Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

ከዚህ ጋር ተያይዞም የ37 ቢሊየን ብር የውጭ ግዢን ያለ ጨረታ ሂደት ማከናወኑን ተናግረዋል።

0 806

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

የብረታ ብረትና ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን (ሜቴክ) ያለ ህጋዊ የጨረታ ሂደት የ37 ቢሊየን ብር የውጭ ሃገር ግዢ መፈጸሙን የፌደራል ጠቅላይ አቃቤ ህግ ገለጸ።

የፌደራል ጠቅላይ አቃቤ ህግ አቶ ብርሃኑ ጸጋዬ በህግ ቁጥጥር ስር የዋሉ ሰዎችንና በፍትህ ስርዓቱ እየተሰሩ ስላሉ ስራዎች   መግለጫ ሰጥተዋል።

በመግለጫቸውም የብረታ ብረትና ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን (ሜቴክ) ከ2004 እስከ 2010 ዓ.ም ድረስ ባከናወናቸው ግዢዎችና ተዛማጅ ጉዳዮች ላይ ምርመራ በማድረግ መረጃ መሰብሰብ መቻሉን ጠቅሰዋል።

በዚህም ተቋሙ በሃገራዊ ግዙፍ ፕሮጀክቶች፣ በንብረት ግዢ እና ፋይናንስ ጋር በተያያዙ የግዢ ሂደቶች ላይ ከፍ ያለ የህግ ጥሰት መፈጸሙን አስረድተዋል።

ከዚህ ጋር ተያይዞም የ37 ቢሊየን ብር የውጭ ግዢን ያለ ጨረታ ሂደት ማከናወኑን ተናግረዋል።

ግዢዎቹ በተቋሙ የበላይ ሃላፊዎች፣ በሃላፊዎቹ የስጋ ዘመድ፣ በጥቅም በተሳሰሩ ግለሰቦችና ተቋማት መካከል እንዲሁም በደላላዎች የተፈጸሙ መሆናቸውንም ነው ጠቅላይ አቃቤ ህጉ የተናገሩት።

ከሃላፊዎቹ ጋር የስጋ ዝምድና ያላቸው ግለሰቦችም እንደ ደላላ በመሆንና ተቋሙን ከተለያዩ አለም አቀፍ ኩባንያዎች ጋር በማገናኘት ግዢው እንዲፈጸም ማድረጋቸውን ጠቅሰው፥ በዚህም በቢሊየን የሚቆጠር የሃገር ሃብትና ንብረት መመዝበሩን አንስተዋል።

የንብረት ግዢው ከአንድ ኩባንያ በድግግሞሽ እንደሚፈጸም ያነሱት ጠቅላይ አቃቤ ህጉ፥ በዚህ ሂደት ግዢው ላይ እስከ 400% የዋጋ ጭማሪ በማድረግ ግዢው ይፈጸም ነበርም ነው ያሉት።

በዋናነትም ቻይና እና ሲንጋፖር ከሚገኙ ኩባንያዎች ግዢው የሚፈጸም ሲሆን፥ የስጋ ዝምድና ያላቸው ደላሎችም በዚህ ሂደት ከፍተኛ ገንዘብ ያገኙ ነበር ነው የተባለው።

በዚህ የግዢ ሂደት በርካታ እቃዎች የመከላከያ ሚስጢራዊ እቃዎችን ተገን በማድረግ መፈጸሙን ያነሱት ጠቅላይ አቃቤ ህጉ ከዚህ ጋር ተያይዞም እስከ 105 ጊዜ ኮንትራት የተፈጸመባቸው ተቋማት መኖራቸውን አስረድተዋል።

በዚህ ሂደትም የአምስት ክሬን ግዢ ተፈጽሞ አራቱ ወደ ኮርፖሬሽኑ ሲገቡ አንደኛው ክሬን በሱዳን በኩል በህገ ወጥ መንገድ ወደ ሃገር ውስጥ በመግባት ለግለሰብ መጠቀሚያ መዋሉን አስታውሰዋል።

ከዚህ ባለፈም ተቋሙ የሃገር ውስጥ ግዥን ሙሉ በሙሉ ያለምንም የጨረታ ሂደት መፈጸሙንም አስረድተዋል።

በዚህ ሂደት ከአንድ ኩባንያ 21 ጊዜ፣ ከሌላው 18 እንዲሁም ከሶስተኛ ኩባንያ ደግሞ እስከ 15 ጊዜ በድግግሞሽ ግዢ የፈጸመ ሲሆን፥ ከአንድ ኩባንያም የ205 ሚሊየን ብር ግዢ መፈጸሙን ጠቅላይ አቃቤ ህጉ አስረድተዋል።

በዚህ መልኩ በተፈጸመ ግዢ በርካታ የሃገር ሃብትና ንብረት የባከነ ሲሆን፥ ተቋሙም ከተቋቋመበት አላማ ውጭ በርካታ ግዢዎች መፈጸሙ ተጠቅሷል።

በዚህም ከ28 አመት በላይ ያገለገሉ አባይ እና አንድነት የተሰኙ በሁለት መርከቦች እንዲሁም እስከ 50 አመት ያገለገሉ አምስት የአውሮፕላን ግዢዎች መፈጸሙንም ጠቅሰዋል።

የአገልግሎት ዘመናቸው አብቅቷል የተባሉት መርከቦች ከፍተኛ ገንዘብ የወጣባቸው ሲሆን፥ ለጥገና 513 ሚሊየን 837 ሺህ ብር ወጪ መደረጉም በመግለጫው ተነስቷል።

ጠቅላይ አቃቤ ህጉ አንደኛዋ መርከብ በህገ ወጥ መንገድ በንግድ ስራ ላይ ተሰማርታ የተገኘው እስከ 500 ሺህ ዶላርም ወደ ሜቴክ ሳይገባ ቀርቷልም ነው ያሉት በመግለጫቸው።

ሜቴክ ኮንትራት የወሰደባቸውን ፕሮጀክቶች ለመከታተል በሚል ከ50 አመት በላይ ያገለገሉ 5 አውሮፕላኖችን ግዥ በ11 ሚሊየን 732 ሺህ 529 ብር መፈጸሙንም አውስተዋል።

ከተገዙት አውሮፕላኖች ውስጥም አራቱ አገልግሎት መስጠት ያቆሙ ሲሆን፥ አንደኛው አውሮፕላን ግን የገባበት አለመታወቁንም ጠቁመዋል።

በአጠቃላይም ተቋሙ በፈጸመው የመርከብና አውሮፕላን ግዥ 24 ሚሊየን 949 ሺህ 500 ብር ጉዳት በመንግስት ላይ ማድረሱንም ነው በመግለጫቸው ያነሱት።

ተቋሙ ከዚህ በተጨማሪም እንደ ሆቴል ባሉ ግዥዎች ላይ በመሳተፍ ከተቋቋመበት አላማ ውጭ የህግ ጥሰት ፈጽሟል ነው ያሉት።

እስካሁን በተደረገው ማጣራትም 27 ሰዎች በሙስና ተጠርጥረው በቁጥጥር ስር የዋሉ ሲሆን፥ የቤት ካርታ፣ የአክሲዮን ደብተር፣ የቤት ውል ሽያጭ፣ በርካታ ተሽከርካሪዎች፣ የባንክ ሂሳብ ደብተር እና የጦር መሳሪዎያዎችን ጨምሮ በርካታ ማስረጃዎች ተገኝተዋል ብለዋል።

ከዚህ ጋር ተያይዞ በቁጥጥር ስር የዋሉት ግለሰቦች ቁጥር ሊጨምር እንደሚችልም ነው በመግለጫው የተነሳው።

አሁን ላይም ምርመራው የተጠናቀቀ ሲሆን፥ ክስ ተመስርቶ ወደ ፍርድ ሂደት በቅርቡ እንደሚገባም አስታውቀዋል።

 

 

በምናለ ብርሃኑ

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy