75“የአጋች ታጋች” ድራማ?!—እንዴት?
እምአዕላፍ ህሩይ
“…በበኩሌ፤ አንድ “ተንታኝ” ነኝ ብሎ ራሱን በሚዲያ በማስተዋወቅ “የሚተነትን” ሰው፤ እንዲህ ዓይነቱ የአሉባልታ ወሬን በስሜታዊነት ግርዶሽ ውስጥ ሆኖ ለሌላው ማቀበሉ “ከመጠምጠም መማር ይቅደም” እንድል አድርጎኛል። ርግጥም እንዲህ ዓይነት ሰው “ኢሳት” ውስጥ ሆኖ በትክክለኛ መረጃ ላይ ተመርኩዞ ምን ያህል “የህዝብ ዓይንና ጆሮ” ሆኖ እንደሚሰራ፤ “ኢሳት” እና ተቋሙን የሚመራው አካል ብቻ…”
ይህን ፅሑፍ አሰናዳ ዘንድ፤ እርጋታንና ነገሮችን በሰከነ መንገድ መመልከት ያስፈልገኝ ነበር። ጉዳዩ፤ ሀገርን ከማንኛውም የውስጥም ይሁን የውጭ ፀረ ሰላም ሃይሎች በመከላከል እንዲሁም አፍሪካ ህብረትና ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ የሚሰጠውን ተልዕኮ በጀግንነትና በብቃት በመወጣት በገዘፈ ስሙ የሚታወቀውን የመከላከያ ሰራዊታችንን የሚመለከት ከመሆኑም በላይ፤ የድርጊቱ መነሻ በአላስፈላጊ መንገድ ሊተረጎም የሚችልበት ዕድሉ ሰፊ በመሆኑ ስክነትን የሚጠይቅ ነው። እናም ነገሩን ቢያንስ በልኬታውና በተሟላ መረጃ ላይ ተመርኩዞ መመልከት ያስፈልጋል ብዬ በማመን በጉዳዩ ላይ እስካሁን ድረስ ምንም ለማለት አልፈቀድኩም።
መረጃዎች፤ በተለይም በማህበራዊ ሚዲያው ላይ በደመ-ነፍስና “በይሆናል” አስተሳሰብና ኃላፊነት በጎደለው ሁኔታ ከቀኝ ወደ ግራ እንዲሁም ከግራ ወደ ቀኝ “በቴስታ” ሲጎኑ መመልከቴ የእርጋታዬን ደርዝ እንዲጨምረው ያደረገ ክስተት ነበር። በእውነቱ አንድን መረጃ ከጉዳዩ ባለቤት (ፈረንጆች እንደሚሉት ‘From The Hourse Mouth’) ሳያረጋግጡ በመላ ምታዊ ፈረስ ላይ ቁጭ ብሎ መጋለብ፤ ምን ያህል ትዝብት ላይ እንደሚጥል፤ ይህ ክስተት የሚያሳይ መሆኑን ሁነኛ ማረጋገጫ ነው።…እንዲህ ዓይነቱን ክስተት ሳይሆን አይቀርም የሀገራችን ሰው “ሳይገድሉ ጎፈሬ፤ ሳያጣሩ ወሬ” የሚለው።…
አዎ! ክስሰቱ 240 የሚሆኑ የመከላከያ ሰራዊት አባላት ወደ ቤተ መንግስት ሄደው ጥያቄ ማቅረባቸው ነው። ‘ጥቂት የመከላከያ ሰራዊት አባላት ግዳጃቸውን ፈፅመው ሲመለሱ እግረ መንገዳቸውን ቤተ-መንግስት ጎራ ብለው በደመወዝና በጥቅማ ጥቅም እንዲሁም በመልካም አስተዳደር ጉዳዩች ዙሪያ ከጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ጋር ተወያዩ’ ከሚለውና በመሃሉም “የኢሳቱ ተንታኝ” አቶ ሃብታሙ አያሌው በፌስ ቡክ ገፁ ላይ ተሽቀዳድሞ “አቶ ደመቀ መኮንን ታገቱ” ያለበትን ስሜታዊ ጥድፊያ (ምናልባትም የራሱ ግብ ያለው አስቂኝ ተረክ) እንዲሁም በስተመጨረሻ ላይ “ወታደሮቹ ወደ ቤተ መንግስት እንዲሄዱ ያቀናጁ፣ ያስተባበሩና የገፋፉ አካላት በቁጥጥር ስር እየዋሉ ነው” እስከሚለው መንግስታዊ ዘገባ ድረስ አድምጫለሁ፤ ተመልክቻለሁ፤ አንብቤያለው። ታዲያ እነዚህን ሁኔታዎች በትክክለኛ መልካቸው መመልከቱ ተገቢ ነው ብዬ አምናለሁ።
የመከላከያ ሰራዊት ሬጅመንት ሁለት የኮማንዶ አባላት በቡራዩና በአካባቢው የተፈጠረውን ችግር ለማረጋጋት ከነበሩበት “ቶጋ” ከሚሰኘው ቋሚ ማዘዣቸው ተነስተው በመምጣት ሀገራዊ ተግባራቸውን በአኩሪ ሁኔታ የፈፀሙ ናቸው። ግዳጃቸውን ተወጥተው ሲመለሱም፤ በዶክተር አብይ ላይ ካላቸው እምነት በመነሳት፤ ‘ችግራችንን ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይፈቱልናል’ በሚል ቅን እሳቤ ወደ ቤተ መንግስት ጎራ ብለው ጥያቄያቸውን ማቅረባቸው ተገቢ ነው።
እዚህ ላይ በቅድሚያ ‘የሰራዊቱ አባላት የሄዱበት መንገድ ምን ያህል ትክክል ነው?’ የሚል ጥያቄ በማንሳት፤ በግሌ ከህገ መንግስቱና ከሰራዊቱ የግዳጅ አፈፃፃም ደንቦች (Rules of Engagement) የሚታየኝን ለመግለፅ እሞክራለሁ። ለጥቆም ‘ኢሳት’ የተሰኘው ጣቢያና ተመሳሳይ ዘውግ ያላቸው የፌስ ቡክ አራምባና ቆቦ ረጋጮች ጉዳዩን “ከአጋች ታጋች” ድራማ ጋር ማያያዛቸው ምን ያህል ትክክል እንደሆነ እቃኛለሁ።
እነዚያ ጥቂት የሰራዊት አባላት ከግዳጃቸው በኋላ መመለስ ያለባቸው ወደ መደበኛ ካምፓቸው ነው። የተለየ ፈቃድ ከሚመራቸው አካል ካልተሰጣቸው በስተቀር ወደየትም መሄድ አይፈቀድላቸውም። ክልክል ነው። ይህ ወታደራዊ ዲሲፕሊን ነው። አባላቱ ምን እንኳን ጥያቄያቸውን እንደ ማንኛውም ዜጋ አግባብ ባለው መንገድ ማቅረብ የሚችሉ ቢሆንም፤ የታጠቁ ሃይል በመሆናቸው ሳቢያ ሰላማዊ ሰልፍ የማድረግ መብት የላቸውም። ይህም በህገ መንግስቱ ላይ በግልፅ ሰፍሯል። ታጥቆ በሰላማዊ ሰልፍ ዓይነት ቅርፅ ይዞ በመሰለፍ ወደየትም መሄድ አይፈቀድላቸውም። ህገ መንግስቱ ለማንኛውም ዜጋ የሰጠው መብት ለሰራዊቱ አባላት የተሰጠ ቢሆንም ቅሉ፤ ከተሰጣቸው ሀገራዊ ሃላፊነትና ግዴታ እንዲሁም ለግዳጅ ከሚያስፈልጋቸው ተልዕኮ አንፃር ትጥቅ ያነገቡ በመሆናቸው መብቱ ተነፍጓቸዋል።
ማንኛውም የሰራዊት አባል ደመወዝና ጥቅማ ጥቅም እንዲሁም የመልካም አስተዳደር ችግሮች እንዲቀረፉለት የመጠየቅ መብት አለው። ይህ መብት የግዳጅ አፈፃፀሙን በማይጎዳ መልኩ መጠቀም ይችላል። ታዲያ ወታደር እንደመሆኑ መጠን፤ መብቱን ሲጠይቅ ህግና ስርዓትን ተከትሎ መሆን ይኖርበታል። ‘ደመወዝ አነሰኝ፣ ጥቅማ ጥቅም ተጓደለብኝ፣ ፍትህና ርትዕ ተጓደለብኝ…ወዘተ.’ የሚል ጥያቄ ያለው የሰራዊት አባል፤ ጥያቄውን ማቅረብ ያለበት ከእርሱ አንድ እርከን ወደ ላይ ከፍ ላለው አለቃው ነው። እንበልና የአንድ ሬጅመንት አባላት እንዲህ ዓይነት ጥያቄ ካላቸው ጥያቄውን የሚያቀርቡት ክፍለ ጦር (Army Division) አዛዣቸው ይሆናል ማለት ነው። ይህም የሰራዊቱ አባላት ጉዳይ ገና ከሬጅመንት አዛዡ አልፎ ክፍለ ጦር ደረጃ እንኳን አለመድረሱን የሚያሳይ ነው። ከክፍለ ጦር በላይም ዕዝ የሚባል አደረጃጀት እንዳለ ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው ወገኖች አጫውተውኛል። ከዕዝ በላይም የጦር ሃይሎች ጠቅላይ ኤታማዦር ሹሙ (ጄኔራል ሰዓረ መኮንን) አሉ። ከእርሳቸው በላይም የጦር ሃይሎች ጠቅላይ አዛዡ (ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ) ይገኛሉ።
ከዚህም ወደ ቤተ መንግስት የሄዱት የሬጅመንት ሁለት አባላት በክፍለ ጦር ደረጃ የሚቀርብ ጥያቄን ወደ ዶክተር አብይ ይዘው እንደቀረቡ ለመረዳት አይከብድም። ይህ አሰራር ‘አድርግና አታድርግ’ (Do’s and Don’ts) በሚል ጥብቅ መመሪያ ካለው ሰራዊት የሚጠበቅ አይደለም። በሰራዊት ውስጥ ትልቁ ቁልፍ ጉዳይ የዕዝ ሰንሰለትን (Chain of command) መከተል ነው። የዕዝ ሰንሰለት ከተጣሰ ምንም ዓይነት ግዳጅ ወይም ተልዕኮ ሊፈፀም አይችልም። ሰራዊት የተደራጀ ሃይል እንደመሆኑ መጠን፤ ሁሉም በየፊናው አዛዥ ሊሆን አይችልም—በአንድ በሚታወቅና ወጥነት ባለው አሰራር ይመራል እንጂ። በተደራጀና ዘመናዊ ሰራዊት ውስጥ ህግና አሰራርን ጠብቆ መሄድ ለነገ የሚተው ተግባር አይደለም—ዛሬ፤ ከዛሬም አሁን የሚፈፀም እንጂ።
ሁሉም በየፊናው አዛዥ የሚሆንበት አሰራር በዘመናዊ ሰራዊት ውሰጥ ሊኖር አይችልም። እንዲህ ዓይነቱ ነገር ይፈፀም ቢባል፤ ሊኖር የሚችለው ተኩስ ሲባል ቦታ የሚይዝ፣ ቦታ ያዝ ሲባል ደግሞ፤ የሚተኩስ ወታደር ብቻ ነው። ይህም ልክ እንደ ባቢሎናውያን፤ ውሃ አቀብለኝ ሲባል ድንጋይ፤ ድንጋይ አቀብለኝ ሲባል ደግሞ ሲሚንቶ የማቀበል ያህል የሚቆጠር ነው። እናም በዘመናዊ ሰራዊት እሳቤ ውስጥ የማይግባባ ሬጅመትንት ቀርቶ አራት ወይም አምስት አባላት ያሉት (አካል) ሊኖርም አይችልም። ዘመናዊ ሰራዊት መናገር ያለበት አንድ ዓይነት የጋራ ቋንቋ ብቻ ነው።
ርግጥ አንድ ዓይነትና የጋራ ቋንቋ የማይናገር ሰራዊት የለንም፤ ወደፊትም ሊኖረንም አይችልም። በጥቂት አባላት የተፈፀመው ድርጊት ከስመ ጥሩ ሰራዊታችን አጠቃላይ ቁመና ጋርም በምንም ዓይነት ተዛምዶ የሌለው ነው። የዕዝ ጠገጉን ወይም ሰንሰለቱን ሳይከተሉ በቀጥታ ወደ ቤተ መንግስት በመሄድ ድርጊቱን የፈፀሙት አባላት ህዝቡንና ሰራዊቱን ይቅርታ የጠየቁት እንዲሁም ሁሉም የመከላከያ ሰራዊት አባላት ድርጊቱ እነርሱን እንደማይወክል በይፋ ያወገዙት ተግባሩ ሀገራችን እየፈጠረች ካለችው የዘመናዊ ሰራዊት ግንባታ ጋር አብሮ ስለማይሄድ ነው። ለነገሩ “ከሁሉም በላይ ለህዝብና ለሀገር” የሚል እሴት ተላብሶ ግዳጁን በጀግንነት፣ በታማኝነትና በብቃት እየፈፀመ ያለው መከላከያ ሰራዊታችን የጥቂት አባላቱ ጉዳይ ሁሉንም ይመለከታል ብሎ መውሰድ አይቻልም።
ያም ሆኖ፤ ጉዳዩ ሲጣራ ወደፊት በሚገባ የምናውቀው ቢሆንም፤ በእኔ እምነት፤ ይህ የጥቂት ሰራዊት አባላት ድርጊት አንድ የሚያሳየን ክፍተት ያለ ይመስለኛል። ይኸውም በሰራዊቱ ውስጥ የሚከናወነው የኢንዶክትሪኔሽን (የስርፀት) ስራ የጥንካሬ መጠንና የአፈፃፀም ሁኔታ ምን ላይ እንደሚገኝ ነው። እኔ እስከሚገባኝ ድረስ፤ በሰራዊት ግንባታ ውስጥ ትልቁ ቁልፍ ስራ ሰራዊቱ ከህገ መንግስቱ ውጭ ሳይሆን በእምነት ስራውን እንዲከውን ማስቻል፣ እሴቶቹን ሳይሸራርፍ በፅናት እንዲቆምላቸው ማድረግ፣ ሲቪል ባላስልጣናትን በማክበርና ለእነርሱም ፍፁም ተገዥ የመሆን ባህሪያቶቹን ማጠናከር…ወዘተ. ይመስለኛል። ይህን የስርፀት ስራ በሁሉም አሃዶች ውስጥ ያለ አንዳች ክፍተት በተጠናከረ ሁኔታ መፈፀም ይገባል ብዬ አምናለሁ። እንኳንስ 240 ሰው ይቅርና ሁለት ሰውም ቢሆን በተሳሳተ መንገድ መጓዝ ይኖርበታል ብዬ አላምንም።
የሰራዊት ስራ ክቡር የሆነውን የሰውን ህይወት የሚጠይቅ በመሆኑም፤ ህግና ስርዓትን ያለ ክፍተት በሁሉም የሰራዊት ክፍሎች ውስጥ በላቀ ሁኔታ ለማስጠበቅ አሁን ካለው በላይ ጠንካራ የኢንዶክትሪኔሽን አደረጃጀትና ስራ ሊኖረው ይገባል እላለሁ። ምንም እንኳን ጠንካራ የስርፀት ስራ በዋነኛነት የሚከናወነው በእያንዳንዱ የሰራዊት አሃድ (Unit) ውሰጥ በሚከናወን የእርስ በርስ መገነባባት ቢሆንም ቅሉ፤ እንደ ሚኒ ሚዲያና መገናኛ ብዙሃን የመሳሰሉ የሚዲያ ውጤቶችን በተገቢው ሁኔታ እንዲሁም በጥናት ላይ ተመርኩዞ የስርፀት ስራው አካል ማድረግ ያስፈልጋል። በሌላ በኩልም፤ የሰራዊቱን የማህበራዊ ሚዲያ አጠቃቀም በተመለከተ በሚዛናዊነት ላይ የተመሰረተ ያላሰለሰ ትምህርት መስጠትም የሚያስፈልግ ይመስለኛል። እኔም እንደ ማንኛውም ሀገሩንና ሰራዊቱን እንደሚወድ ቅን አሳቢ ዜጋ፤ እነዚህን ስራዎች በበቂ በጀት በመደገፍ እስካሁን ሲሰራበት ከመጣው በላይ መፈፀም ከተቻለ፤ የተሻለ ውጤት ማምጣት ይቻላል እላለሁ።
የሰራዊቱን ሁኔታ እዚህ ላይ ልግታውና ድርጊቱ በተፈፀመበት ዕለትና ከዚያ በኋላ ባሉት ጊዜያት ውስጥ ስለተፈፀሙት ሰራዊቱን የማይመለከቱ ጉዳዩችን ላንሳ። በመግቢያዬ አካባቢ ለመጥቀስ እንደሞከርኩት፤ ቀደም ሲል የኢህአዴግ ወጣቶች ሃላፊ የነበረውና አሁን “ኢሳት” የተሰኘው ቴሌቪዥን “ተንታኝ” ሆኖ የምናየው አቶ ሃብታሙ አያሌው፤ በፌስ ቡክ ገፁ ላይ ከጉዳዩ ጋር በተያያዘ ሃላፊነት በጎደለው ሁኔታ ከመሬት ተነስቶ “አቶ ደመቀ መኮንን በሰራዊቱ ታገቱ” የሚል አስገራሚ ልቦለድን ማስፈሩ ትክክል አይመስለኝም። አቶ ሃብታሙ ሙያዊ ክህሎቱና እውቀቱ ምን ያህል እንደሆነ ባላውቅም፤ ህዝብን ወደ ሌላ አቅጣጫ የሚያመራ ልቦለድ ይዞ ብቅ ማለቱ እጅግ የሚያስተዛዝብ ሆኖ አግኝቼዋለሁ።
የሰራዊቱ አባላት ከቡራዩ በቀጥታ ወደ ቤተ መንግስት መጥተውና ትጥቃቸውን ፈትተው አቶ ደመቀ ያወያዩዋቸው መሆኑ እየታወቀ፤ “ላም ባልዋለበት…” እንዲል የሀገራችን ሰው፤ ያለ አንዳች ተጨባጭ ማስረጃ “አቶ ደመቀ ታገቱ” የሚል ነገር ማስፈሩና ሌሎችም ይህን የሐሰት ወሬ መቀባበላቸው ነገሩ ወዴት እንደሚያመራ አቶ ሃብታሙ ያወቀው አይመስለኝም። ወይም እያወቀው ሌላ ነገር ለመፍጠር በማሰብ ይህን አሉባልታ አንጠልጥሎ ‘ፌስ ቡኩ’ ላይ ለጥፎታል እንድንል የሚያስገድደን ነው። እኔ በበኩሌ፤ አንድ “ተንታኝ” ነኝ ብሎ ራሱን በሚዲያ በማስተዋወቅ “የሚተነትን” ሰው፤ እንዲህ ዓይነቱ የአሉባልታ ወሬን በስሜታዊነት ግርዶሽ ውስጥ ሆኖ ለሌላው ማቀበሉ “ከመጠምጠም መማር ይቅደም” እንድንል አድርጎኛል። እንዲህ ዓይነት ሰው “ኢሳት” ውስጥ ሆኖ በትክክለኛ መረጃ ላይ ተመርኩዞ ምን ያህል “የህዝብ ዓይንና ጆሮ” ሆኖ እንደሚሰራ “ኢሳት” እና ተቋሙን የሚመራው አካል ብቻ የሚያውቁት ይመስለኛል።
የዚህን ፅሑፍ አቅራቢ ያስገረመኝ ሌላው ጉዳይ ደግሞ፤ “ኢሳት” የተሰኘው ጣቢያ አቶ ሃብታሙ “አቶ ደመቀ ታገቱ” የሚለውን ጉዳይ እንዲያስተባብል ዕድል ለመስጠት መሞከሩ ነው። ምንም እንኳን ‘የፌስ ቡክ ወለምታ በቅቤ አይታሽም’ ይባል እንደሆን ባላውቅም፤ ጣቢያው ጉዳዩን ከእውነት አኳያ ለመመርመር አስቦ ከሆነ እሰየው የሚያስብል ነው። ሆኖም ነገሩን “የአጋች ታጋች ድራማ” በሚል ርዕስነት ያቀረበው በመሆኑ ዓላማው እንዲያ አልመሰለኝም። አቶ ሃብታሙም ቢሆን ለምን ያንን ነገር ለምን እንደለጠፈው ሲጠየቅ፤ “…አንድ ቦታው ላይ የነበረ ታማኝ ግለሰብ ልኮልኝ…ምንትስ’ ከማለት በስተቀር የነገሩን ተጨባጭነት ሊያስረዳን አልቻለም። ልቦለዱን ከአቶ ሃብታሙ ወስደው የለጠፉ አንዳንድ ሰዎች ‘ተሳስተናል’ ሲሉ ከእርሱ ግን እንዲህ ዓይነት ዓይነት ነገር ባለመስማቴ አዝኛለሁ። በእኔ እምነት፤ ወታደሮቹ ያደረጉት ውይይት አንዳችም “የአጋች ታጋች ድራማ”ን የሚያንፀባርቅ አይደለም።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ሌላ ስብሰባ ላይ በመሆናቸው ምክንያት የሰራዊቱ አባላት ትጥቃቸውን ፈትተው በቀጥታ መወያየት የጀመሩት ከምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን ጋር ነው። በመሃሉም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ስብሰባቸውን ጨርሰው ስለመጡ ከእርሳቸው ጋር ውይይት አድርገዋል። ዶክተር አብይም ከውይይቱ በኋላ፤ ከሰራዊቱ አባላት ጠቃሚ ጉዳዩችን እንዳገኙ መግለፃቸውን እናስታውሳለን። በቃ እውነታው ይኸው ነው። ሌላ ያልሆነን ነገር እየፈጠሩ መዞር አያስፈልግም። ያገተም ሆነ የታገተ አካል የለም። እንዲህ ዓይነት ሃሳብ ያለው ይህንን ነገር በስሜታዊነት በፃፉት ግለሰቦች አዕምሮ ውስጥ ብቻ ነው።
እንደ እውነቱ ከሆነ፤ ጥቂት የሰራዊቱ አባላት ከላይ የጠቀስኩትን የዕዝ ሰንሰለት ከመጣሳቸውና ወታደራዊ ዲሲፕሊንን ካለመጠበቃቸው በስተቀር የማገት ባህል ያላቸው አይደሉም። ለህዝብና ለሀገር መተኪያ የሌለውን ውድ ህይወታቸውን ሲሰጡ፣ ሲወድቁና ሲነሱ እንዲሁም ሲቆስሉና ሲደሙ የነበሩ ናቸው። ምናልባት በውስጣቸው ያለው ችግር ብሶባቸው አሊያም ‘ዶክተር አብይ የእኛው ስለሆነ መፍትሔ ይሰጠናል’ ከሚል ቅን አስተሳሰብ በመነጨ ካልሆነ በስተቀር፤ እኩይ ዓላማን አንግበው ወደ ቤተ መንግስት ሄደዋል ለማለት የሚያስደፍረን አስረጅ አሁን ጉዳዩ ባለበት ደረጃ ማቅረብ የሚቻል አይመስለኝም። ዳሩ ግን “ኢሳት” እና አንዳንድ በውስጡ ያሉ በስሜት ፈረስ ላይ የሚጋልቡ ግለሰቦች፤ ሌላው ቢቀር ቢያንስ ለሚመሩበት “ለህዝቡ ዓይንና ጆሮ የመሆን” መፈክር (Slogan) ታማኝ ሆነው መስራት እንደሚኖርባቸው እንደ ዜጋ ምክሬን ለመለገስ እወዳለሁ። ሰናይ ጊዜ።
ድሮ! ያኔ ድሮ! በጣም ድሮ!
በምኒልክ ጊዜ፤ ሳይሆን ቅርብ እንደ ዘንድሮ!
ሰው ኣጥፍቶ! ወይ ሲከፋ
ይታገት ነበር! እንደ ኣፈላማ፤ ታስሮ በጠለፋ
ኣጋች ዳኛ! ታጋች ያስከፋ
ወይም ጥፋት ያጠፋ
ዛሬ እንኳን ኣለፍናት
ዘበት ሆኖ ኣወራናት!
ኣለፍናት!
ኣጋች! ታጋች ብለናት!