Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

ኧረ የሰው ያለህ…!

0 2,725

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

ኧረ የሰው ያለህ…!

                                                      እምአዕላፍ ህሩይ

 

“…ያኔ “ሰው የሚሆን ሰው” ስንፈልግ ነበር—እንደ ፈላስፋው ዲዩጋን ዓይን በሚያጥበረብር ጠራራ ፀሐይ ፋኖሳችንን ቦግ አድርገን እያበራን። ፈላስፋው ዲዩጋን በቀትር ፀሐይ ፋኖሱን አብርቶ ከሰው መሃል “ሰው” ይፈልግ ነበር። እኛም…”

 

“ሰው ማለት፤ ሰው የሚሆን ነው፤ ሰው የጠፋ ዕለት” የሚል አባባል አለ። አባባሉ ሰው በሌለበት ወቅት፤ ማንም ይሁን ማን፤ “ሰው” ሆኖ በመገኘት ለሚፈለግበት ተግባር መድን መሆን አለበት የሚል አንድምታን ያዘለ ነው። በርካታ ኢትዮጵያዊያን፤ ይህን አባባል ከኮሎኔል መንግስቱ ኃይለማርያም ጋር ያያይዙታል። ኮሎኔሉ በቅርባቸው ያሉትን ሰዎች በመፍጀታቸው ሳቢያ ብቻቸውን ቀርተው ሀገርን የሚመራ ሰው በጠፋበት ወቅት፤ ብቅ ስላሉ የተነገረ ነው የሚሉ ወገኖች በርካታ ናቸው። ነገር ግን ጉዳዩ ‘ሀገር ሲያረጅ ጃርት ያበቅላል’ እንዲሉት ሆነና፤ የ17 ዓመታት አገዛዛቸው ግማሽ ሚሊዮን የሚጠጉ የዚያን ዘመን መፅሐፍትና አብዮት አፍቃሪ ትውልድን ጭዳ አድርጎት ያለፈ የታሪክ ጠባሳ ሆኗል። ይህም “ሰው የሚሆነው ሰው” ለጥፋትም ቢሆን ብቅ ሊል እንደሚችል አንድ ማሳያ ይመስለኛል።

ርግጥ የዚህ ፅሑፍ ዓላማ ስለ ኮሎኔል መንግስቱ “ሰው” የመሆን ጉዳይ ለመተረክ አይደለም። 27 ዓመት ሙሉ ግንቦት 20 በመጣ ቁጥር “ይኼን ነገር የማልሰማበት የት አባቴ ልሂድ?!” ብለን እስክንማረር ድረስ፤ እሬት…እሬት እያለንም ቢሆን በየዓመቱ በትርክት መልክ ስንሰማው ነበር። አዎ! እያንገሸገሸን ቢሆንም እንደ ጥሩ ጠላ ስንጋተው ዓመታትን አስቆጥረናል። አሁን ስለዚያ ጉዳይ ማንሳት ትዝብት ላይ የሚጥለኝ ስለሚሆን፤ ነገርዬውን ‘በሪሞት ኮንትሮል’ም እንኳን ቢሆን ልነካው አልሻም። የሰሜን ሰው፤ ‘የውሾን ነገር ያነሳ ውሾ ይሁን’ እንደሚለው ማለቴ ነው። በቃ! ደርግ ከእነ ኮተቱ ተሸኝቷል። የተሸኘ ነገር ደግሞ፤ ወዳጅም እንኳን ቢሆን አይናፈቅም። ‘ኦሮማይ!’ አለ— ደራሲ በዓሉ ግርማ።

እናም በዚህ ፅሑፌ ላይ “ሰው ማለት፤…” የሚለውን የዚያን ዘመን ይትብሃል ያነሳሁት፤ ጉዳዩ ከዛሬ ስድስት ወር በፊት ከነበረው ሀገራዊ ሁኔታችን ጋር የሚገናኝ ስለሆነ ነው። ያኔ “ሰው የሚሆን ሰው” ስንፈልግ ነበር—እንደ ፈላስፋው ዲዩጋን ዓይን በሚያጥበረብር ጠራራ ፀሐይ ፋኖሳችንን ቦግ አድርገን እያበራን። ፈላስፋው ዲዩጋን በቀትር ፀሐይ ፋኖስ አብርቶ ከሰው መሃል “ሰው” ይፈልግ ነበር። እኛም ከስድስት ወር በፊት እንዲያ ነበርን። አዎ! ከነበርንበት ሁከትና ብጥብጥ የሚታደገን፣ ከምናምጥበት የችግር ቋያ እሳት የሚገላግለን፣ ‘ወንድም በወንድሙ ላይ ይነሳል’ የሚለውን የስምንተኛውን ሺህ መፅሐፍ ቅዱሳዊ ትንቢት የሚያዘገይልን፣ ሀገራችንን፣ መንደራችንንና ቀያችንን ከሰላም ጋር የሚያዋድድልን፣ የእነ ሶሪያን ፈለግ እንዳንከተል የሚያደርግልን…ወዘተርፈ. “ሰው” በእጅጉ አስፈልጎን ነበር። ኧረ የሰው ያለህ…ብለን ነበር።

እናም ከስድስት ወር በፊት “ቲም ለማ” የሚባል ቡድን ብቅ አለ። በወቅቱ የነበረውን አስተዳደር ታግለን እዚህ አድርሰነዋል አለ። በኢህአዴግ ውስጥ ለውጥ መከሰቱን ይፋ ሆነ። እኛም የእፎይታ ፀዳልን ተላበስን፤ በላያችን ላይ አንዣብቦ የነበረውን የስጋት ደመናን ገፍፈን ጣልነው። እዚህም…እዚያም ሲታዩ የነበሩ ብጥብጦች እየረጉ ወይም አራዳዎች እንደሚሉት “መሬት እየያዙ”፣ የሰላም አየር በላያችን ላይ ሽው ሲል ይታወቀን ነበር። “የገዥው ፓርቲ እንቁላል” ከውስጥ በመሰበሩ ህይወትን ዘራልን— ሰሞኑን የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ፤ በሀዋሳው የኢህአዴግ 11ኛ ጉባኤ ላይ “እንቁላል ከውስጥ ሲሰበር ህይወት፤ ከውጭ ሲሰበር ደግሞ ሞት ነው” እንዳሉት ዓይነት ማለቴ ነው። በህይወትና ሞት መካከል የነበርን ዜጎች እንዲሁም ከጣዕረ-ሞት ጋር ስትተናነቅ የነበረችው ሀገራችን፤ የፍቅር፣ የይቅርታና የአንድነት መንፈስ ይረብባት ያዘ።

አዎ! “ሰው” አገኘን። በሚያጥበረብር ፀሐይ ውስጥ ፋኖስ አብርተን ወደ ፊት የሚያራምደን “ሰው” አገኘን። ‘ኧረ የሰው ያለህ…!’ ስንል እንዳልነበርን ሁሉ፤ አሁን በኢትዮጵያዊ መንፈስ አንድ ሊያደርገን የሚችለውን “ሰው” ኢህአዴግ “እንቁላሉን ከውስጥ ሰብሮ” አበረከተልን። እናም ይህ ሰው የዛሬ ስድስት ወር ገደማ የሀገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ሆኖ በፓርላማ ፊት ቃል ገባ። ከዚያን ጊዜ ጀምሮ፤ በለውጥ ሂደት ውስጥ አልፎ…አልፎ ከሚያጋጥሙ ጊዜያዊ ችግሮች በስተቀር፤ አንፃራዊ ሰላምን በአየርነት እየማግነው ነው።

ይህ “የክፉ ቀን ሰው” በወል መጠሪያው “ቲም ለማ” ቢሰኝም፤ በጠቅላይ ሚኒስትር ዶከተር አብይ አህመድ የሚመራ ነው። አንዳንዶች ይህን “ሰው”፤ ‘በፈርኦን ጉያ ውስጥ ያደገው ሙሴ’ ቢሉትም፤ የተሳሳቱ ግን አይመስለኝም—የሙሴን በትር ይዞ ወደ ሰላምና ወደ ልማት ጎዳና እንድንሻገር መንገዱን እያሳየን ነውና። በበትረ ሙሴው፤ “የኤርትራን ባህር” ከፍሎ ወደ ታላቅ ወደምንሆንበት ጎዳና እያመራን ነውና። በበትረ ሙሴው፤ ስለ ፍቅር፣ ስለ መቻቻልና ስለ አንድነት እያስተማረን ነውና። የሙሴን በትር ይዞ፤ የጥላቻንና የመናቆርን ምዕራፍ በይቅርታ ማህተም ፋይሉን ዘግተን ወደ መዝገብ ቤት እንድንመልሰው እየነገረን ነውና። እናም ለእኔ ‘በፈርኦን ጉያ ውስጥ ያደገው ሙሴ’ ይህ ነው።  

ዛሬ በዶክተር አብይ አህመድ እየተመራ ያለው ለውጥ፤ በባህሪው የተለያዩ አስተሳሰቦች የሚራመዱበት ሂደት ነው። እነዚህን ሃሳቦች አስታርቆ ፀሐይ ሳይመታቸው በአንድ ጥላ ስር ለማስቀመጥ የጊዜ ዑደትን ይጠይቃል። ይህ ዑደት የተለያዩ ስንክሳሮችን ማለፉ የግድ ነው። በለውጥ ሂደት ውስጥ አልጋ በአልጋ የሚባል ነገር የለም። እንዲያ ቢሆንማ፤ ለለውጡ ሲባል ምንም ዓይነት የህይወት መስዋዕትነት ባልተከፈለ፣ የአካል መጉደልና የንብረት መውደምም ባልተከሰተ ነበር። እውነታው ግን፤ በለውጥ ሂደት ውስጥ ማንኛውም ነገር የመከሰት ደረጃው ከፍተኛ መሆኑ ብቻ ነው።  

እናም “ሊነጋጋ ሲል ይጨልማል” እንዲል ብሂሉ፤ በለውጥ ወቅት ሊፈጠሩ የሚችሉ አንዳንድ ተጠባቂ ሁነቶችን ብንመለከትም ቅሉ፤ በሂደቱ ውስጥ ህግንና የህግ ልዕልናን ብቻ በማክበርና በማስከበር ሊፈቱ የሚችሉ መሆናቸውን ተስፋ ማድረግ የሚገባ ይመስለኛል። ይህ ሳይሆን ቀርቶ፤ ሁሉንም ነገር በጨለማ ውስጥ ተውጠን የምንመለከት ከሆነ፤ ከለውጡ ባሻገር ብርሃናዊ አድማስን ከቶም ልናይ አንችልም። ስለሆነም በአንድ በኩል፤ ህብረሰተሰቡ እንደ ህዝብ የሚጠበቅበትን ሀገራዊ ሚና እየተወጣ ከመንግስት ጎን በመቆም፤ በሌላ በኩል ደግሞ፤ የሚታዩ ጊዜያዊ ተግዳሮቶችን መንግስት በአፋጣኝ እንዲያርም ጥቆማ በመስጠት፣ ከፍ ሲልም እየገመገሙ የእርምት ርምጃ በመውሰድ፤ የለውጡ ግለት በአንዳንድ አሜኬላ እሾሆች ውሃ ተቸልሶበት እንዳይቀዘቅዝ ማድረግ ያስፈልጋል፤ ይገባልም።  

ታዲያ ‘ኧረ የሰው ያለህ…’ እያልን ተጣርተን ያገኘነው “ሰው”፤ የመጣውና የወጣው ከኢህአዴግ አብራክ መሆኑን ልንዘነጋ አይገባም። 11ኛ ጉባኤውን በሀዋሳ እያካሄደ ያለው ኢህአዴግ፤ ቀደም ሲል በነበረው ቁመናው ከሞት፣ ከሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች ነፈጋ ጋር እንዳላፋጠጠን ሁሉ፤ በጥቂት ወራቶች ውስጥ መዳንንና ነፃነትን “እንካችሁ” ብሎናል። እናም ባለፉት ስድስት ወራቶች የነበሩት ሰላምን የመፍጠርና የሀገሪቱን ነባራዊ ሁኔታዎችን የመቀየር ጠንካራ ስራዎች እውቅና ሊሰጣቸው ይገባል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ “አይነኬና አይጠጌ” የነበረውን የኢትዮ-ኤርትራን ‘ሞት አልባ ጦርነት’ ጉዳይ ወሳኝ በሆነ መለኩ እልባት ከመስጠት ባሻገር፤ በቤተ እምነቶች መካከል የነበረውን መከፋፈል ወደ አንድ ማምጣት ችለዋል። እንዲሁም ዳያስፖራውን በፍቅርና በይቅርታ ከማሰባሰብ ባሻገር፤ ለሀገሩ ደጋፊ ኃይል እንዲሆን በማስቻልና ከጎረቤቶቻችን ጋር የነበረንን የጥርጣሬ መንፈስ በማስወገድ ብሎም እኚሁ ጎረቤቶቻችን በተፈጥሮ የታደሉትን ፀጋ በጋራ እንድንጠቀም በማስተባበር ፋና ወጊ ተግባር ፈፅመዋል።

በተጨማሪም አፍሪካዊያን ወንድሞቻችንና ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ የእርሳቸውን ፈለግ እንዲከተሉና “ልንከተለው ይገባል” የሚል ምክረ ሃሳብ ለሌሎች እንዲያቀርቡ በአጭር ጊዜ ስራቸው “ሃሳባቸውን መሸጥ” የቻሉ መሪ መሆናቸውን መካድ አይቻልም። ኢትዮጵያችንን ከግጭት ወደ ተሰሚነት ምዕራፍ ያሸጋገሩ የህዝብ ልጅም ጭምር። ታዲያ እነዚህ ተግባሮቻቸው “በመደመር ፍልስፍና” የታጀቡ መሆናቸውም፤ ዶክተር አብይ ከአመራር ብቃታቸው በላይ፤ በድፍረት የወሰዷቸው የተለያዩ ርምጃዎች ድጋፋችንን ጮክ ብለን እንድንሰጣቸው ያደረጉን ብቸኛ መሪ ስለመሆናቸው ቅን አሳቢ ዜጋ ሁሉ የሚመሰክረው ነው።        

ይህን ፅሑፍ እያሰናዳሁ ባለበት ወቅት፤ ኢህአዴግ ሊቀመንበሩንና ምክትሉን አየመረጠ ነበርመሆኑን ሰምቻለሁ። በእኔ እምነት፤ ባለፉት ስድስት ወራት “ሰው” ሽተን ሰው ያደረጉን ሊቃነ መናብርት ያከናወኑት ኢህአዴጋዊ፣ ህገ መንግስታዊና ዴሞክራሲያዊ አፈፃፀሞች ከሚጠበቀው በላይ በመሆኑ የሚለወጥ ነገር መኖር ያለበት አይመስለኝም። በጉባኤው መክፈቻ ወቅት የተነገረው የለውጡ ስኬት ይህን እውነታ የሚያረጋግጥ ይመስለኛል። እናም ለውጡ ተጋግሎ እንዲቀጥልና ወጣ ገባ እያሉ የሚታዩት ስርዓት አልበኝነቶች በህግ አግባብ እንዲታረሙ የነበረው ባለበት መቀጠሉ የአማራጮች ሁሉ አማራጭ ነው እላለሁ።

ርግጥ ኢህአዴግ ትናንትም ይሁን ዛሬ ችግሮቹን በብቃት እየፈታ የመጣ ድርጅት በመሆኑ፤ ይህን ማድረጉ የሚቀር አይመስለኝም። እናም ኧረ የሰው ያለህ…! በምንልበት በዚያን ቀውጢ ወቅት፤ “እንቁላሉን ከውስጥ ሰብሮ” የወጣውን “ሰው”፤ በሁሉም መስኮች ልንደግፈውና ልናግዘው እንዲሁም አብረነው እየወደቅንና እየተነሳን በመስራት ሀገራችንን ወደ ቀደመው ገናናነቷ ልንመልሳት ይገባል። ሰናይ ጊዜ።         

            

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy