Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

በህይወት ውርርድ፣ ሌላውን ማትረፍ?

1 16,140

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

በህይወት ውርርድ ሌላውን ማትረፍ?

                                                           እምአዕላፍ ህሩይ

 

“…ኧረ ለመሆኑ የገዛ ህይወታችንን ለሌሎች መስዋዕት ለማድረግ የምናስብ ስንቶቻችን ነን?፣ ስንቶቻችንስ ነን—አንድ የታጠቀ አካልን የተሳሳተ መንገድ እያወቅን በሳቅና በፈገግታ ለመሸኘት የምናስበው?፣ እንዲህ ዓይነቱን ለውጥን የመቀልበስ ፍላጎት እያወቅን ሁሉም ነገር ህግና ስርዓቱን ጠብቆ እንዲጓዝ ለማድረግ የምናስብስና የምንጠይቅ ስንቶቻችን እንሆን?…”

 

መስከረም 30 ቀን 2011 ዓ.ም ከነትጥቃቸው ወደ ቤተ መንግስት “ደመወዝ ለመጠየቅ ነው የሄዱት” ተብሎ የተነገረን የሁለተኛ ሬጅመንት ኮማንዶ አባላት፤ የጉዳዩ አነሳሽ ፍላጎት ኢ-ህገ መንግስታዊና አደገኛ ከመሆኑ በላይ ለውጡን ለመቀልበስ እንደሆነ ጠቅላይ ሚነስትር ዶክተር አብይ አህመድ ዛሬ ከፓርላማ አባላት የቀረበላቸውን ጥያቄ ሲመልሱ አድምጠናል። እኔ በበኩሌ በወቅቱ ሁሉም የሰራዊት አባል ያንን መሰል ያልተገባ ተግባር ለመፈፀም መጥቷል ባይባልም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሁኔታውን ለመቆጣጠር የወሰዱትን ብስለት የታከለበትንና ሙያዊ ብቃትን የጠየቀ የሰከነ አቋም ሳላደንቅ ማለፍ አልሻም።

ዶክተር አብይ በህይወታቸው እየተወራረዱ ጭምር የዜጎችን ህይወት ለመታደግ ወታደርን በወታደራዊ ባህርይና መንፈስ ስሜቱን ለመግራት በመጀመሪያ “በፑሽ አፕ” ስፖርት በሁለተኛ ደረጃ በማወያየት እንዲሁም በስተመጨረሻም ምንም ዓይነት ነገር እንዳልተፈጠረ ዘና ብሎ ለመገናኛ ብዙሃን ቃለ ምልለስ በመስጠት የሌሎቻችንን ህይወት ለማትረፍ ያደረጉትን ጥረት ሳስብ እኔ በግሌ እውነትም ጠቅላይ ሚኒስትሩ በአንድ ወቅት “ለህዝብ መሞት ክብር ነው” በማለት የተናገሩት ንግግርን እንዳስታውስ አድርጎኛል።

ማስታወስ ብቻም ሳይሆን ሁሌም በተናገሩበት ቦታ ያሉ ህዝብ ወዳድ መሪ በመሆናቸው ያለኝን አክብሮት ከተቀመጥኩበት በመነሳት ባርኔጣዬን ከፍ በማድረግ ለመግለፅ እገደዳለሁ። ርግጥ በዚያ ቦታ ላይ የተቀመጡት በአንድ ወቅት የሰራዊቱ ከፍተኛ መኮንን የነበሩት ዶክተር አብይ አህመድ ባይሆኑ ኖሮ ሊፈጠር የሚችለውን ውጥንቅጥ ለመገመት ቀላል አይመስለኝም። አዎ! የሚፈጠረው ነገር እርስ በርሳችን መበላላትና እንደ ሀገር የመቀጠላችን ጉዳይም በሰለለ ክር ጫፍ ላይ እንደተንጠለጠለ ዳቦ መቼ እንደሚበጠስ የማይታወቅ ይሆን ነበር ብዬ አስባለሁ። ወገንንና ሀገርን ከአደጋ የሚታደግ መሪ ይሏል እንዲህ ነው!

በገዛ ህይወት መወራረድ ቀላል ጉዳይ አይደለም። ከውስጣዊ ስሜት በመነጨ መልኩ ህዝባወ ወገንተኛ መሆንን ይጠይቃል። “እሾህን በእሾህ” ከሚባል መጥፎ አመለካካት መላቀቅን ይጠይቃል። እውነት…እውነቱን እንነጋገር ከተባለ ኧረ ለመሆኑ የገዛ ህይወታችንን ለሌሎች መስዋዕት ለማድረግ የምናስብ ስንቶቻችን ነን? ስንቶቻችንስ ነን—አንድ የታጠቀ አካልን የተሳሳተ መንገድ እያወቅን በሳቅና በፈገግታ ለመሸኘት የምናስበው? እንዲህ ዓይነት ለውጥን የመቀልበስ ፍላጎት እያወቅን ሁሉም ነገር ህግና ስርዓቱን ጠብቆ እንዲጓዝ ለማድረግ የምናስብስና የምንጠይቅ ስንቶቻችን እንሆን?…እንደ እውነቱ ከሆነ አብዛኛዎቻችን እንደ ዶክተር አብይ ስክነት በተሞላበት ሁኔታ ችግሩን ለመመልከት የምንሞክር እንኳን አይመስለኝም። ወይም አናደርገውም።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ያደረጉት ግን፤ በራሳቸው ህይወት እየተወራረዱም ቢሆን፤ የተፈጠረውን ጉዳይ በጥበብና በሳይንሳዊ መንገድ መያዝ እንዲሁም በሰከነ ሁኔታ በማርገብ ሌሎቻችንን መታደግ ነው። ከዚያም በኋላ ቢሆን፤ ሁሉም ነገሮች ወደ ነበሩበት ቦታቸው እንዲመለሱና በህጋዊ መንገድ እንዲፈፀሙ ነው ያደረጉ። ይህ የዶክተር አብይ አህመድ ስክነት የተሞላበት የመፍትሔ አሰጣጥ ጥበብ በአንድ ወቅት የአንድ ሀገር ንጉስ “ሞተሃል ተብለሃል! ሞተሃል! በቃ!” አሉት እንደተባለው ተረት ዓይነት ህግና ስርዓትን የተቃረ አለመሆኑ የህይወት ውርርዱ ህዝብን ለማዳን የተሰጠን ስልጣን በትክክል ለመፈፀሙ ማረጋገጫ ሆኖ መቅረብ የሚችል ይመስለኛል።

‘ለመሆኑ ሞተሃል በቃ! የሚለው ተረት ምን የሚል ነው?’ ብሎ ለሚጠይቅ አንባቢ ተረቱን እንዲህ አስታውሳለሁ።…አንድ በጠላቶቹ በእጅጉ ይፈለግ የነበረ ግለሰብ ነበር። ከዕለታት አንድ ቀን ጠላቶቹ መንገድ ላይ ጠብቀው ይደበድቡታል። ቅጥቅን አድርገው ስለደበደቡትም ሰውዬው ራሱን ስቶ ዝልፍልፍ ይልባቸዋል። በዚህን ወቅት የተደናገጡት ሰዎች ‘ጉድ ሆንን እኮ!’ ይሉና በኬሻ ጠቅልለው በቃሬዛ ተሸክመው ጫካ ውስጥ ሊጥሉት ይስማማሉ። ዓላማቸውም ግለሰቡን ማንም ሳያያቸው ጫካ ጥለው በአውሬ ማስበላት ነበር። ታዲያ በጉዟቸው ላይ በድንገት የሀገሪቱ ንጉስ ለአደን ወጥተው ኖሮ ዱር ውስጥ ያገኟቸውና “እናንተ ምንድነው የተሸከማችሁት?” ሲሉ ይጠይቋቸዋል። ሰዎቹም በመደናገጥ “ንጉስ ሆይ! አንድ ወንድማችን ሞቶብን አስከሬኑን ቤተሰቦቹ ዘንድ ለማድረስ እየሄድን ነው” በማለት ይመልሳሉ።

በኬሻ የተጠቀለለው ምስኪን ግን፤ በመንገድ ላይ ነፍስ ዘርቶ ኖሮ፤ በኃይል በመንፈራገጥ አለመሞቱን ንጉሱ እንዲያውቁለት አደረገ። ይህን ሁኔታ የተመለከቱት ንጉሱም፤ “እናንተ ምንድር ነው የምትሉት? ይኸው እየተንፈራገጠ ያለውን ሰው በድን ነው ትሉኛላችሁ እንዴ?፣ የሞተ ሰው እንዴት ይንፈራገጣል?” ሲሉ ይጠይቋቸዋል። ሰዎቹም፤ “ኧረ ሞቷል ንጉስ ሆይ!” ብለው ቃሬዛቸውን መሬት ላይ አስቀመጡ። በዚህን ጊዜ ሲንፈራገጥ የነበረው ሰውዬ እንደምንም ተፍጨርጭሮ ቀና ብሎ አንገቱን አወጣና የሞት ሞቱን “ኧረ ንጉስ ሆይ! አልሞትኩም። እነርሱ ግን በቁሜ ሊቀብሩኝ ነው” በማለት ተናገረ። በዚህን ጊዜ ንጉሱ ለአደን የፈለጉት እንስሳ ድንገት ከፊታቸው ውልብ ሲል በማየታቸው፤ “ሞተሃል ተብለሃል! ሞተሃል በቃ!” አሉና ጠብ-መንጃቸውን አቀባብለውና ፈረሳቸውን ኮርኩረው ሽምጥ ጋለቡ። በዚህም የህዝብ አደራ የተቀበሉት ንጉስ፤ ያልሞተውን ሰው በዓይናቸው እያዩ እንደ ጠላቶቹ ሞት ፈረዱበት ይባላል።…

ታዲያ ከዚህ ተረት የምንማረው ነገር ቢኖር ንጉሱ የህዝብ አደራ እያለባቸውና ፍትህን ለተጎጂው ወገን መስጠት ሲገባቸው ባልሰከነ መንፈስ የሰጡት ፍርደ ገምድልነት ተገቢ አለመሆኑን ነው። አንድን ሀገር የሚመራ ግለሰብ ነገሮችን በሚያከናውንበት ወቅት የራስን ስሜት ተከትሎ ሳይሆን የህዝብን ፍላጎት በመመልከት ህዝቡን ማዳን ይኖርበታል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ የታጠቁ ወታደሮችን የያዙበት አግባብም በራሳቸው ህይወት ተወራርደው ህዝብን ማትረፍ ነው።

አዎ! ዶክተር አብይ አህመድ በሰከነ ሁኔታና ሳይንሳዊ በሆነ መንገድ የታጠቁ ወታደሮችን ውስጣዊ ቁጣ በማብረድ ወታደሮቹ የኋላ ኋላ ተፀፅተው ይቅርታ እንዲጠይቁና ያንን ኢ-ህገ መንግስታዊና አደገኛ ተግባር እንዲፈፅሙ ያደረጓቸውን ሰዎች ሳይቀር እንዲጠቁሙ እንዲያደርጉ ከማድረግ ባለፈ ህዝባቸውንና ሀገራቸውን መታደጋቸው (በራሳቸው ህይወት እየተወራረዱ) ያላቸውን የህዝብ ወገንተኝነት አሳይተዋል። የሀገር መሪ መሆን ማለት ልክ እንደ ንጉሱ የራስን ስሜት በመከተል ሳይሆን ራስን ለህዝብ አሳልፎ መስጠትንና እውነተኛ የህዝብ ልጅ መሆንን ጭምር የሚጠይቅ ነው። የገዛ ህይወትን ለውርርድ ጭምር በማቅረብ ለሌሎች መስዋዕት መሆንንም ይጠይቃል። ርግጥ እንዲህ ዓይነቱን ስብዕና የሚታደሉት ጥቂቶች ናቸው። ታዲያ ለዶክተር አብይ ያለኝን ከበሬታ ሁሌም ከመቀመጫዬ ብድግ ብዬ በመነሳት የምገልፀው ከዚህ ከሁሉም ነገር ቅድሚያ ለህዝብ ካላቸው ከፍተኛ ፍቅር ተነስቼ መሆኑ ልብ ሊባልልኝ ይገባል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ በዛሬው ቀን የተቋማትን አፈፃፀም ከአቅም ግንባታ አኳያ አያይዘው ያነሱት ነጥብም ትክክል ይመስለኛል። በቅርቡ በዚሁ ድረ ገፅ ላይ እጅግ በመገረምና በአንዳንድ ሚዲያዎች ውስጥ ሆነው የታጣቂዎቹን ወታደሮች ተግባር በሌለ ማንነቱ ለማጦዝ የሞከሩ “ተንታኞችን” እንደ ዜጋ ለመምከር በሞከርኩበት “የአጋች ታጋች ድራማ?!—እንዴት?” በሚለው ፅሑፌ ላይ ሰራዊቱ ህገ መንግስቱን በቅድሚያ ራሱ ማክበር ለጥቆም ማስከበር እንደሚኖርበት ገልጫለሁ።

ህግና ስርዓት በማንኛውም ሀገር ሰራዊት ውስጥ በፅናት መከበር ያለበት ጉዳይ መሆኑንም አስረድቻለሁ። ለዚህም በሰራዊቱ ውስጥ በየደረጃው ህገ መንግስታዊ እምነትን አሁንም በሚገባ የሚያጎለብትና በጥንካሬ የሚያስፈፅም እንዲሁም ሰራዊቱን እንደ በአንድ እስትንፋስ እንዲንቀሳቀስ የሚያደርግ ጠንካራ የIndoctrination (የስርፀት ስራ) ወሳኝ መሆኑን አመላክቻለሁ። እናም ከጋዜጣ ከሬዲዩና ከቴሌቪዥን ስራዎች ባለፈ ባለፈ የእርስ በርስ ውስጣዊ መገነባባት እጅግ መጠንከር ይኖርበታል እላለሁ። ተቋሙ በማህበራዊ ሚዲያዎች ራሱንና አፈፃፀሙን በግልፅ በማሳየት ገፅታውን ይበልጥ ማጎልበት እንደሚኖርበት ሳልጠቁም አላልፍም።

ርግጥ 240 የሰራዊት አባላት በአንድነት ተነጋግረውና አቋም ይዘው መሄዳቸው ብዙም የሚደንቅ አይደለም። ምክንያቱም ሰራዊት በአንድ ላይ የሚኖር የተደራጀ አካል እንደመሆኑ መጠን እንዲህ ዓይነቱን መጥፎ አቋም ጭምር ለመያዝ ስለሚችል ነው። ዳሩ ግን እንኳንስ ይህን ያህል ሰው ቀርቶ አምስትና ስድስት ሰው ቢሆንም ለኢ-ህገ መንግስታዊ ጉዳይ መሰለፍ ያለበት አይመስለኝም። ያም ሆኖ ይህን የሰራዊቱን ጠንካራ አደረጃጀት ህገ መንግስቱን ለማክበር መጠቀም አንደሚቻል መረዳት ተገቢ ነው ብዬ አምናለሁ። በመጨረሻም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከታጠቁት ወታደሮች አኳያ የተከተሉት በሳልና የሰከነ አስተውሎትን የተከተለ መንገድ የህዝብን ደህንነት ያስጠበቀ በመሆኑ ታላቅ ስራ መሆኑን ለመግለፅ እወዳለሁ። ሰናይ ጊዜ።

      

  1. Mulugeta Andargie says

    ቃላትን ከቃላት ኣጋጭቶ
    ቋያ ፍም የሌለው ሌሊት ኣብርቶ
    ፈትለክ ይላል ሕዝበኛን ማግዶና ፎትቶ
    ውነት እግዜር ኣለ፣ ለካ
    እዩት ውነት ስትፈካ
    የህዝብ እንባ ሲታበስ፤ በፈገግታ ሲፈካ
    ለካ ኣለህ እንዴ?
    ዋቃ! ላንደፈር በመደዴ!
    እሾ! ብለን ጮኸንም ይሁን በዘዴ
    ኣሹ! እንላለን
    ኣበቃልን!!

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy