Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

አስተውሎ የሚራመድ ብዙ ርቀት ይጓዛል!

0 1,253

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

አንድ በአካባቢው የተወደደና የተከበረ ነጋዴ በመጋዝኑ ውስጥ ሥራ ላይ እያለ በጣም የሚወድደው የእጅ ሰዓቱ ይጠፋበታል፡፡ በመጋዘኑ ውስጥ እየተመላለሰ ቢፈልግም ሊያገኘው አልቻለም። ከመጋዘኑ ውጪ በጨዋታ ላይ ያሉትን ልጆች ይጠራና በመፈለግ እንዲያግዙት ይጠይቃቸዋል፤ ሰዓቱን ላገኘለት ልጅም ሽልማት እንደሚሰጥ ነግሮ ወደ ፍለጋ ያሰማራቸዋል፡፡

ልጆቹም ሽልማት እንዳለው ባወቁ ጊዜ በፍጥነት ሁሉን ቦታ ፈተሹ፡፡ ነገር ግን ሰዓቱን ሊያገኘው የቻለ አንድም ልጅ አልነበረም፡፡ መጋዘኑ ውስጥ ያለው ዕቃ ብዙ በመሆኑ ቢያነሱ ቢጥሉ ማግኘት አልቻሉም፡፡ ነጋዴው ልጆቹ የሚወድደውን ሰዓት እንዳላገኙት ባወቀ ጊዜ ተስፋ ቀረጠ። ይሁን እንጅ የሰዓቱን ፍለጋ ሊያቆም ሲል አንድ ትንሽ ልጅ ጠጋ ብሎ አንድ እድል እንዲሰጡት ጠየቃቸው፡፡

ነጋዴውም እስቲ ይሞክር በሚል ስሜት ፍቃደኛ ሆኑለት፡፡ ከጥቂት ቆይታ በኋላ ትንሹ ልጅ ሰዓቱን እጁ ላይ አንጠልጥሎ ተመለሰ፡፡ ነጋዴውም በሰዓቱ መገኘት እጅግ ደስ እያላቸው ሌሎቹ ልጆች ማግኘት ያልቻሉትን እንዴት ሊያገኘው እንደቻለ በመደነቅ ጠየቁት። ትንሹ ልጅም «እኔ ምንም የተለየ ነገር አላደረኩም፡፡

ያደረኩት ነገር ከመጋዘኑ መሀከል ላይ በጸጥታ በመቆም ማዳመጥ ነበር፡፡ በፀጥታው ውስጥም የሰዓቱ መቁጠሪያ የሆኑት ዘንጎች ሲዞሩ የሚፈጥሩት ጠቅ…ጠቅ የሚለው ድምጽ ተሰማኝ ይህን አቅጣጫ ተከትዬ ስመለከት ሰዓቱን አገኘሁት» አላቸው፡፡ ነጋዴው ደስ አላቸው፤ በህፃኑ የአስተሳሰብ ምጥቀትና አርቆ አስተዋይነት ተደመሙ። ቃል የገቡለትንም ስጦታ በጓደኞቹ ፊት አበረከቱለት።

በርግጥም በጽሞና ውስጥ አዕምሮ ነገሮችን ለይቶ በቀላሉ መረዳት ይችላል፡፡ አርቆ ለማሰብም ፋታ ያገኛል፡፡ ስለሆነም ኳኳታና ጫጫታ በበዛበት ዓለም ካለን ብዙ ሰዓታት ውስጥ የተወሰኑትን ደቂቃዎች ለጽሞና ማዋል ይኖርብናል። ከእራስ ጋር መነጋገር ስንጀምር መድረስ ወደምንፈልግበት የሕይወት ዓላማና አቅጣጫችንን ለማስተካከል ይረዳናል፡፡

የሕይወታችን መመሪያ አድርገን ከምንረዳቸው ታላላቅ ቁምነገሮች አንዱ ሚዛናዊነት ነው። ሰዎች ስንባል እንደ መልካችን መለያየት ሁሉ በነገሮች ላይ ያለን ምልከታም ለየቅል ነው፡፡ ይሄ ተፈጥሮ ከቸረችን የማይሸራረፍ ነፃነት የተገኘ ገፀ በረከት በመሆኑ ለራሳችን አስተሳሰብ ያለን ተቆርቋሪነት ከፍ ይላል፡፡ ይህ ነፃነትና ለራሳችን ያለን ተቆርቋሪነት ደግሞ ሚዛናዊነት ሊጎድለው እንደሚችል ማሰብ ይኖርብናል፡፡

አሁን በሀገራችን ያልተለመዱ ሁካታዎችና ግርግሮች ተበራክተዋል። ሁላችንም በግርግሩ አዙሪት ውስጥ ጠልቀን በመግባት ፈራጅ ሆነናል። መፍረዳችን ባልከፋ፤ ችግሩ የምንፈርድበት ምክንያታዊነት እዚህ ግባ የሚባል አለመሆኑ ነው። የአንድ ሰው የአስተሳሰብ ብቃት የሚለካው በሚዛናዊነቱ ነው ይባላል። በመሆኑም የአንድን ነገር ትክክለኛነት ለማረጋገጥ በፀጥታ ወይም በእርጋታ ብዙ ማሰብ ይገባል።

ሚዛናዊ አስተሳሰብ ደግሞ በችኮላ ወይም በስሜት መመራትን አጥብቆ ይቃወማል። ለመደገፍም ሆነ ለመቃወም ግራና ቀኙን አጢኖ መሃል ላይ መቆምን ይጠይቃል። መሃል ላይ የቆመ ሰው ግራና ቀኙን ለማስተዋል ጊዜ ይኖረዋል።
ብዙዎቻችንን አውቀንም ይሁን ሳናውቅ ሚዛናዊነታችንን ጫጫታውና ሁካታው ወስዶብናል።

አንዳንዶቻችን በብሄር፣ ሌሎቻችን ደግሞ በእምነት፣ እንዲሁም በፖለቲካዊ ወገንተኝነት ጎርፍ ተወስደን ሚዛናዊነታችንን ተነጥቀናል። ነገሮችን የምናይበት መንገድም ተንሻፍፏል፤ እኔነትን ወይም ወገንተኝነትን አስቀድመናል።
ለዚህም ነው መንግሥት አምኖ የሚያወጣቸውን መረጃዎች እንደቅርበታችንና እንደ አመለካከታችን እየተነተንን ወይም እየተረጎምን መግባባት ያቃተን።

ባለመግባባታችን ከምናተርፈው ይልቅ የምናጎድለው ይበረክታል። የሚያለያዩ አስተሳሰቦችን ወደጎን በማቆየት በሚያግባቡን ጉዳዮች ላይ ተስማምተን ወደፊት ብንጓዝ እንደሀገር እንቆማለን። ካልሆነ ግን የሚያለያዩትን አስተሳሰቦች ብቻ እያጎላን የምናራግብና ርካሽ ተደማጭነትን ለማግኘት የምንባዝን ከሆነ ከፍለን የማንጨርሰውን እዳ ለትውልድ እያቆየን መሆናችንን ልንረዳው ይገባል።

ብዙዎቻችን ከዓይናችን ይልቅ ጆሯችንን እናምናለን። በጥልቀት ከማዳመጥ ይልቅ በጨረፍታ መስማትን እንመርጣለን። የመስማትና የማድመጥን ልዩነት ከመረዳት ይልቅ እራሳችን ለራሳችን የሰጠነውን ትርጓሜ ይበልጥ እናምናለን። ለዚህም ነው ስሜታዊነታችን ገዝቶን ማስተዋላችንን የሚነጥቀን። የጠፋውን ሰዓት ያገኘው ህፃን ከሌሎች የተለየ ተአምር አድርጎ ሳይሆን በፀጥታ ውስጥ አስተውሎትን ተሞልቶ ማሰብ በመቻሉ ነው። ማስተዋል ማለትም ይሄው ነው፤ አንድ ውሳኔን ከመወሰን በፊት ከሁካታውና ከግርግሩ ወጥቶ ማሰብ ይገባናል።

አንዳንድ ሰዎች በግርግር መሃል ተጠቃሚ ሊሆኑ ይችላሉ። አብዛኛው ግን ተጎጂ መሆኑ አይቀርም። አሁን አሁን በከፍተኛ ትምህርት ተቋማትም ሆነ በአንዳንድ የሀገሪቱ ክፍሎች በግርግር ለመጠቀም የሚጥሩ ግለሰቦች ወይም ቡድኖች ሊኖሩ እንደሚችሉ መገመት አያዳግትም። በመሆኑም በማስተዋል ተመርተን በሁካታውና በጫጫታው ላለመጠለፍ ራሳችንን ማዘጋጀት ይኖርብናል።

 

«አስተውሎ የሚራምድ ብዙ ርቀት ይጓዛል» እንዲሉ ከግርግር ይልቅ በማስተዋል የሚመራ አዕምሮ ትክክለኛ እሴት ይገነባል። ትክክለኛ እሴት ትክክለኛ አስተሳሰብ ይፈጥራል። ትክክለኛ የሆነ አስተሳሰብ ትክክለኛ የሆነ ድርጊትን ይወልዳል። ትክክለኛ የሆነ ድርጊት ደግሞ ሁልጊዜም በጥሩ ፍሬ ይደመደማልና ነገሮቻችንን ሁሉ በማስተዋል ልናከናውን ይገባል።

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy