Artcles

‘የድንጋይ በረዶ ለሚዘንብባቸው…’

By Admin

October 29, 2018

እምአዕላፍ ህሩይ

 

“…እንግዲህ እናስተውል! የተመራማሪዎቹ ለማጉረስ የተዘጋጁት ችግር ፈቺ እጆች፤ በውሸት ወሬ ስለታማ ጥርሶች ቅርጥፍጥፍ ተደርገው ተበልተዋል። ቅጥፈትን  እንኳን በቅጡ የማያጣራ የአሉባልታ ምርኮኛ የሆነ አዕምሮን ‘የታደሉ’ ሰዎች፤ በልቦለድ ተረክ እንደ ቦይ ውሃ ሳያጣሩ መፍሰስ ሳያንሳቸው፤ ራሳቸው ከሳሽና ፈራጅ…”

 

አንድ ተረት አለ።…ዝንጀሮ አንዲት ልጅ ነበራት አሉ። ልጇንም ካለመጠን ታቀማጥላት ነበር። ታዲያ ያቺ ቅምጥል የዝንጀሮ ልጅ፤ ሌላው ቀርቶ፤ እንደ ሌሎቹ የዝንጀሮ ልጆች የዕለት ቀለቧን እንኳን ፈላልጋ አትመገብም ነበር። እናቷ እስክታመጣላት ድረስ ባገኘችው ኩይሳ ላይ ተቀምጣ ወይም ዛፍ ላይ ቁጭ ብላ ስትጠብቅ ትውላለች። ታዲያ ከዕለታት በአንዱ ቀን፤ አንድ ዛፍ ላይ ሆና፤ እረኛ ጫማ ተጫምቶ ከብቶቹን ሲያግድ ትመለከተዋለች። ታዲያ ይህችው ቅምጥል የዝንጀሮ ልጅ፤ እረኛው የተጫማው ጫማ በጣም ያምራታል። ራሷን በእረኛው ቦታ አስቀምጣም፤ ጫማውን በፊት እግሮቿ ተጫምታ ሰበር…ሰካ ስትል ይታያታል። ያንን ጫማ አድርጋ አምሳያዎቿ ሲቀኑባትና ግመሬ ዝንጀሮዎችም በዓይናቸውና በአካላቸው ሲከተሏት በእዝነ ህሊናዋ ታያት። እናም ያንን ጫማ እናቷ እንድትገዛላት በእጅጉ ተመኘች። ከሄደችበት ስትመጣም ልትነግራት ወሰነች።

አመሻሹ ላይ፤ ፀሐይ ስታዘቀዝቅ፤ እናቷ እንደለመደችው ዞር…ዞር ብላ ለልጇ የምትቀምሰውን ነገር ይዛ ከተፍ አለች። ልጇም ካለችበት ዛፍ ላይ ሆና “እማዬ…እማዬ” በማለት ስትጣራ ሰማቻት። መቼም የእናት አንጀት ቡቡ ነውና እናቷ በደነገጠ አንደበቷ ከአንዴም ሶስቴ “አቤት፣ አቤት፣ አቤት” አለቻት። የዝንጀሮዋ ልጅም፤ ያንን እረኛ በርቀት አሳየቻት። እናትም ወደተጠቆመችበት ቦታ ተመለከተች። ዕይታዋን ከእረኛው ወደ ልጇ በመመለስም፤ “ምነው ሁሌም እዚህ አካባቢ እየመጣ ከብቶቹን የሚያግደው ልጅ አይደለም እንዴ?” ትላታለች። ልጅቱም፤ “አዎ! እሱን መች አጣሁት። እኔ ያልኩሽ ያደረገውን ጫማ ተመልከቺው ነው። አይታይሽም በጣም ያምራል እኮ! ምናለበት ከየትም ፈልገሽ ጫማ ብትገዥልኝ እማዬ?” ትላታለች—ልጅት እንደ ዋዛ።

እናትየውም፤ ለአፍታ የልጇን አባት፤ ባሏን፤ አሰበችው። የልጇ አባት፤ አያ ዝንጀሮ፤ የሚበሉትን ለማሟላት ሲል፤ ከወዲያ ወዲህ ሲንከላወስ፤ በድንጋይ፣ በወንጭፍ፣ በዱላ እየተባረረና የስድብ ናዳ እየወረደበት እየጨኸ ሲሮጥ ለአፍታ ቃኘችው። እናም ፊቷን ወደ ልጇ መለስ አድርጋ፤ “ልጄ ሆይ! ገንዘብም የለኝም። ቢኖረኝም እንኳንስ ላንቺ ጫማ የምገዛበት፤ ለአባትሽ ኩርማን መሬት በገዛሁላቸው፤ የድንጋይ በረዶ ለሚዘንብባቸው” አለቻት ይባላል።…ነገሩ ‘አባትሽ ለእኛ ብለው፤ አፋችን ላይ ጣል የሚያደርጉትን ምግብ ለማግኘት ሲሉ፤ የሰው ልጅ እየደበደበና እያሯሯጠ ከሚያሰቃያቸው፤ ኩርማን መሬት እንኳን ገዝቼላቸው አርሰን ብንበላ ጥሩ ነበር’ ለማለት ነው—በዝንጀሮኛ እሳቤ። ተረቱ፤ ደስተኛ ሆኖና በራስ ኮርቶ በነፃነት ለመኖር፤ የራስ የሆነን ነገር አግኝቶ ጥሮ ግሮ መኖር አስፈላጊ መሆኑን ለማመለካት የተባለ ይመስለኛል። የሰውን ነገር እየተመኙና እየሰረቁ መብላት በስተመጨረሻ ሞትን ጭምር ያስከትላል ለማለትም ታስቦ የተነገረ ሳይሆን አይቀርም። “ምንግዜም የራስ ነው—የሚኮሩበት” እንዲል አዲስ አበቤ ማለቴ ነው።

አዎ! የራስ ነገር ምንግዜም የራስ ነው። የሌላ ያልሆነ የሚኮሩበት የግል ንብረት። አንድ ሰው በላቡ ሰርቶ ያገኘው የራሱ የሆነ ነገር ካለው፤ በማህበረሰቡ ይከበራል፤ ይታፈራል—ስራ ክቡር ነውና። በተቃራኒው ደግሞ፤ በሰውና በሀገር ሃብት ላይ ዓይኑን የሚጥልና ያለአግባብ ለመበልፀግ የሚያስብ ሰው፤ በምድራዊ የህግ አሰራር መጠየቁና በህጉ መሰረትም እንደ ዝንጀሮዋ ባል ‘የድንጋይ በረዶ ሊዘንብበት’ የመቻሉ ጉዳይ ርግጥ መሆኑ አያጠያይቅም። የሰው ልጅ ከዝንጀሮና ከሌሎች እንስሳት የሚለይበት ዋነኛው ጉዳይ፤ ማመዛዘንና ማስተዋል በመቻሉ እንጂ፤ ሰርቶ በመብላቱ አይደለም—እንስሳዎችም ይሰራሉና። ሌላው ቀርቶ፤ በተረቱ ላይ የተመለከትናት የዝንጀሮ እናት እንኳን ኩርማን መሬት ገዝታ ባሏ እያረሰ እንዲያበላት መመኘቷ፤ እንስሳትም ቢሆኑ የተፈጠሩበት ነባራዊ ሁኔታ ስለሚያግዳቸው እንጂ፤ የወዛቸውንና የላባቸውን ማግኘት እንደሚፈልጉ የሚያሳይ ይመስለኛል—ምንም እንኳን ነገሩ “ተረት-ተረት የመሰረት” ቢሆንም።

በዝንጀሮዋ ባል ላይ የሚዘንበው ‘የድንጋይ በረዶ’ ብዙ ነገሮችን የሚያስታውሰን ነው። ሰሞኑን እንኳ፤ በአማራ ክልል በምዕራብ ጎጃም ዞን በጎንጅ ቆላ ወረዳ አዲስ ከተማ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት ውስጥ፤ ለጥናት መረጃ ያሰባስቡ የነበሩ ሁለት ተመራማሪዎች በአሰቃቂ ሁኔታ ድንጋይ እንደ በረዶ ላያቸው ላይ ዘንቦባቸውና ተቀጥቅጠው መገደላቸውን ሰምተናል። በግድያውም፤ አቶ ወሰን ታፈረ የተባሉ የኢትዮጵያ የውሃ ሐብት ኢንስቲትዩት ባልደረባ እንዲሁም ተመራማሪና የመጨረሻ ዓመት የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ይህክምና ፋኩሊቲ የዶክትሬት ተማሪ ብሎም በቅርቡ ከአውሮፓ ዶክትሬታቸውን ይዘው የተመለሱት የዋናው አጥኚ ጓደኛ የሆኑት ዶክተር ማንደፍሮ አቤ የተባሉ ግለሰቦች ህይወታቸው ማለፉ ተዘግቧል። ለግድያው ምክንያት የሆነው ደግሞ፤ ያው የተለመደው ያልተረጋገጠ የወሬ ስርጭት ነው—አንዳንድ የከተማው ሰዎች ‘ልጆቻችንን ፀጉረ ልውጦች የማይታወቅ ነገር እየከተቧቸው ነው’ የሚል የፈጠራ ዶስኩርን  ማናፈሳቸው። ሆኖም ሰዎቹ እያደረጉ የነበሩት፤ በተለይ በህፃናት ላይ በተለያዩ ምክንያት የሚከሰቱ የሆድ ህመሞችን መንስኤ በማጥናት ያስተማራቸውን ህዝብ በምርምር ለመደገፍ ነበር። “አልተስማምቶም” ይላል የጎጃም ሰው—እንዲህ ዓይነቱ እርስ በርሱ የሚጣረስ ጉዳይ ሲገጥመው።

እንግዲህ እናስተውል! የተመራማሪዎቹ ለማጉረስ የተዘጋጁት ችግር ፈቺ እጆች፤ በውሸት ወሬ ስለታማ ጥርሶች ቅርጥፍጥፍ ተደርገው ተበልተዋልል። ቅጥፈትን እንኳን በቅጡ የማያጣራ የአሉባልታ ምርኮኛ አዕምሮን ‘የታደሉ’ ሰዎች በልቦለድ ተረክ እንደ ቦይ ውሃ ሳያጣሩ መፍሰስ ሳያንሳቸው፤ ራሳቸው ከሳሽና ፈራጅ እንዲሁም የደቦ ብይን ሰጪ ሆነው፤ በቀሰሙት ዕውቀት በችግር ፈቺነት ለሀገር የሚጠቅሙ ወገኖችን ደም ደመ-ከልብ አድርገውታል። የሀገሬ ሰው “ዕዳ ከሜዳ” የሚለው እንዲህ ዓይነቱ ያልተጠበቀ ክስተት ሰያጋጥመውም አይደል?

ርግጥ ተግባሩ ከዘግናኝነቱ ባሻገር፤ ‘ሰዎች ወዴት እየሄድን ነው?’ የሚያስብል ነው። የዝቅጠታችን ልኬታ ወርዶ…ወርዶ ወደ ኦሪት ዘመን እንዴት በፍጥነት ያነጉደናል?፣ ህግና ስርዓትን አሽቀንጥረን እየጣልን በደቦ ፍርድ እስከየት ድረስ መዝለቅ እንችላለን?፣ ክቡሩ የሰው ልጅ ህይወት እንደ ዝንጀሮ እንደምን የድንጋይ በረዶ ዘንቦበት ህይወቱን ሊያጣ ይችላል? የሚሉ ጥያቄዎች በእያንዳንዳችን የአዕምሮ ጓዳ ውስጥ መመላለሳቸው የሚቀር አይመስለኝም።…በእውነቱ የሰውነታችን ዋጋ እጅግ ከመውረዱ የተነሳ፤ በሌላው ዓለም ዘንድ መሳቂያና መሳለቂያ እየሆንን ነው። በዘመነው ዓለም ውስጥ ቁጭ ብለን ስልጣኔ የራቀው መሆናችንና የአሉባልታ አራማጆች መናጆ ሆነን ፈራጅና ገዳይ ስንሆን፤ ንፁህ ህሊና ያለውን ዜጋ ሁሉ ያሳምማል፤ ያብሰከስካል።…

እናም በዚያ አካባቢ የታየው እጅግ አሳፋሪ ተግባር፤ ‘አይደገምም፤ ጉዳዩ እየተጣራ ነው፤ ተጠርጣሪዎቹ በቁጥጥር ስር ውለዋል…ምንትስ’ በሚሉ የተለመዱ ዲስኩሮች ማብቃት የለበትም። ማህበረሰባዊ ንቃተ-ህሊናን ሊያጎናፅፉ የሚችሉ የዕውቀት ማስጨበጫ ስራዎች በፍጥነት መከናወን አለባቸው። የጥርጣሬና የጥላቻ መንፈሶችን ከህብረተሰቡ ውስጥ ሊያርቁ የሚችሉ ተጨባጭ ርምጃዎችም ሊወሰዱ ይገባል። ሚዛናዊና ምክንያታዊ መሆንን ህብረተሰቡ እንዲማር መረባረብ ይኖርብናል። የተለያዩ ጥርጣሬዎችን በህብረተሰቡ ውስጥ የሚዘሩ ግለሰቦችም (በመንግስት መዋቅሮች ውስጥ ያሉ ጭምር ማለቴ ነው) አደብ ይገዙ ዘንድ፤ የክልሉና የፌዴራል መንግስት በጋራ ተቀናጅተው፤ ሰላምን ሊያረጋግጡ የሚችሉ ተግባሮችን መፈፀም ይኖርባቻል። ነገሮችን የሚያባብሱ መገናኛ ብዙሃንና ማህበራዊ ሚዲያዎች ካሉም፤ ችግሮቹን ለማስወገድ ህግና ስርዓትን ሊያሰፍኑ የሚችሉ የህግ ማዕቀፎች በፍጥነት ተዘጋጅተው ስራ ላይ መዋል ይኖርባቸዋል።…

ርግጥ እነዚህን ተግባሮች መፈፀም ካልተቻለ፤ ነገም ቢሆን በሌላው አካባቢ የደቦ ፍርድ እንደ ህጋዊ ብይን የማይቆጠርበት ምክንያት ሊኖር የሚችል አይመስለኝም። እናም በቅድሚያ ያልረጋገጡ ወሬዎችን ማክሰም የሚቻልባቸውን ማስተማሪያዎችን መተግበር፣ ለጥቆም ህጋዊ ርምጃ መውሰጃ መንገዶችን ማመቻቸት ለነገ የሚተው ስራዎች መሆን የለባቸውም። በፍጥነት አጥንቶ ወደ ተጨባጭ ስራ መግባት የክልሉም ይሁን የፌዴራል መንግስት ወቅታዊ የቤት ስራ መሆን ይገባዋል። የዝንጀሮንና የሰው ልጅን ንቃተ-ህሊና ማወዳደር ባይቻልም፤ የሰው ልጅ፤ የደረሰ ሰብሉ ሲበላበት፤ በዝንጀሮ ላይ የሚወስደውን የድንጋይ በረዶ የማዝነብ ርምጃ፤ በገዛ ወገኑ ላይ (ለዚያውም በበሬ ወለደ ትረካ) ሲወስድ መመልከት፤ አሳፋሪና አሸማቃቂ በመሆኑ ሁሉም ዜጋ ሊያወግዘው የሚገባ ድርጊት ነው።

“የድንጋይ በረዶ ለሚዘንብባቸው…” ትረት፤ የሰውንና የሀገርን ሃብት አለመመኘትና ከተመኙም ህጋዊ ተጠያቂነት እንደሚያስከትል አንድ ማስተማሪያ ሊሆን የመቻሉን ጉዳይ ቀደም ሲል ገልጫለሁ። ታዲያ በትናንትናው ዕለት በፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ላይ የተመለከትኩት አንድ ዜና ህጋዊ የድንጋይ በረዶ ሊዘንብበት የሚገባ አንድ ማሳያ ሊሆን ይችላል ብዬ አሰብኩ። ከተሳሳትኩ ልታረም እችላለሁ። ዜናው ለአዲስ አበባ ከተማ ስለተገዛው የመንገድ ላይ ካሜራ የሚያወሳ ነው። 142 ካሜራዎች ከ70 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ መገዛታቸውን ያትታል። ሂሳብ ላይ ‘አሪፍ’ ባልሆንም፤ ወዲያውኑ የአንዱን ካሜራ ዋጋ አሰላሁት። የአንዱ ካሜራ ግዥ፤ 493 ሺህ ብር ሊሆን 42 ብር ገደማ ብቻ ነው የሚቀረው። በእውነቱ ግራ ያጋባል። የተጋነነ ሂሳብ ሳይሆን የሚቀር አይመስለኝም።

ለአፍታም ‘ይህ የመንገድ ላይ ካሜራ ከከበሩ ማዕድናት የተሰራ፣ አላፊ አግዳሚው ቁርስ፣ ምሳና እራት ምንና በስንት ሰዓት እንደበላ የሚናገር እንዲሁም በጎዳናው ላይ ሰበር…ሰካ እያልን ስንጓዝ፤ ጭንቅላታችን ውስጥ ምን እያሰብን እንደሆነ መርምሮ የሚይዝ ‘አንጎል’ ያለው ይሆን እንዴ?’ ስል አሰብኩ። ግና ወገኑን እንደ ዝንጀሮ በድንጋይ በረዶ ናዳ የሚቀጠቅጥ ማህበረሰብ ሊመላለስበት በሚችልበት ጎዳና ላይ፤ ‘እንዲህ ዓይነቱን’ ካሜራ ሰቅሎ ደህንነትህን እቆጣጠራለሁ ማለት፤ ታላቅ የኢኮኖሚ ስላቅ መስሎ ስለተሰማኝ ሃሳቤን ወዲያውኑ ተውኩት። ነገሩን ማሰቤ በራሱ አስገረመኝ። ‘አበስኩ ገበርኩ’ አልኩ። ‘የማሪያምን ብቅል እየፈጨሁ ነው’ ብዬም ሶስቴ አማተብኩ።…እዚህ ላይ የሀገርንና የህዝብን ገንዘብ የሚሞጨልፉ ግለሰቦች አለመኖራቸው ርግጠኛ ሆኖ መናገር የሚቻል አይመስለኝም። አዎ! ጠቅላይ ሚኒስትራችን ዶክተር አብይ አህመድ “የማይታለፍ ነው” ያሉት የሙስናው ቀይ መስመር፤ እንዲህ ዓይነቶቹ ግዥዎች ላይ ህጋዊ የድንጋይ በረዶዎችን ማዝነብ ብቻ ሳይሆን፤ ጠንከር ብሎ ‘የትና እንዴት?’ በማለት በረቀቀ ዘዴ የግዥውን እውነተኛነት ማረጋገጥ እንደሚኖርበት መጠቆም የዜግነት ግዴታዬ ይመስለኛል። ምላሽ መስጠትም የሚመለከተው አካል መሆኑ ሳይዘነጋ ማለቴ ነው።

እናም የሀገሬ ሰው፤ እውነተኛውን የድንጋይ በረዶ ማዝነብ የሚኖርበት ለእነዚህ ጉዳዩች ብቻ ሳይሆን፤ የተግባሩን ትክክለኛነት ካረጋገጠ በኋላም ጭምር መሆን ይኖርበታል። ህጋዊው የድንጋይ በረዶ ለሚዘንብባቸው ሰዎች ትምህርት መስጠት ያስፈልጋል።  ከዚህ ውጭ በአሉሽ…አሉሽ የደቦ ፍርድ እየሰጠን አንዲትም ጋት እንኳን ፈቀቅ ልንል አንችልም። አስተሳሰባችንና አመለካከታችን ምን ያህል ኋላ ቀርና ከተቀረው የዓለም ክፍል እንደ ኤሊ በመንቀራፈፍ እየተጓዝን መሆኑን ለማሳወቅ ካልሆነ በስተቀር፤ በሚዛናዊነትና በምክንያታዊነት እንዲሁም በህጋዊነት የድንጋይ በረዶ ሊዘንብባቸው የሚገባ አካላትን አርቀን ልንመልስ አንችልም።  ምንም እንኳን የምዕራብ ጎጃሙ አሳፋሪ ምግባር የሁሉም የህብረተሰብ ክፍል መገለጫ ሊሆን ባይችልም፤ ምልክቶቹና ተግባሮቹ እየተደጋገሙ እየታዩ በመሆናቸው አሸማቃቂውን ድርጊት ለማረም ጊዜ ሊሰጠው አይገባም እላለሁ። ሰናይ ጊዜ።