Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

በሹም ሽሩ—እነማን ከሰሩ?

2 12,043

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

በሹም ሽሩ—እነማን ከሰሩ?

                                                       እምአዕላፍ ህሩይ

 

“…አቶ መሳይ መኮንን በኦሮሚያ ክልል የተሰጠው የሁለቱ ጄኔራሎች ሹመት በፌዴራል መንግስቱ ውስጥ መደገም ነበረበት በማለት በገደምዳሜው ሊነግሩን የፈለጉትን ሃቅ ፈታ አድርገን ስንመለከተው፤ ትናንት “ኢሳት” እና ባልደረቦቹ በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ እየዘመሩለት የነበረው ‘የሽግግር መንግስት’ ጉዳይ፤ ዛሬም ውሉን ሳይስት በተዘዋዋሪ መንገድ እየተቀነቀነ…”

 

ሰሞነኛው ሹም ሸረት ብዙ ነገር እንድታዘብ አድርጎኛል። ተሿሚዎቹ ኢትዮጵያዊያን እንዳልሆኑ ሁሉ፤ የተለያዩ የማህበራዊ ሚዲያው “ጦረኞች” የጦራቸውን ጫፍ ተገቢ ባልሆነ ቦታ ላይ ሲሰኩት መመልከቴ ትዝብቴን ከፍ ሳያደርገው አልቀረም። ‘እገሌ የእገሌ ብሔረሰብ አባል ስለሆነ ብዙ ኮታ አገኘ’ ከሚለው ብቃትንና የስራ ምዘናን ማዕከል ካላደረገ አስገራሚ ትረካ ጀምሮ፤ “ጦረኞቹ” በዘረኝነት ማዕበል እየተናጡ የራሳቸው የሆነን ሰው ሾመው ያበቁና ያ ሳይሆን ሲቀር የነገር ሾተላቸውን ሲመዙ መመልከት ምን ያህል አሳፋሪ እንደሆነ እንኳን የተረዱት አይመስለኝም። ‘እገሌ የተባለው ብሔረሰብ’ ብዙ ተሹሟል የሚሉት የአሉባልታ “ጦረኞች” ራሳቸው ‘ለምን ከእኔ ወገን አልተሾመም?’ እያሉ እርስ በርሱ የሚጣረስን ጉዳይ ሲጠይቁ፤ እንዲያው ለአመል ያህል እንኳን ሃፍረት ቢጤ ‘ጠቅ!’ የሚያደርጋቸው ዓይነት ሰዎች አይደሉም።

በፌስ ቡክ ላይ የመንጋ ሹመት እንዲሰጥላቸው የሚፈልጉት እኚህ “የምናብ ዓለም ጠቅላይ ሚኒስትሮች”፤ ከራሳቸው ሰው ውጭ ሌላ እንዲሾም የማይፈልጉና እሳቤያቸውም ከታጠሩበት ቡድናዊ ክበብ ከፍ የማይል ነው። ‘ዶክተር አብይ እገሌን ካልሾሙ፤ ምኑን ሹመት ሆነ?’ እያሉ ለምርጫ የሚያቀርቡትን ሰው እንኳን ከፎቶው ውጭ በብቃቱና በለውጥ ሃዋሪያነቱ ፈፅሞ አያውቁትም። ወይም ሊያውቁት አይፈልጉም። እንዲያው ሾላ በድፍን ሆኖ የራሳቸው ክበብ አባል ወይም ቅርበት ያለው ግለሰብ ‘መሾም አለበት’ የሚሉ ራስ-ወለድ ጠቅላይ ሚኒስትሮች ናቸው። ፍላጎታቸው ከታጠሩበት ቡድናዊ አጥር ውጭ ሌላ ነገር መስማትም ይሁን ማየት አለመሻት ነው። “ስንቱን አየነው…?” አለ ዘፋኙ። እውነትም ስንቱን ያለፈው ሹመት ስንቱን የውሸት የለውጥ ሃዋሪያ እንድንታዘብ አደረገን።

‘ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ካቢኔያቸውን ያዋቀሩት በዋነኛነት ብቃትን መሰረት አድርገውና ለውጡን ከማስፈፀም አኳያ ተሿሚዎቹ ያላቸውን አፈፃፀም ከግምት ውስጥ አስገብተው ነው’ ብሎ ለእነዚህ ሰዎች መንገር፤ ከጉንጭ ማልፋት በስተቀር ረብ ያለው ነገር አያስገኝም። “እኔ ብቻ ነኝ ትክክል” በሚል የእውር ድንብር ፖለቲካ ንፍቀ-ክበብ ውስጥ ነዋሪዎች በመሆናቸው ማዳመጥ የሚፈልጉት የራሳቸውን ጩኸት ብቻ ነው። ስለ ሀገርና ስለ ህዝብ የሚያስቡም አይመስሉም። በእውነቱ በአያሌው አሳፋሪዎች ናቸው። እናም በእነርሱ ቦታ የሆነ ሰው፤ እነርሱን ተክቶ ቢያፍር የሚፈረድበት አይመስለኝም—ሰዎቹ “በዘያ ዘመን” የደነቆሩ በመሆናቸው ጠቅላይ ሚኒስትሩም ሆኑ የለውጥ ካቢያኔያቸው የሚሰሩትን እንኳን በቅጡ ለመገንዘብ የሚፈልጉ አይደሉምና—ማን ነበር “በእንቁጣጣሽ ቀን ያበደ፤ ዘፈኑ ሁሉ አበባይሆሽ ነው” ያለው?…ምናልባት እነዚህ የፌስ ቡክ “ሿሚዎችና ሻሪዎች” ሳይሆኑ ይቀሩ ይሆን?…

ያም ሆኖ፤ ከመሰንበቻው በጠቅላይ ሚኒስትሩ አቅራቢነት በፓርላማው በሙሉ ድምፅ የፀደቀው ሹመት አቅምንና የለውጥ አስፈፃሚነት ብቃትን መሰረት ያደረገ ለመሆኑ ተነግሯል። በተለይም አዲስ ከተሾሙት ውስጥ 50 በመቶው ያህሉ ሴቶች መሆናቸው፤ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በተደጋጋሚ ከፓርላማ ይነሳባቸው የነበረውን የሴቶች የመሪነት ጥያቄን ለመመለስ ጥረት ያደረጉበት ነው ማለት ይቻላል። ርግጥም የፓርላማው አባላት ከጀርባቸው የወከሉት እጅግ ከፍተኛ ቁጥር ያለውን ህዝብ እንደመሆኑ መጠን ጥያቄያቸው ሊደመጥና ምላሽ ሊያገኝ ይገባል። የተደረገውም ይኸው ነው።

የሆነ ሆኖ ግን፤ ይህ የ50 በመቶ ስሌት፤ በዋነኛነት የሀገራችንን የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንደራሴዎችን ጥያቄን የመለሰ ሲሆን፤ በሌላ በኩልም፤ ኢትዮጵያ ግማሽ በግማሽ ሚኒስትሮቿ ሴቶች የሆኑባት አፍሪካዊ ሀገር እንድትሆን ያደረጋት ይመስለኛል። ይህም ሀገራችን እንደ ትናንቱ ሁሉ፤ ዛሬም የአፍሪካ መሪ በመሆኗ የምታከናውናቸው ማናቸውም ተግባሮች ሁሉ በአርአያነት ሊጠቀሱ የሚችሉ እንዲሆኑ ያደረገ ክስተት ይመስለኛል። ስለሆነም የኢፌዴሪ መንግስት ግማሽ ካቢኔ ሴቶች እንዲሆኑ መደረጉ፤ ይህንንም አፍሪካዊ ቀዳሚ ሚናችንን ለመወጣት የሚያስችለን መሆኑን መገንዘብ የሚያስፈልግ ይመስለኛል።

ርግጥ ማንኛውም ተግባር ሲከወን ሁሉንም ወገኖች በእኩል ሁኔታ ማርካት አይቻልም። ሆኖም እኔ እስከሚገባኝ ድረስ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ‘እነ እገሌን በካቢኔ አባልነት ባካትት የተያዘውን የልማት ዕቅድ ያሳኩልኛል፤ የተጀመረውንም ለውጥ በተቻለ መጠን ሊያስፈፅሙልኝ ይችላሉ’ ከሚል እሳቤ ተነስተው መሆኑ ግልፅ ይመስለኛል። ይሁንና “ኢሳት” ውስጥ እየሰሩ በፌስ ቡክ ደግሞ የራሳቸውን ሃሳብ የሚያንፀባርቁት እንደ አቶ መሳይ መኮንን የመሳሰሉ የጣቢያው ባልደረቦች፤ ሹመቱን የተመለከቱበት መንገድ ትክክል ነው ብዬ ስለማላምን እዚህ ላይ ላነሳው የግድ ብሎኛል። አቶ መሳይ ሹመቱን አስመልክተው ‘የዶክተር አብይ ሹመት ልክ እንደ የኦሮሞ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ኦዴፓ) ዓይነት ቢሆን ጥሩ ነበር። ግን ያ ሲሆን አላየንም’ ብለዋል (አባባላቸው ቃል በቃል የተወሰደ አለመሆኑን አንባቢያን ልብ ይሏል!)

ታዲያ ‘ይህ አባባል ምን ማለት ነው?’ ብለን ስንመረምረውና ርሳቸውም ለመግለፅ እንደሞከሩት፤ ‘የኦሮሚያው ፕሬዚዳንት አቦ ለማ መገርሳ ብ/ጄኔራል ከማል ገልቹን የኦሮሚያ ፍትህ፣ ፀጥታና አስተዳደር ቢሮ ኃላፊ አድርገው እንደሾሙት እንዲሁም ብ/ጄኔራል ኃይሉ ጎንፋን የኦሮሚያ ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር እንዲሆኑ እንዳደረጉት ሁሉ፤ ዶክተር አብይ አህመድም እንዲሁ ከሌላ የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች ካቢኔያቸው ውስጥ ሹመት መስጠት ይኖርባቸው ነበር’ የሚል ግልፅ ዕይታን የሚያንፀባርቅ ነው።

ዳሩ ግን፤ አቶ መሳይ አንድ ያልተረዱት እውነታ ያለ ይመስለኛል። ይኸውም በእኔ እምነት፤ የኦሮሚያው የጄኔራሎች ሹመት (ኋላ ላይም የአማራ ክልል ብ/ጄኔራል አሳምነው ፅጌን የክልሉ ፍትህ፣ ፀጥታና አስተዳደር ቢሮ ሹመት መስጠቱን ያስታውሷል!)፤ ፓርቲዎች በሚያራምዱት ዓላማ መቀራረብ ከቻሉ ሹመቱ ቢሰጥ ምንም ማለት አይመስለኝም። በኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት የተሾሙት ሁለቱ ጄኔራል መኮንኖች፤ የሚመሩት ፓርቲ የፖለቲካ መስመሩ ከኦዴፓ ጋር ተቀራራቢ መሆኑን ብዙዎች ሲገልፁ አድምጠናል። እንዲያውም ‘ሊዋሃዱ ነው’ የሚባል ነገር ስንሰማ መቀየታችን ለእኔም ይሁን ለአቶ መሳይ እንግዳ አይመስለኝም—እየተደጋገመ ሲነገር የነበረ ጉዳይ ነውና። የክልሉ ገዥ ፓርቲ እስካመነበት ድረስ እንዲህ ዓይነት ተመሳሳይ የሆነ አቋም ያላቸው ፓርቲዎች በአንድ ላይ ቢሰሩ ምንም ዓይነት ችግር ሊፈጥር የሚችል አይመስለኝም። እንዲያውም ተገቢውን ክልላዊ አቅም በመፍጠር ዘላቂና አስተማማኝ ሰላምን ለማስፈን ወሳኝ ርምጃ ነው ብዬ አስባለሁ። እናም እኔ እስከሚገባኝ ድረስ፤ ፕሬዚዳንት ለማ መገርሳ ለጄኔራሎቹ የሰጡት ሹመት ይህን ዕውነታ ከግምት ውስጥ ያስገባ ነው።

ታዲያ የኦሮሚያው ሹመት መነሻውና መድረሻው ይህ ከሆነ ዘንዳ፤ ዶክተር አብይ  ባዋቀሩት የለውጥ ካቢኔ ውስጥ ከሌላ ፓርቲ ለመሾም ቢያንስ ከገዥው ፓርቲ ጋር በፖለቲካ መስመር ተመሳሳይ የሆነ ፓርቲ መኖር ያለበት ይመስለኛል የኢህአዴግ ፍላጎት እንደተጠበቀ ሆኖ። ይሁን እንጂ አቶ መሳይ ‘የአርበኞች ግንቦት ሰባት አመራሮች በካቢኔው ውስጥ ቢካተቱ ጥሩ ነበር’ ለማለት ፈልገው ከሆነም፤ በገዥው ፓርቲና በእነ ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ ፓርቲ መካከል ያለውን ልዩነት ያጡታል ብዬ አልገምትም። ሌላው ቀርቶ፤ ኢህአዴግና አርበኞች ግንቦት ሰባት ተመሳሳይ የፖለቲካ መስመር ቢኖራቸው ኖሮ፤ የእነ ፕሮፌሰር ብርሃኑ ፓርቲ ራሱን ችሎ በየክልሉ እየዞረ መቀስቀስ ሳያስፈልገው ከኢህአዴግ ጋር አብሮ ይሰራ እንደነበር ለአቶ መሳይ መንገር “ለቀባሪው ማርዳት” ያህል ይቆጠርብኛል።

እናም አንድ ፓርቲ የሚፈልገውን ዓላማና ግብ ለማሳካት ምርጫው የሚያደርገው የራሱን ፓርቲ ሰዎች መሆኑ ግልፅ ቢሆንም፤ አሁንም ቢሆን ደጋግሞ ማውሳቱ አስፈላጊ ሆኖ አግኝቼዋለሁ። ምክንያቱም የሃሳቡ መነሻ ሌላ ስለሆነ ነው። እንደ እውነቱ ከሆነ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ፤ ከተፎካካሪ ፓርቲዎች ጋር ለአንድ ሀገራቸው በጋራ የሚሰሩት፤ የራሳቸው የፖለቲካ መስመርና አተያይ ላላቸው ተፎካካሪዎች ምቹ የፖለቲካ መወዳደሪያ ምህዳር በመፍጠር እንጂ ፓርቲዎቹን በካቢኔያቸው ውስጥ በማስገባት አይመስለኝም። ሊሆንም አይችልም። እንኳንስ የተለየ ርዕዩተ-ዓለም የሚከተሉ ተፎካካሪ ፓርቲዎችን ቀርቶ በራሳቸው ፓርቲ ውስጥም ቢሆን ‘ለውጡን በብቃት ሊያስፈፅምልኝ አይችልም ወይም የለውጡ እንቅፋት ይሆናል’ ብለው ያሰቡትን ግለሰብ ሊያካትቱ እንደማይችሉ ከማንም የተሰወረ አይደለም። እናም በእኔ እምነት፤ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ የዕድገት ዕቅዱንና ለውጡን ማስቀጠል የሚችሉ ግለሰቦችን በካቢኔያቸው ውስጥ ማዋቀራቸውን በቅንነት መገንዘብ ከስህተት የሚያድን ይመስለኛል።    

ዳሩ ግን፤ አቶ መሳይ መኮንን በኦሮሚያ ክልል የተሰጠው የሁለቱ ጄኔራሎች ሹመት በፌዴራል መንግስቱ ውስጥ መደገም ነበረበት በማለት በገደምዳሜው ሊነግሩን የፈለጉትን ሃቅ ፈታ አድርገን ስንመለከተው፤ ትናንት “ኢሳት” እና ባልደረቦቹ በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ እየዘመሩለት የነበረው “የሽግግር መንግስት” ጉዳይ፤ ዛሬም ውሉን ሳይስት በተዘዋዋሪ መንገድ እየተቀነቀነ መሆኑን ለመገንዘብ የሚከብድ ሆኖ አላገኘሁትም። እንዲያውም ነገሩን በአርምሞ ለሚያጤነው ሰው፤ “ያሰብከው ነገር አልሳካ ብሎህ አላማህ ሲጠጥር፤ የጠበቀውን ትተህ የላላውን ወጥር” እንደሚባለው ዓይነት ሆኖ ያገኘዋል።

አዎ! ትናንት በቀጥታ ይነገር የነበረው “የሽግግር መንግስት” ተረክን በተገኘው አጋጣሚና በአንድ ጉዳይ ላይ በተዘዋዋሪ ለመሰንቀር መሞከር ውጤት ሊያስገኝ የሚችል አይመስለኝም። በጠንካራው ነገር በኩል አልሆን ሲል፤ በላላው በኩል መሞከርም ብዙም ርቀት ያስኬዳል ብዬ አላስብም። ይህ ደግሞ ሌላ ነገር አይደለም—የሀገራችን ሉዓላዊ ባለስልጣኖቹ ህዝቦች ብቻ ስለሆኑ ነው። ለነገሩ የእነ “ኢሳት” እና ባልደረቦቻቸው “የሽግግር መንግስት” ሃሳብ ለምን አሁን ባለንበት ወቅት እውን መሆን እንደማይችል እያወቁ በሰበብ አስባቡ እየደጋገሙ እንደሚያነሱት ይገባኛል—ነገሩ የዓላማ ጉዳይ ነውና። ዳሩ ግን፤ ዶክተር አብይ ራሳቸው በአሜሪካ ባደረጉት ጉብኝት ወቅት፤ “እኔን የሽግግር መንግስት አድርጋችሁ ቁጠሩኝ” ማለታቸው፤ በስራ ላይ ያለው ህገ መንግስት ያንን እንዳያደርጉ ስለሚያግዳቸው መሆኑን መገንዘብ ያለባቸው ይመስለኛል። ያም ሆኖ፤ የተዋቀረውን ካቢኔ ከመቀበል ውጭ ማናችንም ሌላ አማራጭ ያለን አይመስለኝም—የመሾምም ይሁን የመሻር መብት ያለው ገዥው ፓርቲ ብቻ ነውና።

ታዲያ በፅሑፌ ራስጌ ወይም ርዕስ ላይ ‘በሹም ሽሩ— እነማን ከሰሩ?’ የሚል ጥያቄን ያነሳሁት ያለ ምክንያት እንዳልሆነ የዚህ ፅሑፍ አንባቢ እንደሚገነዘበው ተስፋ አደርጋለሁ። አዎ! ጥያቄውን ያነሳሁት፤ አንድ ግለሰብ ስለተሾመና ስላልተሾመ ከስሯል ለማለት ፈልጌ አይደለም። የጥያቄዬ መነሾ፤ የጠቅላይ ሚኒስትሩን የለውጥ ካቢኔ አስመልክቶ፤ በፌስ ቡክና በሌሎች ማህበራዊ ሚዲያዎች ላይ በራሳቸው የዘውግና የቡድን አጥር ውስጥ ሆነው “ሿሚና ሻሪ” መሆን የሚዳዳቸው አንዳንድ ወገኖች የከሰሩ መሆናቸውን ለማመላከት ብቻ ነው። ምክንያቱም ሹመት፤ አሁን ባለው በእኛ ሀገር ተጨባጭ ሁኔታ፤ ሀገራዊ ዕቅድንና እርሱን ማሳካት የሚችል ብቃትንና አቅምን እንዲሁም የተጀመረውን ለውጥ ለማሳካት የሚችሉ ግለሰቦችን ሀገሪቱን በመምራት ላይ በሚገኘው ፓርቲ ፍላጎት ላይ ተመርኩዞ የሚሰጥ ስለሆነ ነው።

ይሁንና የፌስ ቡክ “ጦረኞች” እይታቸው አጭር በመሆኑ እንዲሁም ይህን እውነታ ቢያውቁም ለማወቅ ስለማይፈልጉ ርግጥም እነርሱ ስለመክሰራቸው በማያሻማ ሁኔታ መናገር ተገቢ ይመስለኛል። ታዲያ እዚህ ላይ ከሳሪዎቹን አንስተን ስለ አትራፊዎቹ ምንም አለማለት ዕሑፉን ሙሉዕ ያደርገዋል ብዬ አላስብም። እናም አትራፊዎቹ፤ ከራስ የከበባ አዙሪት ውስጥ የወጡና በእውነተኛነትና በቁርጠኝነት ለውጡን እየደገፉ የሚገኙ የኢትዮጵያዊ አሳቢዎች መሆናቸውን ለሁሉም መግለፅ ያስፈልጋል—እነዚህ ወገኖች ቢያንስ ሹም ሽሩ ሀገርንና ህዝብን የሚጠቅም የለውጡ አንዱ መገለጫ መሆኑን ይገነዘባሉና። ሰናይ ጊዜ።

  1. Mulugeta Andargie says

    ውነት ለኛም ነጋ?
    ጨለማው ሄዶ ንጋት ተጋ?
    ሳንፈራ፣ ራሳችንን ማስተዳደር ሳንሰጋ?
    ጭቃሹም፣ ነፍጠኛን ሳናስጠጋ!
    ውነት ለኛም ዝናም ጣለ? ነጎድጓድ፣መብረቅ፣ ተጋ?
    ዕኩል ሆንን?
    እሾ! ኣልን?
    ገለን ኬቲ! ኣልን??
    እሬቻችንን ኣከበርን??

  2. Mulugeta Andargie says

    እሹሩሩ!እሹሩሩ!እሹሩሩ!
    ኣንቀልባ የነመምሩ
    ሲመቻቸው ማሻጠሩ!
    የሼኮች እንጀራ ማዘውተሩ!
    ህዝባችን ነው! ውሎ ኣደሩ!
    ህፃን ፈልግ እሹሩሩ!
    ማባበል ለእንቅልፍ ማሸለብ ፍጡሩ!
    የለም! የለም! የለም! እሹሩሩ!
    መቀባጠሩ! መዘመሩ!

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy