“ተው ስማኝ ሀገሬ!…”
እምአዕላፍ ህሩይ
“እናትም ብትሞት በሀገር ይለቀሳል፣ አባትም ቢሞት በሀገር ይለቀሳል፣ ወንድም፣ እህትና ዘመድ አዝማድ ቢሞት በሀገር ይለቀሳል፤ ሀገር የሞተ እንደሆን ወዴት ይደረሳል?” በማለት የሀገርን ጠቀሜታ የሚናገር ጃሎታ ባለቤት ሆኖ ሳለ፤ እንደምን በዚህ ዓይነቱ ኢ-ኢትዮጵያዊ የሞራል ክስረት ውስጥ ሊገባ ይችላል?…”
ጀግንነት እንዳይባል፤ የድኩማኖች ሃሳብ ነው። ሞኝነት እንዳይባልም፤ ራስን በራስ የማጥፋት ያህል ነው። ብልጥነት እንዳንለውም፤ አንዱ ተዋጊ ሌላው ተወጊ ሆኖ ፍዳውን የሚያይበት የእርኩሰት ሜዳ ነው። ሰላማዊነት እንዳይባልም፤ አያያዙ ሲታይ፤ ልክ እንደ ድንጋይ፤ ገጀራንና ሌሎች ራስን የማጥፊያ መንገዶች ሁሉ የሚጠቀም ሰው-ጠል እንዲሁም አፍቃሪ አርዮስ ተግባር ነው። የተግባሩ ፈፃሚዎች ሰይጣን እንኳን የሚቀናባቸው የሰዎች ሁሉ መጨረሻ ናቸው—ከሰውነት ተራ ወጥተው ወደ አውሬነት የተለወጡ።
እንግዲህ ልብ በሉ!— ሰይጣን የሚቀናበት ሰው ምን ዓይነት ፍጡር ሊሆን እንደሚችል። በክርስትናም ይሁን በእስልምና እምነቶች ውስጥ ሰይጣን የተኮነነ ፍጡር ነው—መፅሐፉ “ውግዝ ከመ አርዮስ” ያለው። ታዲያ ይህን ፈጣሪ “ዓይንህን ለአፈር” ያለውን እኩይ ፍጡር ተክተው የሚሰሩት በሩህሩሁ አምላክ የተፈጠሩትና “ሰብዓዊ” መሆን የሚጠበቅባቸው የእኛዎቹ ጉዶች አርዮሱን ሰይጣን በልጠውና አስር እጅ አስከንድተው ሲገኙ እጃችንን ከፍ አድርገን በማውጣት መናገራችን የግድ ሆኗል…“ተው ስማኝ ሀገሬ!…” እያልን።
ታዲያ የሰው ልጅ ከሰይጣን የተሻለ ብቃት እንዳለው ሳስብ፤ አንድ ወዳጄ ያጫወተኝ ተረት ትዝ አለኝ። ተረቱ ምን መሰላችሁ?…ከዕለታት በአንዱ ቀን አንዲት ባለትዳርና እግዚሐብሔርን አማኝ ሴት ንሰሃ ለመግባት ወደ ፃድቁ አቦዬ ጋር ትሄዳለች። ፃድቁ አቦዬ ገብረመንፈስ ቅዱስ፤ ያኔ በአንድ እግራቸው ቆመው ለዓለም ህዝቦች ሁሉ ድህነት እየፀለዩ ነበር አሉ።…ታዲያላችሁ ሴትየዋ ወደ ፃድቁ አቦዬ እየሄደች ሳለ፤ አንድ የቀድሞ ወዳጇ የሆነ ሰው መንገድ ላይ ይገጥማታል። ሰላምታ ከተለዋወጡ በኋላ፤ ስለ ድሮ ፍቅራቸው ማውጋት ያዙ። ጨዋታ ጨዋታን ወለደና ሰውዬውና ሴትየዋ ወደ አንዱ ጫካ ጎራ ብለው ያው እንደ ድሯቸው “አመላቸውን” ይፈፅማሉ።
ሰይጣንም እነዚህ ምን ዓይነት አሻጥረኛ ሰዎች ናቸው ብሎ ተደብቆ ይመለከታቸው ነበር። ሴትየዋም መንገድ ላይ ያጋጠማትን የድሮ ወዳጇን ትሰናበተውና ጉዞዋን ወደ አቦዬ ገብረ መንፈስ ቅዱስ ታደርጋለች። ዓላማዋ ንሰሃ ለመግባት ቢሆንም ቅሉ፤ ከባለቤቷ ውጭ ከቀድሞ ወዳጇ ጋር ከአልጋ ወድቃለች። ያም ሆኖ፤ ንሰሃ መግባት አለብኝ ብላ አቦዬ ፃዲቁ ጋር ተደርሳለች። አቦዬም “ልጄ ወደ እኔ ምን አመጣሽ?” ሲሉ ይጠይቋታል—ሴትየዋን። እርሷም “አቦዬ አመጣጤ ንሰሃ ለመግባት ነበር፤ ሆኖም መንገድ ላይ ሰይጣን አሳሳተኝና ሃጠያት ሰራሁ” ትላቸዋለች። አቦዬም “እግዚሐብሔር መሃሪ ነው፤ አይዞሽ ልጄ!” ከማለታቸው፤ ለካስ ሰይጣኑ ሲከታተሏት ኖሮ፤ “አቦዬ ፈፅሞ እንዳይሰሟት። ይህችን ሴት ፈፅሞ አልቀረብኳትም። ሁሉንም በራሷ ፍላጎት የፈፀመችው ነው። እኔ ራሴ ለካስ እንዲህ ዓይነት ነገርም አለ እንዴ? ብዬ ቀንቼባታለሁ” በማለት ‘ከደሙ ንፁህ ነኝ’ ይላል። አቦዬም በቅድሚያ ሰይጣኑን “ሂድ አንተ ከይሲ፤ እዚህ ምንድር ትሰራለህ!” ብለው ገስፀው ካባረሩት በኋላ፤ ሴትየዋን በእርጋታ እንዲህ አሏት—“የሰው ልጅ አንዳንዴ በሚፈፅማቸው ዘግናኝ ተግባራት ከሰይጣን እንደሚበልጡና እንደሰማሽውም ሰይጣንን ራሱ ከማስገረም አልፈው እርኩሱ ፍጥረት የሰው ልጅ የክፋት መጠን ከእርሱ ልቆ ሲያገኘው እንደሚያስቀናው አስገንዝበዋት፤ “ለሰራሽው ሐጢያት እግዚሐብሔር ይፍታሽ” ብለው በሰላም አሰናበቷት ይባላል።
ታዲያ ይህ ተረት የሚያስገነዝበን ነገር ቢኖር፤ የሰው ልጅ ክፋት ምን ያህል ሰይጣንን ሊያስከነዳ እንደሚችል ነው። ሰይጣን ራሱ በቅናት እስኪናውዝ ድረስ የሚፈፀሙ የሰው ልጆች የክፋት ልኬታ ወደር የለውም። በምድር ላይ እርስ በርሱ የሚጠፋፋው የሰው ልጅ፤ “ሰይጣን አስንቄ” ምግባሮቹን የሚፈፅመው በተለያዩ ምክንያቶች ነው። በተለይም አሁን በምንገኝበት ወቅት፤ ፖለቲካዊ አስተሳሰቦች ምን ያህል የሰውን ልጅ በግፍ እንደሚያስገድሉ፣ እንደሚያስደፍሩ፣ አካል የሚያስጎድሉና ንብረት እንደሚያወድሙ እየተመለከትን ያለነው እውነታ ነው።
ሰሞኑን በተለያዩ የሀገራችን ክፍሎች ውስጥ የሚታዩት የህይወት መጥፋቶችና መፈናቀሎች የዚህ ክፋት መገለጫዎች ናቸው። ርግጥ እየተመለከትናቸው ያሉት ተታችለንና በኢትዮጵያዊ መንፈስ መኖር ስንችል በመከፋፈል የምንፈፅማቸው ጉዶች፤ “ተው ስማኝ ሀገሬ…” የሚያስብሉ ናቸው* እናም እኔም “ተው ስማኝ ሀገሬ!…” ለማለት ወደድኩ። አዎ! “ተው ስማኝ ሀገሬ!…” እላለሁ።