሁም የእጅ አዙር ጦርነት ሰለባን ታሪካችንን መቀየር የሚችል ነው—የእኛዎቹ “ቆንጆዎች” አዲስ አስተሳሰብ። እናም “የቆንጆዎቹ” እሳቤ ቁንጅና፤ የምስራቅ አፍሪካ ሀገራት ለዘመናት ከሚታወቁበት የረሃብና የጦርነት አደጋ ሊታደግ የሚችል አዲስ ቀመር ለመሆኑ በርግጠኝነት መናገር የሚቻል ይመስለኛል። ሀገራቱም ራሳቸውን “በቆንጆዎቹ” የመደመር ፍልስፍና ውስጥ ማስገባት ከቻሉ፤ ታሪካቸውን በራሳቸው መቀየር እንደሚችሉ ጥቂት ዓመታቶችን ብቻ በመጠበቅ ማረጋገጥ ይችላሉ። ያኔም፤ “ቆንጆዎቹ” ኢትዮጵያዊ ውስጥ በጊዜያቸው መወለዳቸውን ማረጋገጥ ይችላሉ ብዬ አምናለሁ።

የምስራቅ አፍሪካ ክፍለ-አህጉራዊ የአንድነት ጥንካሬ የአፍሪካን ከብረት የሚልቅ ፈርጣማ ኢኮኖሚያዊ ክንድን የሚያፈረጥምና ወደ ውህደት ለማምራት መደላድል ለመሆኑ በርግጠኝነት መናገርም የሚቻል ይመስለኛል። የቀጣናው አንድነት አህጉሪቱ ያሏትን አምስት ያህል ቀጣናዎች ወደ አንድነት ማምጣቱ አይቀሬ ነው። አፍሪካዊያን ችግሮቻቸውን በጋራ በመወጣት፣ የዴሞክራሲ ቋጠሮቻቸውን ያለ ማንም ጣልቃ ገብነት በራሳቸው በመፍታት እንዲሁም በራሳቸው መንገድ ሄደው “ቆንጆዎች” መሆናቸውን ለተቀረው ዓለም የሚያሳዩበት ጊዜ ቅርብ ይሆናል።

ታዲያ ይህን እውን ለማድረግ ደራሲ አርማህ “ገና ይወለዳሉ” ያላቸው የሀገራችን የአዲስ ዝማሬ ልሂቃን “ቆንጆዎች” የመደመር ፍልስፍናን ይዘው አፍሪካን ለማቅናት መነሳታቸውን መገንዘብ ይኖርባቸዋል። የመደመር ፍልስፍናውንም በመከተል፤ በሰነዳቸው ላይ ያሰፈሩትንና እ.ኤ.አ በ2063 ዓ.ም እውን እናደርጋለን ብለው ወዳቀዱት የውህደት ህልማቸው ማምራት እንዲችሉ ያደርጋቸዋል። እናም እንደ አርማህ ዓይነት አፍሪካዊ ደራሲዎች እንዲሁም አፍሪካዊያን ፖለቲከኞችና ምሁራን፤ “ቆንጆዎቹ ለምን አልተወለዱም?” በማለት ለሚያነሷቸው ጥያቄዎች፤ ወትሮም የአፍሪካዊያን ቀንዲል በሆነችው ሀገራችን ውስጥ “ቲም ለማ” የተሰኘ የመደመር ፍልስፍና አራማጅ “የቆንጆዎች” የዛሬ መንፈቅ አካባቢ ብቅ ማለቱን መገንዘብ ይኖርባቸዋል።

አፍሪካዊያን “የተባበረች አፍሪካን” (United States of Africa) ቢበዛ በራሳቸው የጊዜ ሰሌዳ (እ.ኤ.አ በ2063 ዓ.ም) ለማሳካት ካሰቡ፤ መፍትሔው ይኸው የመደመር ፍልስፍና መሆኑን ማጤን አለባቸው። ለአፍሪካዊ ችግር አፍሪካዊ መፍትሔ በመሆኑም፤ በፍቅርና በአንድነት እንዲሁም በጋራ ተጠቃሚነት ላይ ያተኮረውና ቀጣናዊ ምጣኔ ሃብታዊ ውህደትን ለማምጣት ያለመው ብሎም አፍሪካዊ ውህደትን መፍጠር የሚችለውን “የቲም ለማን” ፍልስፍና መያዝ የግድ የሚል ይመስለኛል።

አዎ! ምስጋና ሁሌም ለአፍሪካዊያን ቀዳሚ ተምሳሌት ለምትሆነው ኢትዮጵያችን ይግባትና “ቆንጆዎቹ” እዚሁ እኛው ውስጥ ተወልደዋል። ‘ለምን አልተወለዱም ወይም ገና ይወለዳሉ’ የሚለው የቅኝ ግዛት ዘመን አስተሳሰብ በአዲስ ኢትዮጵያዊ ፍልስፍና ተሽሯል። ኢትዮጵያ በምትባል ቀዳሚ ሀገር ውሰጥ “ቲም ለማ” የተሰኘ ቡድን የአዲስ አስተሳሰብ መልህቅ ተጥሏል። ርግጥም ሀገራችን ውስጥ “ቆንጆዎቹ” ተወልደዋል። “ቆንጆዎቹ” ከሀገራቸው አልፈው አፍሪካንም “በቁንጅናቸው” ያነጿታል። ያኔም፤ አፍሪካዊ ነፃነት፣ አንድነት፣ ዕድገትና ተምሳሌትነት ከፍ ብለው በዓለም ፊት ይታያሉ። ሰናይ ጊዜ።  

    

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy