Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

“አንተም ጨካኝ ነበርክ፣ ጨካኝ አዘዘብህ…?”

1 11,354

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

“አንተም ጨካኝ ነበርክ፣ ጨካኝ አዘዘብህ…?”

                                                    እምአዕላፍ ህሩይ

 

“…የነሲብ ሙግትንና ምላሽን በመስጠት የፌስ ቡካቸውን ሪኮርድ ሳይበጥሱ የቀሩ አይመስለኝም። ታዲያ ሰዎቹ፤ ‘ሁላችንም አብዲ ኢሌ ነን’ የሚሉን ከሆነ በግልፅ ይንገሩን እንጂ፤ እንደምን በፍርድ ቤት የተያዘን ጉዳይ ብይን ለመስጠት ይዳዳቸዋል?…”

 

ጊዜው ትንሽ ቆየት ብሏል። ለበርካታ ዓመታት በቅርበት የማቀርበው አንድ ጓደኛ ነበረኝ። ያ ጓደኛዬ ታዲያ፤ ሁሉንም ነገር በበጎ የማይመለከትና ለማንኛውም ነገር አሉታዊ ምላሽ የማያጣ ዓይነት ሰው ነበር። አንድ ሰው አጋጣሚያዊ ክስተት ሲፈጠርበት፤ ሰውዬው ከዚህ ቀደም ላደረገው እኩይ ምግባር የተሰጠው ተገቢ ምላሽ አድርጎ ያስባል። እናም ሁሌም እንዲህ ዓይነት ኩነት ሲያጋጥመው፤ ነገሩን “አንተም ጨካኝ ነበርክ ጨካኝ አዘዘብህ፤ እንደ ገና ዳቦ እሳት ነደደብህ” በሚል ፈሊጥ ማስተጋባት ይቀናዋል። አሁን…አሁን ሳስበው፤ የገና ዳቦ ከላይም ከታችም በእሳት መለብለቡ፤ ‘ለበዓሉ ድምቀት’ ታሰቦ እንደሆነ የዘነጋ ይመስኛል—ሁሌም። ርግጥ ጉዳዩ ያጋጠመው ሰው፤ ከዚህ በፊት ይህን ያህል የከፋ ምግባር ይኑረው…አይኑረው በጓደኛዬ ዘንድ ከግምት ውስጥ የሚገባ ነገር አይደለም። ብቻ አንድ ክስተት ከዚህ ቀደም ቢፈፀምም ባይፈፀምም፤ ነገሩን ካለፈው ጉዳይ ጋር የግድ እያጣበቀ በመስፋት በድግግሞሽ መልክ “አንተም ጨካኝ ነበርክ…” ሲል በአያሌው ያስደምመኝ ነበር።

ርግጥ እንዲህ ዓይነት ሰዎች፤ ሁሉም ነገር ከል የለበሰ ደመና የሚመስላቸው ናቸው። ባዘቶ ጥጥ የሚመስለውና ከሰማያዊው ሰማይ ላይ የሚንሳፈፈው ሃጫ በረዶ ደመና ከቶም አይታያቸውም። ነገሮችን ሁሉ፤ በቆፈንና በሐዘን ውስጥ ሆነው የሚመለከቱ እንዲሁም ራሳቸው ማቅ መስለውና ማቅ ለብሰው “እህህ…” ማለት የሚቀናቸው “የጨለማው ዓለም” ሰዎች ናቸው ማለት ይቻላል።

አዎ! እነዚህ ሰዎች ለአፍታም ቢሆን ብርሃናዊ ጭላንጭል እንዲታያቸው አይፈልጉም። ቢታያቸውም፤ በፍጥነት ከል ደመና ያለብሱትና በሃሳባቸው ጥላሸት ይቀቡታል። እንደምንም ብለው ደማቁ ብርሃናዊ ውጋገን እንዳይታያቸው የራሳቸውን ግርዶሽ ያበጃሉ። “ሞኝ የያዘው ፈሊጥ፤ ውሻ ያገኘው ሊጥ” እንዲሉ አበው፤ ጉዳዩን እንደ አቡነ ዘ-በሰማያት እየደጋገሙ ያስደምጡናል። የዘፈናቸው ሁሉ ማሳረጊያ፤ ስጋትና ስጋት ብቻ ነው። በስጋት ተጀምሮ በስጋት ይጠናቀቃል። ስጋታቸው ግን፤ አንድም ጋት ነፍስ ዘርቶ ወደፊት የሚራመድ አይደለም—ባለበት የሚረግጥ ነው። እናም ሁሌም አንድ ነባራዊ ኩነት በተፈጠረ ቁጥር፤ እየቆዘሙና ውሻ እንዳገኘው ሊጥ እየደጋገሙ ያንኑ ጉዳይ መላልሰው እንደ “አይስክሬም” እየላሱ ሲያወጉት መመልከት አዲስ ነገር አይደለም።

እንዲህ ዓይነቶቹ ፅላሎት መስለውና ፅላሎትን ከሽነው የሚያቀርቡ ሰዎች፤ በሁሉም የህይወት ዘውጎች ውስጥ አሉ። በተለይ በፖለቲካው ዘንድ፤ አንድ ዓይነት ጊዜያዊ ችግር ሲፈጠር፤ ተሽቀዳድመው የፅልመት ፖለቲካ የፊት መስመር ተንታኝ ሆነው ብቅ ማለታቸው የተለመደ ነው። በመንግስት የተከናወኑ ነገሮች ሁሉ በእነርሱ ዓይን በበጎነት አይታይም—“ለምንትስ ማር አይጥማት” እንዲሉ አበው። አዎ! በእነርሱ ‘የሚኝ ፈሊጥ’ ትንተና ሁሉም ነገር የሸውራራ ምልከታ መገለጫ ሆኖ እርፍ ይላል።

እዚህ ላይ ጉዳዩን ያስረዳልኝ ዘንድ አንድ ምሳሌ ላንሳ። የቀድሞው የሶማሌ ክልል ፕሬዚዳንት የነበሩትን አቶ አብዲ ‘ኢሌ’ን ጨምሮ በርካታ የክልሉ ከፍተኛ ባለስልጣናት የነበሩ ግለሰቦች፤ በጅግጅጋና አካባቢው ለተፈጠረው ከፍተኛ የሰብዓዊ መብት ጥሰት፣ ለዜጎች መሞት፣ መቁሰልና መፈናቀል እንዲሁም የሃይማኖት ግጭት በመፍጠር ምክንያት ናቸው ተብለው ተጠርጥረው በህግ ጥላ ስር ሲውሉ፤ ‘ወቸው ጉድ!፣ አቤት ጉድ!…ይህ እኮ ቀጥታ ብቀላ ነው” ሲሉ አድምጠናቸዋል። ማን፣ ማንን?፣ ለምንና እንዴት? እንደሚበቀል ግን አሳማኝ ምክንያት ወይም አመክንዮ የላቸውም። በምክንያት የሚቀርብ ትንተናን እንደ ተላጠ የኤሌክትሪክ ሽቦ ስለሚፈሩም ምክንያታዊነት አካባቢ ድርሽ አይሉም። ብቻ፤ ‘አዬ ጉድ…የዚህ ሀገር ነገር እንዲህ ሆኖ አረፈው?፣ ሀገራችን አበቃላት እኮ!’ ሲሉ ይደመጣሉ። ምናልባት እነዚህን ወገኖች አንድ ሰው ‘ምን ገጠማችሁ ጃል?’ ብሎ ቢጠይቃቸው፤ ‘አይሄሄ…እስኪ ተወን ወዳጄ…’ ከማለት በስተቀር፤ የሚያቀርቡት አንዳችም የተጨበጠ ነገር የላቸውም። ወትሮም በባዶ ሜዳ ላይ የሚራወጡና ሁሉንም ነገሮች በብቀላ መነፅራቸው ውስጥ አስገብተው የሚያዩ በመሆናቸው፤ የሚጨበጥና የሚዳሰስ ነገር አለማቅረባቸው ሊገርመን አይገባም። ሊገርመን ይገባን የነበረው፤ የብቀላ “ቴሴራቸውን” ቀይረው ስለ እውነት የቆሙ ዕለት ብቻ ይመስለኛል።

ሰዎቹ፤ ‘የብቀላ ዘመን አክትሞ፣ የሀገሩ አየር ፍቅርና ይቅርታ እየናኘበት ነው’ ተብሎ ቢነገራቸው እንኳን፤ ይህን ፀሐይ የሞቀውን የአደባባይ እውነታ ‘ምናልባት ብቀላ ሊሆን ይችላል’ ከማለት የሚመለሱ እንዳይመስላችሁ። ምንም እንኳን እዚህ ሀገር ውስጥ፤ ፍቅርና ይቅርታ እየረበበ መጥቷል ማለት፤ ማንኛውም ሰው…ባለስልጣን ይሁን ህይወት አድን፣ ቀዳሽ ይሁን ተኳሽ፣ ዳኛ ይሁን ግንበኛ፣ ፖሊስ ይሁን መሃንዲስ፣ ጋዜጠኛ ይሁን ፖለቲከኛ…ሁሉም በየፊናው ህግንና ስርዓትን ተላልፎ እስከተገኘ ድረስ ተጠያቂ እንደሚሆን ለእነዚህ ሰዎች ከምንም የሚቆጠር አይደለም። ‘ሀገራችን በአዲስ የለውጥ ምዕራፍ ውስጥ ገብታ፤ የጉዞዋን ግማሽ መንገድ አጋምሳለች። እናንተም ኢትዮጵያዊ በመሆናችሁ ለምን የለውጡ አካል አትሆኑም?’ የሚል ጥያቄን ‘ጆሮ ዳባ ልበስ’ ብለው ስለሚያልፉም ከእውነት ጋር ጠበኛ ናቸው። ፈሊጣቸው “ሞኝ የያዘው” እንዲሉት ዓይነት በመሆኑም፤ የአመክንዩአቸው መነሻና መድረሻ “አንተም ጨካኝ ነበርክ…” ብቻ ሆኖ በየማህበራዊ ሚዲያው በጨለማው እሳቤታቸው ‘አሼሼ ገዳሜ፣ መቼ ነው ቅዳሜ?!’ እያሉ ዳንኪራ ሲረግጡ መመልከት አያስገርምም። መቼም ወገኖቼ ‘ከመዓት ፈልሳፊ ይጠብቀን!’ እንጂ ሌላ ምን ይባላል?…

እነዚህ ሰዎች፤ በትናንትናው ዕለትም የቀድሞው የሶማሌ ክልል ፕሬዚዳንት የፍርድ ቤት ውሎ ቀልባቸውን ስቦት የተለመደውን “ፍልስፍናቸውን” ሲያስነኩት ተመልክቻቸዋለሁ። ፖሊስ፤ “ተጠርጣሪው አቶ አብዲ ‘ኢሌ’ የእስር ቤት መስኮት ሰብረው ሊያመልጡ ነበር” በማለት ለፍርድ ቤቱ ማስረዳቱን መገናኛ ብዙሃን እንደዘገቡ፤ ወዲያውኑ እንደለመደባቸው በመሽቀዳደም ‘ይህማ የፈጠራ ወሬ ነው፤ አቶ አብዲ ኢሌ እንዲህ ዓይነት ነገር አይነካካቸውም’ የሚል ዓይነት የነሲብ ሙግትንና ምላሽን በመስጠት የፌስ ቡካቸውን ሪኮርድ ሳይበጥሱ የቀሩ አይመስለኝም። ታዲያ ሰዎቹ፤ ‘ሁላችንም አብዲ ኢሌ ነን’ የሚሉን ከሆነ በግልፅ ይንገሩን እንጂ፤ እንደምን በፍርድ ቤት የተያዘን ጉዳይ ብይን ለመስጠት ይዳዳቸዋል?…

ፖሊስ በቀድሞው የሶማሌ ክልል ፕሬዚዳንት ላይ ያቀረበውን ‘የማምለጥ ጉዳይ’ መርምሮ ተገቢውን ውሳኔ መስጠት የሚገባው ባለመብቱ ፍርድ ቤት ሆኖ ሲያበቃ፤ እነ ‘አያ እንቶኔ’ በፌስ ቡክ ፈረሳቸው ላይ ኮርቻቸውን አደላድለው ተቀምጠው መሃል ዳኛ መሆን ሞራላዊም ሆነ ምግባራዊ ‘ማንነት’ የሚኖራቸው አይመስለኝም። ርግጥ የህግ የበላይነትን ለማያውቅ ‘የሞኝ ፈሊጥ’ አሽሞንሟኝ፤ ስለ ፍርድ ቤት አሰራር፣ ስለ ሞራል ልዕልና እና ስለ ግብረ ገብነት ማስተማር ያስቸግር ይሆናል።

ዳሩ ግን፤ ‘ኢትዮጵያ ጨዋነታችንንና ሞራላዊ እሴቶቻችን ማን ነጠቀን?’ ስል እጠይቃለሁ። ኢትዮጵያዊነት ከግለሰብ ተጠቃሚነት ይልቅ እንደ ሰው ሰብዓዊ መሆን በከፍተኛ ደረጃ የሚጎላበት አውድ ነው። ይህ አውድ፤ ለሁሉም ኢትዮጵያዊ የሚሰራ ነው—ለተጠርጣሪውም ይሁን ‘የሰው ህይወት ጠፍቷል፤ አካልም ጎድሏል’ ብሎ ለራሳቸው መቆም ለማይችሉ ሰለባዎችም ለሚከራከረውም ወገን። አውዱ ለሁሉም እኩል ነው። እናም የፍትህ ሚዛን፤ የተከሳሹ ወገን ሰብዓዊ መብት እንዳይጣስና ተከሳሹ ከህግ አግባብ አኳያ ተጠቃሚ የሚሆንበትን መንገድ መፈለግ መሆኑ እየታወቀ፤ ከኢትዮጵያዊ የሞራል ህግ ውጭ ጭምር የሚሰጡ ፍላጎታዊ ብይኖች ተገቢ ባለመሆናቸው፤ በፌስ ቡክም ላይ ቢሆን መስተካከል ይኖርባቸዋል እላለሁ።

ትናንት ሁላችንም ለኢንጂነር ስመኘው በቀለ ፍትህን ጠይቀናል። በአደባባይም ጩኸናል። ምላሽም አግኝተናል። ለኢንጂነር ስመኘው እንደጠየቅነው ፍትህ ሁሉ፤ በሶማሌና በኦሮሚያ አዋሳኞች እንዲሁም በጅግጅጋና በአካባቢው ወይም በሌሎች ቦታዎች በተፈጠሩ ግጭቶች ሳቢያ፤ ህይወታቸውን ላጡ፣ አካላቸው ለጎደለባቸውና ለዘመናት ከኖሩበት አካባቢዎች ለተፈናቀሉ ወገኖቻችንም በተመሳሳይ ሁኔታ ፍትህን ልንጠይቅላቸው ይገባናል። ምከንያቱም ራሳቸውን ለማይከላከሉ ወገኖች የምናደርገው ትግል፤ ማጠንጠኛዎቹ ያደግንባቸው የወል ኢትዮጵያዊ እሴቶቻችን ስለሆኑ ነው።

እነዚህን እሴቶቻችንን በግለሰባዊ ፍላጎትና ጥቅም ላይ ተመርኩዘን አሽቀንጥረን የምንጥላቸው አይደሉም። እንጣላቸው ብንል እንኳ፤ በወዲያኛው ጫፍ ያለው ኢትዮጵያዊ ወገናችን ከመታዘብ አልፎ ፈፅሞ አይሰማንም። አዎ! ይህን ስናደርግ የሚያየንና የሚሰማን ኢትዮጵያዊ፤ አንቅሮ ይተፋን እንደሆን እንጂ፤ የሃሳባችን ተካፋይ ሆኖ ሊቆም አይችልም—እርሱም በተመሳሳይ ኢትዮጵያዊ እሴቶች ተኮትኩቶ ያደረገ ነውና። ስለሆነም እጅግ በፍጥነት በምትጓዘውና ነገሮች ሁሉ በአንድ ጀንበር በሚለዋወጥባት ዓለም ውስጥ እየኖርን፤ በመግቢያዬ ላይ እንደጠቀስኩት ጓደኛዬ አንድ ቦታ ላይ ቆመን፤ “አንተም ጨካኝ ነበርክ፣ ጨካኝ አዘዘብህ፤…” የሚልና ከምንገኝበት ነባራዊ የለውጥ ጉዞ ጋር አብሮ የማይሄድ ብቻ ሳይሆን፤ ግጥምና ዜማውም ፈፅሞ የማይገናኝን የብቀላ ዘፈን ብናቀነቅን፤ ትርጉሙ፤ “ሞኝ የያዘው ፈሊጥ፤ ውሻ ያገኘው ሊጥ” ከመሆን የሚዘል አይሆንም። ሰናይ ጊዜ።      

   

  1. Mulugeta Andargie says

    ኣንተም ጨካኝ ነበርክ
    ጭካኝ ኣዘዘብህ!
    እንደ ቡሄ ዳቦ እክትክት ኣረግሁህ!!
    ለቴዲ የተገጠመ ዜማ መዋዕል!!

    ስንዴ እና እንክርዳድ!
    ዳቤ ላይሆኑ! በሳት መንደድ!
    ዋ! ዋ! ዋ! ያቺ ጊዜ! ኣለፈች??
    ዕውን ለኛም ፀሓይ ወጣች??
    ለካ! ለካ! ለኛም ዝናም ኣካፋች??
    ሃምሌና ነሓሴ ተጓዘች!
    መስከረምም ጠባች?
    ለካ! ለካ! ምድር ፍርድ ታውቃለች!!
    ዱበርቲ! ገለን ኬቲ ትላለች!!

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy