Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

የ29 ዓመቷ የህክምና ዶክተርና ኢንጅነር ዕልልታ ጉዞ

0 3,339

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

የ29 ዓመቷ የህክምና ዶክተርና ኢንጅነር ዕልልታ ጉዞ

(የኢ.ፌ.ዲ.ሪ የሴቶች፣ ሕጻናትና ወጣቶች ሚኒስቴር ፣ ጥቅምት 23 ቀን 2011 ዓ.ም)

” በአንድ የትምህርት ዓይነት ብዙ ተማሪዎች ውጤት ሲበላሽብን መምህሩ ለእናንተ የህክምና ትምህርት አይገባችሁም አለን፤ በጣም ነበር የተናደድኩት”
ቢሾፍቱ ተወልዳ ያገደችው ዕልልታ ነጋ 2001 ዓ.ም. ላይ ነበር የህክምና ትምህርት ለመከታተል መቀሌ ዩኒቨርሲቲ ተመድባ ወደዚያው ያቀናችው ።

ለሶስት ዓመታት ያህል ትምህርቷን ስትከታተል ብትቆይም ነገሮች እንዳሰበችው እንዳልቀለሉላት ታስታውሳለች።

“አንዳንድ ሰው ችሎታሽን አቅምሽን ይንቃል፤ በአንድ የትምህርት ዓይነት ብዙ ተማሪዎች ውጤት ተበላሸብን፤ ህክምና ደግሞ በአንድ ኮርስ ከወደቅሽ ለመቀጠል በጣም ይከብዳል፤ ያኔ አስተማሪው ‘ለእናንተ ሜዲሲን አይገባችሁም’ አለን፤ ሶስት ዓመት ሙሉ ቆይተሽ እንደዚህ ስትባይ በጣም ይሰማል፤ እኔ ደግሞ ከልጅነቴ ጀምሮ ነበር ህክምና መማር የምፈልገው፤ እንደዛ ስባል በጣም ነበር የተናደድኩት፤ ከዚያ ሞራሌ ስለተነካ ቤተሰቦቼን ነግሬያቸው እኔ በቃ እዚህ በፍጹም አልቀጥልም ነበር ያልኩት፤ ግን በህክምና ትምህርት ጨርሼ ተመልሼ ሄጄ እንደማናድደው ነበር ያሰብኩት።”

ዕልልታ አቅሟን ለማሳየት ቆርጣ ወደ አዲስ አበባ ተመልሳ በቤቴል ሜዲካል ኮሌጅ የህክምና ትምህርቷን እንደ አዲስ ሀ ብላ ጀመረች፤ ግን አሁንም አንድ ነገር አዕምሮዋን ይከነክናት ነበር።

“አብሬያቸው ስማር ከነበሩ ልጆች ወደ ኋላ መቅረቴ በጣም ነበር የሚሰማኝ” የምትለው ዕልልታ በጓደኞቿ ጉትጎታ ይህን ስሜት የማሸነፊያ መንገድ አገኘች።

“የነገርኳቸው ሁሉ ‘ያምሻል እንዴ?” ነበር ያሉኝ
“እንዲያውም እኔ ዶክተር ብቻ አይደለም መሃንዲስም እሆናለሁ አልኩኝ፤ የነገርኳቸው ሁሉ ‘ያምሻል እንዴ?’ ነበር ያሉኝ፤ አትችይውም ተይ ይከብድሻል፤ ይቅርብሽ የሚለኝ ብዙ ሰው ነበረ፤ እናቴ ራሱ በጣም ነበረ የተከራከችኝ።”

ዕልልታ የብዙሃኑ ተቃውሞ ቢበረታባትም የሂሳብና የፊዚክስ ትምህርት እንደምትወድ ከሚያውቁት ጓደኞቿን ግን ሙሉ የሞራል ድጋፍ አገኘች። የሲቪል ምህንድስናውን ትምህርት በድፍረት ስትገፋበት ደግሞ አይዞሽ በርቺ የሚላት ሰው እየበዛ መጣ።

“እኔም ትምህርቱን ወደድኩት፤ ለህክምናው ትምህርት ማንበብና ተግባራዊ ልምምዶችን ማድረግ ይጠበቅብኛል፤ ምህንድስናው ደግሞ በብዛት ካልኩሌሽን (የሂሳብ ቀመር) ነው፤ እሱን ስሰራ ጭንቅላቴ ፈታ ይላል፤ የህክምናው ንባብ ሲበዛብኝ ወደ ምህንድስናው ዞር ብዬ ቀመሩን እየሰራሁ ራሴን አነቃቃ ነበር።”

አሁን ዕልልታ ይህንን ፈታኝ ጊዜ አልፋ በሰባት ዓመታት ውስጥ ሁለቱንም ጎን ለጎን እያስኬደች በ29 ዓመቷ ባለፈው ዓመት የህክምናና የምህንድስና ዲግሪ ባለቤት ሆናለች።

በትምህርትና በፈተና ወቅት ያሳለፈቻቸውን ከባድና አልህ አስጨራሽ ጊዜያት ሁሉ የምትረታቸው የመጨረሻውን ፍሬ በማሰብ እንደነበር ትናገራለች።

“በጣም ብዙ ጊዜ ‘ምን እንቀልቅሎኝ ነው?’ ብዬ አውቃለሁ፤ ለምሳሌ ፈተና በጣም ሲደራረብብኝ ሁለቱንም ለማንበብና ለመስራት ስጥር ውዬ የማድርባቸው ጊዜያት ነበሩ፤ የምህንድስናው ፈተና ብዙ ጊዜ 9 ሰዓት ላይ ነበር የሚሆነው። ስለዚህ የህክምናውን ጠዋት ተፈትኜ እየሮጥኩኝ ወደ ምህንድስናው ነበር የምሄደው፤ በጣም ስልችት ብሎኝ ልተወው እልና መልሼ ግን የመጨረሻውን ድሌን ማሰቤ ነው እንድገፋበት ያደረገኝ።”

“ሰው ሳያያኝ ተደብቄ አልቅሼ አውቃለሁ”
የህክምና ዶክተሯና መሐንዲሷ ዕልልታ ነጋ የህክምናውንን ትምህርት በቀን የሲቪል ምህንድስናውን ደግሞ በማታው ክፍለ ጊዜ ነበር የተማረቸው። ለሁለቱም ጊዜዋን ለማብቃቃት ደግሞ አስቀድሞ መዘጋጀት የሁልጊዜ መርኋ ነው።

“የፈተና ቀኖች በብዛት ቀደም ብለው ነው የሚወጡት፤ በተለይም የተደራረቡ ፕሮግራሞች ካሉኝ እነሱን ቶሎ ብዬ ነው ለማጣራት የምሞክረው፤ እስከምችለውና ንቁ እስከሆንኩበት ሰዓት ደረስ በደንብ አጠናለሁ፤ እንቅልፌ ሲመጣ ያው በጭንቀት ቢሆንም እተኛለሁ፤ ፈተናዎች በጣም ከተደራረቡቡኝ ግን አልተኛም፤ እንቅልፍ ይነሳኛል፤ በተለይ ለህክምና ተማሪዎች በየዓመቱ መጨረሻ የሚደረግልን የቃል ፈተና (Oral examination) ሲደርሰ ደግሞ የማልተኛበት ጊዜ ይበዛል'”
ዕልልታ እንዲያውም እንዳንዴ የቤት ውስጥ ስራ በማገዝ የተረፈውን ጊዜዬን እጠቀማለሁ ትላለች።

ይሁንና የሚያስፈልጋትና ያላት ጊዜ አልጣጣም ብሏት መቼም የማትዘነጋገቸው፤ ስሜቷን መቆጣጠር ያልቻለችባቸውም ጊዜያትም አልፈዋል።
“በህክምና ወደተግባራዊ ልምምድ ከመገባቱ በፊት የሚሰጠው የብቃት ማረጋጋጫ ፈተና ላይ ትንሽ ተቸግሬ ነበር፤ በጣም ከመጨናነቄ የተነሳ አስመልሶኝ ነበር፤ አንዳንዴ ደግሞ ፈተና በጣም ሲደራረብብኝ ለምን መረጥኩት? ምን ይሻለኛል? እያልኩኝ ሰው ሳያያኝ ተደብቄ አልቅሼ አውቃለሁ፤ አሁን ያ ቀን አልፎ ሳየው እያስታወስኩ እስቃለሁኝ።”
ዕልልታ ከትምህርቷ አልፎ ከሌሎች ጋር የምታሳልፈው ጊዜ ስላልነበራት እንደመዝናኛ የምትቆጥረው አብረዋት ከሚማሩት ጓደኞቻ ጋር በሻይ ሰዓት የሚኖራቸውን ጨዋታ ነበር።

“እኔ ስጀምር አትችይውም ተብዬ ነበር”
አሁንም ቢሆን ህምክናውንም ሆነ ምህንድስናውን በመቀመር በምህንድስናው ያገኘችውን እውቀት በህክምና ተቋማት በተግባር ልምምድ ያስተዋለቻቸውን የአሰራር ግድፈቶች የማስተካከል ህልም አላት።
“ለምሳሌ በርካታ ሆስፒታሎች ያየሁት በሕክምና ላይ ያለ ሰው ሲያርፍ እስከሬኑ የሚያልፈው በታካሚውና በአስታማሚዎች መሃል ነው፤ ይሄ ደግሞ ሌላው ታካሚን እኔም ቀጣይ ነኝ በሚል ተስፋውን ያሳጣል፣ አስታማሚንም ያጨናንቃል። አንዳንድ ሆስፒታሎች ደግሞ ለአካል ጉዳተኞችና በዊልቼር ለሚንቀሳቀሱ አረጋውያን የሚመቹ አይደሉም፤ ወይ ደረጃ ብቻ ወይ ደግሞ ደረጃና ሊፍት (አሳንሰር) ነው ያላቸው፤ እና ይህ መቀየር አለበት። ታካሚ አመላላሾችም መብራት ጠፍቶ ሊፍት ካልሰራ ተሸክመው ነው የሚሄዱት፤ እነዚህን ነገሮች ለወደፊት በምህንድስና ማስተካከል አፈልጋለሁ።”
በሰባት ዓመታት ውስጥ ያገኘቻቸውን ሁለት የመጀመሪያ ዲግሪዎች በቀጣዮቹ ሰባት አመታት ውስጥ ደግሞ ወደተሻለ የትምህርት ብቃት ለማሳደግ ወጥናለች- መሃንዲሷ ዶክተር ዕልልታ ነጋ።
“በኢንጅነሪንጉ ማስተርስ መስራት ‘በህምክምናው ደግሞሞ የአጥንት ስፔሻሊስት መሆን እፈልጋለሁ። ከሲቪል ምህንድስናውም ጋር እኮ ይሄዳል፤ የተሰበረን አጥንት መጀመሪያ የነበረበትን ቦታ ጠብቆ መስራት ስለሆነ፤ ከዚህም በላይ ግን በተግባር ልምምዴ ወቅት በራስ ደስታ ሆስፒታል ያስተማረኝ ዶክተር የስራ ብቃትና ውጤቶችን ሳይ ወደዚያ አድልቻለሁ።”

ዕልልታ እንዲህ ያሉ ፍላጎቶች የበርካታ ሴቶች መሆናቸውን ብትረዳም እስኪሳኩ ድረስ እስከመጨረሻው መታገልን ያሳለፍኳቸው ፈታኝ ግን ፍሬያማ ዓመታት አስተምረውኛል ትላለች።

“እኔ ስጀምር አትችይውም ተብዬ ነበር፤ ግን ሞክሬው ተሳክቶልኛል፤ መጨረሻውን ብቻ ነበር የማየው። እንደ ሴት ብዙ ነገር ነው እኛ ላይ የሚጣለው፤ ግን ለሰው ብለን ህልማችን አንተወው።”
ምንጭ፡ ቢቢሲ አመሃሪክ

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy