Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

ቋሚ ጥቅም እንጂ ቋሚ ወዳጅ የለም

0 2,788

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

ቋሚ ጥቅም እንጂ ቋሚ ወዳጅ የለም

ለዚህ ጽሁፌ መነሻ የሆነኝ አንድ ጋዜጠኛ /ጸሃፊ/ በድሬቲዩብ “ኢትዮጵያ ጠበቃም፣ አቃቢ ህግም የሆነችበት የኤርትራ ጉዳይ” በሚል ያስነበበንና መቋጫ ጭብጡ ሳይገባን ‘ተደናጊረ’ በሚል ሙዚቃ የተሰናበተበት ጽሁፍ ነው።

ጸሃፊው ኢትዮጵያ በኤርትራ ላይ ማዕቀብ እንዲጣልና በየጊዜውም እንዲራዘም ስትጥር ቆይታ አሁን ደግሞ ማዕቀቡ ሊነሳላት ይገባል በሚል ጥብቅና መቆሟ ‘በአንድ እራስ ሁለት ምላስ’ መሆን ነው ይልና በክቡር ጠ/ሚ ሃይለማርያም ደሳለኝ ወቅት ማዕቀቡ ይራዘም ሲል የነበረው የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴርና ዶ/ር አብይ አህመድ ወደ ስልጣን ሲመጡ ደግሞ ማዕቀቡ ይነሳ ወደሚል ጥብቅና መዞሩ ተቋማዊ አደረጃጀቱን ጥያቄ ውስጥ የሚከት ነው ይላል።

እኛም ይህን ሲል ኢትዮጵያ የማዕቀቡን መነሳት መደገፍ አልነበረባትም ኢትዮጵያ ማዕቀቡ እንዲጣልም ሆነ እንዲራዘም ስትጥር ብትቆይም የአለም አገራት ማዕቀቡ የሚከለክላቸውን ጉዳዮች እየጣሰ ከኤርትራ ጋር ግንኙነቱን በድብቅ በማስቀጠሉ ኤርትራ ተጎጂ አልነበረችም ይለናል።

እሺ ይህንንም አለምዓቀፉ ማህበረሰብ ለተ.መ.ድ ውሳኔ በሚጠበቀው መጠን ተገዢ አልነበረም ማለቱ ይሆናል ብለን ሳንጨርስ ደግሞ ኤርትራውያን ዛሬም የሰላም ሂደቱ ተጀምሮ በአፋኝ ስርዓት ውስጥ የሚማቅቁ መሆናቸውንና የኢትዮ-ኤርትራ የሰላም ሂደቱን ተከትሎ ድንበር ሲከፈት ወደ ኢትዮጵያ የሚጎርፉት ኤርትራውያን ቁጥር መጨመሩን ይተርክልናል።

የኢትዮጵያ መንግስት ኤርትራ ውስጥ ገብቶ የኤርትራውያንን መብት ማስከበር ነበረበት ማለቱ ይሆን? ወይስ የተጀመረው የሰላም ሂደትና አለምዓቀፉ ማህበረሰብ ማዕቀቡን ማንሳቱ ጥሩ ጅምር ሆኖ የኤርትራ መንግስት ለዜጎቹ መብት እንዲቆምም ሊያበረታታው ይገባል ለማለት ነው? ግልጽ የሆነ መደማደሚያ እንድንይዝ ሳይረዳን የተደናገረ ጽሁፍ አስነብቦን ተደናጊረ የሚል ዘፈን ጋብዞን ተሰናበተ።

እኔ በግሌ ጸሃፊው ያጎደላቸው የጭብጥ አንጓዎችን ጨማምሬ በበጎ መልኩ ልገነዘብለት የሞከርኳቸውን ጉዳዮች ከላይ የጸሃፊውን ግልጽ ያልሆኑ ጭብጦች በጥያቄ መልክ ለመረዳት ስሞክር እግረ-መንገዴን የነካካኋቸው በመሆኑ ዋና ትኩረቴ የኢትዮ-ኤርትራን የድንበር ጉዳይ፣ የማዕቀቡን ጉዳይና የሰላም ሂደቱን በሚመለከት የምናውቃቸው እውነታዎችን በማስታወስ ላይ ነው።

እንደሚታወቀው ኢትዮጵያ የአልጀርሱን ስምምነት ያለ ቅድመ-ሁኔታ እንደምትቀበል ገልጻ የሁለቱ አገራት ግንኙነት ከድንበር በላይ ስለሆነ በአፈጻጸምና ሌሎች ሁለገብ የትብብር ጉዳዮች ላይ ከኤርትራ ጋር አደራዳሪ ሶስተኛ ወገን ባለበትም ሆነ በሌለበት በኤርትራ ወገን ምርጫ በጠረጴዛ ዙሪያ ለመነጋገርና ሻካራ ግንኙነቱን ዘግቶ ሰላማዊ ምዕራፍ ለመጀመር ዝግጁ መሆኗን ግልጽ በተደጋጋሚ አድርጋለች። ይህ አቋም በቀድሞ ጠ/ሚ መለስ ዜናዊም ይሁን በቀድሞ ጠ/ሚ ሃይለማርያም ደሳለኝ ወቅት የነበሩና ጠ/ሚ ዶ/ር አብይ ወደ ስልጣን ሲመጡም የነበረ ነው።

አሁን ልዩ የሚያደርገው የኤርትራ ወገን በቀድሞዎቹ ጠቅላይ ሚኒስትሮች ያቀረቡትን የሰላም ጥሪዎች አለመቀበሉና በጠ/ሚ ዶ/ር አብይ የቀረበውን ተመሳሳይ ጥሪ ግን መቀበል መቻሉን ነው። ይህ በአንድ በኩል ፕሬዝዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ በዶ/ር አብይ በሚመራው መንግስታዊ አስተዳደር ላይ ከፍተኛ አመኔታ ማሳደራቸውን፣ በሌላ በኩል ዶ/ር አብይ በጉዳዩ ላይ የግል ክብር ሳያስጨንቃችው ገፍተው መሄድ በመቻላቸው ተጽእኖ መፍጠራቸውን አመላካች ነው።

ምናልባት ማድነቅ ያልለመደበት ሰው ፕሬዝዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ ካለፈው ስህተታቸው ተምረው ተጨማሪ የማዕቀብ ጊዜ መጋፈጥም ሆነ ከአለምዓቀፉ ማህበረሰብ ለተጨማሪ ጊዜ ተነጥሎ መቀጠል እንደማይኖርባቸው፤ በተለይ ደግሞ ከትብብር እንጂ ከግጭት ጥቅም እንማይገኝ ከተጨባጭ ሁኔታው ተገንዝበው ባለበት ሁኔታ በኢትዮጵያ አዲስና ከእረሳቸው ጋር የግልም ሆነ ቁርሾ ውስጥ ያልገቡ ከፍተኛ የመንግስት አመራሮች ወደ ስልጣን መምጣት ነባሩን የሰላም ጥሪ ተቀብለው ወደ ትብብር ምዕራፍ ለመግባት ሁኔታውን ቀላል አድርጎታል ብሎ ሊያስብ ይችላል።

ማዕቀቡ ቀድሞውንም ኤርትራን አልጎዳትም በማለት ጸሃፊው ያነሱት ጉዳይ ማዕቀቡ ድሮውንም ውጤታማ አልነበረም ለማለት ፈልገው ከሆነ ማዕቀቡ እንዲነሳ መጠየቅና መደገፍ አልነበረብንም ከሚለው ሃሳባቸው ጋር የሚጋጭ መሆኑ እንደተጠበቀ ሆኖ ቀድሞውንም ኢትዮጵያ በኤርትራ ላይ ማዕቀብ እንዲጣል ስትጎተጉት የኖረችው የኤርትራ መንግስት ለሰላም ዝግጁ ባለመሆኑ ሊያደርስ የሚችለውን ጉዳት ለመቀነስ የመንግስት ሃላፊዎችንና መንግስታዊ መዋቅሩን የተመለከተ ማዕቀብን እንጂ ህዝቡን ማዕከል ባደረገ መልኩ አልነበረም። ጥረቱ የኤርትራ መንግስት መሳሪያ የመግዛት መብት እግድንና ለዚህ የሚውል የገንዘብ አቅምን የመገደብ አቅጣጫን ማዕከል ያደረገ ነበር፣ ይህም ውጤታማ ነበር።

ጸሃፊው ኤርትራውያን ዛሬም የሰላም ሂደቱ ተጀምሮ በአፋኝ ስርዓት ውስጥ የሚማቅቁ መሆናቸውንና የኢትዮ-ኤርትራ የሰላም ሂደቱን ተከትሎ ድንበር ሲከፈት ወደ ኢትዮጵያ በሽሽት የሚጎርፉት ቁጥር መጨመሩን በተመለከተ ሲጽፉ ምን መልዕክት ማስተላለፍ ፈልገው እንደሆነ ግልጽ ባይሆንም የሰላም ሂደቱ መጀመር ቀጠናዊ ሰላምና ትብብሩን በማሻሻሉና አለምዓቀፉ ማህበረሰብም ማዕቀቡን ማንሳቱን ተከትሎ ሌሎች አገራትም ከኤርትራ ጋር ያላቸውን ዲፕሎማሲያዊ ትብብር ለማደስ አመቺ ሁኔታ የሚፈጠር በመሆኑ በሰብዓዊ መብትም ሆነ በስራ እድል ፈጠራ ረገድ በትብብር ለመስራትና ሁኔታውን በሂደት ለማሻሻል የሚረዳ የተሻለ አቅም ይፈጠራል። ስለዚህ ጸሃፊው ማዕቀቡ እንዲነሳ መጠየቅም ሆነ መደገፍ አልነበረብንም የሚል እምነት ካላቸው የሰብአዊ ሁኔታውን ለማሻሻል የሚጠቅም ሳይሆን እንዲያውም ባለበት እንዲቀጥል የሚያደርግ በመሆኑ ለማሳየት ከሞከሩት የውሸት ሰብአዊነት ስሜት ጋር ፍጹም ተቃርኖ ያለው ነው።

በአጠቃላይ ጸሃፊው የዲፐሎማሲን ባህሪ በደንብ አላወቁትም፤ ወይም “አውቆ የተኛ ቢጠሩት አይሰማም” እንዲሉ በግልጽ ቋንቋ ማብራራት ስላልፈለጉ እንጂ መልዕክታቸው ሌላ ነው። በእርግጥ ጸሃፊው ማዕቀቡ መነሳት አልነበረበትም፤ ኢትዮጵያም እንዲነሳ መጠየቅም ሆነ መደገፍ አልነበረባትም የሚል እምነት ማንጸባረቅ መብቱ ነው። ነውርም አይደለም። ዋናው ሙግቱ ሚዛን የሚደፋ ነወይ? የሚለው ነው።

ነገር ግን ዲፕሎማሲ ሰጥቶ በመቀበል መርህ መሰረት ሊገኝ የሚገባንና የሚችልን ብሄራዊ ጥቅም ማስፋትና በሌላ በኩል ደግሞ ስጋቶችንና ጉዳቶችን ቢቻል ማስወገድና ካልተቻለ ደግሞ መቀነስ ነው። ለጸብ እንጂ ለሰላም ዝግጁ ያልሆነን አካል የሚያደርስብንን ጉዳት ለመቀነስ እንደ አገር ሰርተናል፣ ይህንንም በማዕቀቡም ሆነ በሌሎች መንገዶች አሳክተናል። ሌላው ወገን ከግጭት የሚገኝ ኪሳራ እንጂ ትርፍ አለመኖሩን ተቀብሎ በራሱ ተነሳሽነትም ይሁን በእኛ ጥያቄ ለሰላምና ትብብር ዝግጁ እሰከሆነ ድረስ የጋራ ጥቅምን የሚያሰፉ እድሎችን ለማስፋትም እንደ አገር መንቀሳቀስ ጀምረናል፣ እንደ አገርም ሆነ እንደ ቀጠና ውጤታማ ጅምር ማየትም አስችሎናል።

በእኔ እምነት የጸሃፊው ዋና መልዕክት ጉዳዩን ከተቋማዊ አደረጃጀት ጋር በማያያዝ ሊያስተላልፉ የሞከሩት አደገኛ ጉዳይ ላይ አነጣጥሮ የተዘጋጀ ይመስለኛል።

በእርግጥም ጸሃፊው በክቡር ጠ/ሚ ሃይለማርያም ደሳለኝ ወቅት ማዕቀብ ይራዘም ይል የነበረው ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴርና የተቋሙ ሃላፊ ዶ/ር ወርቅነህ ጠ/ሚ ዶ/ር አብይ አህመድ ወደ ስልጣን ሲመጡ ማዕቀቡ ሊነሳ ይገባል ወደሚል ጥብቅና መዞሩ ተቋማዊ አደረጃጀቱን ጥያቄ ውስጥ የሚከት ነው በሚል ያነሱት ጉዳይ የራስ ጥቅም የሚያሳስባቸውና ድብቅ ፖለቲካዊ አጀንዳ ያላቸው ወገኖች የሚያስተጋቡት አፍራሽ አጀንዳ አካል ነው።

ይህ ትችት የተለመደው አይነት ዘር ተኮር ትችት ይመስልና ውስጡን ሲያዩት ግን የመንግስትን አካሄድ ከአገራዊ አልፎ ድንበር ተሻጋሪ አሉታዊ አሰላለፍ ያለውና በውጭ ሃይሎች ሴራ የሚመራ አድርጎ ለማሳየት የሚደረጉ አፍራሽ እንቅስቃሴዎች አካል የሆነ ጽሁፍ ነው።

በመሰረቱ ከታሪክ እንዳየነው ሰላምን ለማስፈን ከማንም ጋር የሚደረግ ትብብር ጉዳት የለውም፣ እንዳይኖረውም ታስቦበት የሚፈጸም ነው። ከአጋር አገራት ጋር በሰላም ሂደቱ ረገድ ትብብር ተደርጎም ከሆነ ሊጠናከር እንጂ ሊተች አይገባም።

ትርፋማነቱንም በአጭር ጊዜ እያየነውና መላው አለምም እያደነቀው ያለ ጉዳይ ነው። እርምጃው የተጀመረውን አገራዊ ለውጥ ውጤታማነትና የዲፕሎማሲውን ልህቀት ያሳያል እንጂ ትችት የሚገባው አይደለም። በአጠቃላይ አገራችን ማዕቀቡ እንዲነሳ መጠየቋም ሆነ መደገፏ ትክክል ነበር። መንግስት የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት ለኤርትራውያን ወገኖቻችን ማስተላለፉም ተገቢ ነው። የማዕቀብ መነሳትና ግንኝነቱ የተሻለ መሆኑ እንደ ኤርትራውያን ሁሉ ለእኛም ጠቃሚ ነው፡፡ ሌላው መታወቅ ያለበት በዓለም አቀፍ ግንኙነት የተለመደ አባባል አለ፡፡ ቋሚ ጥቅም እንጂ ቋሚ ወዳጅ የለም፡፡ ትናንት ጠላት የነበረ ዛሬ ወዳጅ ይሆናል፡፡ ወይም በተቃራኒው፡፡ በሁለተኛው የዓለም ጦርነት በናዚዎች እስር አበሳዋን ያየቸው ፈረንሳይ ዛሬ የጀርመን ወዳጅ ናት፡፡ እንደዛ ማለት ነው፡፡

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy