Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

ጭብጧቸውን ነሳቸው?!—ማን?

0 4,234

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

ጭብጧቸውን ነሳቸው?!—ማን?

                                                             እምአዕላፍ ህሩይ

ዶክተር አብይ አህመድ አሊ—የኢህአዴግ ሊቀመንበርና የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር። ትላንት ከሀዋሳ ከተማ በኢህአዴግ 11ኛ ጉባኤ የመክፈቻ ስነ ስርዓት ላይ ፅንሰ- ሃሳበ ብዙ የሆነ መሳጭ ንግግር አድርገዋል። ታዲያ ንግግራቸው ምን ያህል ገብቶናል?፣ እንደ ሀገር ትርጓሜውስ ምንድነው? ብሎ መጠየቅ የሚገባ ይመስለኛል።

ርግጥ ዶክተር አብይ በጉባኤው ላይ ያነሷቸው ነጥቦች፤ ደርዛቸው የሰፋና ትርጓሜያቸውም ጥልቀት ያለው መሆኑን ማንም የሚመሰክረው እውነታ ነው። እንዲያውም የዶክተሩን ንግግር እንደ ሀገር መመሪያ አድርጎ እያንዳንዱ ዜጋ በፅናት ቢተገብራቸው፤ እየተከሰቱ ላሉት ሀገራዊ ችግሮችና እፀፆች ማስታገሻ ሳይሆን ፍቱን መድሃኒት ሊሆን የሚችል ይመስለኛል። ብስለት የተሞላበት የዶክተሩ ንግግር፤ ኢትዮጵያችን ውስጥ የሚታዩት ጊዜያዊ ችሮች ሊፈጥሩ የሚችሉትን አደጋ በመቃኘት፤ የአንዳንድ ወገኖችን ሰንካላ የነገር ጭብጦ ከወዲሁ የመንሳት አቅም ያለው ነው። እናም በዚህ ፅሑፌ ላይ፤ ከንግግራቸው ውስጥ ጥቂት የሃሳብ ሰበዞችን በመምዘዝ፤ ሀገራችን እየተከተለችው ካለችው የለውጥ ሂደት ጋር እያያዝኩ በልኬታቸው ላጤናቸው እሞክራለሁ። አብረን እንዝለቅ።…

እንዳልኩት ዶክተር አብይ ያነሷቸው ነጥቦች፤ በአሁኑ ወቅት እዚህ ሀገር ውስጥ የምናስተውላቸውን ችግሮች፣ ተስፋዎችና ስጋቶችን የያዙና እንኳንስ ሀገር ወዳድ ዜጎችን ቀርቶ በውሃ ቀጠነ ሰበብ “የነገር አንካሴ” የሚያነሱ ግለሰቦችን ሳይቀር ሊያስማሙ የሚችሉ ይመስለኛል። በተለይ ባለፉት ዓመታት አንዴ “ሙስና”፣ ሌላ ጊዜ ደግሞ፤ “ኪራይ ሰብሳቢነት” በሚል ስያሜ ይጠራ የነበረው ሀገርን እርቃኗን ያስቀራት የለየለት ተግባርን የዳቦ ስሞቹን በመተው፤ “ሌብነት” ብለን በትክክለኛ ስሙ እንጥራው ማለታቸው ያልተመቸው ስው ይኖራል ብዬ አላስብም። በሌብነት ተግባር ላይ የተሰማራ ወገን ካልሆነ በስተቀር።

ርግጥ ሌብነት በንጉሱ ዘመን ‘እጅ መንሻ’፣ በዘመነ ደርግ ‘ጉቦ’ እንዲሁም በኢህአዴግ የስልጣን ዘመን (እስከ አሁን ድረስ ማለቴ ነው) ‘ሙስና እና ኪራይ ሰብሳቢነት’ በሚሉ የልብ ልብ የሚሰጡ አንቆለጳጳሽ ስሞች እየተሽሞነሞነ ሲጠራ ነበር—ለምን እንደሆነ ባይገባኝም። ይህም ለሌባው ወገን ለሚፈፅመው እንደ ሰንሰለት የተያያዘ የዘረፋ ተግባር በማይጨበጥና በማይዳሰስ ለተግባር እየተጠራ የፈፀመው ነገር እንደ መልካም ተግባር እንዲቆጥረው አድርጎታል። በተለይ ከ1994 ዓ.ም ወዲህ ‘ሙስና’ የሚለው ስም የመንግስት መስሪያ ቤት ሳይቀር መጠሪያው ሆኗል—የፀረ-ሙስና ኮሚሽን። እንግዲህ በመንግስት በኩልም የተለሳለሰ ስም ጥቅም ላይ በመዋሉ አንዳንድ ግለሰቦች ትርጉሙን እንኳን በቅጡ ባልገባቸው ሁኔታ ‘እገሌ የተከሰሰው በሙስና ነው’ ሲሉ እናደምጣለን።

ተከሳሹም፤ መሬት ላይ በቁመት ቢደረደር ‘የአያ እንቶኔን’ ርዝመት የሚያክል የህዝብና የሀገር ገንዘብ ሞጭልፎ ሲያበቃ፤ ‘የተከሰስኩት የመንግስት ስራን በአግባቡ አልመራህም ተብዬ ነው’ የሚል ዲስኩር እንዲናገር ምቹ ሁኔታ ፈጥሮለታል። ይህም በሙስና ስር የተካተቱት በርካታ የወንጀል ዓይነቶች በሰበብነት እየቀረቡ፤ “አካፋን አካፋ ዶማን ዶማ” ማለት እንዳንችል ያደረገን ብቻ ሳይሆን፤ ቃሉ ራሱ ለማጭበርበሪያነት ጭምር እንዲውል ምክንያት ሆኗል።

ርግጥም ‘ሌባን ሌባ ካላልነው ምን ይደንቀው?’ እንደሚባለው፤ ሌባን በአዋራጅ ስሙ መጥራት ብቻ ሳይሆን የሰረቀውን ሳይቀር አሸክሞ ማዞር ይገባል ብዬ አምናለሁ። ይህም ሞራልና ግብረ-ገብነት ባለው ማህበረሰባችን ውስጥ ነውረኛና አሳፋሪ ስለሚሆን እንዲሁም ሌባውን የሚያሸማቅቅ በመሆኑ ብሎም ከህብረተሰቡ የሚነጥለው ስለሆነ አንድ የችግሩ ማስተንፈሻ ሆኖ ሊያገለግል ይችላል ብዬ አምናለሁ። ከዚህ አኳያ ዶክተር አብይ ጥሩ ነገር  የዘየዱ ይመስለኛል። ሌብነትን ለመከላከል ያሰመሩትን ቀይ መስመር ቅላቱን በመጨመር ሀገርን ከዘረፋ የሚታደግ አንድ ማለፊያ መንገድ ነው ብዬ አስባለሁ።

ታዲያ እዚህ ላይ የመንግስት አሰራርም ግምት ውስጥ መግባት አለበት ብዬ አምናለሁ። ለሌብነት ‘ሙስና’ የሚል የተሽሞነሞነ ስም በመስጠት መስሪያ ቤት የከፈተለትና በተለያዩ አዋጆችቸ ውስጥ ይህንኑ ስም ያሰፈረው መንግስት፤ የለውጥ ሂደት እንደመሆኑ መጠን፤ የዶክተር አብይን ማረሚያ ተከትሎ በዚህ ረገድ ተገቢውን ማስተካከያ ማድረግ ያለበት ይመስለኛል። ይህ ተግባር ከሁሉም በላይ፤ ሙስናን ለመደበቂያነት የሚጠቀሙ ሌቦችን አስቀድሞ በስማቸው እየጠሩ በማጋለጥ፤ አያያዛቸውን እያየ ጭብጧቸውን የሚነሳቸው ለመሆኑ በርግጠኝነት መናገር የሚቻል ይመስለኛል።  

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ በጉባኤው ላይ የተናገሩትና የእኔን ቀልብ የሳበው ሌላኛው ነጥብ፤ “…ወደድነውም ጠላነውም አረረም መረረም ትናንት ዛሬ ላይ አድርሶናል። ትናንትን መቀበል እንጅ መቀየር አይቻልም። የምንችለው ነገን አስውበን መስራት ብቻ ነው።…” ይህን አባባል በሌላ አገላለፅም ‘የበሬውን ብልሃትና የወይፈኑን ጉልበት ልንጠቀም ይገባል’ ሲሉ ገልፀውታል። አዎ! ነገን አስውቦ ለመስራት ትናንት መሰረት ነው። ከዜሮ ተነስቶ የሚገነባ ምንም ዓይነት ነገር የለም—በሃሳብ የምናልመው ጉዳይ ካልሆነ በስተቀር። ሃሳብ ደግሞ እንደ ለሊት ቅዥት መቋጫ የለውም። ማጠንጠኛው ደግሞ ያው ሃሳብ ብቻ ይሆናል።

“ሮም በአንድ ጀምበር አልተገነባችም” እንደሚባለው ሁሉም ነገር በአንድ ጊዜ ተፈፃሚ ሊሆን አይችልም። ትናንት ሲሰሩ የመጡ ጉዳዩች ለዛሬ መሰረት ናቸው። ዛሬ ደግሞ ለነገ እርሾ ነው። ይህን እርሾ የትም ልንበትነው አንችልም። ዘለግ ያለ ዕድሜና ብስለት ያለው በሬው ትናንት በግብርናው ስራ ላይ ያካበተው ልምድ እንዴት አድርጎ አፈሩን ብልሃት በተሞላበት ሁኔታ በሞፈሩ እንደሚሰነጥቅ ከጉልበታሙ ወይፈን ይልቅ የተሻለ ተሞክሮ ያለው ነው። ወይፈኑም አርሶ ያልደከመ አፍላ ጉልበት ያለው ቢሆንም እርሻው ላይ የሚያጋጥመውን ችግር ከበሬው በተሻለ ብልሃት ሊወጣው አይችልም። እናም ለገበሬው  በሬውንም ሆነ ወይፈኑን በአንድነት ጠምዶ ማረስ የሁለቱንም እምቅ አቅም ለመጠቀም ያስችለዋል። ይህም እርሻው ውጤታማ እንዲሆን ያደርገዋል።

ርግጥ የፖለቲካ ዑደታዊ ጉዞም ከዚህ የበሬና የወይፈን ትርክት ተለይቶ አይታይም። ዶክተር አብይም ትርክቱን ከፖለቲካ ጋር ለማያያዝ የፈቀዱት ለዚሁ ይመስለኛል። በሬው የትናንት ልምድን ያካበቱ ፖለቲከኞችን የሚወክል ነው። ወይፈኑ ደግሞ በመተካካት ሂደት ውስጥ ብቅ ያሉ አፍላና ስራውን ሌት ተቀን መከወን በሚችሉ ወጣቶች የሚመሰል ይመስለኛል። ርግጥ የሀገራችን ፖለቲካ ባለፉት ዓመታት መጣባቸው መንገዶች በተመጋጋቢነት ላይ የተመሰረተ አይደለም። ሁሉም ሲጀምር የነበረው እያፈረሰ ከዜሮ ነው። ይህም ሀገሪቱን እንደጎዳት አሌ የሚባል ጉዳይ አይደለም።

በዶክተር አብይ የሚመራው የለውጡ ሂደት ግን ይህን መንገድ በመዝጋት ሁለቱንም መሳ ለመሳ የማስኬድ ሃሳብ ያለው መሆኑን “ከበሬውም” ለመማርና የእርሱን ብልሃት ለመጠቀም ፍላጎት እንዳለው እየገለፀ ነው። እያደረገ ያለውም ይህንኑ ይመስለኛል። ለዚህም ሌላውን ትተን፤ ትናንት የህዳሴው ግድብ ዋና ስራ አስኪያጅ ሆነው የተሾሙት ኢንጂነር ክፍሌ ሆሮን ተክለ ስብዕናን ብቻ መዝዘን ብንመለከት፤ እውነትም “የበሬውን ብልሃት” መንግስታቸው ለመጠቀም ያለውን ፍላጎት ለመገንዘብ አይከብድም። ምክንያቱም ኢንጂነሩ የህዳሴው ግድብ በስያሜው ከመጠራቱ በፊት “ፕሮጀክት X” በሚባልበት ዘመን (ከዛሬ ስድስት ዓመት በፊት ይመስለኛል) ኢንጂነሩ የግድቡ ዋነኛ አመራር ከመሆናቸውም ሌላ በሙያው የካበተ ልምድና የገዘፈ ብቃት ያላቸው ስለሆኑ ነው። እናም የእኚህን ሰው አቅም  መጠቀም “የበሬውን ብልሃት” በተገቢውና በትክክለኛው ቦታ ላይ እንዲውል ማድረግ መሆኑን መገንዘብ ተገቢ ነው።

ያም ሆኖ ኢንጂነር ክፍሌን ያነሳኋቸው፤ ኢህአዴግ ትናንትን እንደ እነ እንቶኔ እየኮነነ ብቻ የሚጓዝ ድርጅት አለመሆኑንና “የበሬውን አቅም” ለሀገር ጥቅም የሚያውል ድርጅት መሆኑን ለማስገንዘብ እንደሆነ ውድ አንባቢ ልብ ይሏል። እናም ይህ የዶክተር አብይ ንግግር፤ እንዲያው በጭፍንና በደፈናዊ ጥላቻ ትናንትን አምርረው የሚጠሉና በትናንት ውስጥ ምንም ዓይነት በጎ ነገር የሌለ የሚመስላቸው አንዳንድ አካላትን አያያዝ ያየ እንዲሁም ጭብጧቸውንም የነሳ ነው ብዬ አስባለሁ።    

ከዶክተር አብይ ንግግር ውስጥ፤ “…ማንም ቢሆን ‘ኢትዮጵያን ብቻዬን ሰራሁ’ ማለት አይችልም።…” የሚለው ሃሳብም የሚጠቀስ ነው። በእኔ እምነት በከተማ ‘የእኔ ነው አይደለም’ መንፈስ ለሚጨቃጨቁ አንዳንድ ወገኖች ይህ አባባል የማያሻማ ምላሽ ነው። “ለምን?” ካላችሁኝ፤ እንኳንስ በኢትዮጵያ ውስጥ ያለ ከተማ ቀርቶ ኢትዮጵያም ብትሆን በሁሉም ህዝቦች ጥረት “ኢትዮጵያ” መሆን የቻለች እንደሆነ በግልፅ ስለነገሩን ነው። ኢትዮጵያ የተገነባችው በሁሉም ህዝቦቿ ጥረት እንጂ እነርሱ እንደሚያስቡት በጥቂት አካላት ስላልሆነም ጭምር ነው።

ለነገሩ ዶክተር አብይ እንዳሉት ሰላም የሌለው ውስጣዊ ሽኩቻና ፉክክር እየተገነባ ላለው ለውጥ ፋይዳ አይኖረውም። ‘እኔ እበልጥ…እኔ እበልጥ’ የሚል ሰይጣናዊ ፉክክር የትም አያደርስም። ያለንበት የሉላዊነት (Globalization) አንድ ሀገር ከሌላው ጋር በእኩልነት መርህ የሚወዳደርበት እንጂ፤ እርስ በርሳችን እየተብላላን ሀገርን እንደ ካሮት ቁልቁል ከሚያሳድግ እሳቤ ጋር አብረን የምንነጉድበት አይደለም።

እንኳንስ በውስጣችን ቀርቶ፤ ከሌላው ዓለም ጋር የምናደርገው ፉክክር፤ መንፈሳዊ እንጂ ሰይጣናዊ ሊሆን አይገባውም። የእኛ ሀገር ፖለቲካዊ አስተሳሰብም ከዚሁ አኳያ ሊሞረድ ይገባዋል። እናም እጅግ ኋላ ቀር የሆነውን ላለንበት የለውጥ ጉዞ የማይመጥነውን ጥላቻንና  መጠላለፍን እንዲሁም ‘እኔ እበልጥ’ ባይነትን አሽቀንጥረን በመጣል ወደ ዘመነውና ሰላማዊነትን ወደሚሻው የዕድገት ምዕራፍ መጓዝ ያለብን ይመስለኛል። ኢትዮጵያ የእኔም የእርስዎም የአንቺም ሆነ የእናንተ ናትና።

ያም ሆነ ይህ፤ በእኔ እምነት፤ የዶክተሩ ንግግር፤ “አያያዙን አይቶ ጭብጦውን ነሳው” እንዲል የሀገራችን ሰው፤ በህዝቡ ውስጥ የተለያዩ የተለያዩ ተገቢ ያልሆኑና ከፋፋይ ሃሳቦችን ለሚዘሩ አንዳንድ ወገኖች በቂ ምላሽ የሰጠ በሳል አስተምህሮ ብቻ አይመስለኝም። ይልቁንም በእጃቸው ላይ ያለውን የማደናገሪያ “ጭብጦ” የነሳ ለመሆኑ ከላይ የጠቅስኳቸው ጥቂት ነጥቦች ማረጋገጫዎች ይመስሉኛል። የዚህ ፅሑፍ አንባቢም፤ ንግግሩን “የነገር ጭብጦ ነሺው” ብሎ ሊመዘግበው ይችላል። ሰናይ ጊዜ።

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy