Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

አንዱን ጥሎ፣ ሌላውን አንጠልጥሎ

2 3,011

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

9አንዱን ጥሎ ሌላውን አንጠልጥሎ

                                                  እምአዕላፍ ህሩይ

 

“…እኳንስ የመዋቅር ማሻሻያና አዲስ የስራ ስምሪት ለመስጠት ቀርቶ፤ ለስብሰባም ቢሆን በየሚሲዮኑ የሚገኙ ዲፕሎማቶች ወደ ሀገር ቤት መጠራታቸው የነበረ፣ ያለ፣ የሚኖርና የተለመደ አሰራር ይመስለኛል። እናም ጥሪው አንድ ያልተለመደ ክስተት ለመፍጠር ታስቦ የተደረገ…”

 

ከጓደኛዬ ጋር ወግ ቢጤ ይዘናል። ወጋችን ያጠነጠነው በሰሞነኛው ሹመት ላይ ነው። በሹመቱ ላይ ብዙም ልዩነት አልነበረንም። ሁለታችንም ተመሳሳይ አቋም ነው ያለን— ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ በሰጡት የሚኒስትሮችና የሚኒስትር ዴኤታዎች ሹመት ላይ። ‘አንዳንድ ተሿሚዎችን ከዲሲፕሊን አኳያ መመልከት ይኖርባቸው ይሆን?’ ከምትል እጅግ የሳሳች ጥርጣሬ በስተቀር፤ ሹመቱ ሚዛናዊና ብቃትን ያማከለ መሆኑን በአንድ ዓይነት ቋንቋ ያልመሰከረ የሀገሬ ሰው ያለ አይመስለኝም።

ሆኖም ተሿሚዎቹ በ100 ቀናት ውስጥ ማከናወን ያለባቸው ስራዎች ‘በጥቁርና ነጭ’ ወይም ፈረንጆቹ እንደሚሉት “Black and White” የሆነ ነገር በግልፅ የተቀመጠ በመሆኑ፤ እኛ የምናስባቸውና የዲሲፕሊን ግድፈትና የብቃት ችግር አለባቸው ብለን የምናስባቸው ጥቂት ግለሰቦችም ቢሆኑ ከተቀመጠላቸው መስፈርት አኳያ የሚመዘኑ በመሆናቸው ብዙም ችግር እንደሌለው እንገነዘባለን። በዚያም ላይ ዶክተር አብይ ሁሉንም ተሿሚዎች በተመለከተ ከእኛ የተሻለ መስፈሪያ ሚዛን ያላቸው ብልህና ሩቅ አላሚ መሪ በመሆናቸው የተሻሉ የሚባሉ ሰዎችን እንደመደቡ ግልፅ ነው። በተለይ ምንም ዓይነት ለውጥ ሳይደረግባቸው እንዲቀጥሉ የተደረጉ ሚኒስትሮችና ሚኒስትር ዴኤታዎች ከዚህ በፊት የነበራቸውን ጠንካራ ስራ በማጎልበት እንዲሁም ያካበቱትን በቂ ልምድ በመጠቀም ለሀገራችን የቅርብ ትንሳኤ ጉዞ መሰረት ሊሆኑ ይችላሉ የሚል እምነት አሳድረናል።

እንደ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በመሳሰሉ መስሪያ ቤቶች ላይ የተደረገው ትክክለኛ ሹመት የተሿሚዎቹን አቅም ክህሎት የትምህርት ደረጃና ለውጥን ከማስቀጠል አኳያ ያላቸውን ቁርጠኝነት ያማከለ በመሆኑ በዚህ አጋጣሚ የጠቅላይ ሚኒስትሩን ትክክለኛ ግምገማ ሳላደንቅ ማለፍ አይቻለኝም። ርግጥ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር እያከናወነ ካለው እጅግ አጥጋቢ ስራ እንዲሁም እያደረገ ካለው ተቋማዊ ሪፎርም አኳያ ጠንካራ ሰዎች መመደባቸው አስፈላጊ ነው። በ100 ቀናት ውስጥ ከጎረቤቶቻችንና ከሌሎች ስትራቴጂካዊ አጋሮቻችን ጋር ያለንን ግንኙነትነና ወዳጅነት የማጠናከር፣ በውጭ የሚኖረውን ኢትዮጵያዊ (ዳያስፖራ) ተሳትፎ በሙያ ረገድም ይሁን በሌሎች ሀገራዊ ጉዳዩች ዙሪያ የማጎልበት፣ የሀገሪቱን ገፅታ የመገንባት፣ የዲፕሎማቶችን ስምሪቶች የማሻሻል…ወዘተ. ስራዎችን የማከናወን ተደራራቢ ኃላፊነቶች ላሉት ይህ ትልቅ የሀገራችን ተቋም፤ የተመደቡለት ተሿሚዎች በብቃትም ይሁን በክህሎት ስራውን የሚመጥኑ ናቸው ብዬ አምናለሁ። ስለሆነም መስሪያ ቤቱ ከሹመቱ አስቀድሞ በሪፎርም ስራ ውስጥ የገባ እንደመሆኑ መጠን፤ የጀመረውን ሪፎርም በብቃትና በቁርጠኝነት ለመተርጎምም ተሿሚዎቹ የካበተ ልምዳቸውን እንደሚጠቀሙ አልጠራጠርም።   

ያም ሆኖ፤ አንዳንድ ወገኖች የመስሪያ ቤቱን ተቋማዊ ሪፎርም አስመልክተው የሚያነሷቸው ሃሳቦች ተገቢ ሆነው አላገኘኋቸውም። እንደ እውነቱ ከሆነ ሃሳቦቹ ‘አንዱን ጥሎ ሌላውን አንጠልጥሎ’ እንዲሉት ዓይነት ነው የሆኑብኝ። ርግጥ ሃሳብን በነፃነት ያለ አንዳች መሸማቀቅ መሰንዘር ለውጡ እውን ያደረገው ህገ መንግስታዊ መብት ነው። ሆኖም የምንሰነዝራቸው ሃሳቦች በተጨባጭና በሚታዩ እውነታዎች ላይ ካልተመሰረቱ የትኛውንም ወገን ማሳሳታቸው የሚቀር አይመስለኝም። አንዳንዶቹ ሃሳቦች ጉዳዩን ከትክክለኛ መንፈሱ ካለመረዳትና በቅን እሳቤ ላይ የተመረኮዙ ሊሆኑ ይችላሉ። ሌሎቹ ደግሞ እውነታውን ለማጣመም ከመሻት ቅን ያልሆነ እሳቤ የሚነሱ ይመስላሉ። ይሁንና ሁለቱንም መንገዶች በተገቢው መንገድ ማረቅ የሃሳቡን ባለቤቶችም ይሁን ሌላውን ወገን ይጠቅማል ብዬ ስለማስብ እንደ ዜጋ የበኩሌን ለማለት ብዕሬን አንስቻለሁ።

የመጀመሪያው ሃሳብ፤ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መስሪያ ቤት ቀደም ባሉት ጊዜያት የሁለትዮሽና ባለብዙ ዘርፍ ዲፕሎማሲውን (Bi-lateral and Multi-lateral Diplomacy) ለማጠናከር የመዋቅር ማሻሻያና የሰራተኛ ድልድል ለማድረግ ማሰቡን የተመለከተ ነው። ይህን ለመፈፀምም ከአራት እስ 25 ዓመታት ያገለገሉ ዲፕሎማቶቹን ወደ ሀገር ቤት እንደጠራ መገለፁ ይታወቃል። ሆኖም አንዳንድ ወገኖች በተሳሳተ መልኩ መስሪያ ቤቱ ሁሉንም ዲፕሎማቶቹን ወደ ሀገሩ እንደጠራ አስመልከተው ሲገልፁ አድምጫለሁ። በእውነቱ፤ ይህ ትክክል ያልሆነ ብቻ ሳይሆን መረጃን በማዛባት ኃላፊነትን በአግባቡ አለመወጣት ጭምር ይመስለኛል—ጥሪው የተደረገው በግልፅ በተቀመጠ የጊዜ ገደብ ላይ ተመስርቶ ነውና።

እንደሚታወቀው የውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት ከስራው ባህሪ አኳያ አብዛኛዎቹ ሰራተኞቹ የሚገኙት በተለያዩ ዓለማት ባሉት ቆንስላዎች ውስጥ ነው። ተቋሙ ማንኛውንም ስራ ለመከወን ደግሞ እነዚህን አባላቱን ወደ ሀገር ቤት መጥራት ግድ ይለዋል። እንኳንስ የመዋቅር ማሻሻያና አዲስ የስራ ስምሪት ለመስጠት ቀርቶ፤ ለስብሰባም ቢሆን በየሚሲዩኑ የሚገኙ ዲፕሎማቶች ወደ ሀገር ቤት መጠራታቸው የነበረ ያለ የሚኖርና የተለመደ አሰራር ይመስለኛል። እናም ጥሪው አንድ ያልተለመደ ክስተት ለመፍጠር ታስቦ የተደረገ አለመሆኑን መገንዘብ ያስፈልጋል። በተለያዩ ዘውጎች መረጃን የሚያቀብሉም ሆነ የሚቀባበሉ ወገኖች ይህን ዕውነታ መረዳት ያለባቸው ይመስለኛል። ይሀን እውነታ ጥሎ ያልተባለን ነገር አንጠልጥሎ መሮጥ ተገቢም ትክክለኛም ሊሆን አይችልም።

ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በማካሄድ ላይ የሚገኘውን ሪፎርም የተመለከተው ሌላኛው ሃሳብ፤ ‘መስሪያ ቤቱ እንደምን ሰራተኞችን ብቻ በመደልደል ሪፎርም አካሂጃለሁ ሊል ይችላል?’ የሚል የተሳሳተ ምልከታ ነው። እኔ እስከሚገባኝ ድረስና የመስሪያ ቤቱን ተጨባጭ ስራዎች በአብዛኛው የሚገልፁት ቃል አቀባዩ አቶ መለስ ዓለም እንዳደመጥኩት እንዲህ ዓይነት ፈር የሳተ ነገር ሲነገር አላደመጥኩም። ውጭ ጉዳይን የመሰለ ግዙፍ መስሪያ ቤት ስለ ሪፎርም አሰራር ሳይገነዘብ ‘በሰራተኛ ምደባ ብቻ ሪፎርም አካሂዳለሁ ብሏል’ ማለት አስቂኝ ጉዳይ ነው። አላዋቂነትም ጭምር። ወይም እያወቁ በሌላ ምክንያት ሪፎርምን የመቀልበስ እሳቤም ሊሆን ይችላል።

ያም ሆኖ በየትኛው ሀገር ውስጥ ሪፎርም የሚደረገው፤ ሶስት ጉዳዩችን ታሳቢ በማድረግ ነው—አመለካከትን አሰራርንና አደረጃጀትን። እነዚህ ሶስት ጉዳዩች ሳይነጣጠሉ ለውጦችን ማድረግ ይጠይቃል—የሪፎርም ስራ። የሰው ሃይል ስምሪቱም፤ በእነዚህ ሶስት ጉዳዩች ላይ የተመረኮዘ እንጂ፤ ሰራተኞችን በመመደብ አንዲት ነጠላ ጉዳይ ብቻ የሚቋጭ አይደለም። ምናልባትም የሰራተኛ ምደባ ለማድረግ ታስቦ ከሆነ ማን የትና እንዴት ይመደብ? የሚለው ጉዳይ ከአደረጃጀት ጋር ተያይዞ የሚታይ ይመስለኛል።

በእኔ እምነት፤ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ያደረገውና የሚያደርገውም ይህንኑ እውነታ ምርኩዝ አድርጎ ነው። ርግጥ ሰራተኞችን ብቻ በመመደብ የሚከናወን ሪፎርም የለም። እንዲህ ዓይነቱ ሃሳብ ሪፎርሙን ሙሉዕ ሊያደርገው አይችልም። የሰራተኛ አዲስ ስምሪት የሪፎርሙ አንድ ስራ እንጂ ዋነኛው አይደለም። ሊሆንም አይችልም። ስለሆነም አንድን ሃሳብ እያነሳን ስንጥል፤ ከሪፎርሙ ስራ ውስጥ አንድ ዘለላ ጉዳይ ብቻ እየተነሳን መሆን የለበትም—አጠቃላይ ሪፎርሙንና ምንነቱና አብጠርጥረን ከመረዳትም ጭምር እንጂ። እናም ተንጠልጥሎ የተነሳው የስራተኞች ምደባ ወይም ከአደረጃጀት ጋር የሚያያዘው ዘለላ ጉዳይ፤ አመለካከትንና አሰራርን እንዲሁም በአደረጃጀት ውስጥ ሊነሱ የሚችሉ ሌሎች ጉዳዩችን የተወ በመሆኑ መታረም ይኖርበታል እላለሁ።

ሶስተኛው ‘አንዱን ጥሎ ሌላውን አንጠልጥሎ’ ዓይነት የተሳሳተ ሃሳብ የተሰነዘረው፤ ዲፕሎማሲውን የተመለከተ ነው—አላደገም የሚል። እንዲህ ዓይነት ሃሳብን የሚያራምዱ ግለሰቦች ለሀገር ከመቆጨትና ከማሰብ ጉዳዩ ውይይት ሊደረግበትና የመከራከሪያም ነጥብ ሊሆን ስለሚችል ‘እሰየው’ የሚያሰኝ ነው። ግና ነገርዬው እንዲሁ በደፈናው ‘ዲፕሎማሲው አላደገም’ ለማለት ታስቦ ከሆነ ከእውነታው ጋር መጋጨት የሚሆንባቸው ይመስለኛል። ምክንያቱም እኔ እሰከሚገባኝ ድረስ የዲፕሎማሲ ስራው እመርታን ያሳየ እንጂ አለማደጉን የሚያረጋግጡ ማንፀሪያዎችን በወጉ ማቅረብ ይቻላል ብዬ ስለማላምን ነው። ምንም እንኳን አንድን ተግባር ‘አድጓል ወይም አላደገም’ ለማለት ራሱን የቻለ ሳይንሳዊ ጥናት የሚያስፈልገው ቢሆንም ቅሉ፤ ሲከናወኑ የነበሩ ጉዳዩችን በደምሳሳው ስንመለከታቸው ግን፤ የዲፕሎማሲውን ስራ መዳከም የሚያሳዩ ነገሮችን ጎልተው የሚወጡ አይመስለኝም። እንዲያውም ፍፃሜዎቹ የሚነግሩን ነገር ቢኖር፤ የዘርፉን እመርታ እንጂ ውድቀት አይደለም። ይህን አባባሌን የሚደግፉና ህልቆ ማሳፍርት ጉዳዩችን ማቅረብ ቢቻልም የሰው ልጅ የማስታወስ ችሎታ ውሱን በመሆኑ ጥቂቶቹን ማስታወስ እፈልጋለሁ።

ከጎረቤቶቻችን ጋር በመተማማንና በጋራ ተጠቃሚነት ላይ የተጀመረው ጠንካራ ስራ የዲፕሎማሲው ተግባር አንድ ማሳያ ማሳያ ይመስለኛል። ዛሬ ጂቡቲ፣ ኬንያ፣ ሱዳን፣ ሶማሊያና ደቡብ ሱዳን አጋሮቻችን ሆነዋል። በልማት አንድ ሆነን እየተሳሰርንም ነው። ላለፉት 20 ዓመታት በሀገራችንና በኤርትራ መካከል ይካሄድ የነበረው ጥላሸት የመቀባባትና የመጠላላት አባዜ አክትሞ ወደ በአዲስ የትብብርና እጅ ለእጅ ተያይዞ የመበልፀግ ምዕራፍ እየተጓዝን መሆኑን ማንም አይክድም። በጎረቤትና በመካከለኛው ምስራቅ ሀገሮች ታስረው የነበሩ ዜጎቻችን ሃርነት እንዲወጡ ተደርጓል። የዜጎች እንግልት እንዲያበቃም ህግና ስርዓትን ተከትሎ በርካታ ስራዎች እየተከናወኑ ነው።

በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን “የሀገራቸው ሰው እንዲሆኑ” እና በሀገራቸው ጉዳይ እኩል ተሳታፊ በመሆን የልማት አጋርነታቸውን እንዲያረጋግጡ በማድረግ ረገድ በግማሽ ምዕተ ዓመት ታሪካችን ያላገኘነውን ድል እያጣጣምን ነው። ዛሬ ‘የዳያስፖራ ትረስት ፈንድ’ ተቋቁሞ ወደ ተግባራዊ ስራ ተገብቷል። ሌሎች ዳያስፖራውን ያማከሉ ፍፃሜዎችም ውጤት እያስገኙልን ነው።

በአሁኑ ወቅት ኢትዮጵያ ለሰላም ካላት ቁርጠኛ አቋም እንዲሁም በውስጧ ለምታከናውነው የለውጥ ሂደት ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ አክብሮቱንና ድጋፉን እየገለፀ ነው። ሀገራችን የቀጣናው የሰላምና የልማት ትስስር ድር ፋና ወጊ እየሆነች ነው። የአፍሪካዊያን ወንድሞቻችን አርአያዎች እየሆንን ነው። በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የፀጥታው ምክር ቤት ተለዋጭ አባል ሆናም የቀጣናውንና የአፍሪካንና ጥቅም በማስከበር ላይ ትገኛለች። ታዲያ ይህ በዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ዘንድ የተጎናፀፍነው ግርማና ሞገስ ከምንም ተነስቶ የተገኘ አሊያም የዓለም ህዝብ በመጥፎ ምግባራችን ስለሚያውቀን አይደለም—ግልፅ ሆኖ በሚታየው ሰናይ ምግባራችን ራሱ አፍ አውጥቶ ስለሚናገር እንጂ። አዎ! የአንድ ፍፃሜ ተግባር ማንነትን የሚገልፅ ስለሆነ በዓለም ዘንድ ያለን ተቀባይነት የሚገለፀውም በዚያው ልኬታ ሚዛን ላይ ተቀምጦ ነው።

ታዲያ የዲፕሎማሲው እመርታ በጥናት ላይ ተመርኩዞ የሚከናወን መሆኑ እንደተጠበቀ ሆኖ፤ እነዚህና ሌሎች በግልፅ የሚታዩ ጠንካራ ፍፃሜዎች፤ በማንኛውም መስፈርት የዲፕሎማሲውን አለማደግ የሚገልፁ አይደሉም። ርግጥ እዚህ ላይ የዲፕሎማሲው ስራ “ሙሉዕ በኩሉሄ” ወይም “እንከን አልባ” ነው እያልኩ አይደሉም። የሰው ልጅ በሚያከናውናቸው ስራዎች እንከን መኖሩ የግድ ነው። እንኳንስ ላለፉት አራት ዓመታት በችግር ላይ ለነበረች ሀገር ቀርቶ ባደረጉት ሀገሮች ውስጥም ቢሆን ተግዳሮቶችና ፈተናዎች መኖራቸው ጥያቄ ውስጥ የሚገባ አይደለም።

ችግሮች የትም መኖራቸው የዓለማችን ነባራዊ ሃቅ አንዱ መገለጫ ነው። የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴርም የሪፎርም ስራውን የጀመረው ችግሮችን ለመፍታትና በተለዋዋጩ ዓለም ውስጥ ከሚታዩ ፈጣን ክስተቶች ጋር አብሮ ለመጓዝ ከማሰብ ይመስለኛል። እናም በተቋሙ ውስጥ የሚካሄደው ሪፎርም ይህን እውነታ ከግምት ውስጥ ያስገባ መሆኑን መገንዘብ ያስፈልጋል። በ‘አንዱን ጥሎ፣ ሌላውን አንጠልጥሎ’ የተሳሳተ ምልከታና ሪፎርም- ጠል ስሜት የምንሰነዝራቸው ሃሳቦች፤ በዕውቀትና በተጨባጭ ከሚታዩ ሃቆች አኳያ የተመዘኑ ከሆኑ አንድም ‘የሃሳቦቹ ባለቤቶች ኢ-ሚዛናዊነት ናቸው’ ከሚል ትችት ያድኗቸዋል ሁለትም ሃሳብ የሚሰነዘርበት ወገን ነጥቦቹን በግብዓትነት ወስዶ እንዲሻሻል ሊያደርጉት የሚችሉ መሆኑን ሳልጠቁም አላልፍም። ሰናይ ጊዜ።  

     

 

  1. Mulugeta Andargie says

    የርሻ ዝመና ባገራችን
    በበሬ ነበር ዘዬኣችን
    ለዘናት ዕውቀታችን
    ዛሬ ተሽለን ወጋችን
    ትራክተር መፈለጋችን!
    ታዲያ! ታዲያ! ታዲያ!
    ቤታችን ሲያምር ኧረ ኤድያ!
    ተባለልኝ ፉተታ፤ ያለፈን ማዘናግያ!
    ያዘመነውን ጎታ ከተን!
    ልፋታችንን ድካማችንን ኣስተውለን!
    ለዋቃ ምስጋና ሰጥተን
    ተሳስበን!ተደጋግፈን!
    ካለፈው ስህተት ተምረን
    እንጂ! ቀድሞ ጩኸት ምን ሊበጀን?
    ጅራፍ የስፈራራል! ለማዘመን ዝመናን
    ውጪ ሆንህ? ያንተን ምቾት? ምን ልትሆነን?
    ላልሸውም ኣልደግን ! ያቺ ያንተን ዲሞክራሲን
    ያለ ገደብ የምትላትን!

  2. Mulugeta Andargie says

    ኣንድ ጊዜ ፀጋዬ ገ/መድህን “መርካቶ፣” ብሎ ጽፎ ኣስነበበን። ርዕሱ ብዙ ያፅፍ ስለነበር ፤ ጸጋዬ መጥፎ ሰው ብዬ ረገምኩት። ኣሁን ከሞተ በኋላ፤ ከርዕሱ ጋር ተገናኘን! ኣንዱን ጥሎ ሌላውን ኣንጠልጥሎ መርካቶን ጎብኛት።

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy