እነሆኝ…አሁንም ከጎንህ ነኝ!
እምአዕላፍ ህሩይ
“…ይህን ማንም አይክድም። ይሁንና ሀገሪቱን እየመራ ያለው ገዥ ፓርቲ ኢህአዴግም ሊቀመንበርና የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር መሆናቸውንም መረዳት ያስፈልጋል። እኚህ የሀገር መሪ፤ የሚያስተዳድሩት የኦሮሞን ህዝብ ጨምሮ ሁሉንም ኢትዮጵያዊ በአንድነትና በእኩልነት ነው። በተናጠልና በውግንና የሚመሩት ህዝብ…”
ብዙዎቻችን ሁሉንም ዓይነት ውበት አሟልቶ የሰጠን አይመስለኝም። ውስጫዊና ውስጣዊ ውበትን የታደሉ ሰዎች ጥቂቶች ሳይሆኑ አይቀሩም። አንዱ ካለን፤ ሌላው ሊጎድለን ይችላል። ኧረ እንዲያውም ከባዱን ውስጣዊ ውበትን ትተን፤ ፊት ለፊት የሚታየው ውጫዊ ውበትን ብንመለከት እንኳን፤ ስንት ነገር እንደሚጎድለን የምንገነዘብ ይመስለኛል። ማየት የተሳነው ወንድሜ በግምት የተከለው አጥር የሚመስል ጥርስ ባለቤት እንደሆንኩት እንደ እኔ፤ የተራራቀና የተዘበራራቀ ጥርስ ያለው እድለ ቢስ የዚህ አባባሌ ጥሩ ማሳያ ሆኖ ሊቀርብ ይችላል። ግና እኔ ብቻ አይደለሁም የእንዲህ ዓይነቱ መገለጫ የሆንኩት—ያቺ የመንደራችን ቆንጆ ሜሮን እንኳን፤ የሰፈራችን ልጆች “ሰርቶ ሰርቶ ምነው ከአፍንጫው ነሳት?፤ አፍንጫዋ እኮ ጊዮርጊስ ከእነ ፈረሱ የሄደበት ነው የሚመስለው!” ትባል የለም እንዴ? (እዚህች ላይ ሰውኛ ፈገግታዬንና ምቀኝነቴን ያዙልኝማ!-‘እኔ ብቻ አይደለሁም እገሌም አለችበት’ እያልኳችሁ ነውና!)
ያም ሆኖ፤ የሁሉም ነገሮች ምንጭ የሆነው ፈጣሪ፤ አንዱን ሲሰጥ ሌላውን የሚነሳን የራሱ ምክንያት ይኖረዋል። ‘ምክንያቱ ምንድነው?’ ብትሉኝ…በእውነቱ እኔም አላውቀውም። ደግሞም፤ በፈጣሪ ስራ መመራመር ምድራዊም ይሁን ሰማያዊ ቅጣት እንዳለው ስለማውቅ፤ በማላውቀው ነገር ውስጥ ገብቼ ማንቧቸር አልሻም።…ውይ የእኔ ነገር!…ራሱ ተናግሮ ራሱ ንሰሃ የሚገባ ዓይነት ሰው ሆንኩባችሁ አይደል?…በእውነቱ ከመቀመጫዬ በመነሳት ይቅርታ እጠይቃለሁ። የነገሬ ስረ ነገር፤ ‘ሁሉንም አሟልቶ አይሰጥም፤ ከሰጠም የሚታደኩት ጥቂቶች ናቸው’ የሚለው ሆኖ ሳለ፤ አሁን በማያገባኝ ነገር ገብቼ መቀላመዴ ምን ይባላል?…
አዎ! ፈጣሪ ሁሉንም ነገር አሟልቶ የሰጣቸው ሰዎች እጅግ ጥቂት ይመስሉኛል። በእውነቱ በምድራዊ ዓለም እሳቤ፤ ውጫዊም ሆነ ውስጣዊ ውበት አሟልቶ ከሰጠን እሰየው ነው። ካልሆነ ግን፤ ውስጣዊ ውበት ልህቀቱ የትየለሌ ስለሆነ በእርሱ ላይ ማተኮርን መርጫለሁ። ርግጥ እርሱን ካደለን የስጦታዎች ሁሉ ትልቁ ስጦታ መሆኑን መገንዘብ ይኖርብናል። ታዲያ ‘በውስጣዊ ውበት ውስጥ ምን አለ?’ ብሎ ለሚጠይቅ የዚህ ፅሑፍ አንባቢ፤ እንደ ፈጣሪ ስራ “እኔ አላውቅም” የሚል ምላሽ ልሰጠው አልችልም። ይህ የውበት ዓይነት በገሃዱ ዓለም ላይ በየቀኑ እየተመላለሰ የምናየው ስለሆነ፤ ምላሹም ይኸው መገለጫው ይሆናል ብዬ ስለማምን ነው።
በእኔ እምነት፤ ‘ውስጣዊ ውበት’፤ ቅንነት፣ ታማኝነት፣ አፍቃሪነት፣ ክፋትንና ተንኮልን ተጠያፊነት፣ ታጋሽነት፣ ይቅር ባይነት፣ አስተዋይነት፣ ከእኔ በላይ ለሀገሬና ለህዝቤ ባይነት…ወዘተ. ተግባሮችን በውስጥ መያዝና በተግባርም እውን ማድረግ ይመስለኛል። በአጭሩ በምንኖርበት ዓለም ውስጥ ያሉትን አማካይ ሞራላዊና ግብረ ገባዊ ሰናይ ምግባሮችን አሟልቶ በተሟላ አቅምም ወደ ተጨባጭነት መተርጎም የውስጣዊ ውበት መገለጫ ነው ብለንም ትርጓሜ ልንሰጠው እንችላለን። እንዳልኩት፤ ሁለቱንም የውበት ዓይነቶች አሟልቶ የሰጣቸው ሰዎች ጥቂት ናቸው። ታዲያ በእኔ እይታ፤ ከእነዚህ ጥቂት ሰዎች መካከል፤ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ አንዱ ይመስሉኛል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ፤ ‘በውስጣዊ ውበታቸው’ በአጭር ጊዜ ውስጥ እየከወኑት የመጡት ጉዳይ እጅግ አሰደማሚ ነው። ላለፉት አራት ዓመታት ያህል ስንታመስበት የቆየነው የሰላም እጦት፤ በአንፃራዊነት የተረጋጋ መሆን የጀመረው ርሳቸው ወደ ስልጣን ከመጡ በኋላ ነው። እግር ተወርች ተጠፍሮና መፍቻ በሌለው ትልቅ ሰንሰለት ታስሮ የነበረው የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ፤ አርነት ወጥቶ ለሌሎች አርአያ በመሆንና የታጠቁ የፖለቲካ ሃይሎች ሳይቀሩ ‘ሀገሬ ትሻለኛለች’ ብለው ያለ ጠብመንጃ ባዶ እጃቸውን የገቡት እኚሁ መሪያችን በትረ መንግስቱን ከያዙ በኋላ ነው።
ምን ይህ ብቻ! ልማቱ በውጭ ምንዛሬ እጥረት ‘ባለህበት ሂድ’ ዓይነት ሆኖ ሲንገታገት፤ በበሳል የዲፕሎማሲ ከህሎት ካዝናችን የአዲስ አበቤ አራዳዎች እንደሚሉት “በቻፓ የተሞላው” እና መደበኛ ተቀማጭ እንዲኖረን የተደረገው በእርሳቸው አማካኝነት ነው። ከጎረቤቶቻችን ጋር ከመጠላለፍ ሴራ ወጥተን ወደ መደጋገፍና የጋራ ተጠቃሚነት ጎዳና ገብተን እየተጓዝብ ያለነው በዶክተር አብይ የለውጥ መንገድ ነው። በተለይ፤ ከኤርትራ ጋር የነበረን የ20 ዓመታት የውጥረት ዘመን አክትሞ፤ የወንድማማቸነት፣ የፍቅርና የአብሮነት ተምሳሌት መሆን የቻልነው በዶክተር አብይ አማካኝነት መሆኑን የዚህን ፅሑፍ አንባቢ ምስክር ልቆጥር እችላለሁ።
እናስ ይህን እንደ ስሙ “አብይ” ሆኖ ነገሮችን “በአብይነት” በመከወን ከነበርንበት አረንቋና የአዙሪት እሽክርክሪት ውስጥ እጃችንን ጎትቶ ያወጣንን ሰው፤ “ከጎንህ ነኝ” አለማለት እንደምን ይቻለን ይሆን?—እኔ በበኩሌ፤ ይህን አለማለት ራስን እንደማታለል የሚቆጠር የየዋሆች ተግባር ይመስለኛል። አዎ! እኔ፤ አብይ ሆይ! እነሆኝ…አሁንም ከጎንህ ነኝ ብያለሁ።
ሆኖም “የሚሰሩትን አያውቁምና ይቅር በላቸው!” ብለን እንድንፀልይላቸው እንኳን ‘የማሪያም መንገድ’ የማይሰጡን አንዳንድ የማህበራዊ ሚዲያ የነገር ባለሟሎች፤ እዚህ ሀገር ውስጥ አንድ ነገር ኮሽ ባለ ቁጥር ‘ተጠያቂው ዶክተር አብይ ነው’ ሲሉ ይደመጣሉ። በሌላ በኩልም፤ ዶክተር አብይ ለአንድ ብሔር የቆመ በማስመሰል የአሉባልታ ጣቃቸውን ሲሰፉና ሰተረትሩ ይውላሉ። እነዚህ ወገኖች፤ በትክክለኛ መንገድ ዶክተር አብይንና መንግስታቸውን ቢተቹ የዴሞክራሲያዊ ስርዓት ወግና ማዕረግ መሆኑን ማንም የሚስተው እውነታ አይመስለኝም። መንግስት ትችትንም ይሁን ድጋፍን በእኩልነት ማስተናገድ አለበት ብዬ አምናለሁ።
ዳሩ ግን፤ የእነዚህ ወገኖች ፍላጎት ዶክተር አብይ ከላይ በማሳያነት ያነሳኋቸውን ተግባራት በአጭር ጊዜ ውስጥ በመፈፀሙና ምናልባትም ለውጡ ያልተመቻቸው ይሆናሉ ብዬ አስባለሁ። በእኔ እምነት፤ የእነዚህ ወገኖች ዓላማ፤ የመሪያችንን መልካም ስምና ተግባር ጥላሸት ለመቀባት ከማሰብ የመነጨ ይመስለኛል። ግና፤ “ተግባርህን ንገረኝና ማንነትህን ልንገርህ” እንዲሉ ታታሪዎቹ ጃፓናውያን፤ የዶክተር አብይ ስብዕና፣ አቅምና ብቃት እንዲሁም ተግባር፤ በቀጣናው፣ በአፍሪካና በዓለም ደረጃ በግልፅ የሚታወቅ በመሆኑ፤ ፍላጎታቸው ግቡን ሊመታ የሚችል አይመስለኝም—ተግባር ከቃል በላይ የሚታመን ነውና።
እነዚህ ወገኖች፤ ኢትዮጵያ ውስጥ ቢያንስ ባለፉት 27 ዓመታት ሲንከባለሉ ለመጡ ችግሮች በስድስት ወራት ውስጥ መፍትሔ እንዲሰጣቸው የሚሹ ናቸው። ሀገራችን ውስጥ ያሉትን ፖለቲካዊ፣ ምጣኔ ሃብታዊና ማህበራዊ ችግሮችን በስድስት ወራት ውስጥ እንደምን መፍታት እንደሚቻል ‘ውስጣዊ ውበታቸው’ የሚነግራቸው አይደሉም። ወይም በመግቢያዬ ላይ እንዳልኩት ይህን ውበት ከታደኩት ጥቂቶች ውስጥ አይደሉም። ርግጥም ሊሆኑም አይችሉም። እንደ እውነቱ ከሆነ፤ የዚህ ሀገር ችግሮች፤ ከማህበረሰቡ አስተሳሰብ ጋር አብረው ሲጓዙ የመጡ፤ እንዲያውም እንደ ነውር ሳይቆጠሩ በተለምዷዊ ክስተትነት የሚታዩ የኑሮ ዘይቤ አንድ አካል ሆነዋል ብል ከእውነታም መራቅ አይሆንብኝም።
ታዲያ እንዲህ ዓይነት የተወሳሰበን ነገር በአጭር ጊዜ ውስጥ (ለዚያውም የለውጥ አደናቃፊዎች ባሉበት ሀገር ውስጥ) ለመፍታት፤ ከሁሉም በላይ የአመለካከት አብዮትን ማምጣት የሚጠይቅ ተግባር ነው። የአመለካከት አብዮት የሚከናወነው የሰውን ልጅ አስተሳሰብ በመለወጥ ወይም የሰውን ልጅ ጭልቅላት በማሰብ የሚሰራ ክዋኔ በመሆኑ፤ በሂደት እንጂ የድንገቴ ክስተትነት የሚፈጠር አይደለም—የጊዜን ዑደት ምርኩዝ ማድረጉ የግድ ነውና።
አሁን በምንገኝበት ዲጂታላይዝድ የሉላዊነት ዓለም (The Digitalized Global World)፤ የሰው ልጅ አዕምሮ የያዘውን አስተሳሰብ ከነበረበት እይታ ወደ ሌላ ምልከታ ማሸጋገር ቢቻልም ስራውን አስጋሪ አድርጎታል። ምክንያቱም አስቀድሞ የያዘውን አስተሳሰብ የሚያፀኑ ተመሳሳይ የመረጃ ፍሰት በየጊዜው በህልቆ መሳፍርትነት ስለሚቀርብ ጉዳዩን ውስብስብ ስላደረገው ነው። በዚህም ሳቢያ የአስተሳሰብ አብዮትን በጥቂት ጊዜ ውስጥ ማምጣት ያስቸግራል ብዬ አስባለሁ። የአስተሳሰብ ልህቀት፤ ከማህበረሰቡ ስልጣኔና የአኗኗር ዘይቤ ዕድገት ጋር የተሳሰረ መሆኑም አብዮቱን ለማምጣት የሚደረገውን ትግል አስቸጋሪ ሊያደርገው መቻሉ አጠያያቂ አይሆንም። እናም የአስተሳሰብ አብዮትን፤ “ጧት ተመርቶ፣ ከሰዓት መርካቶ” አድርጎ መጠበቅ አሊያም እንደ ሽሮ ፈሰስ ወዲያው ተሰርቶ ወዲያው እንጀራ ላይ የሚጨለፍ አድርጎ ማሰብ፤ ትክክልም ተገቢም አለመሆኑን ጥላሸት ቀቢዎቹ ሊያውቁት የሚገባ ይመስለኛል። እንዲያ ካልሆነ ግን፤ የሰዎቹን ‘የውስጣዊ ውበት’ መናጋት አንዱ ምልክት አድርጌ የማልቆጥርበት ምክንያት ሊኖረኝ አይችልም።
ያም ሆኖ፤ እዚህ ሀገር ውስጥ ከላይ በጠቀስኳቸው ሲንከባለሉ በመጡ ችግሮች ምክንያት አንድ ነገር ኮሽ ሲል፤ ጣትን ዶክተር አብይ ላይ መቀሰሩ ብዙም ውጤት የሚያመጣ አይመስለኝም። ዶክተር አብይ፤ ሌላው ቢቀር፤ የሀገሪቱን ውስጣዊና ውጫዊ ችግሮች በሰከነና ብልሃት በተሞላበት ሁኔታ ይዘው የለውጡን መንገድ እየጠረጉ መጥተው ግማሽ ላይ በማድረሳቸው ልናበረታታቸውና ከጎናቸው መሆናችንን ልናረጋግጥላቸው የሚገባን ይመስለኛል። ርግጥም ሁላችንም፤ እነሆኝ…አሁንም ከጎንህ ነኝ ልንላቸው ይገባል።
የሀገሬ ሰው ምክንያታዊ መሆኑን አውቃለሁ። ያለ ምክንያት አንድም ነገር ሲያደርግ አይቼው አላውቅም። በውጭም ይሁን በሀገር ውስጥ የሚገኘው ቁጥር ስፍር የሌለው የሀገሬ ሰው፤ ትናንት ዶክተር አብይን እንደደገፋቸው ሁሉ፤ ዛሬም ከጎናቸው መሆኑን አላጣሁትም። ሆኖም፤ አንዳንድ በየማህበራዊ ሚዲያው የምናያቸው “የለውጥ ተቸካዮች”፤ ለዚህች ሀገር መድህን ሆነው ከእነ ‘ውስጣዊ ውበታቸው’ ብቅ ያሉትን ዶክተር አብይን ባልዋሉበት ሊያውሏቸው ሲሞክሩ መመልከት እጅግ ያስገርመኛል፤ ያስደንቀኛልም።
ዶክተር አብይ አንድ ሹመት በሰጡ ቁጥር፤ ስማቸውን ከኦሮሞ ብሔረሰብ ጋር ለማጣበቅ መሞከር የማህበራዊ ሚዲያው “ተቸካዮች” አንድ ስልት እየሆነ የመጣ ይመስላል። ግና፤ እነዚህ ወገኖች ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ ትናንትም ይሁን ዛሬ፤ ለኢትዮጰያዊነትና ለአንድነት የሚዘምሩ ህዝብ አፍቃሪ የሀገር ልጅ መሆናቸውን አሳምረው ያውቃሉ። ይሁን እንጂ፤ “ባልበላውም ጭሬ ልበትነው” እንዳለችው ዶሮ፤ እነርሱም ከዶክተር አብይ ስብዕና ጋር አብሮ የማይሄድ ስም ይዘው መንገታገታቸው ትርፉ ራስን ማስገመት ብቻ ነው የሚመስለኝ።
ርግጥ ነው—ዶክተር አብይ አህመድ አሊ የኦሮሞ ብሔር ተወላጅ መሆናቸው ይታወቃል። ኦሮሚያን የሚመራው የኦሮሞ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲም (ኦዴፓ) ሊቀመንበርም ናቸው። ይህን ማንም አይክድም። ይሁንና ሀገሪቱን እየመራ ያለው ገዥ ፓርቲ ኢህአዴግም ሊቀመንበርና የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር መሆናቸውንም መረዳት ያስፈልጋል። እኚህ የሀገር መሪ፤ የሚያስተዳድሩት የኦሮሞን ህዝብ ጨምሮ ሁሉንም ኢትዮጵያዊ በአንድነትና በእኩልነት ነው። በተናጠልና በውግንና የሚመሩት ህዝብ ያላቸው አይመስለኝም። ሊኖራቸውም አይችልም። እርሳቸውም በቅርቡ እንዳሉት፤ የትኛውም ህዝብ ሁለተኛ ዜጋ እንዲሆን ከቶም አይሹም። ታዲያ ነገሩ እንዲያ ቢሆን ኖሮ፤ ሰሞነኛው የካቢኔ ሹመት ሚዛናዊ ባልሆነና አብዛኛውም ህዝብ የተቀበለው ባልሆነ ነበር። ሆኖም በሹመቱ ላይ የራሳቸው አጀንዳ ያላቸው ወገኖች ካልሆኑ በስተቀር አብዛኛው ህዝብ ተስማምቶበታል። እናም ‘ዶክተር አብይ ኦሮሞ ስለሆኑ ለኦሮሞ ያደላሉ’ ብሎ ማሰብ ወደ እውነታው አለመቅረብ መሆኑን መገንዘብ ያስፈልጋል እላለሁ።
በእኔ እምነት፤ “የለውጥ ተቸካዩቹ” ወደ እውነታው ጓዳ ዘልቀው በመግባት ሃቁን መመልከት ይኖርባቸዋል እላለሁ። እንደ እውነቱ ከሆነ፤ በለውጥ ሂደት ውስጥ ብዙ ችግሮች ሊፈጠሩ ይችላሉ። ችግሮቹ ግን፤ ከላይ የጠቀስኳቸው የተንከባለሉ ችግሮች የወለዷቸው፣ በአስፈፃሚዎች አቅም አሊያም ከእውቀት መጓደል ጋር አብሮ የሚታዩ እንጂ፤ ከጠቅላይ ሚኒስትሩ የመነጩ ናቸው ብሎ ማሰብ ሚዛናዊ አተያይ ነው ብዬ አላስብም። እናም ዶክተር አብይ የሀገሪቱ የህዝብ እንደራሴዎች አምነው የሰጧቸውን ኃላፊነት ሁሉንም ህዝብ ባማከለ መንገድ እያገለገሉበት መሆኑን ዓይንን ከፍቶ መመልከት ያስፈልጋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ፤ ሁሉንም ህዝብ በአንድነትና በእኩልነት የሚመሩ እንጂ፤ የኢህአዴግን ጋራ ስልጣን ለተወከሉበት ህብረ-ብሔራዊ ድርጅት ብቻ የሚሰጡ መሪ አይደሉም። ስብዕናቸውም ከዚህ ዓይነት የጥበት መንገድ የወጣ ነው። እስካሁን የመጡባቸው የጥቂት ወራት ተመክሮዎችም ይህን የሚያረጋግጡ ይመስለኛል። አብዛኛዎቻችን የሌለንን ‘ውስጣዊ ውበት’ የታደሉት ዶክተር አብይ፤ ዛሬም በትናንትናው ህዝባዊ ጎዳና ላይ የሚገኙ ብርቅዬ የህዝብ ወዳጅ ናቸው።
ታዲያ እዚህ ላይ፤ እኔም እንደ “ተቸካዮቹ” ብሔር ቆጠራ ውስጥ መግባት አልሻም። ምክንያቱም ማንም ግለሰብ ኢትዮጵያዊ እስከሆነ ድረስ፤ ከየትኛውም ብሔር ይጣ ከየትም፤ የመስራት ክህሎትና ብቃት እንዲሁም ለውጡን በታማኝነትና በቁርጠኝነት የመምራት አቅምና ችሎታ እስካለው ድረስ፤ ቢሾም በተገቢነቱ ላይ ጥያቄ ያጭራል ብዬ ስለማላምን ነው። እናም ዶክተር አብይን ባልዋሉበትና በማይመጥናቸው ቦታ ልናስቀምጣቸው ባለመሞከር፤ በፍላጎታችን ያመጣነውን ለውጥ፤ በሙሉ አቅም መደገፍ ይኖርብናል እላለሁ። ሁላችንም የለውጡ “አብዮች” ስለሆንን፤ እነሆኝ…አሁንም ከጎንህ ነኝ ልንላቸው ይገባል። ሰናይ ጊዜ።