አይጥ በበላ ዳዋ አይመታም!
እምአዕላፍ ህሩይ
“…ተቋሙ ይህን ያህል የአየር ሰዓት ተሰጥቶት ‘ማንነቴን እወቁልኝ’ ማለቱ፤ እኔንና ጓደኞቼን በእጅጉ አስገርሞናል። “የጉድ ሀገር!” አልን። ግና ነገሩ ‘ጉድ አንድ ሰሞን ነው’ ተብሎ አሊያም በሌላ ተደራራቢ ክስተቶች ተውጠን ነው መሰል ረሳነው። እኔ ግን፤ የሜቴክን የምሽቱን ተረክ እንዳዳመጥኩ፤ ወዲያውኑ ወደ አዕምሮዬ ጓዳ ሽው ያለው፤ ‘በመንግስት ውስጥ ሌላ መንግስት’ (Government with in Government) ወይም “State Capture” እየተባለ የሚታወቀው ፅንሰ-ሃሳብ ነው። ነገሩ እንዲህ ነው።…”
“ሀገር ሲያረጅ፤ ጃርት ያበቅላል” የሚሉት ይትብሃል በእኛ ላይ የደረሰብን ይመስለኛል። ርግጥም ደርሶብናል። አልደረሰብንም የሚል ካለ፤ ሊሞግተኝ ይችላል። በሀገሪቱ ገንዘብ እንዳሻቸው “በሸነኔ’’ የሚሉ የነበሩ፣ በዘመድ አዝማድ ተሰባስበው የሚቀራመቱ፣ ያለ ግብራቸው፤ በውድ ገዝተው በርካሽ የሚሸጡ የሰው ጃርቶች በውስጧ ይዛ ስትጓዝ ነበር—ኢትዮጵያ። አዎ! ይህች ምስኪን ሀገር፤ እንዲህ ዓይነቶቹን ጉደኛ “ጃርቶችን” ማብቀሏን ጠቅላይ አቃቤ ህግ አቶ ብርሃኑ ፀጋዬ ትናንት ነግረውናል። ‘ለሀገራችንም ይሁን ለእኛ ፅናቱን ይስጠን’ እንጂ፤ ከቶ ሌላ ምን እንላለን?
የጃርቶቹ እሾሆች የሀገሪቱን ስጋ እንደ ግንደ ቆርቁር ወደ ውስጥ ሰርስረው በልተውታል። መቅኒዋንም ጠጥተውታል። አጥንቷንም ልገውታል። የኋላ ኋላም፤ ‘ላይዋና ውስጧ አልቆ መለ-መላ ግንዷን የቀረች፣ ስጋም ሆነ አጥንት የሌላት ሀገር-ኢትዮጵያ’ ለማለት የፈለጉ ይመስላል (ትንሽዬ ፈገግታ)። ርግጥም እነርሱ ባይሉት፣ ለማለት የተፈለገው ይኸው ለመሆኑ ምግባራቸው አፍ አውጥቶ ይናገራል—‘ካላስ!’ አለ አረብ—‘በቃ!’ ለማለት ሲፈልግ። የአቃቤ ህጉ “የጠላት ሀገርም ቢሆን እንዲህ አይዘረፍም” በማለት ያሰሙት ቁጭት፤ የመጣው እንዲሁ ዝም ብሎ አይመስለኝም። መነሻውም ይሁን መድረሻው፤ ውስጧ ተቦርቡሮ ቀፎዋ ብቻ የቀረ መሆኗን ከገምት ያስገባ ስለሆነ ይመስለኛል።
የብረታ ብረትና ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን (ሜቴክ) በአንድ ወቅት በፓርላማ አባላት ስራውን በተገቢው መንገድ አልተወጣም ተብሎ ክፉኛ ሲተች አስታውሳለሁ። ታዲያ ሜቴክም ወዲያውኑ ምሽቱን የኢቲቪን ቻናል ገዝቶ ይሁን ተውሶ በውል በማይታወቅ ሁኔታ፤ ከሁለት ሰዓታት ዘለግ ላለ ጊዜ “ድርሳነ-ዘሜቴክ” የተሰኘውን ተረክ ሲያስነግርብን አመሸ። አንድ የመንግስት ተቋም፤ ሀገሪቱ ውስጥ ሌላ ስራ የሌለ ይመስል፤ ይህን ያህል የአየር ሰዓት ተሰጥቶት ‘ማንነቴን እወቁልኝ’ ማለቱ እኔንና ጓደኞቼን በእጅጉ አስገርሞናል። “የጉድ ሀገር” አልን። ግና ነገሩ ‘ጉድ አንድ ሰሞን ነው’ ተብሎ አሊያም በሌላ ተደራራቢ ክስተቶች ተውጠን ነው መሰል ረሳነው። እኔ ግን፤ የሜቴክን የምሽቱን ተረክ እንዳዳመጥኩ፤ ወዲያውኑ ወደ አዕምሮዬ ጓዳ ሽው ያለው፤ ‘በመንግስት ውስጥ ሌላ መንግስት’ (Government with in Government) ወይም “State capture” እየተባለ የሚታወቀው ፅንሰ-ሃሳብ ነው። ነገሩ እንዲህ ነው።…ይህ ፅንሰ- ሃሳብ በተለያዩ ሀገሮች ውስጥ በመንግስት ጓዳ ውስጥ ቁጭ ብለውና በመንግስት ገንዘብ እያዘዙ መንግስትን እንደ ዥዋዥዌ ወዳሻቸው መንገድ የሚመሩ ግለሰቦች አሊያም የተደራጁ ቡድኖችን የሚመለከት ነው። በቀላል ቋንቋ ማፍያዎች ተብለው ሊጠቀሱም ይችላሉ።
የዚህ ፅሑፍ አንባቢ፤ ስለ ፅንሰ ሃሳቡ ያውቅ እንደሆን አላውቅም። ካወቀ ‘ይበል!’ እላለሁ። ካላወቀ ግን ጉዳዩን እንዲህ እገልፀዋለሁ። ‘በመንግስት ውስጥ ሌላ መንግስት’ ወይም “state capture”፤ መንግስት ውስጥ ቁጭ ብለው፤ የራሳቸውን ጥቅም ሊያስጠብቅ እስከሚችል ህግ እስከማውጣት የሚደርሱ፣ በመንግስት ውስጥ ሌላ መንግስት ሆነው እንዳሻቸው የሚያዙ፣ የሚነግዱ፣ የሚያስነግዱ እንዲሁም የራሳቸውን እስር ቤት አቋቁመው ከእነርሱ ተቃራኒ የሆኑ ወገኖችን እንደ ጥጃ የሚያስሩበት ቦታ ያላቸው፣ በሀገር ውስጥና በውጭ የሚገኙ ሚዲያዎችን እንዳሻቸው የሚዙና የሚያሾሩ…ወዘተርፈ ተግባሮችን የሚፈፅሙ ግለሰቦችንና ቡድኖችን ለመግለፅ ጥቅም ላይ የሚውል ፅንሰ-ሃሳብ ነው።
ርግጥ ፅንሰ-ሃሳቡ፤ በታላላቅ የዓለም የፋይናንስ ተቋማት ሳይቀር ብርቱ ጥናት የተካሄደበት ነው። ይሁንና የዚህ ፅሑፍ ዓላማ ፅንሰ-ሃሳቡን ለግንዛቤ ያህል ማስታወስ በመሆኑ፤ (ጊዜ ካገኘሁ ወደፊት በዝርዝር እመለስበታለሁ)፤ በመንግስት ውስጥ ሌላ መንግስት መስርቶ በሀገርና በወገን ሃብትና ንብረት ላይ አዛዥና ናዛዥ መሆንን ለማመላከት መሆኑን አንባቢዎቼ እንድትረዱልኝ እሻለሁ። እናም እዚህ ሀገር ውስጥ በሜቴክ ሲከናወን የነበረው ጉዳይ፤ (ለአብነት ያህል ኢቲቪ ላይ ከሁለት ሰዓት በላይ የፈጀ ፕሮግራምን ማቅረብ)፤ የዚሁ በመንግስት ውስጥ ሚዲያውን ይዞ ለሚፈለግበት ዓላማ የማዋል የ“State capture” አንድ መገለጫ ነው።
በመንግስት መዋቅር ውስጥ የሚገኙ ግለሰቦች ለዘረፋ ተደራጅተው እንደ ሰንሰለት እስከ ተያያዙ ድረስ፤ “State Capture”ን ለመዋጋት እጅግ ፈታኝ ይሆናል። ለዚህም ነው—የሙስና ተግባር ውስብስብ ስለሆነ መንግስት ራሱ ሊቆጣጠረው እስከማይችልበት ደረጃ ሊደርስ ይችላል። ዳሩ ግን፤ በህይወት እየተወራረደ ይህን ተግባር ለማስወገድ የሚፈልግ ጠንካራ መሪ ከተገኘና የመንግስትን መዋቅር ከ“State Capture” እንደ ሜቴኩ ሁሉ ሌላውንም ፍርስርሱን ማውጣት ይቻላል። የዶክተር አብይ አህመድ አመራር ያደረገው ይህንኑ በመሆኑ ሊደነቅ ይገባዋል ብዬ አምናለሁ።
ይህም የድሮው “ሀገሬ ኢትዮጵያ የሞተልሽ ቀርቶ የገደለሽ በላ” የሚለው የዋህ ይትብሃል በዚህ ዘመን ሰሚ አልባ መሆኑን የሚያመላክት ነው። አዎ! “ሀገሬ ኢትዮጵያ የሞተልሽ ቀርቶ…” አባባል ድሮ ቀረ ተብሎ ሊመዘገብ ይችላል—አሁን በምንገኝበት የለውጥ ሂደት። ርግጥም በዚህ የለውጥ ዘመን ሊኖር የሚገባው ይትብሃል “እምዬ ኢትዮጵያ የሰራልሽ በላ” ብቻ ነው። የለውጡ ዓላማ፤ የህግ የበላይነትን ብቻ ማስከበር ነው። ለሀገር ዕድገትና ልማት ማነቆ የሆነውን የ“State Capture” ሰንሰለትንና ፈፃሚዎቹን በቁጥጥር ስር ማዋል ነው። ተጠርጣሪ ግለሰብ ወንጀለኞችን በህግ ጥላ ስር እንዲውሉ ማድረግ ነው።
የህግ የበላይነት ከየትኛውም ብሔር ጋር ግንኙነት የለውም። ተርጣሪ ግለሰብ ወንጀለኛው የሚወክለው ራሱን ብቻ እንጂ የትኛውንም ብሔር አይሆንም። ሊሆንም አይችልም። አበበ የሚባል ተጠርጣሪ ወንጀለኛ የሚወክለው አበበን እንጂ “እገሌ” የተሰኘን ብሔር አይደለም። እንደዚያ ዓይነት አስተሳሰብ “አይጥ በበላ ዳዋ ተመታ” ይሆናል። እናም አይጥ በበላበት ዳዋ የሚመታበት አሰራርን ማሰብ፤ ሁላችንም ስንጮህለት የነበርነው የህግ የበላይነት ተፃርሮ ከመቆም ውጭ የሚሰጠው ሌላ ትርጉም አይኖርም። እናም ‘እነሆ አይጥ ሆይ! አንተ በበላኸው እኔ መመታት የለብኝም’ ማለት ይኖርብናል። ይህን ስናደርግ፤ የምንሻው የህግ የበላይነት በፍጥነት ይመጣል። ሁሉም ዜጋ ከሀገሪቱ ሀብት እኩል ተጠቃሚ ይሆናል።
የህግ የበላይነትን ስንጎናፀፍ፤ ዜጎች በህግና በስርዓት ይመራሉ። ማንም ከማንም የበላይም ሆነ የበታች አይሆንም። ሁሉም እኩል ይሆናል። በመንግስት መዋቅር ውስጥ የሚገኙ ባለስልጣናትም፤ ህዝቡ በእምነት የሰጣቸውን ስልጣን በግልፅነትና በተጠያቂነት እንዲሁም ህግና ስርዓትን መሰረት አድርገው ስራቸውን ይፈፅማሉ። ይህ ከሆነም፤ የመንግስትን አንድ እጅ አስሮ መንግስትንና ህዝቡን መበዝበዝ ያቆማል። በእኔ እምነት፤ ሜቴክ በመገለጫነት የቀረበበት የ“State Capture” ትግበራም ዳግም ላይመለስ እስከ ወዲያኛው ይሰናበታል። ወይም ተፅዕኖው ችግር የማይፈጥር እንዲሆን ይደረጋል። ይህ እንዲሆን መንግስት የህግ የበላይነትን ለማስከበር ልክ እንደ ሰሞኑ ሲነሳ፤ ሁሌም “አይጥ በበላ ዳዋ አይመታም!” የሚለውን ይትብሃል እንደ ህዝብ መያዝ ይኖርብናል። የበላውም ይሁን ያልበላው ‘በእገሌነት” መብላላት አይኖርበትም። ሰናይ ጊዜ።
ህሩይ! ለምን ኣይመታ ዳዋ!
ጎታ መች ሆነ ? ኣይዋ?
እየደበቀ ኣይጥን፤ መሸሸጊያ ከሆነ ለሌባዋ
ኣይመታ ታዲያ፤ ዳዋ?
በጨፈቃ!
ምርቱም እንዳይረግፍ፣ ብዙም ባይሆን በለበቃ
ቸብ ቸብ እንጂ! ድበቃ?
ያሳጣል እኮ ኣጉል ጠበቃ!